Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአፋር የቀጠለው ጦርነት የጨው ምርት ዋጋ እንዲጨምር ምክንያት መሆኑን ጥናት አመላከተ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአፋር ክልል የተከሰተው ጦርነት እንዲሁም ተሽከርካሪዎች በበቂ ሁኔታ በቦታው ካለመሄዳቸው ጋር ተያይዞ የተፈጠረው የትራስፖርት ችግር፣ ለወቅታዊው የጨው ምርት ዋጋ ማሻቀብ ዓይነተኛ ምክንያት እንደሆነ የማዕድንና  የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በትብብር ያደረጉት ጥናት አረጋገጠ፡፡

በአገሪቱ በዚህ ወቅት ለተከሰተው የጨው ምርት እጥረትና ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሬ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው የትራንስፖርት ችግር እንዲሁም ምርቱ በብዛት በሚመረትበት የአፋር ክልል በተከሰተው ጦርነት ተሽከርካሪዎች በተፈለገው ልክ ለፋብሪካዎች የጥሬ ጨው ምርት ባለማቅረባቸው እንደሆነ የጥናት ቡድኑ አረጋግጧል፡፡

ጨውን ለማጠብና ለማቀነባበር በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ከ14 በላይ ፋብሪካዎች ቢኖሩም፣ በግብይት ሰንሰለቱ ውስጥ ባለው ውስብስብ ችግርና የተንዛዛ አሠራር ምክንያት ሁሉም በሚባል ደረጃ ምርት ማምረት ካቆሙ ረዥም ጊዜያት እንዳስቆጠሩ በጥናቱ የተለየ ጉዳይ ሲሆን፣ በአፋር ክልል የሚገኙ ሁለት የማጠቢያና የማነባበሪያ ፋብሪካዎች እንዲሁም በሶማሌ ክልል በሚገኝ አንድ የማጠቢያና የማቀነባበሪያ ፋብሪካ ብቻ ወጥነት የሌለውና በቂ ያልሆነ የምርት አቅርቦት መቅረቡ፣ በገበያው ውስጥ የምርት እጥረትና የዋጋ መጨመር እንዲከሰት አድርጎታል፡፡

የጥናት ቡድኑ በመስክ ምልከታ ባረጋገጣቸው የአገሪቱን የጨው ምርት ፍላጎት አብዛኛውን የሚሸፍኑት በአፋር ክልል የሚገኙት ኤስቪኤስ (SVS) እና ቲቲአር (TTR) የተባሉት ዋነኞቹ የጨው ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች በተለያዩ ምክንያቶች ምርት ካቆሙ ከአንድ ወር በላይ ቢሆናቸውም፣ በገበያ ውስጥ እጥረት እንዳይከሰት መፍትሔ እንዲፈለግ አስቀድመው ያሳወቁ ባለመሆኑ ችግሩ ሊሰፋ ችሏል ተብሏል፡፡

የአገሪቱን ከፍተኛውን የጨው ምርት የሚሸፍኑት ሁለቱ ፋብሪካዎች ሥራ ማቆማቸው በገበያ ውስጥ ከፍተኛ የአቅርቦት እጥረት እንዲከሰትና በዚህም ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዲኖር እንዳደረገው በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡   

የጥምር ጥናቱ ውጤት እንዳመላከተው በአገር ውስጥ የሚመረተው ጨው ከውጪ አገሮች ከሚገባው ዋጋው በእጥፍ የተጋነነ መሆኑ እንዲሁም የኮታ ድልድል ከተደረገ በኋላ በአስፈጻሚው አካል ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር የማይደረግበት መሆኑ ሕገወጥነት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲሰራፋና ጥቂቶች በሀብቱ ላይ እንደፈለጉ እንዲያዙ በር ከፍቷል፡፡

የጨው ምርት አቅርቦትና ግብይት ሰንሰለት በጥቂት የንግድ ተዋንያን በብቸኝነት የተያዘ መሆኑ ተወዳዳሪነት እንዳይኖርና በማምረቻ ቦታ በቂ ምርት እያለ ሆን ተብሎ እንዳይነሳ በማድረግ በገበያው ላይ ምክንያታዊ ባልሆነ ሁኔታ ዋጋው እንዲጨምር ተደርጓል ተብሏል፡፡

