Monday, March 4, 2024

የሕዝብ ብሶት በሕዝባዊ ውይይት መድረኮች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

‹‹አገር ውስጥ ሲመረት እናያለን፡፡ ከውጭ አገርም ሲገባ እናያለን፡፡ ይህ ሁሉ ምርት ወዴት እየሄደ ነው በየገበያው ሸቀጥ የለም የምንባለው?›› በማለት ነበር የአዳማ/ናዝሬት ከተማ ነዋሪ የሆኑ አንዲት እናት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድርን አቶ ሽመልስ አብዲሳን በጥያቄ ያፋጠጡት፡፡ እኚህ እናት የፖለቲካ ካድሬና ኢኮኖሚስቱ በየሚዲያው ልራቀቅበት የሚለውን የአቅርቦትና የፍላጎት መሠረታዊ የኢኮኖሚ ጽንሰ ሐሳብ ለምን እንዳልሠራ በአንዲት ዓረፍተ ነገር በቀላሉ ጠይቀዋል፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአቅመ ፖለቲካ አልደረሰም ለሚለውና ሕዝብን ያታለለ ለሚመስለው ጥቂት የፖለቲካ ልሂቅ አስተማሪነቱ ሳይጠቀስ የማይታለፍ መሆኑ ብዙዎችን ያስማማል፡፡

አንድ አንጋፋ ፖለቲከኛ በአንድ ወቅት፣ ‹‹ሕዝብ የፈለገውን ያህል ባያውቅ ዳቦና ሰላም የሚሰጠውን ፖለቲካ ለመለየት ተቸግሮ አያውቅም›› ብለው እንደተናገሩት ሁሉ፣ ሕዝቡ በአካባቢው ስለሚሆነው ነገር በሚገባ ይታዘባል፡፡ እንዲናገር ሲፈቀድለትም ይህንኑ ያንፀባርቃል ተብሎ ነው የሚገመተው፡፡ ከሰሞኑ በአዳማ፣ በአዲስ አበባ፣ በመቱ፣ በባህር ዳር፣ በደሴ፣ በኮምቦልቻ፣ በጎንደር፣ በጅማ፣ በአምቦ፣ በሐዋሳ፣ በአሶሳ፣ በጋምቤላና በመላ ኢትዮጵያ ባሉ ከተሞች በተደረጉ ሕዝባዊ ውይይቶች ላይ ኅብረተሰቡ ያነሳቸው መሠረታዊ ጥያቄዎችም ይህንኑ ያረጋግጣሉ፡፡ 

አገር የሚመራው ብልፅግና ፓርቲ ኅብረተሰቡን ላወያይ ብሎ ተነሳሽነት በመውሰድ ያካሄደው ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች ታላላቅ ጉዳዮች የተነሱባቸው ነበሩ፡፡ መድረኮቹ ሕዝቡ ብሶቱን ለብልፅግና ፓርቲ በሚገባ የተናገረባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ መድረኮቹ ከሁሉ በላይ ደግሞ ሕዝቡ የተሸከመውን መከራና አገሪቱ የምትገኝበትን የፖለቲካ ምስቅልቅል በብዙ መንገዶች ያመላከቱ ናቸው ብሎ መደምደምም ይቻላል፡፡ በእነዚህ መድረኮች ላይ የተስተጋቡ የኅብረተሰቡን ብሶቶች ተመርኩዞ አገር የሚመራው ገዥ ፓርቲ አፋጣኝ የመፍትሔ ዕርምጃዎች ካልወሰደም፣ የአገሪቱ ዕጣ ፈንታ ወዴት እንደሚያመራ ጠቃሚ ጥቆማ አድርገዋል ተብሎም ነው የሚታመነው፡፡

አንድን አገር ወይም ኅብረተሰብ የጋራ ድንበር፣ ባህልና ቋንቋ ብቻ ሳይሆን የጋራ ችግርም እንደሚያስተሳስረው በእነዚህ መድረኮች ታይቷል፡፡ ከጎንደር እስከ ጅግጅጋ የኑሮ ውድነት ወይም የዳቦ ጥያቄ ዋነኛ አጀንዳ ነበር፡፡ ከባህር ዳር እስከ አዳማ ሰላም ተናፋቂ ጉዳይ ሆኖ ነበር፡፡ ከጋምቤላ እስከ ሐዋሳ የመሠረተ ልማት ጥያቄ በተመሳሳይ ሲነሳ ታይቷል፡፡ ከአሶሳ እስከ አምቦ፣ ደሴና ኮምቦልቻ በሰላም ወጥቶ በሰላም የመግባት ጥያቄ በእኩል ደረጃ ሲስተጋባ በእነዚህ መድረኮች ማየትም ተችሏል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የተለያየ ነው፣ የጋራ ማንነትም ሆነ የሚያገናኘው ድልድይ የለም ብሎ ሲፎክር ለኖረው ጥቂት ጠርዘኛ የፖለቲካ ልሂቅ ይህ አጋጣሚ ሕዝቡ ከባህልም፣ ከታሪክም አልፎ ችግርም እንደሚጋራ መመልከት የሚችልበት አጋጣሚ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡

ለዚህ ይመስላል የብልፅግና ዋነኛ ካድሬዎች ከሚመሩት ክልልና አካባቢ ወጥተው በተለያዩ ከተሞች በማቅናት ሕዝባዊ የውይይት መድረኮችን እንዲመሩ የተደረገው፡፡ ስለዚሁ ጉዳይ የሚያብራራ የብልፅግና ሰው ባይገኝም፣ ሆኖም ባህልና አኗኗርን ብቻም ሳይሆን ችግርን በመጋራትና ለመፍትሔ በጋራ በመቆም አንድነትን ማፅናት ይቻላል ብሎ በማመን ፓርቲው ይህን እንዳደረገ መገመት ይቻላል፡፡ የአካባቢያቸውን ብሶት ብቻ አጉልተው ለሚያጮሁ ጥቂት የጊዜው ፖለቲከኞች፣ ከአካባቢያቸው ወጥተው በሌሎች አካባቢዎችም ተመሳሳይ ዓይነት ብሶት መኖሩን እንዲያደምጡ ማድረጉ ትልቅ የአመራር ልምድ የሚሰጥ ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡

ከሁሉ በላይ ግን አገሪቱ የምትገኝበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ማመላከት የሚቻለው በእነዚህ መድረኮች የተገኙ ሹመኞችን በመቁጠር ሳይሆን፣ ሕዝቡ ያስተጋባቸውን ቅሬታዎች በማሳየት ነውና የተነሱ ቅሬታዎች ምን እንደሆኑ መመልከት ተገቢነት ይኖረዋል፡፡ ዋና ዋና በሚባሉት ፋና፣ ኢቲቪ፣ አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ፣ አማራ ሚዲያ ኔትወርክ፣ ኦቢኤንና በሌሎችም ሲዘገብ ከሰነበተው በመነሳት፣ የኅብረተሰቡ ብሶት ምን ገጽታ እንደነበረው መዳሰስ ተገቢ ነው፡፡

ብልፅግና ጉባዔውን ባደረገበት ወቅት የፓርቲው ፕሬዚዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ከሕዝብ ጋር በቀጥታ መወያየት አለብን አሉ፡፡ የምንችለውንና የማንችለውን፣ ልናደርግ የምንፈልገውን ነገር ከሕዝቡ ጋር ፊት ለፊት ተቀምጠን መነጋገር አለብን ሲሉም አከሉ፡፡ የሕዝቡ መከራ የእኛም መከራ ነውና ሕዝቡን እናዳምጠው ሲሉ ለብልፅግና ካድሬዎች አሳሰቡ፡፡ እኛ ስለቁርጥ እያወራን ሕዝቡ ሽሮ ካረረበት አይሆንምና የሕዝቡን ብሶት ማድመጥ ይገባናል ብለው ጥብቅ መመርያ ለካድሬዎቹ አስተላልፈው ነበር፡፡

ብልፅግና ጉባዔውን ባጠናቀቀ ማግሥት በአዲስ አበባ ከተማ የሕዝብ አስተያየት ኢቲቪ ሲሰበስብ፣ አንዲት የአዲስ አበባ ነዋሪ እናት የነጋዴ መጫወቻ ሆነናል ብለው ተናገሩ፡፡ ሕዝቡ የሚተነፍስበት አጥቶ እንጂ ከሚችለው በላይ ኑሮ መሮታል ሲሉም አስተያየታቸውን አከሉ፡፡ ይህ ከሆነ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ክፍላተ ከተሞች በተስተናገዱ ሕዝባዊ ውይይቶች ላይ የተስተጋባው የሕዝብ ስሜት ደግሞ፣ ሕዝቡ እየገፋው ያለውን ከባድ ሕይወት ከብዙ በጥቂቱ ያመላከተ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

በየክፍላተ ከተሞቹ በተደረጉ ስብሰባዎች ኅብረተሰቡ ብልፅግናን እስኪበቃው ድረስ ነግሮታል፡፡ ፓርቲው አሁንም ቢሆን ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ እንዳለው በአንዳንድ መድረኮች የተንፀባረቀ ቢመስልም፣ ነገር ግን በሰሞነኞቹ ስብሰባዎች ለብልፅግና አድናቆት ከማንቆርቆር ይልቅ ብዙ የሕዝብ ምሬት ነበር የተስተጋባው፡፡ በየመድረኮቹ በዋናነት የተስተጋቡ ብሶቶችን ሰብሰብ ሲደረጉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አገልግሎት የሚጠይቁ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ በየክፍላተ ከተሞቹ ከተደረጉት ውጪ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመሩት የማጠቃለያ መድረክ ላይ የተስተጋባውን የሕዝብ ቅሬታ ሲታወስ፣ ይህንኑ የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ የከተማው ሕዝብ ጥያቄ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየጠጠረ መሄዱን ማመላከቻ ሆኖ ሊቀርብም ይችላል፡፡

በዚህ መድረክ ከተገኙ አንድ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት አባት ከተናገሩት ውስጥ፣ ‹‹ብዙ አውርተን ሳይሆን ጥቂት ሠርተን ነው ችግሮችን የምንቀርፈው፤›› የሚል ከባድ መልዕክት ተሰምቷል፡፡ ‹‹ከንቲባ አዳነች ከእርስዎ ሠራተኞች ጀምሮ ከተማ መሀል ለመኖር የሚችል ብዙም የለም ሲሉ፤›› የአገልግሎት ሰጪ ሠራተኞችን ሸክም የጠቀሱት ተናጋሪው፣ ‹‹ሕገወጥ ድለላና ጉዳይ አስፈጻሚነት ሕጋዊ አልሆነም ወይ?›› ሲሉ በጥያቄ መልክ በአገልግሎት ሰጪ መሥሪያ ቤቶች የተስፋፋውን ሕገወጥነት ጠቁመዋል፡፡

‹‹በሥነ ምግባር ትምህርት ልጆች ተምረው ማደግና በግብረ ገብ ዕውቀት መኮትኮት አለባቸው፤›› ሲሉ፣ ሌላኛው የካቶሊክ ሃይማኖት አባት ሊያሳስበን ይገባል ስላሉት ጉዳይ አውስተዋል፡፡ ‹‹የፖለቲካ ሰዎችና ምሁራን ለዚህ ደሃ ጉስቁል ሕዝብ እረፍት ቢሰጡት ይበጃል፤›› ሲሉም ለአገር ይጠቅማል ያሉትን ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ መከባባርና ወንድማማችነት ይጠቅማል፤›› ያሉ አንድ አባት ደግሞ፣ የዓድዋ በዓል ሲከበር እንፎክራለን፣ እንናቆራለን፡፡ ነገር ግን የዓድዋ ተራራን እንኳ ደን አላለበስነውም፤›› ሲሉ ነበር በታሪክ ላይ እየተጣሉ ነገር ግን የጋራ ታሪክን እንኳ ጠብቆ እንደ አገር መቆም ችግር እየሆነ የመጣበትን ሁኔታ ያስረዱት፡፡ ተናጋሪው ሲቀጥሉም፣ ‹‹እኛ የመረጥናቸውን ባለሥልጣኖቻችንን የሚሰድቡብን ሰዎች በሕግ ይገሩልን፤›› ሲሉ አንዳንዶችን ኮንነዋል፡፡ ‹‹ብልፅግና ሦስት ዓይነት አመራሮች አሉት፡፡ የገባው፣ ያልገባውና ግራ የገባው፤›› ያሉት እኚህ አባት፣ ያልገባውን አስተምሮ መመለስ ቢቻልም ነገር ግን ግራ የተጋባውንና በሁለት ቢላዋ ለመብላት ያሰፈሰፈውን ማረቅ ከባድ ነው ብለዋል፡፡

የሥራ አጥነት ችግር፣ የመሥሪያ ቦታ እጥረት፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች ችግርና ለስፖርቱ ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት በዚህ መድረክ በሰፊው ተጠይቀዋል፡፡ ሕግ ላልቷል ያሉ አንዲት አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው፣ ‹‹ወንጀለኛ ወንጀል ሠርቶ ይለቀቃል፡፡ ወንጀለኛ ደረቱን ነፍቶ እየሄደ ንፁኃን አንገታቸውን ደፍተው ይሄዳሉ፤›› በማለት ነበር የዘመኑ ሕግ የማስከበር በሽታ ያሉትን ጉዳይ ያነሱት፡፡

የኑሮ ውድነት ችግር ጥያቄ የዚህ መድረክ አንገብጋቢ ጉዳይ ሲሆን፣ ከንግዱ ማኅበረሰብ ተወካዮች በኩል ሰፋ ተደርጎ እንዲታይ ምክር ተለግሷል፡፡ የኑሮ ውድነት ምንጩ ብዙ ነው ያሉ አንድ የንግድ አመራር የውጭና የአገር ውስጥ ተፅዕኖዎች ተብሎ በየፈርጁ መጠናትና የመፍትሔ ሐሳቦች መፍለቅ እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡ ‹‹በዋናነት የአገራችን የኑሮ ውድነትና የዋጋ አለመረጋጋት ምንጭ የአቅርቦት ችግር ነው፤›› ሲሉ ያብራሩት ነጋዴው ተናጋሪ፣ በዚህ ላይ ተጨማሪ ሐሳቦችንም ሆነ የመፍትሔ ዕርምጃዎችን ለማካፈል ዝግጁነታቸውን አመልክተዋል፡፡ ሕግ የማስከበር ሥራ ቅድሚያ ከተሰጠው ሀቀኛ በሆነ መንገድ በሁሉም ዘርፎች ተገቢ ዕርምጃ መወሰድ ይኖርበታል ያሉት ነጋዴው፣ የንግዱ ሥርዓት እንዲዛባ የሚያደርጉ የመንግሥት ወገኖችና አሠራሮች ጭምር መገራት እንዳለባቸው ነው አያይዘው ያስረዱት፡፡

ከሁሉ በላይ አገር ለሚመራው ብልፅግና ፓርቲ ከባድ የቤት ሥራ የሰጠው ደግሞ፣ ከአንዲት ተሳታፊ የቀረበው ከፓርቲው አሰያየም ጀምሮ ጥያቄ የሚያነሳው ሐሳብ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ፣ ብአዴን፣ ኦሕዴድ፣ ደኢሕዴን፣ ሕወሓት እያለ ሌሎችን በአጋርነት ይዞ ሲሠራ ቆየ፡፡ ብልፅግና ኅብረ ብሔራዊና አገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር አንድ ፓርቲ መሠረትኩ ቢልም፣ ይህ ከስሙ ጀምሮ ሲሆን አናገኘውም፤›› ነበር ያሉት አስተያየት ሰጪዋ በንግግራቸው፡፡ ‹‹ብልፅግና ኅብረ ብሔራዊ ነኝ ካለ የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የትግራይ ብልፅግና ከምንለው የኢትዮጵያ ብልፅግና ብንል አንድነትን ለማምጣት መሠረታዊ ቁም ነገር አይሆንም ነበር ወይ?›› ሲሉ ነበር ተናጋሪዋ በመሠረታዊነት የአገር አንድነትና ሰላምን የማስጠበቁ ጥረት ከየት እንደሚጀምር የጠቀሱት፡፡ ብልፅግና ልክ እንደ ኢሕአዴግ ችግሮችን በማወያየት ላይ ብቻ ሳይሆን፣ መፍትሔ በመስጠት ላይ ማተኮር አለበት ሲሉ ያከሉት ተናጋሪዋ፣ ከሰሞኑ በሕዝባዊ ውይይቶች የተካፈለውን ኅብረተሰብ የብስለት ስብጥር ያመላከተ ጠጣር ሐሳብ ወርውረዋል ማለት ይቻላል፡፡

ከሁሉ በላይ ሕዝቡ እየተጋፈጣቸው ያሉ ችግሮች ምን ያህል እያስመረሩት እንደሆኑ በአንዳንድ ጠያቂዎች የተነሱ ሐሳቦች ቁልጭ አድርገው ያሳዩ ነበር፡፡ ‹‹የቤት ኪራይ የመንግሥት ሠራተኛውን ሊያሳብደው ነው፡፡ የአዲስ አበባ ነዋሪ ተከራይቶ ቤተሰብ መርቶ በደመወዙ ለመኖር አቅቶታል፤›› ነበር ያሉት አንድ ተናጋሪ፡፡ ‹‹የዚህ ከተማ ሀብታሞች ደሃዎች ስንኖር ነውና የምትኖሩት እባካችሁ እኛንም አኑሩን፤›› ሲሉ ከባድ ጥያቄ ያነሱ አንድ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው፣ ቱጃር ነጋዴዎች በማኅበረሰቡ ስቃይ መነገዳቸው የፈጠረውን የምሬት ደረጃን ለማመላከት ሞክረዋል፡፡

‹‹ለጤና መድን ክፈሉ ይባላል፡፡ ነገር ግን በየሆስፒታሉ ያለው አገልግሎት ያስመርራል፡፡ ለልማት አዋጡ፣ ለአገር ተረባረቡ፣ ከመንግሥት ጎን ቁሙ እየተባለ ሕዝብ ይጠየቃል፡፡ ነገር ግን ችግራችን አይቀረፍም፤›› የሚለው ምሬትም በዚህ መድረክ የጎላ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን በሁሉም ደረጃ የሚወክል ጥያቄ ነበር ማለት ይቻላል፡፡

ከአዲስ አበባ ሲወጣም በተለያዩ ክልል ከተሞች በተካሄዱ ሕዝባዊ ውይይቶች ላይ ብዙ ምሬቶችና የሕዝብ ብሶቶች ተስተናግደዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል በኢሉአባቦር ዞን መቱ ከተማ የተካሄደ ስብሰባ፣ ብዙ የሕዝብ ብሶቶች የተስተጋባበት መድረክ ነበር፡፡ መብራት፣ መንገድና መናኸሪያ ይገንባልን ከሚሉ የአገልግሎት ጥያቄዎች ጀምሮ የኑሮ ውድነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመቱ መድረክ ተስተጋብተዋል፡፡

‹‹ሲሚንቶ 900 ብር ገባ ተብሎ ሱቆች ታሸጉ፡፡ ሲከፈቱ ግን ሲሚንቶው 1,300 ብር ገባ፤›› ይላል የአንድ ነዋሪ ምሬት፡፡ ‹‹በያዩ ወረዳ በወያኔ ዘመን የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን እንኳ ብልፅግና ጨርሶ ሕዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ አልቻለም፤›› ይላል የአንዲት ተናጋሪ አስተያየት፡፡ ‹‹የመሠረታዊ ሸቀጦች ዋጋ የናረብንና ኑሮ የተወደደብን በሌላ ሳይሆን፣ የንግድ ቢሮ በአግባቡ ገበያውን ለመቆጣጠር ባለመቻሉ ነው፤›› የሚለው ወቀሳም በሌላ ተናጋሪዎች የቀረበ ነበር፡፡

ከኦሮሚያ ክልል ሳይወጣ በባሌ ዞን ወደ የተካሄደው መድረክ ላይ ደግሞ፣ ‹‹አንድ ኪሎ ጨው በ30 ብር እየገዛን ነው፤›› የሚል የነዋሪ ብሶት ይሰማል፡፡ የመንገድ ፕሮጀክቶች በመጓተታቸውና በመዘግየታቸው ተማረናል የሚሉ ዜጎች ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡ የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች ጥያቄም ሌላው የነዋሪዎች ምሬት ነበር፡፡ በባሌም ቢሆን ልክ እንደ ሌሎች አካባቢዎች በተመሳሳይ የኑሮ ውድነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች የነዋሪዎች ጥያቄዎች ነበሩ፡፡

በአምቦ ከተማ በተካሄደው የምዕራብ ሸዋ ዞን 22 ወረዳዎች የማጠቃለያ የሕዝብ መድረክ ላይ ደግሞ የሰላምና ደኅንነት ጥያቄ ከሁሉ የቀደመ የነዋሪዎች ጥያቄ ነበር፡፡ ‹‹ሰብል መሰብሰብ እንኳ ተቸግረናል፤›› ከሚል ምሬት ጀምሮ፣ ‹‹አዝመራችን በማሳ ላይ እየተቃጠለ ነው፤›› የሚል አሸባሪና ታጣቂ ኃይሎች በነዋሪዎች ላይ እያደረሱት ያሉትን ሰቆቃ የተመለከተ ጥያቄ ከተሳታፊዎች ሲደመጥ ነበር፡፡

‹‹ሽምግልናው ይብቃችሁ ወይም አሸባሪዎቹን የምታስታግሱልን መቼ ነው፤›› የሚለው የምዕራብ ሸዋ ዞን ነዋሪዎች አንገብጋቢ ጥያቄ ነበር፡፡ ‹‹ሰላም አጥተንም በኑሮ ውድነት ተሰቃይተንም እንዴት እንችለዋለን?›› ያሉት ነዋሪ ጥያቄ ደግሞ የአካባቢው ኅብረተሰብ የተጫነበትን መከራ ክብደት ማሳያ ሊሆን የሚችል ነው ተብሎ ይገመታል፡፡

የምዕራብ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዲዳ ጉደታ ከሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹ከዞናችን ሸኔን ለማፅዳት የሄድንበት መንገድ ትክክል ባለመሆኑ ነው ያልተሳካልን፤›› የሚል ሐሳብ ይገኛል፡፡ በሕዝቡ ስለሚጠቀም ነው ኦነግ ሸኔን መንቀል ያቃተን፤ የሚል ሐሳብም ያክሉበታል፡፡

ወደ ቡናው ምድር ጅማ ዞን ሲደረስ፡፡ እዚያ የሕዝብ ብሶት አቦል፣ የቅሬታ ቶና የምሬት በረካ ይገኛል፡፡ ‹‹ቆጮ 120 ብር የምንገዛው ከአሜሪካ ስለሚመጣ ነው ወይ?›› ይላሉ አንዲት እናት በጅማ ሕዝባዊ ውይይት ላይ አስተያየት ሲሰጡ፡፡ ‹‹በርበሬስ በኪሎ 300 ብር የምንሸምተው ከውጭ አገር እያስመጣን ስለሆነ ነው እንዴ?›› ሲሉ ገበያው በኅብረተሰቡ ላይ የፈጠረውን ምሬት አክለዋል፡፡ በጅማ ዞን ውስጥ ያሉ ስድስት ያህል ከተሞች መብራት የላቸውም ይላሉ አንድ ነዋሪ፣ የመሠረተ ልማት ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ፡፡ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ደግሞ፣ ‹‹በሦስት ዓመታት በፈተና ውስጥም ሆኖ ብልፅግና ብዙ ለውጥ አምጥቷል፡፡ ሕዝቡም ደግፎታል፡፡ ነገር ግን የሕዝቡ ድጋፍ ሳይቋረጥ እንዲቀጥል ከተፈለገ ለውጡ በፈጣን ሁኔታ መቀጠል አለበት፤›› ሲሉ ነበር ብልፅግና የነዋሪውን ጥያቄ ከመመለስ ውጪ ምንም ድጋፍ የማግኛ አማራጭ እንደሌለው ያሳሰቡት፡፡

የአዳማ ከተማው ሕዝባዊ ውይይት ደግሞ አስገራሚ ሐሳቦች የተደመጡበት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በኦሮሚያ ርዕሰ መስተዳደር በአቶ ሽመልስ አብዲሳ የተመራው መድረክ ስለኦነግ ሸኔና ስለንግዱ ማኅበረሰብ በተነሳው ሐሳብ አነጋጋሪ ዘገባዎች የተሠሩበት ነበር፡፡ በመድረኩ የኑሮ ውድነትና የሥራ አጥነት ችግር ተስተጋብቷል፡፡ በአገር ቤት የሚታረሰውና ከውጭ የሚገባው ወዴት እየገባ ነው የሸቀጦች ዋጋ የናረው የሚል መሠረታዊ ጥያቄን ጨምሮ፣ ምርት እየደበቁ ሕዝቡን በመንግሥት ላይ እንዲነሳ የሚያደርጉ አሻጥረኛ ነጋዴዎች ለምን አንድ አይባሉልንም የሚሉ ምሬቶችም ተስተጋብተዋል፡፡

አስገራሚው ደግሞ፣ ‹‹ኦነግ ሸኔ ማን እንደሆነ ለምን አጣርታችሁ አትነግሩንም? ኦነግ ሸኔ ማን ነው? ከተማ ነው ወይስ ገጠር ነው?›› በማለት ከአንድ ነዋሪ የቀረበ ጥያቄ ነበር፡፡ አንድ አስተያየት ሰጪ ደግሞ ክልሉ በሙስና የነቀዘና ያለ ገንዘብ አገልግሎት የማይገኝበት መሆኑን በድፍረት አውስተዋል፡፡ ፋይል ለማውጣትም ሆነ ፊርማ ለማግኘት በብር ነው ሲሉ ነበር ነዋሪው ምሬታቸውን ያሰሙት፡፡

ይህን ተከትሎ ምላሽ የሰጡት አቶ ሽመልስ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ሌባ እንጂ ነጋዴ የለም፣ ሌብነት እንጂ ንግድ አይታወቅም፤›› ሲሉ ነበር የተናገሩት፡፡ ‹‹አርሲ ላይ በ13 ብር አንድ ኪሎ ሽንኩርት ገዝቶ አዲስ አበባ ላይ 50 ብር መሸጥ ሌብነት እንጂ ንግድ አይደለም፡፡ ይህን ዓይነት ንግድም በዓለም ላይ አይታወቅም፤›› በማለት ነበር አቶ ሽመልስ ሐሳባቸውን የበለጠ ያጠናከሩት፡፡ በአገሪቱ ግብይት ውስጥ ፍትሐዊ የንግድ ውድድር አለመስፈኑን ያሰመሩበት አቶ ሽመልስ፣ በንግድ ስም የተደራጀውንም ሆነ በአመራሩ ውስጥ የተሰገሰገውን ሌባ ማረም ያስፈልጋል ሲሉ ነበር የገለጹት፡፡

በሙስናና በምዝበራ ሲበዘበዝ የቆየው የኦሮሚያ ክልል ከለውጡ በኋላ በተሠሩ ሥራዎች ገቢው በሦስት ዕጥፍ ማደጉንና በጀቱን ደግሞ በሁለት ዕጥፍ ማሳደጉን ያስረዱት አቶ ሽመልስ፣ ሌብነትን ሥራ ያደረጉ ኃይሎች ግን በብሔር፣ በፖለቲካና በዘመድ ተደራጅተው በኦንላይን ሚዲያዎች ዘመቻ እየከፈቱ ዘረፋቸውን ለመቀጠል ይሞክራሉ ሲሉ ነበር የችግሩን ውስብስብነት ያብራሩት፡፡ ስለኦነግ ሸኔ ለተነሳው ጥያቄ ደግሞ አጋጣሚ ሲያገኝ ጥቃት የሚሰነዝርና አንዴ ጫካ፣ ሲመቸው ሕዝብ መሀል የሚደበቅ ቡድን ነው በማለት ፈርጀውታል፡፡ ቡድኑ የፖለቲካ ዓላማ የሌላቸው ሽፍታዎች ስብስብ ነው ያሉት አቶ ሽመልስ፣ ‹‹ወጣቶችን አባ ገዳዎች ከጥፋት ልትመልሷቸው ይገባል፤›› በማለት ነበር ጥሪ ያቀረቡት፡፡

በጋምቤላ ከተማም በተካሄደው ሕዝባዊ ውይይት ላይ በተመሳሳይ የኑሮ ውድነትን፣ የፀጥታ ችግርንና መልካም አስተዳደርን በሚመለከት የተስተጋባው ሕዝባዊ ቅሬታ ከፍ ያለ ነበር፡፡ በጋምቤላ ድንበር ተሻጋሪው የሙርሌ ጎሳ ጥቃት ጉዳይ በአሳሳቢነት ተነስቷል፡፡ የትምህርት ጥራትና የመምህራን ጥቅማ ጥቅም ጥያቄ በመድረኩ ሲወሳ ነበር፡፡ የመሬት አቅርቦትና ሥራ ፈጠራ ጋምቤላ ላይ የነዋሪው ጥያቄ ነበሩ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ከተማው የተመቻቸ የገበያ ቦታ ስለሚያስፈልገው ገበያ ይቁምለት የሚል ጥያቄም ቀርቧል፡፡ አሻጥረኛ ነጋዴ የሚል ወቀሳም የንግዱ ማኅበረሰብ ላይ ሲቀርብ ነበር፡፡

ይህን ሁሉ አድምጠው ምላሽ የሰጡት የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡመድ ኡጁሉ በበኩላቸው፣ መንግሥት እንደ ከዚህ ቀደሙ ሰምቶ ዝም እንደማይልና በተጨባጭ ተግባራዊ ምላሽ እንደሚሰጥ ቃል ገብተዋል፡፡ አገሪቱ በኑሮ ውድነት የምትፈተነው በአቅርቦትና በምርታማነት ችግር ነው ያሉት አቶ ኡመድ፣ ሰፊና ለመስኖ ምቹ የሆነ ለም መሬት ያለው ጋምቤላ ክልል ለዚህ ችግር መፍትሔ የሚሆን ሥራ እንደሚሠራም ቃል ገብተዋል፡፡

በቤንሻንጉል ጉምዝ አሶሳ ከሚገኙ ሦስት ዞኖችና አንድ ልዩ ወረዳ ውስጥ በአንፃራዊነት አሶሳ ከተማ ብቻ ነው ሰላም ያለው የሚል የነዋሪዎች አንገብጋቢ የሰላም ጥያቄ ተነስቷል፡፡ መተከል ከመንግሥት አቅም በላይ ሆኖ ነው ወይ ሰው ሲታረድ ዝም የሚባለው የሚለው ጥያቄም በዚህ መድረክ ሳይነሳ አላለፈም፡፡ ቲማቲም፣ ሽንኩርትና ሙዝ ከውጭ ስለሚመጣ ነው ወይ የተወደደብን የሚል ምሬትም የኑሮ ውድነቱ የክልሉ ነዋሪ አንዱና ወሳኙ አጀንዳ መሆኑን ያሳያል፡፡ ‹‹በክልላችን በተትረፈረፈ ሁኔታ የሚመረተው ማንጎ በኪሎ 25 ብር ይሸጣል፤›› የሚል ቅሬታ ተሰምቷል፡፡ መስኖና መሬት የተረፈው ክልል እያለ ምርቶች ለምን ከገበያ ይታጣሉ የሚለው ከኑሮ ውድነት ችግር ጋር የተሳሰረ የአሶሳ መድረክ አጀንዳ ነበር፡፡

የመከላከያ ሚኒስትሩ አብረሃም በላይ (ዶ/ር)፣ ከምንም በላይ መንግሥታቸው ለሰላም ቅድሚያ እንደሰጠ በዚህ መድረክ ለተሰበሰቡ ለአሶሳ ነዋሪዎች ነግረዋቸዋል፡፡ ‹‹በችግር ውስጥም ሆነን በዚህ ክልል የታላቁ ህዳሴ ግድብን እያስቀጠልን ነው፤›› ያሉት አብረሃም (ዶ/ር)፣ ‹‹ሌባን የማያቅፍ ሽፍታን የማይደብቅ ሕዝብ እስካለን ድረስ ችግሮቻችንን ከሕዝብ ጋር ሆነን እንፈታለን፤›› በማለት ለነዋሪው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ከእሳቸው ጎን ሆነው የሕዝቡን ቅሬታ ያደመጡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው፣ መንግሥትና ሕዝብ መተባበር እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ በኢትዮጵያ ግጭት እንዲፈጠርና በሕዝቦች መካከል መጠራጠር እንዲስፋፋ የሚፈልገው ኃይል እጅግ ሰፊ መሆኑን የተናገሩት አቶ አሻድሊ፣ ይህን በተረዳ መንገድ ምላሽ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ የገንዘብ ሚኒስትር ደኤታው ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እና የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ በመሩት ስብሰባ፣ የድርቅ ችግር ዋናው ጥያቄ ነበር፡፡ የውኃ እጥረት ብቻ ሳይሆን ነዳጅ በኮንትሮባንድ ወደ ጎረቤት አገሮች ይወጣል የሚል ምሬትም ከሕዝቡ ቀርቧል፡፡ በኋላ የመንግሥት ሠራተኞች በሥራ ገበታቸው አይገኙም የሚል የዕርምት ጥያቄ የቀረበ ሲሆን፣ የኑሮ ውድነትና የመሠረተ ልማት አቅርቦት ችግሮችን በሰፊው የተሰማበት ነበር የጅግጅጋው መድረክ፡፡ መንግሥት ችግር ብቻ ከማድመጥ ባለፈ በተግባር መልስ ይስጠን ሲሉ የጅግጅጋ ነዋሪዎች ጠይቀዋል፡፡

በአርባ ምንጭ በደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳውና በጤና ሚኒስትሯ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) የተመራ ሕዝባዊ ውይይት የተካሄደ ሲሆን፣ የመልካም አስተዳደርና የኑሮ ውድነት ችግሮች በዋናነት በነዋሪዎች ተነስተዋል፡፡ አርባ ምንጮች በሚገኙባት ባለባት ከተማ ውኃ እያጣን ነው የሚል ስሞታ ይቀርባል ተብሎ ማመን ቢከብድም፣ በመድረኩ የተሰማው ግን ይኸው ነው፡፡ የአደረጃጀት ጥያቄን በአስቸኳይ ለመፍታት ምንድነው ችግሩ የሚለው አጠቃላይ የደቡብ ክልል ጥያቄ ተብሎ ነበር የቀረበው፡፡ ኢንቨስትመንትና የተለያዩ መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ወደ አርባ ምንጭ መስፋፋት አለባቸው የሚል ጥያቄም ተስተጋብቷል፡፡ ከአርባ ምንጭ በተጨማሪ በሐዋሳ ተስተናግዶ በነበረው ሕዝባዊ ውይይት ላይም የመሠረተ ልማትና የፕሮጀክቶች መዘግየት ዋና አጀንዳ ሆነው ቀርበዋል፡፡ የሥራ ፈጠራና የኑሮ ውድነት የሐዋሳ ነዋሪዎች አንገብጋቢ ብለው ካቀረቧቸው ነጥቦች ከብዙ በጥቂቶቹ ነበሩ፡፡

በሌላ በኩል በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ቦንጋ ከተማ የመሠረተ ልማት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በነዋሪዎች የቀረበ ጉዳይ ነበር፡፡ ዳውሮ፣ ኮንታ፣ ካፋና በሌሎችም አካባቢዎች መንገድም ሆነ መሠረታዊ የውኃና ሌላም መሠረተ ልማት የላቸውም ነው የነዋሪዎች ዋና ቅሬታ፡፡

በመላው ኢትዮጵያ በተለያዩ ከተሞች የተስተናገዱ ሕዝባዊ ውይይቶች ላይ በተሳታፊዎች የተነሱ ቅሬታዎች ብዙዎቹ ተመሳሳይነት ያላቸው ሲሆን፣ በብዙዎቹ መድረኮች የመሠረተ ልማት፣ የመልካም አስተዳደር፣ የኢኮኖሚ፣ የኑሮ ውድነትና የአገልግሎት አቅርቦት ችግሮችን የተንተራሱ ሐሳቦች ነበሩ የተነሱት ማለት ይቻላል፡፡ እነዚህ መሠረታዊ የሚባሉ የመንግሥትን ምላሽ የሚሹ ጥያቄዎች ደግሞ አገር ለሚመራው ፓርቲ ለብልፅግና ብቻ ሳይሆን፣ አገር ለመምራት ለሚፎካከር ለሌላ የፖለቲካ ኃይል ወሳኝ ግብዓት እንደሚሆኑ ነው የሚታመነው፡፡

በአማራ ክልል ከተሞች የጥያቄዎቹ ይዘት ከሌሎቹ አካባቢዎች በተለየ በአንድ ወሳኝ ጉዳይ ላይ ያጠነጥናል፡፡ በአማራ ክልል በተለይ በጎንደር፣ በደሴ፣ በኮምቦልቻና በባህር ዳር ከተሞች የተደረጉ ውይይቶች ላይ የክልሉን ሕዝብ የልብ ትርታ ሊያመላክቱ የሚችሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ በሁሉም (ማለትም በአራቱም ከተሞች) በተስተናገዱ ስብሰባዎች ላይ ሕዝቡ ካነሳቸው ጥያቄዎች መካከል፣ የአማራ ሕዝብ ህልውና ፈተና ላይ ወድቋል የሚለው ወሳኝ ነጥብ ጎልቶ ሲስተጋባ ነበር፡፡

አማራን እንደ ሕዝብ ከሥጋት ቀጣና የማውጣትና ህልውናውን የማስጠበቅ ጉዳይ በደሴም፣ በኮምቦልቻም፣ በባህር ዳርም ሆነ በጎንደር ተነስቷል፡፡ በመላው ኢትዮጵያ ያለው አማራ ማኅበራዊ እረፍት እያጣ ነው የሚል እምነት በአማራ ክልል ሕዝብ ዘንድ ጎልቶ እንደሚብላላ በአራቱም መድረኮች ከተነሱ ጥያቄዎች መገምገም ይቻላል፡፡ ይህን መሰሉ መሠታዊ የህልውናና የደኅንነት ዋስትና ጥያቄ ደግሞ በብዙዎች ዘንድ በየደረጃው ባለ መዋቅር ሳይሆን፣ በፖለቲካ ውሳኔ እንደሚፈታ ከመድረኮቹ በተነሱ የውይይት ሐሳቦች መገምገም ይቻላል፡፡

የአማራ ክልል ከተሞች ነዋሪዎች ከተጋሯቸው ሌሎች ጥያቄዎች መካከል ደግሞ የፀጥታ መዋቅሩን መከፋፈል የተመለከተው ነጥብ ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡ በፋኖ ስም መነገድና መዝረፍ የነዋሪዎች አንዱ ስሞታ ነበር፡፡ ሌላው በፖለቲካ አመራሩ በኩል በቀዬና በጎጥ የማሰብ አባዜ ሕዝቡን ለክፍፍል እየዳረገው ነው የሚለውም ከሕዝቡ የተነሳ ነበር፡፡ በሃይማኖትም ሆነ በፖለቲካ ጠርዝ የመያዝ ችግርም እንዲሁ የክልሉ ሰላምና አንድነት በጽንፈኝነት እንዲፈተን ያደረገ አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑ ተነስቷል፡፡ አማራ ክልል በጦርነት ደቆና ብዙ ጉዳት ደርሶበት ሳለ መልሶ ማቋቋሙ ግን በመንግሥት ተዘንግቷል የሚለው የሕዝብ ብሶትም ጎልቶ ነው የቀረበው፡፡ በሌላም በኩል የወልቃይት ጠገዴ፣ እንዲሁም የራያ ማንነት ጥያቄዎች በፖለቲካ ውሳኔ እንዲፈቱ የሚጠይቁ ሐሳቦች ቀርበዋል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ በወረራ የተያዙ አካባቢዎች ነፃ እንዲወጡ ይደረግ የሚል ቅሬታም ከነዋሪዎች ተስተጋብቷል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ሕዝባዊ መድረኮችን የመሩት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የአሁኑ ሕዝባዊ ውይይት ሕዝቡ የሚሰማውን ቅሬታና ብሶት አመራሩ እንዲሰማ ዕድል መፍጠሪያ ነው ብለው ነበር፡፡ በደሴ ከተማ ሕዝባዊ ስብሰባን የመሩት የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል፣ ‹ብዙ ሰምተናል፣ ቀጣዩ የቤት ሥራችን የሰማነውን በተግባር መተርጎም ነው?›› ብለው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ደግሞ፣ አመራሩ ታች ድረስ ወርዶና ሕዝቡ ውስጥ ገብቶ በማወያየት የኅብረተሰቡን ፍላጎት ተከትሎ መፍትሔ መስጠት እንደሚገባው መመርያ መስጠታቸው አይዘነጋም፡፡

በኢትዮጵያ ፖለቲካ የሕዝብ ብሶትና ምሬትን መስማት ለአመራሩ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ኢሕአዴግም የአንዳንድ ነዋሪዎችን ብሶት የሚሰማባቸው አደረጃጀትን የተከተሉ ሕዝባዊ ስበሰባዎች ነበሩት፡፡ ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን እንደመጡ በየክልሉ ዞረው ሕዝብ ያወያዩባቸው መድረኮች ብዙ ነበሩ፡፡ የአሁኑን መድረክ በተስተጋባበት ቅሬታ ዓይነትና ብዛት ብቻ የተለየ ነበር ማለት የማይቻለው በብዙ ምክንያቶች ነው፡፡ ከየመድረኩ የተገኘውን ሐሳብ የብልፅግና መንግሥት ግብዓት አድርጎ በመውሰድ ምላሽ ለመስጠት ከተጠቀመበት ግን፣ አጋጣሚው ከዚህ ቀደም ያልተሞከረና በዓይነቱ ልዩ ይሆናል ተብሎ ይታመናል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -