Wednesday, October 5, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናመንግሥት የግብይት ሥርዓቱን የሚከታተልበት አሠራር እንዲዘረጋ ማሳሰቢያ ተሰጠ

  መንግሥት የግብይት ሥርዓቱን የሚከታተልበት አሠራር እንዲዘረጋ ማሳሰቢያ ተሰጠ

  ቀን:

  ከዕለት ወደ ዕለት የሕዝቡን ህልውና ሰቅዞ የያዘው የኑሮ ውድነት መፍትሔ እንዲያገኝ ከተፈለገ፣ መንግሥት የግብይት ሥርዓቱን የሚከታተልበት አሠራር ሊያበጅ እንደሚገባ ማሳሰቢያ ተሰጠ፡፡

  በመላው አገሪቱ በመሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ንረትና ግሽበት መታየት ከጀመረ ውሎ ማደሩን ከሰሞኑ ያስታወቀው መንግሥት፣ ለዚህም አባባሽ ያላቸውን ምክንያቶች በዝርዝር ማሳወቁ ይታወሳል፡፡

  የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (/ር) በሳምንቱ መጨረሻ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ከአባባሽ ምክንያቶቹ የመጀመሪያው ከዓለም አቀፍ የሸቀጦች ዋጋ መናር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሁለተኛው ለኑሮ ውድነት መባባስ መሠረታዊ የሆነው ምክንያት በአምራቾችና በሸማቾች መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት አለመኖሩ ሲሆን፣ በሦስተኝነት የተነሳው ከመሠረታዊ ፍጆታዎች ፍላጎት ማደግ ጋር የሚመጣጠን ምርትና ምርታማነት አለማደጉ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ይህም የኅብረተሰቡን የአኗኗር ሁኔታ ከተለዋዋጭ ዓለም አቀፍ ሁኔታ ጋር እያስማሙ ካለመሄድ የሚመነጭ እንደሆነ ለገሰ (/ር) ተናግረው ነበር፡፡

  መንግሥት  የተባባሰውን የዋጋ ንረት ለመቀነስ ከያዘው ዕቅድ ውስጥ በንግድ  ሥርዓቱ  ላይ  ቁጥጥር  ማድረግ፣ የተገዙ  ሸቀጦችን በፍጥነት  ወደ  አገር  ውስጥ  ማስገባት፣ አዲስ ፈጣን የሸቀጦች ግዥ ማካሄድ፣ በአገር ውስጥ ምርትና  ምርታማነትን  ማሳደግ፣ እንዲሁም ማኅበረሰቡን ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር የተስማማ ማድረግ  ነውብሏል።

  መንግሥት የዋጋ ንረትንና የኑሮ ውድነትን በተመለከተ በተደጋጋሚ ማኅበረሰቡን ከመዋሸት ይልቅ፣ ስላለው ሁኔታ በግልጽ አስረድቶ የመፍትሔው አካል ማድረግ ይገባል የሚል ምክረ ሐሳብ ከዚህ በፊት ደጋግሞ በኢኮኖሚ ባለሙያዎች ሲነሳ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ መንግሥት ከሰሞኑ ያቀረባቸውን ምክረ ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ የጀመረውን እንቅስቃሴ በአበረታችነቱ እንደሚያነሱት ሁሉ ውሳኔው የዘገየ እንደሆነ የሚናገሩ አሉ፡፡

  የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቁምላቸው አበበ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከሰሞኑ በመንግሥት ስለዋጋ ንረት በተመለከተ የቀረበው የመፍትሔ ሐሳብ የዘገየ ነው፡፡

  አገሪቱን ላለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት እየገፋት መጥቶ ለምስቅልቅል ችግር  ሊዳርጋት እየተቃረበ ያለው የኑሮ ውድነት ጉዳይ፣ አሁንም በቂ ትኩረት እንዳላገኘ ገልጸዋል፡፡

  መንግሥት ችግሩን ለመፍታት ወጥ የሆነ የፖለቲካ ቁርጠኝነት አይስተዋልበትም ያሉት አቶ ቁምላቸው፣ ከላይ እስከ ታች ያለው አመራር ተናቦና ተግባብቶ ስለማይሄድ ከሰሞኑም በመንግሥት የተነገረው መፍትሔ የሚያመጣ ነው ተብሎ አይታሰብም ብለዋል፡፡

  ይህ ወቅት የኑሮ ውድነት ‹‹ችግሩን ተገንዝበናል›› የሚባልበት ሳይሆን፣ መፍትሔ በቶሎ ሊያመጣ የሚችል ዕርምጃ ሊወሰድበት የሚገባ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

  መንግሥት ወደ ተግባር ይግባ ሲባል በድጎማ የሚያመጣውን ሸቀጥ በአግባቡ ለሸማቹ እየደረሰ መሆኑን ከላይ እስከ ታች መከታተልና መቆጣጠር የመጀመሪያው ተግባር እንደሆነ ያስረዱት አቶ ቁምላቸው፣ በተጨማሪም መንግሥት ሕገወጥ የገበያ ሰንሰለቱን ማስተካከል እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡

  ‹‹ሙዝ አርባ ምንጭ በሰባት ብር እየተሸጠ አዲስ አበባ 40 ብር የሚሸጥበት ምክንያት ምንድነው? የሚለውን ማጣራት የሚገባው መንግሥት ነው፡፡ ሕዝቡ በመንግሥት ላይ አመኔታ ያጣው፣ ማድረግ የሚችለውን ነገር እያደረገ ባለመሆኑ ነው፤›› ሲሉ አቶ ቁምቸው አክለዋል፡፡

  መንግሥት ማድረግ ከሚገባው መሠረታዊ ነገሮች የሕግ የበላይነትን በኢኮኖሚውና በገበያው ውስጥ ማስከበር እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህንን ማድረግ አለመቻል አንዱ መንግሥትን የሚያስተቸው ጉዳይ እንደሆነ ሌላው በባለሙያዎች የሚነገር ነው፡፡

  በሩሲያና በዩክሬይን ጦርነት ሳቢያ የዋጋ ጭማሪና ያንንም ተከትሎ የኑሮ ውድነት እንደሚኖር ሕዝቡ የሚረዳው ጉዳይ እንደሆነ ያስረዱት አቶ ቁምላቸው፣ በዚህ ወቅት ሕዝቡን አያማረረ ያለው መንግሥት መሥራት የሚችለውን ጉዳይ በጊዜውና በሰዓቱ አለመሥራቱ ወይም ለመሥራት የተግባር እንቅስቃሴ አለማድረጉ ነው ብለዋል፡፡

  ከሁሉም በላይ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት አንገብጋቢ መሆኑን፣ የህልውናና የፀጥታ፣ የሰላምና የደኅንንት ችግር በሚያስብል ደረጃ ላይ መድረሱን መንግሥት በቅጡ ተረድቶታል ወይ? ተብሎ ሲጠየቅ፣ አመላካች ነገር እንደሌለ የሸማቾች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል፡፡

  የምርት እጥረት፣ የአቅርቦትና የፍላጎት አለመጣጣም የሚባሉ ችግሮችን ሕዝብ እንደሚረዳቸው ታሳቢ ተድርጎ መንግሥት የሕግ የበላይነትን አለማስከበሩ፣ ደላላውን ከገበያ አለማስወጣቱ የሚያስተቸው እንደሆነ ተነግሯል፡፡

  ‹‹መንግሥት በዚህ ወቅት በአጠቃላይ የገበያው ወሳኝ የሆነውን ደላላ እንዴት ከገበያው ሥርዓት ውስጥ አውጥቶ ሥርዓት ማስያዝ ያቅተዋል?›› ብለው የጠየቁት አቶ ቁምላቸው፣ ችግሮችን ውጫዊ ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

  የመንግሥት መዋቅር ከነጋዴውና ከደላላው በጥቅም የተሳሰረ መሆኑና ኃላፊዎች በሙስና የተዘፈቁ መሆናቸው፣ በዚህ ወቅት ለተስተዋለው የዋጋ ንረት ዓይነተኛ ምክንያት እንደሆነ በሌላ በኩል መንግሥትም ሆነ ባለሙያዎች የሚያወሱት ነው፡፡

  በዚህ ወቅት ያለው ትልቁ ችግር የአቅርቦት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ በገበያው ውስጥ የሰፈነው ሥርዓት አልበኝነት እንደሆነ የገለጹት አቶ ቁምላቸው፣ የዩክሬይንና የሩሲያ ጦርነት ቆሞ ሰላም ቢመለስም፣ በኢትዮጵያ የተፈጠረው የኑሮ ውድነት ቶሎ የሚሻሻል ባለመሆኑ መንግሥት የገበያ ሥርዓት ማስከበር እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡

  ቁርጠኝነት የሌለው አመራር ለሸማቹ መቆርቆር የተቋቋመን ድርጅት ጥያቄንም ሆነ የሸማቹን ጥያቄ ለመስማት ጆሮ የለውም ያሉት አቶ ቁምላቸው፣ ይህም የሚያሳየው የኑሮ ውድነት አንገብጋቢነት ለዚህ አመራር የተጋረጠበት ችግር አለመሆኑን እንደሚያሳይ ገልጸዋል፡፡

  የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በተለይም ከሸማቹ ጋር በተገናኘ ለሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መፍትሔ ያበጃል የሚል ዕምነት እንደነበራቸው ያስታወቁት የሸማቾች መብት ተቆርቋሪዎች ድርጅት ሥራ አስኪያጁ፣ ድርጅታቸው ከሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ጋር የድጋፍ ደብዳቤ ለማግኘትና የመግባቢያ ሰነድ ለመፈራረም ያደረገው ጥረት እስካሁን አመርቂ ምላሽ እንዳላገኘ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም የዋጋ ማረጋገት ግብረ ኃይሉ ውስጥ ለመሳተፍ ይሁንታ ተሰጥቶት ለነበረው አቅጣጫም አስፈላጊ የሆነው ደብዳቤ እንኳን ማግኘት እንዳልቻለ ጨምረው ተናግረዋል፡፡

  ‹‹የሸማቾችን ጉዳይ የእኔም ጉዳይ ነው ብሎ የሚያግዝና አብሮ የሚሠራ አካል ከሌለ አንድም ዕርምጃ መራመድ አይቻልም፤›› ያሉት አቶ ቁምላቸው፣ ከመገናኛ ብዙኃን አንስቶ ሁሉም ነገር በመንግሥት መዋቅር ቁጥጥር ሥር በመሆኑ የኑሮ ውድነት ጉዳይን ነገሬ አድርጎ ለመቀነስ ተነሳሽነቱ ዝቅተኛ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

  በዚህ ወቅት እንደ መሠረታዊ መፍትሔ ተደርጎ ከሚወሰዱ ነገሮች ውስጥ መንግሥት ደጉሞ የሚያመጣቸውን መሠረታዊ ሸቀጦች ለሸማቹ መድረሱን የሚያረጋጥበት አሠራር ማበጀት ይገባዋል ያሉት አቶ ቁምላቸው፣ ምርቱን ማስገባት ብቻ መፍትሔ አለመሆኑን ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት የታየ ችግር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

  ነዳጅም ሆነ መሠረታዊ ሸቀጦች በድጎማ ቢገቡም በአግባቡ ለኅብረተሰቡ እየተዳረሱ እንዳልሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም የሆነው ተጠያቂነት ስለሌለና የግብይት ሥርዓቱን የሚመራ አሠራርና አደረጃጀት ባለመኖሩ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

  መንግሥት በድጎማ የሚያቀርበውን ሸቀጥ በትክክል ለሸማቹ መድረሱ፣ ምርቱ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ቀበሌ ወርዶ በሸማቾች ሱቅ ሲሸጥና ሲከፋፈል መከታል የሚያስችል አሠራርና አደረጃጀት መፍጠር እንደሚገባ አቶ ቁምላቸው አሳስበዋል፡፡

  በሌላ በኩል የመኖሪያ ቤትም ሆነ የንግድ ቤት ኪራይ ተመን በሕግ መደንገግ  እንደሚገባው የተመላከተ ሲሆን፣ ባለንብረቱንም ሆነ ተከራይን የማይጎዳ ወቅታዊ ገበያን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ የኪራይ ተመን ሊኖር እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

  መንግሥት ከነጋዴው ጋር ያለውን ያልተገባ መርህ አልባ ግንኙነት ሊያቆም እንደሚገባ የተገለጸ ሲሆን፣ ብዙ ባለሀብቶች ከመንግሥት ጋር የሚገናኙ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ስፖንሰር ሲያደርጉ ይስተዋላል ተብሏል፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ መንግሥት በንግዱ ማኅበረሰብ ላይ ጠበቅ ያለ ዕርምጃ እንዳይወስድ ከሚጎትቱት ምክንያቶች አንዱ ይህ ውለታ እንደሆነ በባለሙያዎች የሚሰነዘር አስተያየት ነው፡፡

   

   

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img