Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየጭካኔ በትሩን ኢትዮጵያውያን ላይ ያበረታው የሳዑዲ እስር ቤት

የጭካኔ በትሩን ኢትዮጵያውያን ላይ ያበረታው የሳዑዲ እስር ቤት

ቀን:

ከቡታጅራ ከተማ ተነስታ ከአራት ዓመት በፊት በሕገወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ ያቀናችው ለይላ አወል፣ ከአስከፊው የአራት ወራት የሳዑዲ እስር ቤት ቆይታ በኋላ፣ ረዕቡ መጋቢት 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ገደማ በአንድ እጇ ቋጠሮዋን የሸከፈችበትን የላስቲክ ከረጢት በሌላኛው ደግሞ የሦስት ዓመት ልጇን ይዛ አዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ ከአውሮፕላን ስትወርድ፣ የረገጠችውን መሬት እየሳመች ከማልቀስ በስተቀር ያሳለፈችውን ሰቆቃ የሚገልጽ ድርጊት አልነበራትም፡፡ አዲስ አበባ ስትደርስ በሚኒስትሮችና ሌሎች ባለሥልጣናት የተደረገላትን አቀባበል ልብ ያለችውም አይመስልም፡፡

‹‹ኤምባሲው አንድም ቀን ዞር ብሎ ዓይቶን አያውቅም፡፡ በሪያድ ያለውን የእኛ ኤምባሲ ከመጠበቅ ጭራሽኑ የሉም ብሎ መቀመጥ ይቀላል፤›› ስትል ያሳለፈችውን ጭንቀትና ሰቆቋ ተናግራለች፡፡

ለይላ እንዲሁ እዚህ ዓይነት ምሬት ላይ አልደረሰችም በላስቲክ ከያዘችው ልብስ ጋር ወደ አገር ቤት ይዛው የመጣችው ልጇ አንድ ወር ሙሉ እስር ቤት ውስጥ ታሞ ሕክምና አላገኘም፡፡ ሕክምና ለማግኘት የታሰሩበትን ክፍል በር ሲያንኳኩ ጠባቂዎች ይሰጧቸው የነበረው ምላሽ ‹‹ሰው ሲሞት ብቻ ነው የምታንኳኩት›› የሚል እንደነበር ከመከራው ወጥታ አዲስ አበባ ከገባች በኋላም አላባራ ያለውን እንባዋን እያፈሰሰች ትናገራለች፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹በሳምንት አንዴ ወይም ደስ ያላቸው ቀን የታመመ አለ ወይ ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ሰው በድንገት ታሞ ትንፋሽ ቢያጥረው ግን ይሙት አያገባንም አታንኳኩብን ነው የሚሉት፤›› በማለት የከረሙበትን ሁኔታ ታስረዳለች፡፡

የሦስት ዓመት ልጇ አንድ ወር ሙሉ ታሞ ያለ ሕክምና ሲሰቃይ ዓይኑን እያየች መቀመጥ በራሱ ለእናት አስከፊ ቢሆንም፣ ይሄ እስር ቤት ውስጥ ካሳለፈቻቸው ሌሎች ሁኔታዎች አንፃር ከባዱ ላይባል ይችላል፡፡ በሳዑዲ እስር ቤት 300 እና 400 ሆነው በታጎሩበት ክፍል ውስጥ ሰዎች ታመውም ሆነው ራሳቸውን አጥፍተው ሲሞቱ፣ ሬሳቸው አጠገብ መዋል ሲሰማ ሐሰት የሚመስል የሳዑዲ እስር ቤት እውነታ መሆኑን ታስረዳለች፡፡

ለይላ እስር ቤት ውስጥ ባለው ሁኔታ ተስፋ የቆረጠች፣ በእስር ቤት ጠባቂዎች በሆነው ባልሆነው መሰደብ ያስመረራት አንዲት ኢትዮጵያዊት ስደተኛ ምሽት አራት ሰዓት አካባቢ እራሷን ካጠፋች በኋላ ያሳለፉትን እያነባች ትናገራለች፡-

‹‹አንዷ ክፍላችን ውስጥ ማታ አራት ሰዓት አካባቢ ታንቃ ስትሞት ጠባቂዎች እንዲመጡ በሩን ስንደበድብ አደርን መጥተው ራሱ አላዩንም፡፡ ጠዋት ላይም ቁርስ አንበላም ብለን በሩን ብንደበድብም ዝም አሉን፡፡ ምሣ አመጡልን አሁንም አንበላም ብለን በሩን ስንደበድብ፣ በሩን አታንኳኩብን ብለው ሰደቡን፡፡ ሲጨንቀን ኤምባሲ ብንደውል እንመጣለን እያሉ እነሱም ቀሩ፡፡ ወላሂ ማታ የተሰቀለች ልጅ መግሪብ (ምሽት 12፡30 አካባቢ) ድረስ አስበው ቀኑን ሙሉ ሬሳዋ ተሰቅሎ እኛ ቁጭ ብለን እያየናት ዋልን፡፡ ጠባቂዎቹ ሲመሽ መጥተው የተሰቀለውን ሬሳዋን ፎቶ አንስተው ሲጨርሱ እኛ አንነካውም ሴቶች እናንተ ወደ ውጪ አውጡት አሉን፡፡ ወላሂ እኛ ነን አውጥተን የጣልናት፤››

‹‹አንድ ጊዜም አንዷን ሐኪም ቤት አንወስዳትም ብለውን መሬት ላይ ቁጭ ባለችበት ደሟ መሬት ላይ እየፈሰሰ ሁለት ልጆቿን ጥላ ሞተች፡፡ ስትሞት ተነስታችሁ አውጧት አሉን እሷንም አውጥተን ጣልን፡፡ ኤምባሲ መጥቶ አላያትም፤›› በማለት ሌላ ገጠመኝ አንስታ በሳዑዲ እስር ቤቶች ውስጥ ሰብዓዊነት እጅጉን መርከሱን ታስረዳለች፡፡

ኢትጵያውያን ኑሯቸውን ለማሻሻል ከሚፈልሱባቸው የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ውስጥ ቀዳሚ የሆነችው ሳዑዲ ዓረቢያ ለስደተኞች የምታደርገውን አቀባበል በተመለከተ ጥሩ ስም የላትም፡፡ ሒዩማን ራይትስዎች የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም በ2011 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርት ሳዑዲ ከአሥር ያላነሱ ስደተኞችን የምታጉርበት እስር ቤትና ማቆያ ሥፍራዎች አሏት፡፡ በአንድ ማጎሪያ ክፍል ውስጥ ከ300 ያላነሱ እስረኞች እንዲኖሩ የሚደረጉ ሲሆን፣ ሴቶችና ወንዶች አንድ ላይ የሚታሰሩባቸው ክፍሎችም እንዳሉ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

በሳዑዲ ዓረቢያ 750 ሺሕ ገደማ ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩ የሚገመት ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 450 ሺሕ ያህሉ ወደ አገሪቱ የገቡት በሕገወጥ መንገድ እንደሚሆን ይታሰባል፡፡  ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥም የሳዑዲ መንግሥት 352 ሺሕ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን እንዲመለሱ አድርጓል፡፡

ምክንያቱ ይሄ ነው ተብሎ ባይጠቀስም ከሌሎች ስደተኞች ይልቅ እንግልቱ የሚጠናባቸው ኢትዮጵያውያን በተለይ ከኮቪድ-19 መከሰት በኋላ ያለበት ሁኔታ እጅግ አስቸጋሪ መሆኑ ይነገራል፡፡ ከሳዑዲ ዓረቢያ እስር ቤቶች ውስጥ የሚወጡ ቪዲዮዎች፣ ታሳሪዎች እጅግ ብዙ ሰዎች በአንድ ክፍል ውስጥ ታጉረው፣ ጥቁር ፌስታል ለብሰውና የቆዳ በሽታ በሚመስሉ ሕመሞች ተጠቅተው ያሳያሉ፡፡ ታሳሪዎቹ ውስጥ ሕፃናት፣ ነፍሰ ጡሮችና ሕመም ያለባቸው መኖራቸው ሁኔታውን አክብዶታል፡፡ ምግብና ሕክምና አለማግኘት ተጨማሪ ፈተናዎች ናቸው፡፡

