Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊድርቅ ባጠቃቸው አካባቢዎች የደመና ማበልፀግ ቴክኖሎጂ እየተሞከረ ነው

ድርቅ ባጠቃቸው አካባቢዎች የደመና ማበልፀግ ቴክኖሎጂ እየተሞከረ ነው

ቀን:

ዘርፉ የሚመራበትን ፖሊሲ ለማርቀቅ ብሔራዊ ኮሚቴ በመዋቀር ላይ ነው

በኢትዮጵያ ደመናን በማበልፀግ የዝናብ መጠንን ለመጨመር የሚደረገው የቴክኖሎጂ ሙከራ፣ ዘንድሮ ድርቅ ባጠቃቸው አካባቢዎች በመካሄድ ላይ መሆኑ ተነገረ፡፡ የቴክኖሎጂ ሙከራውን ከሚያስተባብረው ብሔራዊ ግብረ ኃይል አባላት ሪፖርተር እንዳረጋገጠው ከሆነ፣ በቦረና ዞንና በሶማሌ ክልል አካባቢዎች ዳመና የማበልፀግ ቴክኖሎጂ በሰፊው እየተካሄደ ነው፡፡

ከምድር ኬሚካል የሚረጩ መሣሪያዎችን በመትከልና በአውሮፕላን ርጭት ሥራው እየተካሄደ መሆኑን ባለሙያዎቹ ገልጸዋል፡፡ ባለሙያዎቹ አክለውም ዘርፉ የሚመራበትን ፖሊሲና ሥርዓት ለመዘርጋት ብሔራዊ ኮሚቴ በመቋቋም ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስተባባሪነት፣ በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩትና በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ባለቤትነት የሚመራው የቴክኖሎጂ ፕሮጀክቱ ውጤት እየታየበት መሆኑን፣ ዘርፉን የሚመሩ የሥራ ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡ ድርቅ ያጠቃቸውን የኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን፣ እንዲሁም የሶማሌ ክልል አካባቢዎችን ያዳርሳል የተባለው ሙከራው በበልግ ወራት በአካባቢው የሚገኝ ደመናን አበልፅጎ የዝናብ መጠንን ለመጨመር ታቅዶ የሚተገበር መሆኑ በባለሙያዎቹ ተብራርቷል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ሥር ዘርፉን የሚያስተባብሩት አቶ ዮዳሔ አርዓያ ሥላሴ፣ ‹‹ቦረና ዞን ውስጥ ያቤሎ፣ ሜጋና ነጌሌ፣ እንዲሁም በሶማሌ ክልል ቀብሪ በያህና ጅግጅጋ አካባቢዎች የምድር ላይ ጭስ መልቀቂያ (ግራውንድ ጄኔሬተር) ተተክሏል፡፡ ጀኔሬተሮቹ በፀሐይ (ሶላር) ኃይል የሚሠሩ ሲሆን ጭስ ያተናሉ፡፡ የመደበኛ ጨው (ሶዲየም ክሎራይድ) እንዲሁም ፖታሺየም ክሎራይድ ኬሚካሎች የሚሞሉ መርጫዎች (ፍሌሮች) ያሏቸው ሲሆን፣ በአካባቢዎቹ ጥሩ የደመና ይዘት ሲኖር ከመሬት ወደሰማይ ኬሚካሎቹን ያተናሉ፡፡ በእነዚህ ከተሞች ከምድር ወደ ሰማይ ጭስ ከማትነን በዘለለ በአውሮፕላንም የደመና ማበልፀጊያ ኬሚካል ርጭት እየተሠራ ይገኛል፡፡ የደመና ሽፋን ከሚታይባቸው ከኮንሶ ጀምሮ በቦረና አሻግሮ እስከ ሶማሌ ክልል ባሉ አካባቢዎች የደመና ማበልፀግ ሥራ በአውሮፕላን እየተካሄደ ይገኛል፤›› በማለት ቴክኖሎጂው እየተተገበረ ያለበትን አካባቢና ሒደት አስረድተዋል፡፡

ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ሚቲዎሮሎጂ ተቋም የመጣ ፕሮጀክቱን የሚያግዝ ቡድን መኖሩን የጠቀሱት አቶ ዮዳሔ፣ ቡድኑ የኬሚካልና የቴክኖሎጂ ዕገዛ ያደርጋል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት እንዲሁም፣ የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) በዚህ ሙከራ ይሳተፉበታል ያሉት አቶ ዮዳሔ፣ ‹‹መቆጣጠሪያውንና ኬሚካል ርጭቱን የሠራው ኢንሳ ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት ደግሞ የማስተባበር ሥራውን ይሠራል፤›› በማለት የሙከራውን ቅንጅታዊ አሠራር አስረድተዋል፡፡

በዘርፉ ላይ የተዛባ አመለካከት በአንዳንዶች ዘንድ እንዳለ የጠቀሱት አቶ ዮዳሔ፣ ደመና ሲኖር ነው ቴክኖሎጂው የሚሠራው ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ደመና ሲኖር ቴክኖሎጂውን በመጠቀም አበልፅጎ ማዝነብ ይቻላል እንጂ፣ ደመናን የሰው ልጅ እስካሁን መፍጠር አልቻለም፤›› ሲሉ ሊታረም ይገባል ስላሉት አመለካከት ጠቁመዋል፡፡ 

በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) የኤሮስፔስ ሥራ ክፍል ኃላፊ አቶ አፈወርቅ በዜ በበኩላቸው፣ ድርቅ ባጋጠማቸው የቦረና ዞንና የሶማሌ ክልል የሚተገበረው ቴክኖሎጂው በሌሎች አገሮች እንደተገኘው ሁሉ ጥሩ ውጤት ይመጣበታል ተብሎ እንደሚገመት ተናግረዋል፡፡ ‹‹ደመና በተፈጥሮው ጥሩ እርጥበት ካለው ከ30 እስከ 50 በመቶ ይዘንባል፡፡ በዚህ ቴክኖሎጂ አማካይነት ደግሞ የደመናን የመዝነብ መጠን ከ15 እስከ 30 በመቶ ማሻሻል እንደሚቻል ተረጋግጧል፡፡ ቴክኖሎጂው የዝናብ ምጣኔን በድምሩ ወደ 80 በመቶ የሚያሸጋግር ነው፤›› ሲሉ እንደ ቻይና፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስና ሌሎች አገሮች ያገኙትን ውጤት ጠቁመዋል፡፡ 

አቶ አፈወርቅ አክለውም፣ ‹‹ቴክኖሎጂው ከብሔራዊ ደኅንነት ጉዳይ ጋር በቀጥታ የተገናኘ ነው፡፡ የአቪዬሽን ጉዳይ ይነሳል፡፡ በይፋ ባይናገሩትም አንዳንድ አገሮች ቴክኖሎጂውን ለወታደራዊ አገልግሎት ተጠቅመውበታል ይባላል፡፡ ደመና መሰራረቅ ወይም የውኃ አካላትን አትንኖ መጠቀም የሚባለው ጉዳይ አሁን ባለው ሁኔታ ባይረጋገጥም፣ ነገር ግን ዘርፉ ራሱን የቻለ ክትትል የሚያስፈልገው መሆኑ አይታለፍም፤›› ሲሉ ስለዘርፉ ምንነትና የሚጠይቀውን አብራርተዋል፡፡

አሁን ወደ ቴክኖሎጂው መገባቱ ነው ቅድሚያ የሚሰጠው የሚሉት በኢንሳ ውስጥ የኤሮስፔስ ክፍል ኃላፊው አቶ አፈወርቅ፣ ‹‹ዘርፉን በዘላቂነት ለመጠቀም እንዲረዳ ግን ከአዋጪነቱ ጀምሮ አጠቃቀሙን የተመለከተ የአሠራር መመርያና ፖሊሲ ለማዘጋጀት ዕቅድ ወጥቶ ወደተግባር ተገብቷል፡፡ ዘርፉ የሚመራበትን ፖሊሲ ጨምሮ አሠራሩ ሊከተል የሚገባውን አዋጪ መንገድ በተመለከተ ብሔራዊ ኮሚቴ ለማቋቋም በሒደት ላይ ይገኛል፡፡ ዘርፉ የራሱ ሕግና ሥርዓት እንደሚያስፈልገው መንግሥት በፅኑ ያምንበታል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የራዳርና ሳተላይት ክፍል ተመራማሪ አቶ ለታ በቀለ፣ ‹‹በእኛ በኩል ከባቢ አየሩን ወይም የአየሩን ሁኔታ በማጥናት ቴክኖሎጂው በየት ቦታ፣ በምን ጊዜና በምን ሁኔታ መተግበር እንዳለበት መረጃ መስጠት ነው ሚናችን፤›› ብለዋል፡፡  

አቶ ለታ አክለውም፣ ‹‹የሚቲዎሮሎጂ ባለሙያው ሚና የደመናን እርጥበት ሁኔታና አቅጣጫ አጥንቶ ማቅረብ ነው፡፡ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ከሳተላይት መረጃዎችን በመሰብሰብ አሁናዊና ወቅታዊ የአየር ሁኔታ ትንበያዎችን ማቅረብ ይጠበቅበታል፤›› ይላሉ፡፡ ይህን መረጃ ተንተርሰውም የደመና ማበልፀጊያ ኬሚካል የሚረጩ የሥራ ዘርፎች ከምድር ወደሰማይ ወይም ከሰማይ በአውሮፕላን ርጭት ያካሂዳሉ ብለዋል፡፡

አቶ ለታ ማብራሪያቸውን ሲቀጥሉም፣ ‹‹አንዳንድ አገሮች በቴክኖሎጂው ውጤታማ ናቸው፡፡ በእኛ አገር ድርቅ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች ይህንኑ ቴክኖሎጂ ብንተገብር ውጤታማ እንሆናለን፤›› በማለት ሙከራው እንደሚካሄድ አስረድተዋል፡፡

‹‹ሥራው መሠራት ያለበት በዝናብና የዳመና ሽፋን በሚጠናከርባቸው ወቅቶች ነው፤›› ያሉት አቶ ለታ፣ ከዚህ ውጪ ግን በግንዛቤ ማጣት ቴክኖሎጂውን ከፈጣሪ ሥራ ወይም ከሃይማኖት ጋር በማገናኘት የተዛባ አመለካከት የሚያራምዱ ወገኖች ሊታረሙ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ‹‹የምንሠራው የሳይንስ ወይም የቴክኖሎጂ ሙከራ ነው፡፡ ውጤታማ ከሆነና በድርቅ የሚጠቁ አካባቢዎች ዝናብ አግኝተው ከችግር ከተላቀቁ ትልቅ ውጤት ነው፤›› በማለት ቴክኖሎጂው ከእምነት ጋር ፀብ እንደሌለው ገልጸዋል፡፡

በዚህ ቴክኖሎጂ ምን ያክል ውጤት እንደተገኘ የተረጋገጡ መረጃዎች ባይገኙም፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስና ቻይና ከቴክኖሎጂው ብዙ እንዳተረፉ ሲነገር ቆይቷል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1950ዎቹ ጀምሮ በሙከራ ላይ የሚገኘው ደመናን የማዝነብ (ክላውድ ሲዲንግ) ቴክኖሎጂ አሜሪካ በቬትናም ጦርነት ወቅት ጠላቶቿን በዝናብ ለማዳከም ተግብራዋለች ሲባል ነበር፡፡

በቅርብ ጊዜ ደግሞ ቻይና በቤጂንግ ኦሎምፒክ ወቅት የከተማውን ጭጋግና ደመና አዝንቦ ለማፅዳት ተግብራዋለች ተብሎ ሲዘገብ ተሰምቷል፡፡ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የግድቦቿን የውኃ ይዘት ለመጨመር ተግብራዋለች መባሉም ይነገራል፡፡

በኢትዮጵያም ባለፈው ዓመት በዓባይ ተፋሰስና በወሎ አካባቢዎች የተሞከረው ቴክኖሎጂው፣ ዘንድሮ ደግሞ በድርቅ በተጠቁ አካባቢዎች ለውኃ እጥረት መፍትሔ ተብሎ በሰፊው እየተሞከረ መሆኑ ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...