Monday, May 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርከዘይት እጥረት በስተጀርባ መታየት ያለባቸው አሳሳቢ ችግሮች

ከዘይት እጥረት በስተጀርባ መታየት ያለባቸው አሳሳቢ ችግሮች

ቀን:

በመታሰቢያ መላከ ሕይወት

የዘይት እጥረት ለመፈጠሩ በዋነኛነት ዜጎች በፆም ወቅት የሚጠቀሙት የዘይት መጠን እየጨመረ እንደሚሄድ ነጋዴዎች ስለሚያውቁ፣ ፆም ሊደርስ አካባቢ በርካታ ነጋዴዎች ዘይት ለመደበቅ ስለሚሞክሩ እንደሆነ ብዙ የተባለለት ነው፡፡

በተጨማሪ መንግሥት በውጭ ምንዛሪ ገዝቶ ወደ አገር ውስጥ ያስገባውን ዘይት ወደ ጎረቤት አገሮች በመላክ ተጠቃሚ ለመሆን የሚሠሩ ኃይሎች መኖራቸው ደግሞ፣ ሌላው ምክንያት እንደሆነ ሰምተናል፡፡

በንግድ ዓለም የምርት እጥረት የሚፈጠረው ገበያው የሚፈልገውን ምርት በበቂ ሁኔታ ማቅረብ ሳይቻል ሲቀር እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ መንግሥት የግሉን ዘርፍ በኢኮኖሚው ውስጥ በስፋት መሳተፍ እንዲችል በሩ በጣም ጠባብ በመሆኑ በተደጋጋሚ የምርት እጥረት ሲፈጠር እያየን ነው፡፡

እኔ በልጅነቴ ባደግኩበት አካባቢ ስድስት ኪሎ ሠፈር ውስጥ እንኳን ሦስት ዘይት ጨማቂዎች ነበሩ:: ከእነዚህ ቤቶች በልጅነቴ ዘይት ስገዛ ትዝ ይለኛል፡፡ አሁን ግን እነዚህ ማምረቻዎች የሉም፡፡

በየትም ዓለም መንግሥት ዜጎች የሚፈልጉትን ሁሉ ማሟላት አይችልም፡፡ በየትም ዓለም ያለ አሠራር ቢኖር ዜጎች እንደ ዝንባሌያቸው የተለያዩ ምርቶችን እያመረቱ ያለውን የገበያ ጉድለት መሙላት መቻል አለባቸው፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ ዜጎች በፈለጉት ጊዜ መሬት እየገዙ የፈለጉትን ሥራ መሥራት እንዲችሉ ሁኔታዎች የተመቻቹ መሆን አለባቸው፡፡

መሬት የመንግሥት እስከሆነ ድረስ፣ ገበሬው በይዞታው ሥር የሚገኝን መሬት እሴት መጨመር፣ ማከራየት፣ መሸጥና መለወጥ የመሳሰሉ መብቶች ተገድበው ባሉበት ሁኔታ ዜጎች መሬት ገዝተው በፈለጉት ቦታ ያሰቡትን ሥራ መሥራት ችለው በቂ ምርት ወደ ገበያ ማቅረብ እስካልቻሉ ድረስ የምርት እጥረት አሁንም ይኖራል፣ ወደ ፊትም ይቀጥላል፡፡

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ለብልፅግና ባለሥልጣናት መመርያ በሰጡበት መድረክ ላይ ከነገሩን ነገሮች አንዱ፣ ቻይና በማኦ ሴቱንግ ዘመን በኮሙዩኒስት ሥርዓት ስትመራ እንደነበርና በዚህ ሐሳብ ያልተስማሙና በ1989 ወደ ሥልጣን የመጣው ዲያንግ ዜሚን ሐሳቡን ይዞ ሥልጣን እስኪያገኝ ድረስ እንደጠበቀ ነግረውን ነበር፡፡

እዚህ ላይ ‹‹አሁን እኔ ተመርጫለሁ አትቃወሙኝ ተራችሁ ደርሶ ሥልጣን እስክትይዙ ጠብቁ›› የሚል ዓይነት መልዕክት ለማስተላለፍ እንደፈለጉ ነው የገባኝ፡፡

ነገር ግን  ዓብይ (ዶ/ር) ትልቁ ያልነገሩን ነገር ቻይና እ.ኤ.አ. ከ1989 ጀምሮ ሥልጣን የያዘው ዲያንግ ዜሚን ምን ሠራ? ቻይናንስ የቀየረበት መንገድ ምንድነው? የሚለውን ትልቁን ቁም ነገር ሳይነግሩን ነው ያለፉት፡፡ እሳቸውም ከዚህ ተምረው ኢትዮጵያን በዚያ መንገድ ለመለወጥ ቢሠሩ የአገር ባለውለታ ይሆኑ ነበር፡፡  

በቻይና እ.ኤ.አ. 1989 ወደ ሥልጣን የመጣው ዲያንግ ዜሚን በዋናነት ከሠራቸው ሥራዎች ውስጥ (Socialist Market Economy) የሚል ፕሮግራም አዘጋጅቶ፣ በተለይ ከእሱ በፊት የነበሩ መሪዎች ያልሠሩትን ሥራ ማለት የግሉን ዘርፍ በቻይና ኢኮኖሚ ውስጥ በስፋት የማሳተፍ በተግባር በማከናወኑ ነው ቻይና በተከታታይ አስደናቂ ዕድገት እንድታመጣ መሠረት ጥሎ ያለፈው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቻይና እንዴት የሥርዓት መስተካከል አድርጋ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ቻለች? እኛስ ከቻይና ምን እንማራለን? ብለው ሊነግሩን ሲገባ፣ ሐሳባችሁን ይዛችሁ ቁጭ በሉ፣ ሥልጣን ስትይዙ ሐሳባችሁን ተግባራዊ ታደርጉታላችሁ የሚመስል ዓይነት መልዕክት ነው ያስተላለፉት፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን ከመላው ዓለም አስተሳሰብ እጅግ በተቃራኒው ቆመን፣ የትም ዓለም ተቀባይነት የሌለው ፍልስፍና እያራመድን፣ የአገራችንን ሕዝቦች በዘር ከፋፍለን፣ እርስ በርስ እንዲናቆሩ አድርገን፣ ሊታረስ የሚችል ሰፊ መሬት እያለን፣ በአሁኑ ዘመን የዓለም ሕዝቦች እጅግ ለተራቀቁ ሳይንሶች እየተጨነቁ ባሉበት ወቅትና ስለዘይት እጥረት እያወራን በአገር እየቀለድን ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር በዚህ በሠለጠነ ዘመን ስለዘይት እጥረት ማውራት ዘመኑን አይመጥንም፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት በተለይ አርብቶ አደር ማኅበረሰብ በሚኖርባቸው አካባቢዎች ዘይት ለምግብነት መጠቀም ያልተለመደ ነበር፡፡ አርብቶ አደሮች የግመሎቻቸውን ወተት ይጠጣሉ ወይም ደግሞ ፍየል አርደው ሥጋ ጠብሰው ይበላሉ፡፡ አሁን ግን ዘይትን ተጠቅመው ምግብ ማዘጋጀት ጀምረዋል፡፡ በሌላም አካባቢ የተለያዩ  ምግቦች ዘይት ሳይገባበት ተዘጋጅቶ መብላት የተለመደ ነበር፡፡ አሁን ግን የዜጎች ቁጥር መጨመርና የዜጎች ፍላጎት መጨመር በከፍተኛ ሁኔታ እየተመዘገበ በመሆኑ፣ መንግሥት ከዜጎች ብዛትና ፍላጎት አኳያ ለውጥ ማምጣት ካልተቻለ ችግሮች ተጠናክረው መቀጠላቸው አይቀርም፡፡ በየሠፈሩ ድንች በዘይት እየጠበሱ የሚሸጡ ዜጎች አሁን ያለና በፊት ያልነበረ ልምድ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ እያንዳንዱ ዜጋ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ ያለውን አበርክቶና እያንዳንዱ ዜጋ የሚጠቀመውን የውጭ ምንዛሪ ብናሰላው የዜጎች የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም በእጅጉ ልቆ እናገኘዋለን፡፡ መሆን የነበረበት ግን የተገላቢጦሽ ነበር፡፡

በአንድ ቦታ ጥሩ ምግብ አብሳይ ካለ፣ ጥሩ ምግብ ይኖራል፡፡ በአንድ ቦታ ጥሩ  ሙዚቀኛ ካለ፣ ጥሩ ሙዚቃ ማዳመጥ ይቻላል፡፡ ጥሩ እግር ኳስ ተጫዋች ካለም ጥሩ ጨዋታ ማየት ይቻላል፡፡

ፖለቲካውም እንደዚሁ ነው፡፡ በአንድ አገር ብቃት ያለው ፖለቲካኛ ሥልጣን ከያዘ በየጊዜው አሰቃቂ ዜና ሳይሆን እጀግ የሚያስደስቱ ዜናዎችን ለመስማት እንታደላለን፡፡

አሁን በአገራችን እየታዘብን ያለነው ለተፈጠሩ ችግሮች ሁሉ መልስ የሚያዘጋጅ መንግሥት እንጂ፣ መፍትሔ የሚያመጣ መንግሥት አይደለም፡፡

ከላይ እንደ ተጠቀሰው ፕሬዚዳንት ዲያንግ ዜሚን ቻይናን እንዴት በፍጥነት ለወጣት? ያንን ዘዴ ተጠቅመን ኢትዮጵያንስ እንዴት መለወጥ እንችላለን? የሚለው ሐሳብ እጅግ ወሳኝ ጥያቄ ሆኖ ሳለ፣ አሁን የተመረጥኩ እኔ ነኝ የእኔ ሐሳብ ነው ተግባራዊ የሚደረገው፣ እናንተ እስክትመረጡ ሐሰባችሁን ይዛችሁ ተቀመጡ ማለት ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፡፡

አንድ ሐሳብ የማንም ይሁን የማን፣ ሥልጣን ላይ ማንም ይቀመጥ ማን፣ ቁምነገሩ አንድ ሐሳብ ጠቃሚ ነው ተብሎ ከታመነበት ተግባራዊ መደረግ ነው አለበት እንጂ፣ እስክትመረጡ ጠብቁ የሚል አስተሳሰብ ለአገር አይጠቅምም፡፡

ኢትዮጵያ አገራችን በአሁኑ ጊዜ እጀግ በተሳሳቱ አስተሳሰቦች ውስጥ ገብታ እየተቸገረች ያለች አገር ነች፡፡ ለምሳሌ በኢሕአዴግ ዘመን የነበረው አስተሳሰብ ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ›› ማንም ሳይገባው ነው ከሥራ ውጪ የሆነው፡፡ አሁን ደግሞ ‹‹መደመር›› የሚለው ፍልስፍና ራሳቸው ዓብይ (ዶ/ር) የገባቸው አይመስለኝም፡፡ ሁለቱም አስተሳሰቦች ጠቃሚ ቢሆኑ ኑሮ የዓለም ሕዝብ ተሻምቶ ኮፒ ያደርጋቸው ነበር፡፡   

አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት እየተባለ ያለ መፈክር አንዱ ‹‹ኅብረ ብሔራዊ አንድነት›› የሚል አባባል ነው፡፡ ይህ አባባል በተዓምር ተግባራዊ ሊደረግ የሚችል አይደለም፡፡ ምክንያቱም አንድነትና ኅብረ ብሔራዊነትን ነጣጥሎ ማስኬድ አይቻልም፡፡ ፈረንጆች (Diversity is a Curse) ይላሉ፡፡ ልዩነት የግጭት፣ ያለ መግባባትና የውጥረት ምንጭ እንጂ ለአንድነት አብሮ ለመሥራት፣ ውጤት ለማምጣት የሚጠቅም አስተሳሰብ አይደለም፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን ያለን አማራጭ ሁለት ብቻ ነው፡፡ አንደኛው ኢትዮጵያን 85 ቦታ ከፋፍለን 85 መንግሥት መፍጠር፣ ወይም ደግም ተጨፍልቀን አንድ አገር አንድ ማንነት ፈጥረን ታላቅ ኢኮኖሚ በመገንባት ሌሎች ውጤት ያስመዘገቡ አገሮች የሄዱበትን መንገድ መጓዝ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ሌላ አማራጭ የለም፡፡

በኢሕአዴግ ዘመንም አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚለው አባባል ከራሱ ከአባባሉ ብንነሳ አብዮት ማለት አመፅ፣ አንድን ነገር ከሥሩ ፈንግሎ መጣል፣ የሥርዓት ለውጥ ማምጣት ማለት ሲሆን፣ ዴሞክራሲ ማለት ደግሞ ራስን በራስ ማስተዳደር፣ የዜጎችን ሁሉንም ዓይነት መብት ማክበር ማለት ነው፡፡ እነዚህን ሁለት ተፃራሪ አስተሳሰቦችን አንድ ላይ ማድረግ አይቻልም፡፡

ዛሬ በዓለማችን ታላቅ ውጤት ያስመዘገቡ አገሮች ሁሉንም አንድ የሚያደርጋቸው ልዩነትን አጥብበው፣ ለአንድ ዓላማ ቆመውና በአንድ ርዕዮተ ዓለም ሥር ተሠልፈው በመጓዛቸው ነው ታላቅ ውጤት ማስመዝገብ የቻሉት፡፡

መንግሥት እንደ መፈክር፣ ‹‹ኅብረ ብሔራዊ አንድነት›› ይበል እንጂ፣ የብሔሮች ማንነት በከፍተኛ ፍጥነት በመጥፋት ላይ ነው፡፡ የብሔሮች ማንነት እንዲያድግ የሚንከባከብ ተቋም የለም፡፡ ወጣቱ ትውልድ ደግሞ ይጠቅመናል ያለውን ማንነት ብቻ በመከተል ላይ ነው፡፡

እስኪ የተከበራችሁ አንባብያንን አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፡፡ ‹‹መደመር›› የሚለው አስተሳሰብና ‹‹ኅብረ ብሔራዊ አንድነት›› የሚለው አስተሳሰብ ሁለቱን አንድ ላይ ማስኬድ ይቻላል? እስኪ በዚህ ጉዳይ ተወያዩበት፡፡

በአንድ አገር ከብዙ ብሔሮች ጋር አብሮ እየተኖረ፣ የብሔር ጽንፍ ይዞ ስለአንድነት ማውራት አይቻልም፡፡ በአስተሳሰብ ደረጃም አንድ ላይ የሚሠሩ ስብስቦች አስተሳሰብ ጽንፍ ይዘው አንድ ላይ ሠርተው ውጤት ሊያመጡ አይችሉም፡፡

በርዕሱ እንደ ተጠቀሰው የብሔር ፖለቲካ ገኖ መገኘት፣ የአስተሳሰብ ጽንፍ መበራከት፣ በጋራ ለአንድ ዓላማ ሠርተን ውጤት ማስመዝገብ እንዳንችል ስላደረገን በቀላሉ ማምረት የምንችለውን ዘይትን እንኳን አምርተን ሕዝባችንን ተጠቃሚ ማድረግ አልቻልንም፡፡ ኢትዮጵያ ያለባት ችግር ዘይት ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎች እጅግ በርካታ ችግሮች አሉባት፡፡ ለሁሉም ችግር መሠረቱ በአገሪቱ ተግባራዊ የተደረገው ሥርዓት ነው፡፡

እኔ ልጅ እያለሁ የዛሬ 50 ዓመት ገደማ የዳቦ ሠልፍ ነበር፣ አሁንም የዳቦ ሠልፍ አለ፡፡ የሌሎችም በርካታ መሠረታዊ ምርቶች እጥረት አለ፡፡ ይህ የሚያሳየን በአገራችን ምንም መሠረታዊ ለውጥ እንዳልመጣ ነው፡፡

ሰሞኑን ከአፍሪካ አገሮች በምግብ ራስን መቻል በተመለለከተ በኢንተርኔት የተለቀቀ (Global Food Index) ተብሎ በወጣው መረጃ ላይ፣ ከዚህ የሚከተሉ አገሮች በምግብ ዋስትና (በአፍሪካ ውስጥ) ራሳቸውን እንደቻሉ ያመላክታል፡፡

1ኛ. ሲሸልስ 96.5 በመቶ፣ 2ኛ ደቡብ አፍሪካ 96.2 በመቶ፣ 3ኛ ሞሮኮ 92.6 በመቶ፣ 4ኛ ሞሪሸስ 92.4 በመቶ፣ 5ኛ በትስዋና 98.8 በመቶ፣ 6ኛ ቱኒዝያ 88.7 በመቶ፣ 7ኛ ናምቢያ 86.5 በመቶ፣ 8ኛ ግብፅ 86.0 በመቶ፣ 9ኛ አልጄሪያ 86.0 በመቶ፣ 10ኛ ጋና 85.5 በመቶ ራሳቸውን ችለዋል፡፡

