Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምሩሲያ ተኩስ ካቆመች ዩክሬን ራሷን ከወታደራዊ ጥምረት ገለልተኛ እንደምታደርግ አስታወቀች

ሩሲያ ተኩስ ካቆመች ዩክሬን ራሷን ከወታደራዊ ጥምረት ገለልተኛ እንደምታደርግ አስታወቀች

ቀን:

የቱርክ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን በኢስታንቡል ለድርድር የተቀመጡትን የሩሲያና የዩክሬን ልዑክ አባላት ሩሲያና ዩክሬን ‹‹የገቡበትን አስከፊ ጦርነት እንዲያቆሙ›› ሲጠይቁ፣ ዩክሬን ደግሞ ሩሲያ ተኩስ አቁም ስምምነት ከተገበረች ወታደራዊ ጥምረት ውስጥ እንደማትገባና ገለልተኛ ሆና እንደምትቆይ አስታወቀች፡፡

ሩሲያና ዩክሬን ከገቡበት ጦርነት እንዲወጡ የሰላም ድርድር በማመቻቸት ግንባር ቀደም የሆነችው ቱርክ፣ ከዚህ ቀደም የሁለቱን አገሮች ልዑካን ያወያየች ሲሆን፣ ማክሰኞ መጋቢት 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ዳግም ውይይቱን አስቀጥላለች፡፡

ከዚህ ቀደም በርካታ ውይይቶችን በቪዲዮ ኮንፈረንስ ያካሄዱት የሁለቱ አገሮች ልዑካን፣ በቱርክ ኢስታንቡል በመገኘት ውይይታቸውን አድርገዋል፡፡

ታይምስ ኦፍ ኢንዲያ እንደዘገበው፣ የሁለቱ አገሮች ውይይት ያስፈለገበት ቀዳሚ ዓላማ እስከ 20 ሺሕ ያህል ሰዎች የሞቱበትን፣ ከአሥር ሚሊዮን በላይ ከቀያቸው የተፈናቀሉበትንና የተሰደዱበትን ጦርነት ማስቆም ነው፡፡

ጦርነቱን ማስቆም ላይ ትኩረት አድርገው የተናገሩት ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን፣ ሁለቱም አገሮች የሚያነሷቸው የየራሳቸው ተገቢ የሆነ ሐሳብ ቢኖራቸውም፣ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ሊቀበለው የሚችለው መፍትሔ ላይ መድረስ ይቻላል ብለዋል፡፡

‹‹አስከፊውን ጦርነት ማስቆም የሁለቱ አገሮች ውሳኔ ነው፣ የጦርነቱ መራዘም የማንም ፍላጎት አይደለም›› ሲሉም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

ከሃያ ቀናት በፊት የሩሲያንና የዩክሬንን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ያወያየችው ቱርክ፣ አገሮቹ ጦርነቱን አቁመው ወደ መፍትሔ እንዲያመሩ ጥረት እያደረገች ሲሆን፣ በውይይቶቹ ቁልፍ የሆኑ የሁለቱ አገሮች ሐሳቦች ላይ የሰላም ስምምነት ከተደረገ በኋላ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንና የዩክሬን አቻቸው ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ የፊት ለፊት ውይይት ሊያደርጉ ይችላሉ ሲሉ የሩሲያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮብ መናገራቸውን የሂንዱስቲያን ታይምስ ዘገባ ያሳያል፡፡

ከስብሰባው አስቀድሞ ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን ለፕሬዚዳንት ፑቲን ስልክ መደወላቸውና የሁለቱ አገሮች ልዑካን በቱርክ ውውይት እንዲያደርጉ መስማማታቸውን የኤርዶጋን ቢሮ ያስታወቀ ሲሆን፣ ሁለቱ አገሮች ተኩስ ማቆም እንዳለባቸው ኤርዶጋን ማሳሰባቸውን አክሏል፡፡

በጦርነት አካባቢ የሰብዓዊ ሁኔታ እንዲሻሻል መጠየቃቸውም ተገልጿል፡፡  ከዚህ ቀደም በዩክሬንና ሩሲያ ልዑካን መካከል የተደረገ ውይይት ከስምምነት ላይ ባይደርስም፣ ወደ ሰላም ለመምጣት የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩ ይታወሳል፡፡

ትናንት በተካሄደው የልዑካን ቡድኑ የፊት ለፊት ውይይት ግን ከዚህ ቀደም ከነበሩ ውይይቶች በተለየ ሁለቱን አገሮች የሚያስማማ ሐሳብ ከዩክሬን ቀርቧል፡፡

ፍራንስ 24 ለድርድር የተቀመጡትን ልዑካን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ሩሲያ የተኩስ አቁም ስታደርግ ዩክሬን ደግሞ ለደኅንነቷ ዋስትና ወታደራዊ ጥምረትን ላለመቀላቀል ወይም በአገሯ የጦር መንደር ላለመገንባት ሐሳብ አቅርባለች፡፡

ከዩክሬን የተገነጠለችውን ከራያሚያ አስመልክቶ የ15 ዓመታት የውይይት ጊዜ እንዲኖር የሚያደርግና ይህ ግን ዕውን የሚሆነው ሙሉ ለሙሉ ተኩስ አቁም ከተተገበረ እንደሆነ በተወያዮቹ የቀረበው ምክር ሐሳብ ያሳያል፡፡

በሁለቱ አገሮች ተወያዮች በኩል አዎንታዊ ውጤት በመገኘቱም፣ በፑቲንና በዜሌኒስኪ መካከል የሚደረግ ውይይት ሊኖር እንደሚችል በኢስታንቡል የተገኙት የሩሲያ ቃል አቀባይ ገልጸዋል፡፡

ሩሲያ በበኩሏ በዩክሬን የጀመረችውን ወታደራዊ ኦፕሬሽን እንደምትቀንስ አስታውቃለች፡፡

ዩክሬንና ሩሲያ ወደ ጦርነት ከገቡ አምስት ሳምንታት የተቆጠሩ ሲሆን፣ የሁለቱ አገሮች ጦርነት በዓለም ኢኮኖሚ ላይ መዋዥቅንና የኑሮ ውድነትን አስከትሏል፡፡

በተለይ አውሮፓና አሜሪካ በሩሲያ ላይ እየጣሉ ያለው ማዕቀብ እነሱንም ጭምር እየጎዳ ሲሆን፣ ጦርነቱ የፈጠረው የአቅርቦት እጥረት ደግሞ በተለይ በደሃ አገሮች ተፅዕኖው ወዲያው ታይቷል፡፡

የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት አብዛኞቹ የዓለም ሕዝቦች ለከፍተኛ የዋጋ ውድነት እንዲጋለጡና የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሚዛኑንም እንዲዛባ አድርጓል፡፡

ምግብ ለመሥራት አብዛኛው የዓለም ሕዝብ የሚጠቀምባቸው የበቆሎ፣ የገብስና የሌሎች ጥራጥሬዎች ምርቶች ትልቅ አቅራቢዎች በመሆናቸውም፣ ጦርነት ውስጥ መግባታቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ የዋጋ ንረት እንዲከሰት አድርጓል፡፡

ኢንተርናሽናል ግሪን ካውንስል እንደሚለውም ጦርነቱ የካቲት 2014 ዓ.ም. ላይ ከተጀመረ ወዲህ የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ዋጋ በ17 በመቶ ጨምሯል፡፡ ስንዴ በ28 በመቶ፣ በቆሎ በ23 በመቶ እንዲሁም ገብስ 22 በመቶ ዋጋ ጨምረዋል፡፡ የገብሱ ብቻ ቢታይ አንድ አምስተኛ የሚሆነው የገብስ አቅርቦት ከእነዚሁ አገሮች የሚላክ ነው፡፡

የሱፍ ዘይት አምራቾቹ ሩሲያና ዩክሬን ለዓለም ከሚቀርበው የሱፍ ዘይት 70 በመቶውን ይሸፍናሉ፡፡ ስንዴን በብዛት ከዩክሬንና ሩሲያ የምታስገባው ግብፅ ከአሁኑ በዳቦ ዋጋ ውድነት እየተሸበረች ሲሆን፣ አልጄሪያ፣ ናይጄሪያ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ቱርክና ፊሊፒንስ የአገሮቹ ትልልቅ ተቀባዮች በመሆናቸው በዋጋ ንረቱ ቀዳሚ ተፈታኝ ሆነዋል፡፡

የአገሮቹ ጦርነት ውስጥ መግባትና በአቅርቦቱ ላይ እጥረት መፈጠር በተለይ ደሃ አገሮችንና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ይፈትን እንጂ ችግሩ ዓለም አቀፋዊ ነው፡፡

የስንዴ፣ በቆሎና ገብስ መወደድ በቁም ከብቶችና በዶሮ ተዋጽኦ ላይ ሳይቀር የዋጋ ንረት ችግር ፈጥሯል፡፡ የሥጋና የእንቁላል ዋጋ ከዚሁ ጋር ተያይዞ እየጨመረ ነው፡፡ ሩሲያ የሰብል ምርቶቿን ለጊዜው ወደ ውጭ እንዳይላክ ማገዷም ችግሩን የሚያባብስ ነው፡፡

ሆኖም በቱርክ የተደረገው የፊት ለፊት ውይይት ትርጉም ያለው ለውጥ ይዞ መጥቷል ሲል ፍራንስ 24 ዘግቧል፡፡

 (ጥንቅር በምሕረት ሞገስ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኩባንያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ባንኮች ውጤታማነት

የጠቅላላ ጉባኤ፣ የጥቆማና ምርጫ ኮሚቴ፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...