ከጅማ ተነስታ ዱባይ ከገባች በኋላ ከሦስት ዓመታት በፊት ወደ ሳዑዲ የተሻገረችው ራህማ ኡመር፣ ረዕቡ መጋቢት 21 ቀን 2014 ዓ.ም. አዲስ አበባ የደረሰችው ስትታሰር አድርጋ የነበረውንና ላለፉት አምስት ወራት የለበሰችውን ጥቁር አባያ አድርጋ  ነው፡፡

ራህማ በሳዑዲ ሦስት ዓመት ሙሉ ቆይታ ፌስታል ብቻ አንጠልጥላ አዲስ አበባ መድረሷን እንደ ምሬት አትቆጥረውም፡፡ ወደ አገሯ መመለሷን ብቻ እያሰበች ከአውሮፕላን ወርዳ የአየር ማረፊያው ግቢ ውስጥ ለኮቪድ-19 ምርመራ ወደ ተዘጋጀው ድንኳን በአየር መንገዱ መኪና እየሄደች ደጋግማ ‹‹አላህምዱልላሂ›› ስትል ትሰማለች፡፡ ጭንቀቷ አሁንም እዚያው ለቀሩት ኢትዮጵያውያን ነው፡፡

ከ‹‹አላህምዱልላሂ›› ቀጥሎ የመጣው ንግግሯ ‹‹እኔስ በአምስት ወሬ መጣሁ፡፡ እዚያ ስምንት ወርና አንድ ዓመት የታሰሩ አሉ፡፡ ወረቀታቸው ገና አልመጣም፡፡ ቁጭ ብለው እያለቀሱ ነው፤›› የሚል ነው፡፡

ብዙ ታሳሪዎች ሕክምና አያገኙም፡፡ እዚያው እስር ቤት ውስጥ ታጉረው እንደሚገኙ የምትናገረው ራህማ ታሳሪዎች ውስጥ የካንሰር ሕመምተኛ የሆነች ሴት እንደምትገኝ ታስረዳለች፡፡ ‹‹የሆነች ልጅ ካንሰር ይዟት እጇ እዚያው እስር ቤት ውስጥ ተቆረጠ፡፡ ኤምባሲ የት ደረሽ አላላትም፡፡ አሁን እንኳን ዕድል ገጥሟት አልመጣችም እዚያው እስር ቤት ውስጥ ነች፤›› ብላለች፡፡

ለመተኛ የሚሆን ፍራሽ እንኳን የማያገኙት ኢትዮጵያውያን የሳዑዲ ስደተኞች ልብስና መኝታቸው ‹‹ኪስ›› እያሉ የሚጠሩት ጥቁር ላስቲክ ነው፡፡ የታመሙ፣ ነፍሰጡር፣ አራስ ሴቶችም ሆኑ ሕፃናት አብረው በሚታጎሩበት ክፍል ውስጥ መሬት ላይ ታፍጎ ለመዋል መሬት ላይ መተኛት ይገደዳሉ፡፡

ራህማ የሳዑዲ ፖሊሶች ፈቃድ የሌላቸው የሌሎች አገሮች ዜጎችም የሚያስሩ ቢሆንም፣  ለኢትዮጵያውያን ያላቸው አመለካከትና የሚሰነዝሯቸው ስድቦች እጅግ የሚጎዱ መሆናቸውን ትናገራለች፡፡

‹‹ከታመምን ሕክምና አናገኝም፡፡ ታመናል ካልናቸው በጥፊ ነው የሚመቱን፣ እናንተ ኢትጵያውያን ቆሻሻ ናችሁ፣ አገር የላችሁም፣ መንግሥታችሁ አይፈልጋችሁም እያሉ ይሰድቡናል፤›› በማለት ምሬቷን ገልጻለች፡፡

በሳዑዲ ዘጠኝ ዓመታት የቆየችው ሙንታ ጀማል ስለ ሳዑዲ እስር ቤት ጠባቂዎች ስድብ ስታስረዳ ‹‹አንድ ፖሊስ የአገራችሁ መንግሥት አይፈልጋችሁም፡፡ እኛም አንፈልጋችሁም፡፡ ቆሻሻ እንኳን ቆሻሻ ነው ተብሎ ይጣላል፣ እናንተን የሚያያችሁም የለም፣ እኛ ምን እናድርጋችሁ? አለን ወላሂ የዚያኔ ነው ልቤ የተነካው እንደዚያ ያለቀስኩበት ቀን የለም፤›› በማለት ተናግራለች፡፡ ያለምንም ወንጀል አምስት ወራት እንደታሰረች የምትገልጸው ሙንታ፣ ለዚህ ሁሉ መከራ የዳረጋት የፈቃድ ወረቀቷ አለመታደሱ ብቻ መሆኑን ትናገራለች፡፡

በዘግናኝ ሁነቶች የተሞላው የኢትዮጵያውያኑ የሳዑዲ እስር ቤት ቆይታ የተለየ እንክብካቤ ለሚያስፈልጋቸው ነፍሰ ጡርና ሌሎች ሴቶች ሕይወታቸውን በሰቆቃ ስለመሙላቱ ይነገራል፡፡ በሪያድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እስረኞቹን ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ምዝገባ ካደረገላቸው በኋላ ቀሪውን አጭር ጊዜ መጠበቅ አቅቷቸው የአዕምሮ ሕመም ያጋጠማቸው ሴቶች እንዳሉ ተመላሾቹ ይናገራሉ፡፡

ለአራት ወራት የታሰረችው አስማ በላይ፣ ‹‹ብዙ እህቶቻችን ቀውሰዋል፣ ሞተው ራሱ በሥነ ሥርዓት መጥተው አስከሬን አያነሱም፣ መጥተው አስከሬኑን በእርግጫ ነው የሚመቱት ይሄ ሁሉ ግፍ ነው፤›› ትላለች፡፡ ታሳሪዎቹ የሚጠቀሙበት መፀዳጃ ቤት የቆሸሸ ከመሆኑ ባሻገር እዚያው የሚተኙበት ክፍል ውስጥ መሆኑን ታስረዳለች፡፡

አስማ ‹‹አንዲት ሴት ያለሞዴስ አትቀመጥም፡፡ እነሱ በ15 ቀን አንድ ሞዴስ ብቻ ነበር የሚሰጡት፤ ልብሳችንን እየቀደድን ነው የምንጠቀመው፤›› ብላለች፡፡

በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ ቆይተው የከረሙት ሴቶች በሙሉ እነሱ ካሳለፉት መከራ ይልቅ በእስር ላይ ያሉት ወንዶች ስቃይ እንደሚልቅ ያስረዳሉ፡፡ ጠባቂዎቹ ለሴቶች ትንሽም ቢሆን በሚያሳዩት ርህራሔ ምግብ ለማግኘት ይታደላሉ ወንዶቹ ግን የሚያገኙት ምግብ በጣም ትንሽ መሆኑን፣ ልብስ ስለሌላቸው ራሳቸውን በላስቲክ እንደሚጠቀልሉና አንዳንዶቹ እግራቸው ጭምር መንቀሳቀስ እንደማይችል ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈው ዓመት በተከታታይ በረራዎች ከ40 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው ቢመልስም አሁንም ከ100 ሺሕ በላይ የሚሆኑት በሳዑዲ እስር ቤቶች ውስጥ እየማቀቁ ነው፡፡

መንግሥት ጥር ወር ላይ በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ የተመራና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ በሳዑዲ ዓረቢያ  የኢፌዴሪ ባለ ሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ክቡር ሌንጮ ባቲ፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ክቡር ተቀዳሚ ሙፍቲሕ ሐጂ ኡመር ኢድሪስ (ዶ/ር) እና ሌሎች የመንግሥትና የሃይማኖት ኃላፊዎችን ያካተተ ከፍተኛ ልዑካን ቡድን በሳዑዲ ዓረቢያ በመላክ በአገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ጉዳይ መክሯል፡፡ በሳዑዲ ለአራት ቀናት የቆዩት የልዑኩ አባላት ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር ሲወያዩ ሰንብተው እስር ቤት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አያያዝ ስለሚሻሻልበት፣ የመኖሪያ ፈቃዳቸው ተቃጥሎ ቅጣቶች የሚጠብቃቸው ነገር ግን በራሳቸው ገንዘብ ተሳፍረው አገራቸው መግባት ለሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ቅጣት ተነስቶላቸው በምሕረት ወደ አገራቸው የሚመለሱበት መንገድ ላይ መወያየቱ ተገልጾ ነበር፡፡ እስር ቤት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው መመለስም የባለሥልጣናቱ የውይይት አጀንዳ ነበር፡፡

ይሄ ንግግር ከተደረገ ከሁለት ወራት በኋላ ባለፈው ረዕቡ መጋቢት 21 ቀን 2014 ዓ.ም. በተደረጉት ሁለት በረራዎች፣ የመጀመርያዎቹ 936 ኢትጵያውያን ከሪያድ ወደ አገር ቤት ተመልሰዋል፡፡ ዓርብ ዕለት ደግሞ ሁለት ሺሕ ገደማ የሚሆኑ የመጀመርያዎቹ የጅዳ ተመላሾች አዲስ አበባ ደርሰዋል፡፡ በእነዚህ በረራዎች ቅድሚያ የተሰጣቸው ሕፃናትና ሴቶች ናቸው፡፡

በየአንዳንድ ቀን ልዩነት በቀን ሦስቴ በረራ በማድረግ ከሰባት እስከ 11 ወራት በሚወስድ ጊዜ ውስጥ 102 ሺሕ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው ለመመለስ ያቀደው መንግሥት እስካሁን ከ45 ሺሕ በላይ ስደተኞችን መዝግቧል፡፡ የምዝገባ ሒደቱ ብሔራዊ መረጃ፣ ኢሚግሬሽንና ዜግነት ጎዳዮች ፌዴራል ፖሊስ፣ ስደትና ስደት ተመላሾች አስተዳደር በሳዑዲ ዓረቢያ ካለው ኤምባሲው ጋር በመሆን የሚከናወን ነው፡፡  ምዝገባው ሲከናወን ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ያለው ሙሉ የስደተኞቹ መረጃ የሚሰበሰብ ሲሆን፣ የመረጃ ማጣራቱ ላይ ደግሞ የታሳሪዎቹ ዜግነት፣ የወንጀል ላይ መሳተፍና አለመሳተፋቸው እንዲሁም ወንጀል ከፈጸሙ ደረጃው ከግምት ውስጥ ይገባል፡፡

ብዙዎቹ ታሳሪዎች በሕገወጥ መንገድ የሄዱ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ከተፈቀደላቸው ጊዜ በላይ የቆዩ ወይም ማሳደስ ሲገባቸው ያላሳደሱ ሌሎቹ ደግሞ ጥቃቅን ጥፋቶችን አጥፍተው እስር ቤት የገቡ መሆናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታዋ ብርቱካን አያኖ (አምባሳደር) ተናግረዋል፡፡

እንደ ሚኒስትር ዲኤታዋ ገለጻ ተመላሾቹ እንዲያገግሙ ተደርጎ ሥልጠና ከተሰጣቸው በኋላ የመጡበት ቀበሌ ወርደው እንዲቋቋሙ ይደረጋል፡፡ ሥልጠናውን የሚያዘጋጀው ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር መሆኑ ታውቋል፡፡ ተመላሾቹን የማሳረፍና የማሰማራቱን አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሚመራውና 16 ተባባሪ ተቋማት የሚሳተፉበት መሆኑን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ዓለም አቀፍ የስደተኞች ተቋም ሐሙስ መጋቢት 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ወደ ኢትዮጵያ የሚመለሱት 100 ሺሕ ስደተኞችን ከምልሰት በኋላ ለመርዳት 11 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል የሚል ግምቱን አስቀምጧል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም ይሄንን ገንዘብ ለማግኘት ለተለያዩ አካላት ረጂ አካላት፣ ለተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎችና ለሌሎች የሰብዓዊ ዕርዳታ ባለድርሻዎች ጥያቄ እያቀረበ መሆኑን ገልጿል፡፡ የ100 ሺሕ ስደተኞችን ፍላጎት ማሟላት ለኢትዮጵያ መንግሥት ፈተና እንደሚሆን መግለጫው አክሏል፡፡

በጦርነት ላይ የከረመውን መንግሥት የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በየካቲት ወር መጀመርያ ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ማብራሪያ በሰጡ ጊዜ የምክር ቤቱ አባላት የሳዑዲ ስደተኞችን የተመለከቱ ጥያቄዎችን አቅርበውላቸው ነበር፡፡

ዓብይ (ዶ/ር) ምላሽ ሲሰጡም፣ የሳዑዲ መንግሥት የአገሬው ሰዎች ከዚህ ቀደም በሌላ አገር ሰዎች ይያዙ የነበሩ ሥራዎችን እንዲሠሩ ለማድረግ ሪፎርም ላይ መሆኑን በመጥቀስ ከሳዑዲ መንግሥት አንፃር ጉዳዩ ልክ ቢሆንም የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ግን ችግር መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡ ቀጥለውም ‹‹ፈተናው ምንድነው? ሰዎቹ በሕገወጥ መንገድ የሄዱ ናቸው፡፡ ሁሉም ፓስፖርት ያለው አይደለም፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለመሆኑ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ሁሉም ከዚህ ሳዑዲ የሄደ መሆኑን ማወቅ ያስቸግራል፡፡ የሠለጠኑ ገዳዮች አሉበት ይባላል፤›› ብለዋል፡፡ መንግሥት ስደተኞቹን ሲያመጣ ‹‹መከራ›› አብሮ እንዳያመጣ በመጠንቀቅ ላይ መሆኑን በመግለጽ መንግሥት ‹‹ጥፋት የሚያስከትሉ ሰዎች›› አብረው ሊመጡ ይችላል የሚል ሥጋት እንዳለበትም ተናግረው ነበር፡፡

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በሳዑዲ ከሚገኙት ከስደተኞች ውስጥ ብዛት ያላቸው የአማራና ኦሮሚያ ክልል ተወላጆች ናቸው፡፡ በመቀጠል የደቡብ ክልል ተወላጆች የተቀመጡ ሲሆን፣ ከሶማሌ አፋር ደብብ ምዕራብ ኢትዮጵያና ትግራይ ክልሎች እንዲሁም ከድሬዳዋና አዲስ አበባ ከተማ መስተዳድሮች የሄዱ ስደተኞችም እንዳሉ ተገልጿል፡፡

መንግሥት ታስረው የከረሙትንና ኢትዮጵያዊ ተብለው የተለየ መከራ የደረሰባቸውን የሳዑዲ ስደተኞች የመጡበትን አካባቢ እየለየ ሊመልሳቸው ቢያስብም በብሔር የመከፋፈሉ ጉዳይ ግን መከራን ባዩበት የሳዑዲ እስር ቤት ውስጥም የነበረ ስለመሆኑ ስደተኞቹ ይናገራሉ፡፡ ብሔርን መሠረት ያደረገ ጥቃትና ፀብ በሳዑዲ እስር ቤቶች ውስጥ የጥበቃዎች መሳለቂያም እንዳደረጋቸው ገልጸዋል፡፡

የእስር ቤት ጥበቃዎች ‹‹አገራችሁ ስምምነት የለም እዚህም እንደዚያው ናችሁ፡፡ ለእናንተ ከምናበላ ውሻ ብንቀልብ ይሻላል፤›› ይሉን ነበር የምትለው አስማ፣ በላይ በታሰሩበት እስር ቤት ውስጥ በተደጋጋሚ ብሔርን መሠረት ያደረገ ፀብ ይከሰት እንደነበር ታስረዳለች፡፡

ግንባሯ ላይ ያሰረችውን ‹‹ኢትዮጵያ›› የሚል አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ያለበት ስካርፍን እየጠቆመች ‹‹ይችን ግንባሬ ላይ ያሰርኳትን ባንዲራዬን ገና ዛሬ ነው ያወጣኋት፡፡ አራት ወራት ሙሉ ወገቤ ላይ ታጥቄ ደብቄው ነበር፡፡ ይሄንን ባንዲራ ያወጣ ሰው ሕይወቱን ያጣል፡፡ እስር ቤቱ ውስጥ ይመታል፣ ብዙ ሀይላንድ ነው የሚወርድብን፤›› ብላለች፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...