እዚህ ላይ የግድ ሊቆጨን የሚገባው ነገር እነዚህ አገሮች በቅኝ ግዛት ሥር በነበሩበት ወቅት ኢትዮጵያ ነፃነቷን ስታጣጥም የነበረች አገር ነች፡፡ ነገር ግን በልማቱ ዘርፍ ብዙ ባለመሥራታችን አሁንም እጅግ መሠረታዊ የሆኑ ጉዳዮች እያሳሰቡን ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከላይ ከተጠቀሱት አሥር አገሮች ውስጥ መካተት አለመቻሏ በእጅጉ ሊቆጨን ይገባል፡፡ መሪዎቻችን እንዲህ ዓይነት ዓለም አቀፋዊ ሪፖርት ሲወጣ የቁጭት ስሜት ሲፈጠርባቸው አይታይም፡፡

የዚህን ጽሑፍ አዘጋጅ አሁንም በጥልቅ የሚያሳስበኝ ወደ ተሻለ ዕድገት መጓዝ እንድንችል፣ አሁንም ትክክለኛውን መንገድ ለመጓዝ ሥራ አለመጀመሩ ሲሆን፣ በዚህ ምክንያት ዛሬ ያሉብን ችግሮች ወደፊት ተጠናክረው ይቀጥላሉ እንጂ መሻሻል የሚባል ነገር መጠበቅ የሚቻልበት ሁኔታ የለም፡፡

የዛሬ 30 ዓመታት ገደማ በዓለማችን በርካታ አገሮች የተሳሳተ ርዕዮተ ዓለም መከተላቸው ገብቷቸው ዕርምት ተግባራት በማከናወን አሁን አመርቂ ዕድገት ላይ ደርሰዋል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን የዛሬ 30 ዓመታት ጀምሮ መጥፎ ከነበረው የደርግ ሥርዓት እጅግ በጣም መጥፎ የሆነ የዘር ፖለቲካ ጀምረን እስካሁን በመቸገር ላይ ነን፡፡ እንዲያውም የዘር ፖለቲካው እየከረረ ሄዶ ወደ ብሔር ጦርነት ተለውጧል፡፡ በብዙ አካባቢዎች መደበኛ የሆነ የልማት ሥራ ሙሉ በሙሉ ቆሟል፡፡ በመሆኑም መጪው ጊዜ አሁን ካለው ጊዜ የከፋ እንጂ የተሻለ አይሆንም፡፡

ማንኛውም መንግሥት በሰበሰባቸው የሰዎች ዓይነት ልክ ነው ውጤት የሚያስመዝግበው፡፡ የዓብይ (ዶ/ር) መንግሥት በአሥር ሺሕ አባላቱ ላይ ዕርምጃ መውሰዱን ሰምተናል፡፡ ለመሆኑ ይህንን ያህል የሰው ብዛት በግምገማ መወገዱ በራሱ ትልቅ መልዕክት አለው፡፡ መልዕክቱም መጀመሪያ ፓርቲው ያገኘውን ሰው ሁሉ ሲያግበሰብስ ነበር ማለት ነው፡፡ የፓርቲ አባል ለመሆን የተዘጋጀ ምንም ዓይነትን የብቃት መመዘኛ አለመኖሩን ያመላክታል፡፡

በኢሕአዴና በብልፅግና ዘመን ስንሰማቸው የነበሩ ሪፖርቶች እንደሚያመላክቱት፣ ኢኮኖሚው በ10 በመቶ አደገ፣ በ11 በመቶ አደገ እየተባለ፣ ገበሬው ሚሊኒየር ሆነ እየተባለ፣ አሁን ደግሞ እጀግ ዝቅተኛና መሠረታዊ የሆነ ዘይት፣ ዳቦና የመሳሰሉ ምርቶች እጥረት መፍጠር በጭራሽ አብሮ የሚሄዱ ጉዳዮች አይደሉም፡፡ በመሆኑም ሥልጣን በእጃችሁ ያለ አመራሮች እባካችሁ ተጠንቅቃችሁ ተጓዙ፡፡ ስህተትን ማረም የሚቻልበት ደረጃ አለ፡፡ ማረም የማይቻልበት ደረጃም መኖሩን ተገንዘቡ፡፡     

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...