የኦሮሞ ነፃነት ንቅናቄ ፓርቲ (ኦነን) ጠቅላላ ጉባዔውን አስመልክቶ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያቀረበው ሰነድ በሕግ እስከሚጣራ ድረስ መታገዱን ምርጫ ቦርድ አስታወቀ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትናንት ማክሰኞ መጋቢት 27 ቀን 2014 ዓ.ም. ለፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ በጻፈው ደብዳቤ፣ ፓርቲው ባቀረበው ሐሰተኛ መረጃ ላይ ምርመራ እንዲጀመር ጠይቋል፡፡
ኦነን መጋቢት 15 ቀን 2014 ዓ.ም. ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔ 541 የጠቅላላ ጉባዔ አባላት መገኘታቸውን ለምርጫ ቦርድ ሪፖርት አድርጎ ስብሰባውን አስጀምሮ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የምርጫ ቦርድ ታዛቢዎች ስብሰባው እየተካሄደ ሳለ ዳግም ቆጠራ ሲያደርጉ 250 አባላት ብቻ መሳተፋቸውን አረጋግጠዋል፡፡
ኦነን አገር አቀፍ ፓርቲ በመሆኑ የጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ ምልዓተ ጉባዔ የሚሟላው 500 የጉባዔ አባላት ከተገኙ ነው፡፡ ፓርቲው መጋቢት 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ለቦርዱ በጻፈው ደብዳቤ 634 የጉባዔ አባላት መታደማቸውን ገልጾ፣ ይህም አስቀድሞ የቦርዱ ታዛቢዎች ካደረጉት ቆጠራ በላይ ነው ብሏል፡፡
ምርጫ ቦርድ ለወንጀል ምርመራ ቢሮ በጻፈው ደብዳቤ፣ ኦነን ሐሰተኛ የተሳታፊዎች ዝርዝርና ፊርማ ማቅረቡን አትቶ፣ አጠራጣሪ ሰነዶች በወንጀል ምርመራ እስኪጣራ ድረስ ፓርቲውን ማገዱን ገልጿል፡፡
የኦነን ኃላፊዎች በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ሪፖርተር ያደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡
ምርጫ ቦርድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተነሳ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያካሂዱ ማዘዙ ይታወሳል፡፡ ኦነን በአንዳንድ የአሪቱ ክፍሎች የፀጥታ ችግር ስላለ የጠቅላላ ጉባዔ አባላቱ በተጠቀሰው ጊዜ መድረስ እንደማይችሉ ለምርጫ ቦርድ አሳውቆ ነበር፡፡
ቦርዱ የደረሰበት ጊዜያዊ ዕገዳ ለፓርቲዎች የሚሰጠውን ገንዘብ ለኦነን ከማስከልከል ጀምሮ እስከ ማሰረዝ ሊያደርስ እንደሚችል ይታወቃል፡፡