Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊዕፎይታን ያገኙ የጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚዎች

ዕፎይታን ያገኙ የጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚዎች

ቀን:

አቶ በፍቃዱ ጌታሁን የሚኖሩት በሸዋሮቢት ከተማ በዙጢ ወረዳ በላየንጮ ቀበሌ ነው፡፡ በእርሻ የሚተዳደሩትና የሦስት ልጆች አባት  የሆኑት አቶ በፈቃዱ፣ የስኳር ሕመም እንዳለባቸው ያወቁት የዛሬ አሥር ዓመት ነበር፡፡

እሳቸውና ቤተሰባቸው በወቅቱ በ80 ብር የጤና መድኅን ሽፋን እንደገቡ ይገልጻሉ፡፡ ሕመማቸው እየባሰባቸው በመሄዱ ወደ ደብረብርሃን ከፍተኛ ሪፈራል ሆስፒታል ሪፈር ተብለውና አልጋ ይዘው ይታከሙ እንደነበር ያስታወሱት አቶ በፈቃዱ፣ ከክኒን ወደ ኢንሱሊን መርፌ እንዲቀይሩ በተባሉበት ጊዜ የጤና መድን ሽፋን ባይኖራቸው ኖሮ ለመከታም ሊከብዳቸው ይችል እንደነበር ይገልጻሉ፡፡

ከደብረ ብርሃን ሕክምናቸው ሲመለሱ በጦርነቱ ውድመት ደርሶበት በነበረውና ድጋሚ ሥራ በጀመረው የሸዋሮቢት ጤና ጣቢያ እሳቸውም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው በጤና በመድን ሽፋን እየታከሙ እንደሆነ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡  

የኢትዮጵያ የጤና መድኅን ኤጀንሲ በደብረ ብርሃን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሥር በሚገኙት የሸዋሮቢት ወረዳዎች በጤና መድኅን ሥር የተጠለሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚነት አስመልክቶ ረቡዕ መጋቢት 14 ቀን 2014 ዓ.ም. ለሚዲያ አካላት የመስክ ጉብኝት አዘጋጅቶ ነበር፡፡

ከአዲስ አበባ በ200 ኪሎ ሜትር ርቀት በስተ ሰሜን የምትገኘው ጥንታዊቷ ሸዋሮቢት ከተማ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ በተፈረጀው ሕወሓት ታጣቂዎች ወረራ ከተፈጸመባቸው ከተሞች አንዷ በመሆኗ ብዙ ጉዳቶችን አስተናግዳለች፡፡

በከተማ የሚገኘው የሸዋሮቢት ጤና ጣቢያም ከጥቃት ሰለባዎቹ አንዱ የነበረ ሲሆን፣ ከአምስት እስከ አሥር ሚሊዮን የሚገመት ንብረት እንደወደመበት የሸዋሮቢት ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ተወካይ አቶ አድማሱ አታሎ ይገልጻሉ፡፡

በከተማዋም ብቸኛው ጤና ጣቢያ እንደሆነና በከተማዋ ከሚኖሩት 62 ሺሕ ነዋሪዎች በተጨማሪም ለአምስት ከአጎራባች አካባቢዎች ማለትም ከአፋር፣ ከኦሮሚያ፣ ከቀዎት እንዲሁም ከአጣዬ የሚመጡ ታካሚዎችን ጨምሮ ከ100 ሺሕ በላይ ተገልጋዮች የሚጠቀሙበት ነው፡፡

አቶ አድማሱ እንደሚሉት፣ ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት የጤና መድኅን ሽፋን የተጀመረ ሲሆን፣ እስካሁንም ከ9,973 በላይ የአካባቢው ነዋሪዎችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡

ኃላፊው እንደሚሉት፣ የተጠቃሚውን ቁጥር የማሳደግ ዕቅድ በመድኃኒት እጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

በጤና ጣቢያው እንደ አቶ ፍቃዱ ጌታሁን ያሉ በርካታ ታካሚዎች የተገኙ ሲሆን፣ የልብ፣ የሳንባ፣ የኤች አይቪ የማሕፀን ዕጢና የተለያዩ ሕመም ያለባቸው ናቸው፡፡ አባትና ልጅ ጎን ለጎን ቀዶ ሕክምና ተደርጎላቸው የተገኙም ይገኙበታል፡፡

ሁሉንም የሚያስማማቸው አንድ ነገር ቢኖር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩ አርሶ አደሮች መሆናቸውና እጃቸው ላይ ከዕለት ጉርስ ያለፈ ገቢ የሌላቸው መሆናቸው ነው፡፡

ለሕክምና የሚከፍሉ ቢሆን ደግሞ የመኖር ዕድላቸው የመነመነ፣ በሕይወት ቢኖሩም ትዳራቸው ተበትኖ ቤት ንብረት አልባና ኑሮዋቸው ጎዳና እንደነበር በእንባ በታጀበው ፊታቸው በሥፍራው ለተገኙ ጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፡፡

የጤና መድን በመግባታቸው ‹‹የሕክምና ወጪ ከማውጣት ዕፎይታን ሰጥቶናል›› የሚሉት ተገልጋዮቹ፣  ጤና ጣቢያው ሥራ ሲጀምር ተቋርጦ የነበረው የጤና መድኅን ሽፋን በመጀመሩ መታከም መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጤና መድኅን በኢትዮጵያ ‹‹ኅብረተሰቡን ያማከለ የጤና ኢንሹራንስ›› በሚል መደበኛ ባልሆነ ክፍለ ኢኮኖሚ የተሰማራውን ሰፊ የኅብረተሰብ ክፍል፣ አርሶ አደሩን፣ ነጋዴውንና በግል ሥራ የተሰማራውን የሚያቀፍ ነው፡፡

ይህ የጤና መድኅን በ2003 ዓ.ም. በትግራይ፣ በአማራ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እንዲሁም በኦሮሚያ በ13 ወረዳዎች በሙከራ ደረጃ የተጀመረ ሲሆን፣ ዛሬ ላይ በሁሉም ክልሎችና በሁለቱም ከተማ አስተዳደሮች ከ50 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች አገልግሎትን እየሰጠ ይገኛል፡፡

አቶ ጉደታ አበበ በኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት የአባላትና ምዝገባና መዋጮ ዳይሬክተር ሲሆኑ፣ እስካሁን የጎላ ችግር አለመታየቱን ገልጸዋል፡፡ በዘመድ አዝማድ ምዝገባ ማካሄድና በጤና ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግሮች የነበሩ ቢሆንም፣ እነዚህን ለማስተካከል በየጤና ጣቢያው አንድ አንድ ኦፊሰር በማሰማራት ችግሮቹ እየተቃለሉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...