Sunday, April 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከጂኦተርማል የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችል የግንባታ ምዕራፍ ሊጀመር ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን ኢተያ ወረዳ 150 ሜጋ ዋት የጂኦርተርማል ኃይል ለማመንጨት ቁፋሮው የተጀመረው የቱሉ ሞዬ ጂኦርተርማል ኩባንያ፣ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚያቀርብበትን የግንባታ ምዕራፍ ሊጀምር ነው፡፡

ኩባንያው ይህንን የኃይል ምንጭ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የሚደረገውን የኢንጂነሪንግ፣ የግዥና የግንባታ ስምምነት ዓለም አቀፍ ጨረታን መሠረት በማድረግ በጥምረት አሸናፊ ከሆኑት የጃፓኑ ሚትስቡሺ ኮርፖሬሽን፣ እንዲሁም የቻይናው ሴፕኮ ሦስት የአሌክትሪክ ኃይል ኮንስትራክሽን ኩባንያ ጋር ባለፈው ሳምንት ተፈራርሟል፡፡

ከኩባንያዎቹ ጋር የተደረገው ስምምነት ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሆነ የታወቀ ሲሆን፣ ይህንን የገንዘብ ፈሰስ የፈረንሣይ ኢንቨስትመንት ፈንድ አቅራቢ የሆነው ሜሪዲየም፣ እንዲሁም የአይስላንድ ጂኦተርማል ድርጀት የሆነው ሬዬጃቪክ ይሸፍኑታል ተብሏል፡፡

የቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል ቺፍ ቴክኒካል ኦፊሰር አቶ የትምጌታ ፋንቱ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ሁለቱ ኩባንያዎች አሸናፊ የሆኑበት የፍላጎት ማሳወቂያ ለመጀመሪያ ጊዜ የወጣው በሚያዚያ 2011 ዓ.ም. ነበር፡፡

በፕሮጀከቱ የቅድመ ምዘና ሒደት ላይ እንዲሳተፉ 22 ድርጅቶች መጋበዛቸውን፣ ከዚህ ውስጥ ሰባቱ ድርጅቶች ተመዝነው መመረጣቸውንና የዋና ጨረታ ሰነድ የተላከላቸው መሆኑን፣ ከእነሱ ውስጥ አምስቱ የጨረታ ተሳታፊነት ሰነድ መልስ እንዳስገቡ ታውቋል፡፡ በመጨረሻም የሁለቱ ድርጅቶች ጥምረት ሊመረጥ እንደበቃ ተገልጿል፡፡

አሸናፊ የሆኑት ድርጅቶች ለጂኦተርማል ኃይል ከተቆፈረው ጉድጓድ ውስጥ የኃይል ማስተላለፊያ ቱቦ (ፓይፕ) ዘርግተው ወደ ኃይል ማመንጫ አካባቢ እንደሚያመጡ ያስረዱት አቶ የትምጌታ፣ የዋና ኃይል ማመንጫ ግንባታውንና ለኃይል ማመንጫነት የሚረዳውን 50 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለውን ተርባይን፣ እንዲሁም ጄኔሬተር ከግዥ አንስቶ እስከ ተከላ ያለውን ሥራ እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል የጂኦተርማሉ ኃይል ከመነጨ በኋላ ከብሔራዊ የኃይል ቋት ጋር የሚገናኝበትን ሰብስቴሽን የሚሠሩት ድርጅቶቹ፣ በተያዘው ዕቅድ መሠረት ከጂኦተርማል የሚገኘውን የኤሌክትሪክ ኃይል እ.ኤ.አ በኅዳር 2024 ለማመንጨት የቀነ ገደብ እንደተቀመጠላቸው አቶ የትምጌታ አስረድተዋል፡፡

‹‹ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ያለን ሰምምነት በመጀመሪያ የሚመነጨውን የ50 ሜጋ ዋት ኃይል ተቀብለው ወደ ዋና የኃይል መስመር እንደገባ ነው፤›› ያሉት ዳይሬክተሩ፣ የቱሉ ሞዬ ጂኦርተርማል ሚና የሚመነጨውን ኃይል ወደ ኤሌከትሪክ ኃይል ቋት ማስተላለፍ ብቻ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

ከኢትዮጵያ አሌክትሪክ ኃይል ጋር የሚደረገው የኃይል ሽያጭ ግብይት የሚመነጨውን ኃይል መሠረት ያደረገ እንደሆነ ያስረዱት አቶ የትምጌታ፣ በሰዓት 50 ሜጋ ዋት የሚመነጭ ከሆነ ይህ በ24 ሰዓታትና በ365 ቀናት ተባዝቶ የሚታሰብ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ከውኃ ከሚመነጨው የኃይል አማራጭ ጀምሮ ከንፋስም ሆነ ከፀሐይ ብርሃን የሚገኙ የኃይል አቅርቦቶች ከእንፋሎት (ጂኦተርማል) ጋር ሲነፃፀሩ ከተፈጥሯዊ ባህሪያቸው አንፃር የሚያመነጩት የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ከፍና ዝቅ እንደሚል የተነገረ ሲሆን፣ ነገር ግን ጂኦተርማል አረንጓዴነት የተላበሰና አትራፊ ወይም ገበያ ሊገኝለት የሚችል አማራጭ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡

የተለያዩ አገሮች ፋይናንስ አቅራቢ ድርጅቶች የፕሮጀክቱን ውጤታማነት ወይም ተስፋ ሰጪነት ተመልክተው ወደ ኢትዮጵያ ገቡ ማለት ኢንቨስት የሚያደርጉበት ሁኔታ ተፈጠረ ማለት ነው ያሉት አቶ የትምጌታ፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ የግል ዘርፎች ላይ ድጋፍ ማድረጋቸው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቱን የሚያሳድግ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በመጀመሪያው ምዕራፍ ብቻ 270 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት የሚደረግበት እንደሆነ ያስረዱት ዳይሬክተሩ፣ ይህም ለመንግሥትም ሆነ ሌሎች ኢንቨስተሮች ጥቅሙ የጎላ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ቱሉ ሞዬ ከመንግሥት ጋር ያለው ኮንትራት በሁለት መዕራፎች የሚያደርጋቸው የኃይል ሽያጭ ስምምነቶች ሲሆኑ፣ የሁለቱንም ደረጃዎች የጊዜ ፍሰት ተከትሎ እየሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ በተለይም ይህ የኃይል አማራጭ ታዳሽ፣ ከመሬት ወጥቶ መልሶ የሚጠቅም በመሆኑ በተለይም ወጥነት ያለው የኃይል አማራጭ ለሚፈልጉ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመሳሰሉ ተቋማት አስፈላጊ እንደሆነ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

‹‹አንድ የኃይል ማመንጫ አማራጭ ላይ ጥገኛ ሆኖ መቆየት አይቻልም፤›› ያሉት አቶ የትምጌታ፣ በመሆኑም በአንድ አገር ላይ የተለየ የኃይል አማራጮችን መጠቀም አስፈላጊነቱን ጠቅሰዋል፡፡  

ከሚታደሱ የተፈጥሮ የኃይል ምንጮች መካከል የጂኦተርማል ኃይል አንዱ ሲሆን፣ ይህ ኃይል ከከርሰ ምድር የሚወጣውን የጭስ ሙቀት ወደ ጉልበት እንዲቀየር በማድረግ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡

በኢትዮጵያ የአሉቶ ላንጋኖ ጂኦተርማል ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በተጠቀሰው የኃይል አማራጭነት ለመጠቀም ጥረት የተደረገበት ነገር ግን ተጀምሮ የቆየ ሲሆን፣ ቱሉ ሞዬ ይህንን ኃይል በአማራጭነት ለመጠቀም እየተቃረበ እንደሆነ ይነገራል፡፡

በኬንያው የቁፋሮ ድርጀት ኬንጂን የሚከናወነው ቁፋሮ በዚህ ወቅት አራተኛው ቁፋሮ ላይ እንደደረሰ ታውቋል፡፡

በመጀመሪያው የፕሮጀክቱ ምዕራፍ 50 ሜጋ ዋት ኃይል የሚመነጭ መሆኑን፣ በሁለተኛው የፕሮጀክቱ ምዕራፍ ደግሞ 100 ሜጋ ዋት ኃይል በድምሩ እ.ኤ.አ 2025 ድረስ 150 ሜጋ ዋት ኃይል ይመነጫል ተብሎ ይጠበቃል ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች