በኢትዮጵያ ያለው የኮቪድ ክትባት ፍላጎት ዝቅተኛ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የኮሮና ቫይረስ ክትባት የማምረት ዕቅዱን መሰረዙን የኢትዮጵያ መድኃኒት ፋብሪካ አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ መድኃኒት ፋብሪካ ሥራ አስፈጻሚ ሞሐመድ ኑሪ (ዶ/ር)፣ ፋብሪካው የኮሮና ቫይረስ ክትባት ለማምረት የሚያስችለውን ጥናት በማድረግ ላይ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ክትባቱን የማምረት ዕቅዱን መሰረዙን አስረድተው፣ ለዚህም እንደ ምክንያት ያቀረቡት በኢትዮጵያ ያለው የኮቪድ ክትባት ፍላጎት ዝቅተኛ መሆን አንደኛው ነው፡፡ ስሙን መግለጽ ካልፈለጉት የቻይና ኩባንያ ጋር በጥምረት ለማምረት ተስማምተው እንደነበር፣ ነገር ግን የኅብረተሰቡ የመከተብ ፍላጎት ዝቅተኛ ከመሆኑም በተጨማሪ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት አነስተኛ ሆኗል የሚለው አመለካከት ወደ ማምረት እንዳይገቡ እንዳደረጋቸው ሞሐመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
ሌሎች የክትባት ዓይነቶችን ለማምረት ፍላጎት እንዳለው ገልጸው፣ ነገር ግን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመድኃኒትና ለሕክምና ግብዓት አምራቾች ፈተና እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡
ፋብሪካቸው በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ፓራሲታሞልን ጨምሮ ሲያመርታቸው የነበሩ በርካታ መድኃኒቶችን ማምረት ማቆሙን፣ በአሁኑ ወቅት ከ30 በመቶ በታች አቅማቸው እያመረቱ መሆኑንና የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ካልተፈታ፣ ምርታቸው አሁን ካለውም በታች እንደሚቀንስ አክለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የተለያዩ መድኃኒቶችን ወደ ሱዳን፣ ሶማሌላንድ፣ ደቡብ ሱዳንና ሌሎችም አገሮች በመላክ በዓመት እስከ አምስት ሚሊዮን ዶላር ያገኙ እንደነበር የገለጹት ሞሐመድ (ዶ/ር)፣ በአሁኑ ወቅት ወደ ውጭ መላክ ሙሉ ለሙሉ ማቆማቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መድኃኒት ፋብሪካ በዓመት እስከ 25 ሚሊዮን ዶላር የመጠቀም አቅም ቢኖረውም፣ የሚያገኘው የውጭ ምንዛሪ ከ20 በመቶ በታች እንደሆነም አብራርተዋል፡፡
የመድኃኒትና የሕክምና ግብዓቶች አምራቾች ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መመርያ መሠረት ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ባስቀመጠው መመርያ መሠረት፣ የውጭ ምንዛሪ እንዲሰጣቸው በማኅበራቸው በኩል መጠየቃቸውን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የመድኃኒትና የሕክምና ግብዓት አምራቾች ማኅበር ፕሬዚዳንትና የክሊች ኢስትሮ ባዮቴክ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል ዋቅቶሌ፣ የመድኃኒት አምራቾች በሌሎች ዘርፎች ከተሰማሩ አምራቾችና አስመጪዎች ጋር እኩል እየተስተናገዱ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡
ነገር ግን የመድኃኒትና ሕክምና ምርት ዘርፍ ከሌሎች ቢዝነሶች አንፃር የሚያስገኘው ትርፍ ዝቅተኛ በመሆኑ፣ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ለማቅረብ ፍላጎት እንዳይኖራቸው አድርጓል ብለዋል። አምራቾቹ ከአጠቃላዩ የኢትዮጵያ የመድኃኒት ፍጆታ 40 በመቶ የሚሆነውን የመሸፈን አቅም ቢኖራቸውም እየሸፈኑ የሚገኙት ከአምስት በመቶ ያልበለጠውን እንደሆነ የገለጹት አቶ ዳንኤል፣ በአጠቃላይ ከማምረት አቅማቸው ከ25 በመቶ በታች የሚሆነውን አቅማቸውን እየተጠቀሙ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ለዚህም ለዘርፉ ከሚመደበው የውጭ ምንዛሪ ውስጥ ከ65 በመቶ በላይ የሚሆነው ለአምራቾች ብቻ እንዲመደብና ቀሪው 35 በመቶ ለአስመጪዎች እንዲሆን ጠይቀዋል። እንደ አቶ ዳንኤል ገለጻ፣ የውጭ ምንዛሪ ምደባን ጨምሮ ለመድኃኒትና የሕክምና ግብዓት አምራቾች የወጡ ፖሊሲዎች በተገቢው መንገድ እየተተገበሩ አይደለም፡፡
በመመርያ አለመኖር ምክንያትም ያላግባብ ታክስ እየከፈሉ መሆኑን ገልጸው ለጤና ሚኒስቴር፣ ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ለገቢዎች ሚኒስቴር፣ ለጉምሩክ ኮሚሽንና ለሌሎችም ከዘርፉ ጋር የሚገናኙ የመንግሥት ተቋማት ማስተካከያ እንዲደረግ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ማኅበሩ 13 አባላት ያሉት ሲሆን፣ በአጠቃላይ በዓመት ከ160 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ያስፈልጋቸዋል፤›› በማለት፣ ከሚያመርቷቸው ምርቶችም 70 በመቶ የሚሆነውን ለመንግሥታዊ የሕክምና ተቋማት የሚያቀርቡ መሆናቸውን፣ እንዲሁም 30 በመቶ ለግል እንደሚያቀርቡ አቶ ዳንኤል አስረድተዋል፡፡