Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመር ለኮንትራክተሮች ትልቅ ፈተና መሆኑ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ በግንባታ ዕቃዎች ላይ የታየው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ፣ በኮንትራት በተቀበላቸው ፕሮጀክቶች ከመፈተኑም በተጨማሪ፣ በቀጣይ ለሚረከባቸው ፕሮጀክቶችም ምን ማድረግ እንዳለበት እንዳሳሰበው አስታወቀ፡፡

የግንባታ ዕቃዎች ዋጋ ከሁለት እስከ ሦስት እጥፍ መጨመራቸው ለኮንትራክተሮች ትልቅ ፈተና በመሆኑ፣ ከዚህ በኋላ ወደ ኮርፖሬሽኑ የሚመጡ ኮንትራቶች ላይ ትኩረት አድርጎ እይሠራ ነው ሲሉ በኮርፖሬሽኑ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምርያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥንፉ ሙጬ ተናግረዋል፡፡

ለጊዜው ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች በግብዓት እጥረትና ዋጋ መወደድ ምክንያት ከገበያ ውጪ መሆናቸው እየተነገረ ነው፡፡

ኮርፖሬሽኑ የገበያ ዋጋ የማይረጋጋ ከሆነ ችግር ውስጥ የሚገባ መሆኑን ገልጾ፣ ከዚህ በኋላ የሚመጡ ኮንትራቶችን አሁን ባለው ዋጋ መቀበል እንደማይችል አስታውቋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በተያዘው በጀት ዓመት 37.1 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ 49 ፕሮጀክቶችን ቀደም ሲል ባስገባቸው ግብዓቶችና በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን በመጠቀም ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አቶ ጥንፉ ገልጸዋል፡፡

በአገር ውስጥ የሚተኩ ምርቶችን አሁን ካለው የምርት መጠን  በላይ ጨምሮ  ለማምረት እየሠራ መሆኑንም ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲቪል ኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አበበ ድንቁ (ፕሮፌሰር) በበኩላቸው፣ የግንባታ ግብዓቶችን ከዚህ ቀደም በአገር ውስጥ መተካት ጥረት ባለመደረጉ አሁን ሁኔታዎችን እያከበዳቸው ነው ብለዋል፡፡

‹‹በአሁኑ ጊዜ አገሪቱ ያለችበት የፀጥታ ችግር በቅፅበት በአገር ውስጥ አምርተን ፍላጎት ማሟላት አንችልም፡፡ በየክልሉ ያሉ እንደ ዕምነበረድ ያሉ ምርቶችን ለመጠቀም የሰላም አለመኖር ትልቅ ችግር እየፈጠረ ይገኛል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በአገር ውስጥ የሚመረት የዕምነበረድ ውጤት ዋጋ ከዓመት በፊት ከነበረው መቶ ፐርሰንት የነበረ መሆኑን፣ ከወር በፊት ከነበረው ደግሞ 20 በመቶ መጨመሩን አበበ (ፕሮፌሰር) አክለዋል፡፡

ግንባታ የረዥም ጊዜ ሥራ ስለሆነ ሲጀመር ትክክለኛ የዋጋ ተመን ሊኖር ስለማይችል 20 በመቶ ጭማሪ ወይም ቅናሽ ሊኖረው እንደሚችል፣ ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ የመቀነስ ሁኔታ ባይታይም በተገመተበት ዋጋ ስለማይጠናቀቅ የዋጋ ጭማሪ መከተሉ አይቀሬ ነው ብለዋል፡፡

የግንባታ ግብዓቶች ዋጋ የሚጨምርባቸው ምክንያቶች ከውጭ የሚመጡ ዕቃዎች የሚገቡበት የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የነዳጅ ዋጋ መጨመር፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ታሪፍ መጨመርና ሰው ሠራሽ የዋጋ ጭማሪ መሆናቸውን ደግሞ የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ሀብተማርያም አስረድተዋል፡፡