በአፋር አፍዴራ የሚገኙ 1,300 በላይ የጨው አምራቾችን ቢያንስ አምስት ወይም ስድስት ማኅበራት አደራጅቶ የጨው ምርት ማቅረብ እንዲችሉ ማድረግ እየተቻለ ሁሉንም በአንድ ማኅበር ጠርንፎ በአንድ መንገድ ብቻ የጨው ምርት እንዲቀርብ መደረጉ የግብይት ሰንሰለቱን ጤናማ እንዳይሆን ማድረጉ ሌላው የተለየ ጉዳይ ነው፡፡

በጨው ምርት የተራዘመና ጤናማ ያልሆነ የግብይት ሰንሰለት ምክንያት ለሕገወጥ ጨው አቅራቢዎች በር እንደተከፈተ በጥናቱ የተመላከተ ሲሆን፣ ምርቱ በአነስተኛ ዋጋ ከጎረቤት አገሮች በኮንትሮባንድ እንዲገባ መደረጉ በአገርና በተጠቃሚው ላይ ጉዳት የሚያስከትል፣ ጥራቱን ያልጠበቀና በአዮዲን ያልበለፀገ ጨው በገበያው ውስጥ በስፋት እንዲኖር አድርጎታል ተብሏል፡፡

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የሚገኙት የጨው ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ምርቱ በበቂ ሁኔታ እንዳይደርሳቸው በማድረግ አብዛኞቹ ማምረት በማቆም ከገበያ እንዲወጡ መደረጉን ያመላከተው ጥምር ጥናቱ፣ በምርት ላይ የሚገኙት ጥቂቶችም በደላሎች ጣልቃ ገብነት በከፍተኛ ዋጋ ምርቱን እየገዙ እንዲያቀነባብሩ የተገደዱ ሲሆን፣ ይህም ምርቱን አቀነባብረው በከፍተኛ ዋጋ ለሸማቹ እንዲያቀርቡ አስገድዷቸዋል ተብሏል፡፡

በትራንስፖርት ችግር ምክንያት ከማምረቻ ቦታ መነሳት ያልቻለውን የጥሬ ጨው ምርት ከሚመለከተው የትራንስፖርት ሥምሪት አካላት ጋር በመነጋገር ከጨው አምራች ቦታዎቹ እንዲነሳ መደረግ አለበት የተባለ ሲሆን፣ ሥራ ያቆሙ የማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችም ሥራ እንዲጀምሩ በማድረግ ምርቱን በፍጥነት ወደ ገበያ ማቅረብ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

ጨው በማጠብና ማቀነባበር ሥራ ላይ የተሰማሩ ፋብሪካዎችን በሙሉ አቅም እንዲሠሩና ምርቱን የሚያገኙበት የኮታ ድልድልና አሠራርን በመፈተሽ የግብይት ሰንሰለቱን በውድድር ላይ የተመሠረተና ጤናማ እንዲሆን ማድረግ ሌላው በአጥኚ ቡድኑ የቀረበ ምክረ ሐሳብ ነው፡፡

አፍዴራና ዶቢ በተባሉ ቦታዎች ላይ ያለውን የጨው ግብይት ሥርዓት በመፈተሽ አምራቾች ከአንድ አቅራቢ በተጨማሪ ሌሎች አቅራቢዎች የሚገቡበት አደረጃጀት በመፍጠር ወደ ሥራ ማስገባት እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡

በተያያዘም የጨው ምርትና ግብይት ላይ ያተኮረ እንዲሁም የምርት ሒደቱ በዜጎች ጤና ላይ ባለው ተፅዕኖ ዙሪያ የንግድ ሚኒስቴርና የማዕድን ሚኒስቴር ባለሙያዎች በትብብር ያደረጉትን ጥናት መሠረት በማድረግ ባሳለፍነው ሳምንት የማዕድን ሚኒስትሩ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) እና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ አቶ ገብረ መስቀል ጫላ፣ እንዲሁም ከአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባ ጋር በሰመራ ከተማ ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች