Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊከ134 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቀው የሰብዓዊ ድጋፍና የመልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት

ከ134 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቀው የሰብዓዊ ድጋፍና የመልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት

ቀን:

በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይና አፋር ክልሎች በተከሰተው የፀጥታ መታወክ፣ ጦርነትና የተፈጥሮ አደጋዎች ሳቢያ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖች ለችግርና ለከፋ ረሃብ መጋለጣቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ የዚህ ዓይነቱ አደጋ ከተጋረጠባቸው ወገኖች መካከል አብዛኞቹ በጦርነትና በፀጥታ መደፍረስ ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎችና በየአካባቢያቸው ሆነው ዕርዳታ በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡

እነዚህን ወገኖች መልሶ ለማቋቋምና ወደ ምርት ሥራቸው እንዲመለሱ የማድረጉ ሥራ ቀዳሚ አጀንዳ ቢሆንም ለተግባራዊነቱ ግን ለአንድ አካል ወይም ለመንግሥት ብቻ የሚተው አይደለም፡፡ ስለሆነም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪልና የሙያ ማኅበራት የየበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የጳጳሳት ጉባዔ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ያስጀመረው የ134,884,285 ብር የሰብዓዊ ድጋፍና የመልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት የርብርቡ አካል ሆኖ ይታያል፡፡

- Advertisement -

በጠቅላይ ጽሕፈት ቤቱ የስብሰባ አዳራሽ መጋቢት 6 ቀን 2014 ዓ.ም. በተከናወነው የማስጀመርያ መርሐ ግብር ሥነ ሥርዓት ላይ የጽሕፈት ቤቱ ጠቅላይ ጸሐፊ አባ ተሾመ ፍቅሬ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ በተጠቀሱት ክልሎች ሰባት ዞኖችና አሥራ አንድ ወረዳዎች ለሚገኙና እ.ኤ.አ. በ2022 ለተፈናቀሉ 227,250 ወገኖች ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን ለማቅረብ የሚያስችል ነው፡፡

በክልሎቹ በፀጥታ ችግርና በጦርነት በተጎዱ ማኅበረሰቦች ላይ የደረሰውን ስቃይና ሰቆቃ ለመቀነስና በክልሎች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶችን በመቅረፍ ረገድ ፕሮጀክቱ  የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሎ እንደታመነበት ነው የተናገሩት፡፡

ከዚህም ሌላ በጦርነት ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ወገኖችና ተፈናቃዮችን ተቀብለው የሚያስተናግዱ ማኅበረሰቦችን ችግሮች ለመካፈል ዕገዛ ያደርጋል፡፡ እንዲሁም በጦርነቱ በተጎዱ አካባቢዎች በሚኖሩ ብሔረሰቦች መካከል በተለይም በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች የሚኖሩት ማኅበራዊ ትስስራቸው እንዲጠናከር በማመቻቸት ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ጠቅላይ ጸሐፊው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ገንዘቡን ለማሰባሰብ ድጋፍ ያደረጉት የካሪታስ ዓለም አቀፍ አባልና ሌሎች የቤተ ክርስቲያን አጋር ድርጅቶች መሆናቸውን ገልጸው፣ ከእነዚህም መካከል የካቶሊክ ዕርዳታ አገልግሎት፣ ካሪታስ ተብለው የሚታወቁት የጀርመን፣ ጃፓን፣ ስዊዘርላንድ፣ አውስትራሊያ፣ ኮሪያና ቤልጂየም ተቋማት እንዲሁም ካርድ ኤአይድ፣ ማኖስ ዩኒዳስ ስፔን፣ ካፎድ/ትሮኪስ ወዘተ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ፕሮጀክት ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ተፈናቃዮችን የሚያስተናገዱ ማኅበረሰቦች የተፈናቃዮችን፣ የስደተኞችን፣ ከስደት ተመላሾች የምግብ ዋስትና እንደሚያረጋግጥ፣ የመጠለያ ድጋፍና አስፈላጊ ቁሳቁሶችን በማቅረብ መሠረታዊ ኑሮዋቸውንና የመጠለያ ፍላጎቶቻቸውን መመለስ ያስችላል ያሉት ኃላፊው፣ ከዚህም በተጨማሪ በጦርነት በተጎዱ አካባቢዎች የሚኖሩ የተለያዩ ብሐረሰቦች እርስበርስ መተማመንና መቻቻልን በማጎልበት የሰላም ግንባታ ዕርምጃዎችን ያጠናክራል ብላ ቤተ ክርስቲያን በፅኑ እንደምታምንም አመልክተዋል፡፡

ከአባ ተሾመ ፍቅሬ (ዶ/ር) ማብራሪያ ለመረዳት እንደተቻለው፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በመላው ኢትዮጵያ በምታከናውናቸው የማኅበራዊ ልማት ፕሮጀክቶች በቢሊዮን የሚቆጠር መዋለ ነዋይ በመመደብ በትምህርት፣ በጤና፣ በንፁህ ውኃ፣ እንዲሁም በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ለተጎዱ ወገኖች አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ከሰባት ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን በየዓመቱ ተግባራዊ ታደርጋለች፡፡

ከዚህ ቀደም በትግራይ፣ በአማራና በአፋር በተከሰተው ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለመደገፍ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፎችን ማድረጓን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...