Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቀላል ባቡር አገልግሎት መቆራረጥ የትራንስፖርት ፍሰቱን እየጎዳ መሆኑ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት በተደጋጋሚ የሚስተዋልበት የአገልግሎት መቆራረጥ ችግር የከተማው የትራንስፖርት ፍሰት ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አረጋዊ ማሩ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በቀላል ባቡር አገልግሎት ላይ የሚፈጠረው የአገልግሎት መቆራረጥ ተፅዕኖ በከተማው የትራንስፖርት ፍሰት ላይ ቀጥታ ግንኙነት አለው፡፡

የቀላል ባቡር አገልግሎት አልሰጠም ማለት የትራንስፖርት አማራጩን ሲጠቀሙ የነበሩ ተገልጋዮች ወደ ሌሎች አማራጮች ማለትም ወደ ታክሲና አውቶብሶች ስለሚሄዱ ተጨማሪ ጫና የሚፈጥር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ከባቡር መስመር ዲዛይን ጋር ተያይዞም በተሽከርካሪ ፍሰቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው ያስታወቁት አቶ አረጋዊ፣ ለአብነትም ከጦር ኃይሎች ተነስቶ ወደ ሲኤምሲ የሚሄደው የምሥራቅ-ምዕራብ ባቡር መስመር ተሽከርካሪዎች በቀላሉ እንደ ልብ ስለማይንቀሳቀሱ መንገድ እንዲዘጋጋ ምክንያት ሆኗል ብለዋል፡፡ ይህም የተሽከርካሪ ፍሰቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደረ አስረድተዋል፡፡

ከሰሜን-ደቡብ ያለው መስመር እንደዚሁ ሌላው ችግር የሚስተዋልበት እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህ ከዲዛይን ጋር ተያይዞ የሚስተዋለው ችግር በእግረኛ መንገዶች ላይም ሆነ ተሽከርካሪዎች እንደ ልብ አቋርጠው እንዳይንቀሳቀሱ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ ተነግሯል፡፡

ይህ ጉዳይ መፍትሔ እንዲያገኝ ከትራፊክ ማኔጀመንት ኤጀንሲ ጋር የተጀመሩ ጥናቶች እንዳሉ የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ የቀላል ባቡር አገልግሎቱ በትራንስፖርት ቢሮ ሥር በሚሆንበት ጊዜ መፍትሔ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ ይህ ይሆናል ብለዋል፡፡  

በመስከረም ወር የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ጉዳይ የከተማ አስተዳደሩ  የትራንስፖርት ችግሩን የሚፈታበት አንዱ መፍትሔ መሆኑ ታምኖበት፣ በትራንስፖርት ቢሮ ሥር መደራጀት አለበት ተብሎ በከፍተኛ አመራሮች ውሳኔ የርክክብ ሒደቶቹ ተጀምረው እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፣ ነገር ግን በተለያዩ አገራዊና ወቅታዊ ምክንያቶች ሒደቱ በፍጥነት ወደ የሚፈለገበት ደረጃ እንዳልደረሰ ታውቋል፡፡

አቶ አረጋዊ እንዳስታወቁት፣ በተያዘው ዓመት የትራንስፖርት ዘርፉ እንቅስቃሴ በአዲስ አበባ ደረጃ በጥቅሉ ሲታይ የመሻሻል ሁኔታ የታየበት ነው፡፡

አምና በተመሳሳይ ወቅት አንድ ሰው ተሽከርካሪ ለማግኘት ይወስድበት የነበረው ጊዜ በአማካይ 30 ደቂቃ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ከየካቲት አጋማሽ አንስቶ አንፃራዊ የሆነ የትራንስፖርት መጨናነቅ ቢኖርም፣ ነገር ግን የጊዜ ቆይታው ወደ 15 ደቂቃ መውረዱ ተገልጿል፡፡

በአንፃሩ የተሽከሪካሪዎች ቁጥር በፊት ከነበረው ጊዜ ሲታይ በተለያዩ ምክንያቶች የተመናመነበት ሁኔታ እንደሚስተዋል፣ ያሉት የብዙኃን ተሽከርካሪዎች ከዚህ በፊት የነበራቸውን ስድስት የሚደርስ የምልልስ ጊዜ ከዘጠኝ እስከ አሥር ለማድረስ እንደተቻለ ተመላክቷል፡፡

ከላይ የተመዘገቡት ዓይነት አበረታች ሥራዎች ቢከናወኑም፣ አሁንም ቢሆን ረጃጅም ሠልፎች ከመኖራቸውም ባሻገር፣ የአቅርቦትና የፍላጎት አለመጣጣም እንደሚስተዋል አቶ አረጋዊ ተናግረዋል፡፡

ከተሽከርካሪ ፍሰት ጋር ተያይዞ በተለይ ባለፈው አንድ ወር ውስጥ ማለትም ከየካቲት አጋማሽ እስከ መጋቢት አጋማሽ ባለው ጊዜ ውስጥ በፍሰቱ ላይ የተስተዋለው ተግዳሮት በትራንስፖርት አቅርቦት፣ እንዲሁም በቆይታው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደፈጠረ ተጠቅሷል፡፡

ይህንን የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም ለመቀነስ 110 አውቶብሶችን ለመገጣጠም ለቻይና ኩባንያ ዕድል እንደተሰጠ፣ በመጪዎቹ ስምንት ወራት አውቶብሶቹን ወደ ሥራ ለማስገባት የሚደረገው ሥራ አንድ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም በከተማ አስተዳደሩ አማካይነት በግዥ መልክ የሚገቡ ሌሎች አውቶብሶች እንዳሉ ያስታወሱት አቶ አረጋዊ፣ የአስተዳደሩ የግዥ አቅም ታይቶ ወደ ሥራ የሚገቡት አውቶብሶች ከላይ ከተገለጹ ጋር በማጣመር የሚስተዋለውን የአቅርቦትና የፍላጎት አለመጣጣም ችግር ለመፍታት የራሳቸው የሆነ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች