ከሳዑዲ ዓረቢያ የሚመለሱ ኢትዮጵያዊያንን ለማቋቋም 7.4 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ፣ ከስደት ተመላሾች መልሶ ማቋቋም ኮሚቴ አስታወቀ።
መንግሥት በሳዑዲ ዓረቢያ የነበሩ ስደተኞች ለበርካታ ጊዜያት በእስር ከቆዩ በኋላ ከመጋቢት 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ጀምሯል። በሳዑዲ ዓረቢያ በአጠቃላይ ከ750 ሺሕ ዜጎች እንደሚኖሩና 450 ሺሕ የሚሆኑት በሕገወጥ መንገድ የሄዱ መሆናቸውን፣ የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (አይኦኤም) መረጃ ያመለክታል። መንግሥት ወደ ኢትዮጵያ ለመለለስ በዕቅድ የያዘው 102 ሺሕ ዜጎችን ሲሆን፣ ይህም ከሰባት እስከ 11 ወራት እንደሚወስድ ተገልጿል።
ከስደት ተመላሾቹ ኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ መጠለያዎች የሚቆዩ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ስድስት ሺሕ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችሉ ሰባት መጠለያዎች መዘጋጀታቸውን ከስደት ተመላሾች መልሶ ማቋቋም ኮሚቴ ተጠሪ አቶ ተፈሪ ታደሰ ገልጸዋል። ዜጎቹ ከደረሰባቸው ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ሲያገግሙም፣ የራሳቸውን ሥራ ለማስጀመር የማቋቋም ሥራ እንደሚከናወን አክለዋል።
መልሶ ማቋቋሙን ለማከናወን በአጠቃላይ እስከ 7.4 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ የገለጹት አቶ ተፈሪ፣ ይህም መንግሥትን ጨምሮ ከረጂ ድርጅቶችና ከፋይናንስ ተቋማት ለማግኘት መታቀዱን ዓርብ መጋቢት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ከፋይናንስ ተቋማትና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር በተደረገበት ወቅት ተናግረዋል።
ገንዘቡን በብድር መልክ ለማቅረብ ቢታሰብም በተለይም ከፋይናንስ ተቋማት ለሚገኘው ብድር እንደ ችግር የሚነሳው የማስያዣና የወለድ ችግር መሆኑን አስረድተዋል። ለዚህም የፋይናንስ ተቋማት የሚሰጡት ብድር በአነስተኛ ወለድ በአፋጣኝ እንዲያቀርቡ ተጠይቀዋል።
የብድር አቅርቦቱን በተመለከተ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጥቃቅንና አነስተኛ ብድር አቅርቦት ዳይሬክተር ወ/ሮ መልካም በለጠ፣ መንግሥትም ሆነ ረጂ ድርጅቶች ዋስትና ከገቡ ብድሩን ማቅረብ እንደሚቻል ገልጸዋል።
ለዚህም በተለይ ባንኮች እንደ መሥፈርት የሚጠይቁት የአዋጭነት ጥናት በመሆኑ፣ ተቀባይነት ያለው የአዋጭነት ጥናት ተደርጎ መቅረብ ይጠበቅበታል ብለዋል። ከስደት ተመላሾችም ሆነ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ብድር ሲጠይቁ ያለ በቂ ጥናት በመሆኑ ባንኮች ብድሩን ለመስጠት እንደሚቸገሩ የገለጹት ወ/ሮ መልካም፣ ለዚህም መንግሥትም ሆነ ሌሎች አካላት ደረጃውን የጠበቀ የብድር መጠየቂያ ጥናት በመሥራት ሊደግፏቸው ይገባል ብለዋል።
የእናት ባንክ የቅርንጫፍ ሥራ ማስተባበሪያና ሀብት ማሰባሰብ ዳይሬክተር ወ/ሮ በዓለምላይ አየነው በበኩላቸው፣ እናት ባንክ ለሴቶች ቅድሚያ ሰጥቶ የሚሠራ ባንክ ስለሆነ ከስደት ተመላሽ ለሆኑ ሴቶችም ብድር ለማቅረብ ፈቃደኛ መሆኑን ተናግረዋል።
ተቀባይነት ያለው የሥራ ምክረ ሐሳብ ለሚያቀርቡም ያለ ማስያዣ እስከ 300 ሺሕ ብር ከእናት ባንክ መበደር እንደሚችሉ ገልጸዋል። በተለያየ መንገድም እስከ 70 በመቶ የሚሆነውን መጠን ለሚያስይዙ ብድር እንደሚቀርብላቸው አክለዋል።
ብድር ከተገኘ በኋላ ወደ ሥራ ለሚገቡት የመሥሪያ ቦታዎችን ክልሎች እንደሚያቀርቡ አቶ ተፈሪ ገልጸው፣ የመሥሪያ ቦታዎችን ሙሉ ለሙሉ ማቅረብ ካልተቻለ ደግሞ በኪራይ እንደሚጠቀሙና ክፍያውንም መንግሥት እንዲሸፍን ይደረጋል ብለዋል።