Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የድምፅ ብክለት የሕግ ማስከበር ሥራ ከጤና ጉዳቱ አንፃር

አለነ መሸሻ (ዶ/ር) በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የጆሮ፣ የአፍንጫና ጉሮሮ ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስትና መምህር፣ እንዲሁም የጆሮና መስማት እንክብካቤ ፕሮጀክት አስተባባሪ ናቸው፡፡ የጆሮና መስማት ችግሮችና ተያያዥ  በሽታዎችን አስመልክቶ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በዓለም ውስጥ የመስማት ችግር ያለባቸው ሰዎች ምን ያህል ናቸው? በኢትዮጵያ ያሉትስ ብዛታቸው ይታወቅ ይሆን? ችግሩ/በሽታውን ከሌሎች በሽታዎች አንፃር የሚያሳድረው ጫና እንዴት ይታያል?

ዶ/ር አለነ፡- በዓለም ከአንድ ቢሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች የመስማት ችግር እንዳለባቸው የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ያሳያል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያህል ይሆናሉ ለተባለው ትክክለኛውን ለማወቅ የሚያስችል የዳሰሳ ጥናት በቅርቡ ይካሄዳል፡፡ በዘርፉ በአሁኑ ጊዜ ይሄን ያህል ናቸው ለማለት አያስደፍርም፡፡ የዳሰሳውን ውጤት መጠበቅ ግድ ይላል፡፡ ነገር ግን የዓለም ጤና ድርጅት ከሰሀራ በታች ባሉት አገሮች ላይ ካካሄደው የዳሰሳ ጥናት በመነሳት በኢትዮጵያ ከመቶ ሰዎች መካከል አምስቱ ወይም ከመቶ ሚሊዮን ሕዝብ መካከል አምስት ሚሊዮን ያህሉ በተወሰነ ደረጃ ለመስማት ይቸገራሉ ተብሎ ይገመታል፡፡ ይህም ሆኖ ግን በትንሽ ወጪ ግንዛቤን በማስጨበጥ መከላከል ይቻላል፡፡ በተረፈ የመስማት ችግርና ተያያዥ ከሆኑት ሌሎች በሽታዎች ጋር የሚያመጣው ጫና በጣም ከፍተኛ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ብዙዎቹ የጆሮ ሕመሞች በተለይ በተላላፊና ተላላፊ ካልሆኑት በሽታዎች ሁሉ ከፍተኛ ጫና በማሳደር አራተኛ ደረጃን ይይዛሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የመስማት ችግር መንስዔው ይታወቃል?

ዶ/ር አለነ፡- የመስማት ችግር መንስዔዎችን ሁሉንም ለመዘርዘር ቢያስቸግርም ለአብነት ያህል ጥቂቶቹን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ስለሆነም የመጀመርያ መንስዔ ከጽንሰት ጀምሮ የሚመጣ የመስማት ችግር አለ፡፡ ከውልደትም በኋላ በሚመጡ ኢንፌክሽኖች የጆሮ መመርቀዝን ያስከትላል፡፡ ከዚህም ሌላ የጆሮ ታምቡር በኢንፌክሽን እንደሚቀደድም መታወቅ ይኖርበታል፡፡ በተቀደደው ታምቡር በታች ያሉት ትንንሽ አጥንቶች ይሰበሩና ድምፅ ወደ መካከለኛውና ወደ ውስጠኛው ጆሮ እንዳይተላለፉ ያደርጋሉ፡፡ እወዳለሁ፡፡ ከዚህም ሌላ በዕድሜ የሚመጣ የነርቭ መድከም ችግር አለ፡፡ ይሄም ችግር ከሌሎች ተያያዥ ከሆኑ እንደ ስኳርና ደም ግፊት ከመሳሰሉት እንዲሁም ከጉዳት ጋር ተያይዞ ሊመጣ ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- የማስገንዘቡን ሥራ የምታከናውኑት በተዘረዘሩት ችግሮች ዙሪያ ነው? ወይስ የለያችሁት ችግር አለ?

ዶ/ር አለነ፡- በዚህ ዓመት በተለይ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ አጉልተን የምናከናውነው ‹‹ጥንቃቄ በጎደለው መስማት/ማዳመጥ›› ላይ ትኩረት ያደረገ ወይም ከማዳመጫ መሣሪያዎች (ኢር ፎን) እና ከድምፅ ጋር የተያያዘውን የመስማት ችግር በተመለከተ ይሆናል፡፡ ብዙዎቹ ወጣቶች ኢርፎንና ሄድ ፎን አጠቃቀማቸው ጥንቃቄ የጎደለው ነው፡፡ ከፍተኛ ድምፅ ይጠቀማሉ፡፡ ከዚህም ሌላ በመዝናኛ አካባቢዎች፣ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪዎችና በትራፊክ ፍሰት ላይ ከፍተኛ የሆነ የድምፅ ብክለት አለ፡፡ ይሄንንም ብክለት በቀላሉ መከላከል ይቻላል፡፡ አለበለዚያ የሚያስከትሉት የጎንዮሽ ጉዳዮች ከፍተኛ እንደሚሆን ይህንንም ለመቀልበስ የሚያስፈልገው ወጪ በጣም ከፍተኛ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ዓይነቱ ችግር ለመላቀቅ ዋናው መፍትሔ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ማከናወን አማራጭ ሆኖ ተገኝቷል፡፡  

ሪፖርተር፡- የድምፅ ብክለትን ለመከላከል የሚያስችል ሕግ ወጥቶ ወደ ሥራ ከገባ ቆይቷል፡፡ ሕጉን ተግባራዊ ለማድረግ ለምንድነው ያልተቻለው?

ዶ/ር አለነ፡- ሕግ መውጣቱ ጥሩና መልካም ነገር ሆኖ ሕጉ የወጣው ወይም በባለቤትነት የሚመለከተው የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንን ነው፡፡ ባለሥልጣኑ ደግሞ ሕጉን የሚረዳበት አግባብ ይኖረዋል፡፡ ሰዎች ከእንቅልፋቸው ተረበሹ፣ ሥራም አላሠራ አላቸው ወዘተ. የሚል ሊሆን ይችላል፡፡ የጤና ችግሩን አብሮ ለማየት ግን ከጤና ጋር አብሮ መሥራትን ይጠይቃል፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን ትስስርን መፍጠር ይገባል፡፡ የድምፅ ብክለት የሕግ ማስከበር ሥራ በተለይ ከጤና ጉዳቱ አንፃር አጽንኦት ሊሰጠው ይገባል፡፡ በአጠቃላይ ይህ ጉዳይ በተለይም በትስስር መሠራት አለበት ብለን እናምናለን፡፡ ይህም ሆኖ ግን ሕግ ከማስከበሩ በፊት ረዘም ያለ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ መከናወን አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- የጆሮና የመስማት እንክብካቤ ፕሮጀክት አስተባባሪ እንደሆኑ ነግረውናል፡፡ እስኪ ስለ ፕሮጀክቱ አብራሩልን?

ዶ/ር አለነ፡- ፕሮጀክቱ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ አማካይነት የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ ፕሮጀክቱን የሕክምና ኮሌጁ እንዲያስተዳድረው የተደረገበት ምክንያት ከአንገት በላይ የሕክምና አገልግሎትና ለድኅረ ምረቃ ተማሪዎችም በዘርፉ የስፔሻላይዜሽን ሥልጠና በመስጠቱ ነው፡፡ የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት ከሚመጡት ታካሚዎች መካከል ከ50 እስከ 60 በመቶ የሚሆኑት የጆሮ ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡ ባለፈው ዓመት ብቻ የጆሮ ታምቡር ለተበላሸባቸው 893 ታካሚዎች ሰርጀሪ (ቀዶ ሕክምና) ተደርጎላቸዋል፡፡ ይህ እና መሰል ሥራዎች ፕሮጀክቱ በሕክምና ኮሌጁ እንዲተዳደር ሊያደርገው ችሏል የሚል እምነት አለን፡፡

ሪፖርተር፡- የጆሮና የመስማት ችግር ላለባቸው ወገኖች በአቅራቢያቸው ወይም በያሉባቸው አካባቢዎች ሕክምናውን ተደራሽ ለማድረግ ምን የታሰበ ነገር አለ?

ዶ/ር አለነ፡- ይህንን ችግር ለመቅረፍ እንዲረዳን የአሠልጣኞቹ ሥልጠና ለመስጠት አስበናል፡፡ ሥልጠናውንም የሚከታተሉት ሐኪሞች፣ ጤና መኰንኖችና ነርሶች ናቸው፡፡ በነዚህ የጤና ባለሙያዎች ላይ የማብቃት ሥራ ከተከናወነ ብዙዎቹን እንደርሳለን ብለን እናስባለን፡፡

ሪፖርተር፡- በጆሮና መስማት ችግሮች ላይ ለሚደረገው ሕክምና እንደ ተግዳሮት የሚታዩት ምንድናቸው?   

ዶ/ር አለነ፡- ችግሮቹ ብዙ ናቸው፡፡ ከችግሮቹም መካከል ጥቂቶቹን ለመግለጽ አንደኛው ችግር ብቃቱንና ጥራቱን የጠበቀ የጤና ተቋም አለመኖር፣ እንዲሁም የአገልግሎት ሰጪ ባለሙያዎች በብቃት፣ በብዛትና በየሙያ ስብጥር አለመኖር/አለመገኘት፣ ለሕክምና የሚያስፈልጉ መገልገያዎችና መሣሪያዎች እጥረት ናቸው፡፡

 

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ሥጋቶች

ዘ ኮንቨርሴሽን ላይ ‹‹What Next for Ethiopia and its...

 የክልሎች ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በመከላከያ ሠራዊት ተጠባባቂ ኃይል እንዲካተቱ ጥናት እየተደረገ ነው

የክልሎችን ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በአገር መከላከያ ሠራዊት ተጠባባቂ ኃይል...

ኢትዮጵያ በትክክለኛ ግንዛቤ ላይ የተመሠረተ ሕገ መንግሥት ማበጀት እንደሚገባት ማሳሰቢያ ተሰጠ

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ከተረቀቀበት ጊዜ አንስቶ ለተለያዩ ጥያቄዎችና ሐሳቦች...