Thursday, September 21, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ያልቻሉ ኩባንያዎች በአገር ውስጥ እንዲሸጡ ተጠየቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሦስት ትልልቅ የጫማ ፋብሪካዎች ማምረት አቋርጠዋል

ኢትዮጵያ ከአሜሪካ መንግሥት ታገኘው የነበረው ከኮታና ከቀረጥ ነፃ የንግድ ዕድል (አጎዋ) በመነሳቱ ምክንያት፣ የገበያ ዕድላቸው የተዘጋባቸው የቆዳ ውጤቶች አምራች የውጭ ኩባንዎች ከምርታቸው ውስጥ የተወሰነውን ለአገር ውስጥ ገበያ ለማቅረብ እንዲፈቀድላቸው፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ለኢንቨስትመንት ኮሚሽንና ለገንዘብ ሚኒስቴር ጥያቄ አቀረበ፡፡

ፋብሪካዎቹ ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ ከመንግሥት ጋር የተስማሙበት ውል፣ የሚያመርቱትን የቆዳ ውጤት ሙሉ ለሙሉ ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ የሚል ሲሆን፣ ፋብሪካዎቹም የአሜሪካን ከቀረጥ ነፃ ገበያ ታሳቢ አድርገው ወደ ኢትዮጰያ ገብተዋል፡፡ ይሁንና የአሜሪካ መንግሥት ኢትዮጵያ ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ ለአጎዋ ተጠቃሚነት የሚያበቁ መሥፈርቶችን አላሟላችም በሚል ተጠቃሚ እንዳትሆን የተጣለው ዕግድ ከእ.አ.አ. ጥር 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ተፈጻሚ መሆን ጀምሯል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም የአጓዋ ዕድል በታገዱ 64 በመቶ የሚሆነውን ቆዳና የቆዳ ውጤት ወደ አሜሪካ ለመላክ አስቸጋሪ ሁኔታ መፈጠሩን አስታውቆ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ላለፉት 21 ዓመታት አጎዋን ተጠቅማ በተለይ የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶችን ወደ አሜሪካ ከቀረጥ ነፃ ስትክል የቆየች ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚመረቱ ጫማዎችና የቆዳ ውጤቶች ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው መዳረሻው አሜሪካ ነበር፡፡

የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ፍርጀቦ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በኮቪድ-19 እጅጉን ሲፈተኑ የከረሙት ወደ ውጭ ላኪ የቆዳ ውጤት ማምረቻ ፋብሪካዎች፣ አሁን ደግሞ የአጎዋ መታገድ እጅጉን ጎድቶዋቸዋል፡፡ በቆዳ፣ በጫማ፣ በጓንት፣ እንዲሁም ቦርሳና ኮት ባሉ የቆዳ አልባሳትና ዕቃዎች ከተሰማሩ ፋብሪካዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ እየተንቀሳቀሱ ያሉት በአቅማቸው 50 በመቶ በታች ነው፡፡

ሁጃን (Huajian Shoe Factory)፣ ጆርጅ ሹ (George Shoe Ethiopia Plc.) እና ዮባንግ (Youbang Manufacturing Of Shoes Plc) የሚባሉት ትልልቅ ጫማ አምራች የውጭ ፋብሪካዎች ሙሉ ለሙሉ እያመረቱ አይደሉም፡፡ እነዚህ ኩባንያዎቹ ኮቪድ-19 ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ሲፈተኑ የቆዩ ቢሆኑም፣ አሁን ደግሞ የአጎዋ ዕድል መቋረጡ ሥራ እንዳይጀምሩ አድርጓቸዋል፡፡

ከአጎዋ መቋረጥም ተጨማሪ የቆዳ ውጤቶች ኤክስፖርት ዘርፉ በኮቪድ-19፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትና ተያይዞ በመጣው የፕሮፖጋንዳ ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ ብርሃኑ ገለጻ፣ በበጀት ዓመቱ ስምንት ወራት ከአጠቃላይ ዘርፉ 51 ሚሊዮን የአሜካ ዶላር ለማግኘት ታቅዶ ማሳካት የተቻለው 27.3 ሚሊዮን ዶላር ያህሉን ነው፣ ይህም የዕቅዱን 53.3 በመቶ የሚሸፍን ነው፡፡ የዘርፉን ዕቅድ በትልቁ የጎዳው በጫማ ኤክስፖርት ላይ ማሳካት የተቻለው 30 በመቶ ብቻ በመሆኑ ነው፡፡ ይኼም ከሦስት ትልልቅ ጫማ አምራች ፋብሪካዎች ምርት ማቆም ጋር እንደሚያያዝ አቶ ብርሃኑ አስረድተዋል፡፡

የፋብሪካዎቹ አንደኛው ጥያቄ ሲገቡ የተስማሙበት ውል ተሻሽሎ ለአገር ውስጥ ገበያ ምርታቸውን የሚያቀርቡበት መንገድ የሚቻል እንደሆነ የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ጉዳዩ ውል ማሻሻልን የሚጠይቅ በመሆኑ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንደማይመለስ አስረድተዋል፡፡ ይህንን ጥያቄ መመለስ የሚችሉት ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ገንዘብ ሚኒስቴርና የጠቅላይ ሚኒስተር ጽሕፈት ቤት በመሆናቸው፣ ሚኒስቴሩ ለእነዚህ አካላት ጥያቄውን ማቅረቡን አስረድተዋል፡፡

ከፋብሪካዎቹ ጋር የተገባውን ውሉ የማሻሻል ሥልጣን ያላቸው እነዚህ አካላት በጉዳዩ ላይ ውይይት እያደረጉ መሆኑንና ጥያቄ ዕልባት ለማግኘት ጫፍ ላይ መሆኑን አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል፡፡

ፋብሪካዎቹ ያቀረቡት ጥያቄ የምርታቸውን 50 በመቶ ለአገር ውስጥ ገበያ ለማቅረብ ቢሆንም፣ ይህንን ያህል መጠን ላይፈቀድላቸው እንደሚችል የጠቆሙት አቶ ብርሃኑ ‹‹20 በመቶውን እንዲያቀርቡ ሊፈቀድላቸው ይችላል፤›› ብለዋል፡፡ ጥያቄው ተቀባይነት ካገኘ ከዚህ ዕድል ተጠቃሚ የሚሆኑት የቆዳ ምርቶችን ሙሉ ለሙሉ ኤክስፖርት ብቻ ሲያደርጉ የነበሩ ዘጠኝ የቆዳ፣ አራት የጫማና ሁለት የጓንት የውጭ ፋብሪካዎች ናቸው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ከዘርፉ ይገኝ የነበረው ገቢ በአጎዋ ምክንያት እንዳይታጣ ወደ አፍሪካና መካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ገበያ የማፈላለግ ሥራ እንደተጀመረ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ሲባል በተለይ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ሥራዎችን ለማጠናከርና በሰጥቶ መቀበል መርህ የአገሮቹ ገበያ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡበትና የኢትዮጵያዎቹም የሚጠቀሙበትን ሁኔታ ለመፍጠር የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች ከአገሮቹ ባለሥልጣናት ጋር ንግግር እያደረጉ መሆኑ ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች