Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልየውጮቹን የመጋቢቱን ‹‹መፀው›› ያከበረችው ኢትዮጵያ የራሷን የመስከረሙን ‹‹መፀው›› የምታከብረው መቼ ነው?

የውጮቹን የመጋቢቱን ‹‹መፀው›› ያከበረችው ኢትዮጵያ የራሷን የመስከረሙን ‹‹መፀው›› የምታከብረው መቼ ነው?

ቀን:

አዲስ አበባ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ የአምስት አገሮችን የአዲስ ወቅትና የአዲስ ዓመት መባቻን ከአገሮቹ ጋር አክብራለች፡፡ ከእስያና ከአውሮፓ የተወጣጡት ህንድ፣ ፓኪስታን፣ ካዛኪስታን፣ አዘርባጃንና ቱርክ በኤምባሲዎቻቸው አማካይነት ከኢትዮጵያ ጋር ያከበሩት ‹‹ኖውሩዝ›› ተብሎ የሚታወቀውን በዓላቸውን ነው፡፡

ኖውሩዝ በልሳነ ፋርስ ‹‹አዲስ ቀን›› ማለት ሲሆን፣ በየዓመቱ ማርች 21 ቀን ይውላል፡፡ ቀኑ የአዲስ ዓመት መነሻ ብቻ ሳይሆን ከአራቱ ወቅቶች አንዱ የሆነው መፀው (ስፕሪንግ) የሚጀምርበት ነው (በኢትዮጵያ ግን ፀደይ ነው፡፡ እነሱ ጋ በጋ ሲሆን እኛ ጋ ክረምት እንደሚሆነው)፡፡ በተጨማሪም ዕለቱ ቀንና ሌሊት እኩል (12፣ 12 ሰዓት) ከሚሆኑበት እንዲሁም የኢራን/ፋርስ ኢስላማዊ የፀሐይ ካሌንደር መባቻ ከሆነው ፋርቫርዲን ጋርም ይገጥማል፡፡

ከጥንት መሰጶጣሚያ ሥልጣኔና ከፋርስ ግዛተ አፄ (ኢምፓየር) የፈለቀው ኖውሩዝ፣ በተለያዩ አገሮች የሚገኝ የሁሉም እምነት ተከታይ ሕዝብ የሚያከብረው ቤተሰባዊ በዓል በመሆኑ የመንግሥታቱ ድርጅት የባህል ተቋም ዩኔስኮ የሰው ልጆች ወካይ ቅርስ አድርጎ መዝግቦታል፡፡ መመዝገብም ብቻ ሳይሆን በዓሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ማርች 21 ቀን እንዲታሰብም ቀን ቆርጦለታል፡፡

- Advertisement -

ይህንኑ የዩኔስኮ ድንጋጌ ተከትሎ ነው በአዲስ አበባ የሚገኙ አምስት ኤምባሲዎችና ዩኔስኮ ዓለም አቀፉን የኖውሩዝ ቀን ኢትዮጵያ ጋር ተባብረው መጋቢት 18 ቀን 2014 ዓ.ም. ያከበሩት። በዓሉን ከተጠቀሱት አምስቱ አገሮች በተጨማሪ አፍጋኒስታን፣ ኢራን፣ ታጃክስቲያን፣ በእስያ ውስጥ የሚገኙ ጥቂት የቀድሞዋ ሶቪዬት ኅብረት ሪፐብሊኮች ያከብሩታል፡፡ እንዲሁም ትውልዳቸው ከፋርሳውያንና ኢራን የሚመዘዙትም አዲስ ዓመታቸውን ይቀበሉበታል፡፡ በጆርጂያ፣ በኢራቅ፣ በሶርያና በቱርክ የሚገኙ ኩርዶችም ሲያከብሩ በየቦታው የሚገኙ ማኅበረሰቦችም የክብረ በዓሉ ተጋሪ ናቸው፡፡

ከሦስት ሺሕ ዓመታት በላይ ሲከበር መቆየቱ የተዘገበለትና ከአሥራ ሦስት ዓመታት በፊት በዩኔስኮ የተመዘገበው ኖውሩዝ፣ በአዲስ አበባ ለመጀመርያ ጊዜ ሲከበር
በኢትዮጵያ የካዛኪስታን አምባሳደር ባርሊባስ ሳዲኮቭ እንደገለጹት፣ ኖውሩዝ የስፕሪንግ [መፀው] ወቅት መግቢያ፣ የተፈጥሮ መታደስና የአዲስ ዘመን ማብሰሪያ ቀን ነው።
በዓሉ ሰላምን፣ አንድነትንና መልካምነትን እንደሚያመላክት ጠቁመው፣ ይህም በመከባበር ላይ የተመሠረተውን ግንኙነት ለማጠናከርም ትልቅ ፋይዳ እንዳለው መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡ በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር) በበኩላቸው፣ በዓሉ በኢትዮጵያ መከበሩ  ከአገሮቹ ጋር ያለውን ግንኙነትማጠናከር ባለፈ ከሕዝቦቻቸው ጋር ያለውን የባህል ትስስር ለማጠናከርና ወዳጅነትን ለመፍጠር እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

ይህ የኖውሩዝ የእነሱ የመፀው መጀመርያ በዓል በቀዳሚው የጁልያን ካሌንደር መሠረት ማርች 21 ቀን ይውል የነበረው ከኢትዮጵያው የመጋቢት 25 ቀን የፀደይ መቀበያ ዋዜማ ጋር የሚገጥም ነው፡፡ የግሪጎርያን ካሌንደር ጁሊያንን በ15ኛው ምዕት ሲከልስ በ13 ቀን ወደ ኋላ በመሳቡ መጋቢት 12 ላይ እንዲውል አድርጎታል፡፡

ኢትዮጵያስ የራሷን የመፀው ወቅት መጀመርያ የምታከብረው መቼ ነው?

የእስያና የመካከለኛ አውሮፓ አገሮች የወቅት መለወጫቸውን ከክረምት ወደ መፀዋቸው መሸጋገሪያ ኖውሩዝን እንዳከበሩት ሁሉ፣ በኢትዮጵያም ዛሬ እሑድ መጋቢት 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ቀንና ሌሊቱ እኩል 12፣ 12 ሰዓት የሚሆንበት፣ በጋ ወጥቶ ነገ መጋቢት 26 ፀደይ የሚገባበት ነው፡፡ በክብረ በዓል ደረጃ ባይከበርም በጥንታዊ ካሌንደሮች ሁሌ እንደታሰበ ነው፡፡

በክብረ በዓል ደረጃ ግን ሰኔ 26 ቀን የሚገባው የኢትዮጵያ ክረምት የሚወጣበት መስከረም 25 ቀን ከቅድመ አክሱም ጀምሮ ከአራት ሺሕ ዓመታት በላይ የመፀው (አበባ ማለት ነው) በዓል ‹‹ተቀጸል ጽጌ›› (አበባን ተቀዳጅ) እየተባለ ይከበር ነበር፡፡ በጽሑፍ ደረጃ ተሰንዶ የምናገኘው በስድስተኛው ምዕት ዓመት የተነሳው የኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍና የዜማ አባት ቅዱስ ያሬድ በጻፈው ድጓ ላይ ነው፡፡ ንጉሠ ነገሥቱን ገብረ መስቀል በማንሳት ‹‹ተቀጸል ጽጌ ገብረ መስቀል ሐፀጌ›› (አፄ ገብረ መስቀል አበባን ተቀዳጅ) እያለ ዘምሯል፡፡ ይኸው በዓል በ15ኛው ምዕት ግማደ መስቀሉ መስከረም 10 ቀን መምጣቱን ተከትሎ ተቀጸል ጽጌም አብሮ እንዲከበር መደረጉ በታሪክ ተመዝግቧል፡፡

ተቀጸል ጽጌ እስከ 1966 ዓ.ም. ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ድረስ በኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት ሲከበር ቆይቷል፡፡ በዘመነ ደርግ በመዘለሉ ዳግም መስከረም 10 ቀን አበባ እየተያዘ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በ1987 ዓ.ም. መከበር የተጀመረ ሲሆን አሁንም ትውፊቱ ቀጥሏል፡፡

ፈ ሊቅ አክሊሉ ገብረኪሮስ እንደጻፉት፣ የክረምት  ተረካቢው መፀው  እንደ  ክረምት  የውኃ  ባህርይ ያፈላል፡፡ ይገናል፡፡ እንቡር እንቡር ይላል፣ ይዘላል፣ ይጨፍራል፡፡ ከዚህም የተነሳ ወንዞች ይሞላሉ፡፡ ምንጮች ይመነጫሉ፡፡  አዝርዕትና  አትክልት  ሐዲሳን  ፍጥረታት ሆነው ይነሳሉ፡፡ ይበቅላሉ፣ ይለመልማሉ፡፡

አበባና ነፋስን ቀላቅሎ የያዘው ዘመነ መፀው ምሥጢሩ መዓዛ መስጠት፣ እንቡጥና ፍሬ ማሳየት እንደሆነም ተመልክቷል፡፡

ዐደይ አበባን ያቀፈችው መፀውን ብሎም የተቀፀል ጽጌ በዓልን ዳግም እንደ ዘመነ አክሱም ነፍስ ዘርቶ በመስከረም 25 ቀን በኢትዮጵያ እንዲከበር የሚያደርገው ማን ይሆን?

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...