Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ብልፅግና የሚለካበት የወቅቱ ሚዛን

የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች ከአዲስ አበባና ከክልል ከተሞች ነዋሪዎች ጋር ሰሞኑን ባካሄዷቸው ሕዝባዊ ውይይቶች ላይ ማኅበረሰቡ የገጠመውን የኑሮ ውድነት ፈራ ተባ ሳይል በምሬት ገልጿል፡፡ ኑሮዬ ምሬቴን የመሰለ ነው ብሎ ብሶቱን አሰምቷል። ሰላማችንን ተነጥቀናል፣ ሰላማችንን አስከብሩልን ሲል አብዝቶ ጠይቋል፡፡

አሉብኝ ያላቸውን ችግሮች ሁሉ በዝርዝር በድፍረት የተናገረበት መድረክም ነበር፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ መኖር እንዳቃተውና ከዚህ በላይ መሸከም እንደማይችል ለገዥው ፓርቲ አመራሮች በግልጽ እወቁልኝ ብሏል።

በተለይም የኑሮ ውድነትን በተመለከተ ከማኅበረሰቡ የተሰነዘሩ አስተያየቶች ችግሩ ምን ያህል ሥር የሰደደና ማኅበረሰቡ እንደተሰቃየ የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ የዋጋ ንረትና የግብይት ሥርዓቱን ስድነት ዘርዝሮ የተገላቢጦሽ ከላይ ወደታች ለመሪዎቹ ያስረዳው ማኅበረሰቡ፣ በቀን አንዴ እንኳን ለመብላት መቸገሩን እወቁልኝ ብሎ ጩኸቱን አሰምቷል፡፡ 

በእነዚህ የሕዝብ የውይይት መድረኮች ላይ የተሰሙት ድምፆች የብዙዎችን ስሜትና መሬት ላይ ያለውን እውነታ ያንፀባረቁ ናቸው፡፡ በጥልቅ ስሜት ሲገለጹ የነበሩ የኅብረተሰቡ ችግሮች በዚያው መድረክ ላይ በተለያየ መንገድ ምላሽ የተሰጠባቸው ቢሆንም፣ ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታት የሚያግዙ ናቸው ተብሎ አይታመንም፡፡ በእርግጥ የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ገዥው ፓርቲና መንግሥት በአግባቡ እንዲረዱ የጠቀሱት መድረኮች እንደነበሩ አይካድም፣ አመራሮቹም በየመድረኩ መፍትሔ እንደሚሰጡ ቃል ገብተዋል።

ወቅታዊው የኢትዮጵያ ችግር የበዛ ነው፡፡ ስለዚህ እዚያው መድረክ ላይ በሚነገሩ ቃላቶች መፍትሔ የሚያገኙ አይደሉም፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን በሁሉም መድረኮች የቀረቡትን የሕዝብ ጥያቄዎች አንድና ሁለት ብሎ ዘርዝሮ በአግባቡ መፍትሔ ለመስጠት ይረዳሉ፣ ይህንንም ማድረግ ከመንግሥትና ከገዥው ፓርቲ የሚጠበቁ ኃላፊነቶች ብቻ ሳይሆኑ ግዴታዎችም ናቸው። በተለይ የኑሮ ውድነትና አጠቃላይ የኢትዮጵያ የግብይት ሥርዓት ላይ የሚስተዋለውን እጅግ ሥር የሰደደ ችግር ቀድሞ ምላሽ መስጠት አዋጭ ይሆናል፡፡

በእርግጥ ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ያለፈችባቸው ተደራራቢ ችግሮች ዛሬ ኅብረተሰቡን ላማረረው የዋጋ ንረት መባባስ አስተዎጽኦ ማድረጋቸው ቢታመንም፣ እያንዳንዱን ለዋጋ ንረቱ መንስዔ የሆኑትን ጉዳዮች ግን በቀላሉ መንግሥት በሚወስዳቸው የመፍትሔ ዕርምጃዎች የሚስተካከሉ በመሆናቸው፣ መንግሥት ለእነዚህ ጉዳዮች ጊዜ ሳይሰጥ ሊያስተካክላቸው ይገባል፡፡ 

በአንዳንድ መድረኮችም ሕዝባዊ ውይይቱን ከሚመሩ የፓርቲው አመራሮች ቃል እንደተገባውና ከዚህም ከማዕከል የብልፅግና ጽሕፈት ቤት እንዳስታወቀው፣ አሉ የተባሉ ችግሮችን ለመፍታት ዝግጅቱና ቁርጠኝነቱ አለ፡፡ ይህ ቃል መሬት ጠብ ሳይል መተግበር አለበት፡፡ ቁልፍ ጉዳዩ ያለውም እዚህ ላይ ነው፡፡ እነዚህን የሕዝብ ጥያቄዎቹን ይዞ አንድ በአንድ ለመመለስ ቃል በተገባው ልክ በተግባር መታየትና ይህንንም ማሳወቅ የመንግሥት ግዴታ ነው፡፡

ይህ ካልሆነ በቀጣይ እስኪ ችግራችሁን ንገሩን ብሎ ሕዝብን ለመጥራት ይቅርና ማሰቡ እንኳን የሚከብድ ይሆናል፡፡ የኅብረተሰቡን ወቅታዊ ስሜት ለመረዳት ታች ድረስ ወርዶ ለማወያየት የተደረገው ጥረት መልካም የመሆኑን ያህል፣ ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ ስለመስጠቱ ሕዝቡ ማረጋገጥ ይፈልጋል፡፡ ያላግባብ የተደረገ የዋጋ ጭማሪ ካለ ይህ እንዲስተካከል ማድረግ የግድ ነው፡፡ 

ያላግባብ ለመበልፀግ አሊያም ሆን ተብሎ የግብይት ሥርዓቱን ለማመስ ሲባል ማኅበረሰቡን ላልተገባ የዋጋ ንረት የዳረጉ አሉ ተብሎ መተማመን ላይ ተደርሷልና እነዚህ አካላት ያሉት እዚሁ በመሆኑ እነሱ ላይ ዕርምጃ በመውሰድ ይኼው አንድ የመፍትሔ ዕርምጃ ወስጃለሁ ማለት ከመንግሥት ይጠበቃል፣ ይገባልም፡፡ 

ለግብይት ሥርዓቱም ሆነ በአጠቃላይ ከሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የተነሱ ችግሮች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እዚያው ፓርቲ ውስጥ ባሉ ግለሰቦች ጭምር በሚፈጸም ደባ የሚፈጠሩ በመሆናቸው፣ እነዚህን የሕዝብ ምሬት ምክንያት የሆኑ ግለሰቦች ሳይውል ሳያድር ማጥራት፣ ለሕግም ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡

በየመሥሪያ ቤቱ የተንሠራፋው ሌብነት፣ በተለይም አንድ ጉዳይ ለማስፈጸም የሚጠይቀው ጉቦ ‹‹ሐላል›› እየታየ መሆኑን ሕዝቡ ያረጋገጠው ነውና፡፡ የተንሰራፋን ሌብነት ማፅዳት የብልፅግና ሌላው የቤት ሥራ ነው፡፡

ለዋጋ ንረቱና በኢኮኖሚው ውስጥ እየተስተዋለ ላለው አለመረጋጋት አንድ ምክንያት የሆነው የፀጥታ ችግር ነውና ይህ ችግር ተቀርፎ ምርት ያለ ችግር እንዲጓጓዝ መደረጉን ማረጋገጥ ይገባል። ይህ ካልሆነ ሕዝብ በገዥው ብልፅግና ፓርቲ ላይ ያሳደረው እምነት አሁን ካለበት በባሰ መልኩ ሊሸረሽር እንደሚችል ማሰብ ተገቢ ነው፡፡

ብልፅግና በውስጡ ያሉ አስተኳሾችን ለመንቀል የሚችልበት ጊዜ አሁን ነው። ይህንን ሳያቅማሙ ማድረግ ለፓርቲው ህልውናን፣ ለሕዝቡም ዕፎይታ የሚሰጥ በመሆኑ አዎንታዊ ዕርምጃ ይውሰድ፡፡ ስለዚህ ከሰሞኑ የሰማናቸው ብዙ ምሬቶችን ፓርቲው ለራሱም ሲል በአግባቡ ሊመልሳቸው ይገባል፡፡ ጥያቄውን ለመመለስ የሕዝብ ትብብር ካስፈለገም ይህንኑ በማድረግ በቶሎ ምላሹን ማሳየት አለበት፡፡

በተለይ የገበያ ሥርዓቱ ወግ እንዲኖረው አሁንም የአሠራር ማሻሻያዎች ያስፈልጋሉ፡፡ የአሠራር ማሻሻያ ብቻ ሳይሆን ማሻሻያዎቹን ተገንዝቦና ከእሱ የሚጠበቅበትን ተረድቶ የሚፈጽም ካድሬ ሳይሆን የሚሠራ ባለሙያ ወደፊት መምጣት አለበት፡፡ ኑሮ ጣሪያ የነካበት፣ ነጋዴው በዘፈቀደ የቤት ኪራይና የመሠረታዊ ሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ በአናት በአናቱ ሲጨምር እየተመለከተ መፍትሔ የማይሰጥ አመራርን መንግሥት አስቀምጦ መፍትሔ የሚጠብቅ ከሆነ ሕዝቡን እያደመጠ እንዳልሆነ መታወቅ አለበት፡፡

ሁሉም ነገር ሥርዓት ያስፈልገዋል፣ በሕግ መመራት አለበት ከተባለ ሁሉንም የሚገዛ አሠራር መዘርጋት ግድ ነው፡፡ ጠንካራ አስፈጻሚን ይሻል፡፡ ዛሬ የተደመጡ ብሶቶች መንስዔ ፈርጀ ብዙ ቢሆንም፣ አንዱ ችግር ሕግ አለመከበሩ ነው፡፡ ተጠያቂነት የሰፈነበት አሠራር ስለጎደለ ነው፡፡ ለምሳሌ የቤት ኪራይ ዋጋ ጉዳይ በዚህ ወቅት በጣም አሳሳቢ ከሆኑ የኅብረተሰቡ ጉዳዮች መካከል በዋናነት የሚጠቀስ ነው፡፡ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ረዣዥም እጆች ያላቸው ደላሎች የሚፈጽሙት ደባ በቤት ኪራይ ዋጋ አተማመን ላይ ጭምር የሚንፀባረቅ በመሆኑ ደላሎችን አደብ ማስገዛትም አንዱ የመፍትሔ አካል ነው፡፡ 

ዜጎች በቀላሉ የቤት ባለቤት የሚሆኑበትና በተመጣጠነ ዋጋ ተከራይተው መኖር የሚችሉበት ዕድል ማረጋገጥ መሠረታዊ ነገር ሆኖ፣ አሁን ባለው ሁኔታ አሠራሩን ሕጋዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ በሰበብ አስባቡ ዕድለኞች መረከብ ያለባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ጉዳይም ከዚሁ ችግር ጋር የሚያያዝ በመሆኑ እነዚህ በቶሎ ካልተፈቱ ብልፅግና ቃል የገባውን እየፈጸመ አይደለም ማለት ነው፡፡ የወር ደሞዝተኞች ትልቁ ወጪ የመኖሪያ ቤት ኪራይ መሆኑን መንግሥት ማወቅ አለበት። ይህንን የተረዳ መንግሥት ደግሞ፣ ችግሩን የመፍታት ኃላፊነትን ለከተማ አስተዳደር ብቻ ሰጥቶ የበኩሌን ተወጥቻለሁ አይልም። ከከተማ አስተዳደሩ በላይ ያሉ ማነቆዎችን ለምሳሌ፣ የመኖሪያ ቤት ብድር የሚቀርብበትን መንገድ ያመቻቻል፣ ለመኖሪያ ቤት ግንባታ የሚውል መሬት የሊዝ ዋጋ የሚቀንስበትን መንገድ በልዩነት እንዲስተካከል ያደርጋል።

በተጨማሪም አዋራ እየጠጣ ያለው የአከራይና የተከራይ የሚገዙበት፣ እንዲሁም የቤት ኪራይ ዋጋ ተመንን የሚደነግገው ረቂቅ ሕግ አዋራው ተራግፎ ሊተገብር ይገባል፣ ይህ ካልሆነ የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር ከባድ ይሆናል፡፡ ኅብረተሰቡ አሉኝ ያላቸውን ችግሮች ለመቅረፍ ቆራጥ መሆን ያስፈልጋል፡፡ እየተበደለና እየተቸገረ ያለው ሕዝብን ለመታደግ ጊዜያዊ መፍትሔዎች የትም እንደማያደርሱ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

ስለዚህ ብልፅግና ነገውን ለማሳመር ከሰሞኑ ከሕዝብ የተሰሙ ድምፆችን በአግባቡ መመለስን ሊያረጋግጥል ካልቻለ፣ ከሕዝቡ ጋር የሚኖረውን ግንኙነት ሊያሻክር ይችላል፡፡ 

ጥያቄዎቹ ግልጽ ናቸው፡፡ ነገር ግን ግልፅና በተግባር የሚታዩ ምላሾችን ይሻሉ፡፡ ከዋጋ ንረት ጋር በተያያዘ የሚታዩ ችግሮች በሙሉ አገር ውስጥ ባሉ ምክንያቶች ብቻ የተከሰቱ ናቸው ማለት ባይቻልም፣ ውጫዊ ምክንያቶቹን ሕዝቡ በሚገባው መንገድ ማስረዳት ግን ተገቢ ይሆናል፡፡ ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ ባሉ ዓለም አቀፋዊ ምክንያቶች ወደ አገር የተሻገሩ የዋጋ ንረቶች እንዲህ ያሉ ናቸው ብሎ ማስረዳትና ሕዝቡም እንዲቀበል ማድረግ ይቻላል። ነገር ግን በቅድሚያ አንገብጋቢ የሆኑ ችግሮችን በቶሎ መፍታት ብልፅግና የሚለካበት የወቅቱ ሚዛን መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፣ ይገባልም።      

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት