ወገኖቼ ባለንበት ዘመን የምናስተውላቸው በርካታ ጉዳዮቻችን በተለያዩ ማዕዘናት ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድዱናል፡፡ ሁሌም የነገሮች መነሻና መድረሻ መንግሥት በመሆኑ ከሰሞኑ የመንግሥት ክራሞት ጋር አያይዤ የማነሳቸው ጉዳዮች አሉኝ፡፡ በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት የሚመራው ገዥው ፓርቲ ብልፅግና በመሆኑ የገጠመኜ መነሻም እሱ ይሆናል፡፡ ካለፈው ሰሞን ጀምሮ የብልፅግና ሰዎች ከጉባዔያቸው ጀምሮ በተለያዩ ስብሰባዎች ተጠምደው ነበር የከረሙት፡፡ በተለይ ባለፈው ሰሞን በተለያዩ አካባቢዎች ከሕዝብ ጋር ያደረጓቸው ስብሰባዎች ይታወሳሉ፡፡ የሕዝብ ምሬትና ቁጣ የተሰማባቸው ስብሰባዎች ለገጠመኜ መነሻ ሆነዋል፡፡
በ1983 ዓ.ም. ወርኃ ግንቦት አዲስ አበባን የተቆጣጠረው ኢሕአዴግ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ገብቶ አገሪቱን ማስተዳደር ሲጀምር፣ ከያኔው የንግድ ሥራ ትምህርት ቤት (ኮሜርስ) በዲፕሎማ ተመርቄ ሥራ ከያዝኩ አንድ ዓመት አልሞላኝም ነበር፡፡ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የኢሕአዴግ አገዛዝ ዘመን በተለያዩ የመንግሥትና የግል ድርጅቶች በሥራ ከማሳለፌም በላይ የራሴን ቤት ሠርቼ፣ ትዳር መሥርቼ የሦስት ልጆች አባት ሆኜአለሁ፡፡ በእነዚህ ዓመታት የነበሩትን ውጣ ውረዶችን ከማንም አውቃለሁ ከሚል ሰው ባልተናነሰ ሁኔታ እረዳለሁ፡፡ በኢሕአዴግ አገዛዝ ወቅት በሕዝብ ላይ የደረሱ መከራዎችን በሚገባ ከማወቄም በተጨማሪ፣ በተለይ በምርጫ 97 ምክንያት የደረሰውን ቀውስና ሕመም አስታውሳለሁ፡፡ የአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ከየት ወዴት እየተንሳፈፈ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረሱም ምስክር መሆን እችላለሁ፡፡ የኢሕአዴግን ጥቂት በጎ ነገሮችንና በርካታ እኩይ ሥራዎችንም መናገር አያቅተኝም፡፡ ብዙ ነገሮችን አውቃለሁ ለማለት ነው፡፡
በከፍተኛ የሕዝብ ትግል ከመንበሩ ገለል የተደረገው ኢሕአዴግ ወራሽ የሆነውን ብልፅግና ደግሞ ሁላችንም በሚገባ እናውቀዋለን፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት ያለፍንባቸው ዘግናኝ መከራዎች አሁንም አልተለዩንም፡፡ በበርካታ ውጣ ውረዶችና ከዚያም አልፎ ተርፎ እጅግ አስከፊ የሚባል ጦርነት ተካሂዶ የደረሰውን ዕልቂት፣ ውድመትና መፈናቀል ዓለም ጭምር የታዘበው ነው፡፡ በታሪካችን ታይተው የማይታወቁ ጭካኔዎችና ነውረኝነቶች ጭምር የዘመናችን ታሪክ ሆነዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአገሬ ህልውና የሚበልጥ የለም ብሎ፣ ብልፅግና ፓርቲ ከገባበት መከራ እንዲያወጣው ለአምስት ዓመታት ቆይታ መምረጡ የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን ብልፅግና እንደሚጠበቀው ሊሆን ባለመቻሉ እንደገና ከሕዝብ ጋር ስብሰባ ተቀምጦ በቁጣ የታጀበ ምክር ተለግሶታል፡፡ ነገሩ “ጨው ሆይ ለራስህ ስትል ጣፍጥ፣ ካልሆነ ግን ድንጋይ ነህ ተብለህ ትጣላለህ” ማለት ነው፡፡
የበቀደሙ የሕዝብ ውይይቶች ከመከናወናቸው አስቀድሞ ስለመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ ስለፍትሕ መጓደል፣ ስለሌብነት መስፋፋት፣ ስለባለሥልጣናትና ነጋዴዎች መመሳጠር፣ ስለኑሮ ውድነትና ስለመሳሰሉት ጉዳዮች ብዙ አስተያየቶች ቀርበዋል፡፡ በሰሞኑ ስብሰባዎችም እነዚህ ጉዳዮች በስፋት ተነስተው በጣም አደገኛ ማስጠንቀቂያ የተላለፈባቸው ድምፆች ተሰምተዋል፡፡ እነዚህ በብሶት ላይ ብሶት በተደጋጋሚ የተንፀባረቀባቸው ጩኸቶች ወደ አመፅ ሊሸጋገሩ ይችላሉ፡፡ ብልፅግና ፓርቲና መንግሥት ውስጣቸውን አጥርተው ለእነዚህ ብሶቶች ተግባራዊ ምላሽ ካልሰጡ፣ በበኩሌ የሚታየኝ ማንም ሊያቆመው የማይችል ተቃውሞ እንደሚከሰት ነው፡፡
ይህንን የሕዝብ እሪታና እሮሮ አስመልክቶ ከሥራ ባልደረቦቼ ጋር በትኩረት ስንወያይ ነበር፡፡ አንድ በዕድሜና በትምህርት የገፋ ወዳጃችን ሁሌም ረጋ ባለና በሰከነ ሁኔታ የሚያነሳቸው ቁምነገሮች ስላሉት እሱን ማዳመጥ ጀመርን፡፡ ይህ ከፍተኛ ልምድ ያለው ጓደኛችን፣ ‹‹የብልፅግና አመራሮች ከሕዝብ ውስጥ የወጡ በመሆናቸው ሕዝቡ ውስጥ የሚባለውን በልጆቻቸው፣ በባለቤቶቻቸው፣ በእህቶቻቸውና በወንድሞቻቸው፣ በአባቶቻቸውና በእናቶቻቸው፣ እንዲሁም በቅርብ ወዳጆቻቸው አማካይነት ስለሚሰሙ ከሕዝቡ የራቁ ናቸው ለማለት ይከብደኛል…›› አለ፡፡ በመቀጠልም በተለያዩ አቅጣጫዎች መረጃዎች የሚደርሷቸው ከሆነ ለምን ሕዝብ ዘንድ ሲደርሱ አዲስ እንደሚሆኑ እንደማይገባው ተናገረ፡፡ ‹‹ብልፅግና አንድ ጫፍ ላይ ከደረሰ በኋላ ለምን ጨከን ብሎ ዕርምጃ እንደማይወስድ ያሳስበኛል፡፡ አሁንም በዕቅድ ላይ ተመሥርቼ ዕርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጅቻለሁ ቢልም፣ እኔ ግን እንዳለፈው ጦርነት መንገድ ላይ አቁሞ ግራ ሊያጋባን ይችላል…›› ሲለን በጣም ነበር የደነገጥኩት፡፡ ምክንያቱም የሕዝቡ ብሶት መቋጫ ካልተደረገለት መጪው ጊዜ አስፈሪ ነውና፡፡
‹‹ሕዝቡ ፍትሕ ተጓደለብኝ፣ ጉዳዬን በአግባቡ ተረድቶ የሚያስተናግደኝ አጣሁ፣ ሰብዓዊ መብቴ ተጣሰ፣ በጠራራ ፀሐይ በጉቦ ተዘረፍኩ፣ የአገሪቱ ሀብት የጥቂቶች መጫወቻ ሆነ፣ ገንዘብ ያለው ሲፈነጭ ሀቀኛ ዜጋ ተበደለ፣ ቅሬታ የሚሰማ ጠፋ፣ ኑሮን መቋቋም አልቻልኩምና የመሳሰሉ ብሶቶች በየአቅጣጫው ሲቀርቡ ችግሩ መኖሩን አምኖ የመፍትሔ ዕርምጃ ለመውሰድ ሲያቅት ምን ይባላል?›› በማለት ጥያቄ አቀረበ፡፡ በእርግጥም እሱ እንዳለው ብልፅግና የሕዝብ ወገን ነኝ ካለ እንዴት የሕዝብ ፀር የሆኑ ቡድኖችን ኔትወርክ መበጣጠስ አቃተው? ከጥቅምና ከአድልኦ አልፈው ከሽፍቶች ጋር የሚሠሩ ሹሞችን ለምን አያስወግድም? ከሕዝብ ይልቅ ለባለገንዘብ የሚሰግዱ ሹሞችን ለምን አያባርርም? እያልን ብንነጋገርም እኛ ዘንድ መፍትሔ ባለመኖሩ ከወሬ የዘለለ ምንም ማድረግ አልቻልንም፡፡
በተለያዩ ጊዜያት በዚህ ጋዜጣ ጭምር ብዙ ችግሮች ተነስተዋል፡፡ የአገሪቱን መሬት የሚቸበችቡ፣ በኮንትሮባንድ ንግድ የሚበለፅጉ፣ ታክስ ሊከፈልበት የሚገባን ከውጭ የገባ ሸቀጥ በጉቦ የሚለቁ፣ ግብር በአግባቡ እንዳይከፈል የሚደራደሩ፣ ያለ ጨረታ ግዥ የሚፈጽሙ፣ በጠቅላላው በሙስና የተዘፈቁ ግለሰቦችን የሚናገራቸው በመጥፋቱ “ቄሱም ዝም መጽሐፉም ዝም” የሆነ ይመስላል፡፡ ለሥርዓቱ አደገኛ ነው የተባለው ሌብነት ችላ ከተባለ አገርን እንዴት ማስተዳደር ይቻላል? ሕዝቡ ከድህነት ለመውጣት ሲጥር በኑሮ ውድነት እየተሰቃየ እንዴት መቀጠል ይቻላል? የችግሩ ብዛት ታከተን፡፡
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ከሕልፈታቸው ጥቂት ወራት በፊት ስለመንግሥት ሌቦች መኖርና የሥርዓቱ አደጋ መሆናቸውን በምሬት ቢገልጹም፣ እነዚህ ሌቦችን የሚነካ በመጥፋቱ ሌብነት ተቋማዊ ሆኖ አገር ተዘረፈች፡፡ የሕዝቡ ብሶት ጫፍ ደርሶ መንግሥትን እያሳሰበው ነው ቢባልም የመፍትሔ ዕርምጃ አልነበረም፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሲተኩ ደግሞ ጭራሽ ሥርዓቱ ሙሉ በመሉ በሌቦች ታገተ፡፡ እሳቸው ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ቢተኩም፣ ሥርዓቱ በሌቦች እጅና እግሩ እንደተያዘ ነው ያለው፡፡ በባለሥልጣናትና በባለሀብቶች መካከል ያለው ግንኙነት ገደብ ይደረግበት ሲባል ሰሚ በመጥፋቱ፣ አንዳንዶቹ ባለሀብቶች አገር የሚመሩ ይመስላሉ፡፡ የንግድ ሰንሰለቱን አንቀው ይዘውታል፡፡ ሕዝብ ግን ያለ ኃጢያቱ ይገደላል፣ ይፈናቀላል፣ በኑሮ ውድነት እየተቃጠለ ይራባል፡፡ ታዲያ ምን ይሻል ይሆን ስንል አንጋፋው ጓደኛችንን፣ ‹‹ሰው አልሰማ ካለ እንግዲህ አቤቱታው መቅረብ ያለበት ለፈጣሪ ነው፡፡ ፈጣሪ በቃ ሲል ደግሞ የሚሆነውን እናያለን…›› ሲለን የመጨረሻው አማራጭ መሰለን፡፡
(ያሲን አብዱራዛቅ፣ ከቤተል)