በተቆረጠ ዋጋ የሚዋዋሉ ኮንትራክተሮች በአሁኑ ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ከገበያ የመውጣት ዕድላቸው ሰፊ ነው ሲሉ አበበ (ፕሮፌሰር) ጠቁመው፣ እነዚህ ኮንትራክተሮች ሠርተው ከሚከስሩ ይልቅ ፕሮጀክቶቹን ማቆማቸው የተሻለ ነው ብለዋል፡፡

ባልተቆረጠ ዋጋ የሚሠሩ ፕሮጀክቶች የዋጋ ማሻሻያ ማድረግ የሚችሉት 20 በመቶ ቢሆንም፣ አሁን ባለው የገበያ ዋጋ መሠረት ግን እስከ 50 በመቶ ጭማሪ በማድረግ ከሕግ ውጪ መሄድ ይኖርባቸዋል ሲሉም አክለዋል፡፡

‹‹ይህ ሕግ ከመጣሱ በፊት የሚመለከተው አካል ደንቡን ማሻሻል ይኖርበታል፣ ይህ ደንብ የማይሻሻል ከሆነ ደግሞ የግል ብቻም ሳይሆን የመንግሥት ፕሮጀክቶችም ሙሉ ለሙሉ ይቆማሉ፤›› ብለዋል፡፡

ወደፊት የሚከናወኑ የመንግሥት ፕሮጀክቶችም ቢሆኑ አሁን ከሚጠቀሙበት የግንባታ በጀት በእጥፍ እንዲያድግላቸው ለፓርላማ ጥያቄ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል በማለት አበበ (ፕሮፌሰር) አስረድተዋል፡፡

በርካታ የዩኒቨርሲቲዎች፣ የመንገድና ሌሎች ትልልቅ የመንግሥት ፕሮጀክቶች በአሁኑ ጊዜ መቆማቸውን ገልጸው፣ ምክንያቱ ደግሞ ለአንድ መሥሪያ ቤት የሚፀድቀው ዓመታዊ የግንባታ በጀት አሁን ካለው  የዋጋ ጭማሪ ጋር ባለመመጣጠኑ ነው ብለዋል፡፡

ኮንስትራክሽን በዕድገት ላይ ላሉ አገሮች ትልቁ የሥራ ዕድል የሚፈጠርበት ዘርፍ ስለሆነ አስቸኳይ መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባ የጠቆሙት አበበ (ፕሮፌሰር)፣ ይህ ዘርፍ ከተናጋ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ይከተዋል ብለዋል፡፡

የመንግሥት ጨረታዎችን አለማግኘት፣ ብሔራዊ ባንክ ለተወሰነ ጊዜ የብድር ዕገዳ ማድረጉ፣ በፀጥታ ችግር ሳቢያ፣ በኮቪድ-19 እና በርካታ ፕሮጀክቶችን በሞኖፖል መያዝ፣ ለኮንትራክተሮች ከገበያ መውጣት ምክንያቶች ናቸው ሲሉ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ጠቁመዋል፡፡

ከ30 ዓመታት በፊት የተመሠረተው የሥራ ተቋራጮች ማኅበር ከ2,400 በላይ አባላትን በመያዝ ለዘርፉ ማነቆ የሆኑ መመርያዎች እንዲሻሻሉ የተለያዩ ሥራዎችን እንደሚያከናውን ይነገራል፡፡

አብዛኞቹ የግንባታ ዕቃዎች ከውጭ የሚገቡ በመሆናቸውና የተለያዩ የዋጋ ዓይነቶች መኖራቸው፣ ለኮንትራክተሮች ትልቅ ችግር መፍጠራቸውን፣ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ባህሪም በጣም ተለዋዋጭ መሆኑን ያወሱት አቶ ግርማ፣ መንግሥት በግንባታ ግብዓቶች ላይ የገበያ ቁጥጥር ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች