Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከተማ አስተዳደሩ በስምንት ቢሊዮን ብር ሊያስገነባቸው የነበሩ ተገጣጣሚ ቤቶች ግንባታ በፍርድ ቤት...

ከተማ አስተዳደሩ በስምንት ቢሊዮን ብር ሊያስገነባቸው የነበሩ ተገጣጣሚ ቤቶች ግንባታ በፍርድ ቤት ታገደ

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በስምንት ቢሊዮን ብር በጀት ያስጀመረውና በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ አምስት ወርቁ ሠፈር ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ሊያከናውነው የነበረው የአምስት ሺሕ ተገጣጣሚ የመኖሪያና የንግድ ቤቶች ሕንፃዎች ግንባታ፣ በፍርድ ቤት ዕግድ እንዲቆም መደረጉ ተገለጸ፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በ21.8 ሔክታር መሬት ላይ የተገጣጣሚ ቤቶች ግንባታ ለማስጀመር ጥር 4 ቀን 2014 ዓ.ም. መሠረተ ድንጋይ ቢያስቀምጥም፣ መሬቱ የባለቤትነት ጥያቄ ተነስቶበት ፍርድ ቤት ዕግድ በማውጣቱ ግንባታው እንዲቆም መደረጉን የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮና የቤቶቹን ግንባታ የሚያካሂደው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን አስታውቀዋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምርያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥንፉ ሙጬ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ግንባታው ይፋ ከተደረ በኋላ ኮርፖሬሽኑ 291 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የተገጣጣሚ ሕንፃ አካላት ኮንክሪትና ሌሎች ተያያዥ ምርቶችን ወደ ቦታው አስገብቷል፡፡ በግንባታ ቦታው ላይ አሥር ሚሊዮን ብር የሚያወጣ አፈር ጠረጋና ምንጣሮ ሥራ መካሄዱንም አስረድተዋል፡፡

ይሁንና የመሬቱ ባለቤትነት ይገባኛል ያለ ግለሰብ ጥያቄ በማንሳቱ፣ ኮርፖሬሽኑ ሥራ በጀመረ በቀናት ውስጥ ዕግድ ወጥቶበታል፡፡ ኮርፖሬሽኑ እግዱ ቢወጣም የግንባታ ሥራውን እንደቀጠለ ያስረዱት አቶ ጥንፉ፣ ለሁለተኛ ጊዜ ዕግድ ከመጣ በኋላ ግን መሬቱ ላይ ያለው ሥራ እንዲቆም መደረጉን ተናግረዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ሊያስገነባቸው ያቀደው ከ90 በላይ ባለ አራትና ዘጠኝ ፎቅ የተገጣጣሚ ቤት ብሎኮች ግንባታቸው የሚያርፍበት መሬት፣ በሕገወጥነት ተይዞ የነበረና ወደ መሬት ባንክ የገባ መሆኑን አስታውቆ ነበር፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ የቤት ልማት ትግበራና የሥራ ዕድል ፈጠራ ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተር ኪያ በሬቻ (ኢንጂነር)፣ ቢሮው ከከተማው መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ መሬቱን በሊዝ ተረክቦ ካርታ መቀበሉን ተናግረዋል፡፡ ዳይሬክተሩ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ መሬቱን በሊዝ ሊወስድ የሚችለው፣ ይዞት የነበረው ተቋም የሊዝ ውል ሲቋረጥ ወይም ሲመክን መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይሁንና መሬቱ ከዚህ ቀደም የነበረበትን ሁኔታ መግለጽ የሚችለው የከተማው መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ በመሆኑ፣ የክርክር ሒደቱ አካል የሆነውም ይኸው ቢሮ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ዕጣ ወጥቶባቸው ለዕድለኞች ካልተላለፉት ከ50 ሺሕ በላይ ቤቶች ባሻገር፣ ሁለት ጊዜ በተደረገው ምዝገባ ተካተው ቤት ያልወጣላቸው 700 ሺህ ሰዎች ይገኛሉ፡፡ የቤት የፈላጊዎችን ጥያቄ በተለያዩ አማራጮች ለመፍታት እየሞከረ ያለው የከተማ አስተዳደሩ፣ ግንባታቸውን በቶሎ ለማጠናቀቅ ይቻላል የተባለላቸውን የተገጣጣሚ ቤቶች ግንባታ ከሦስት ወራት ገደማ በፊት አስጀምሯል፡፡

የቤቶቹን ግንባታ የማከናወን ኃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ ለሕንፃ ግንባታው የሚውሉትን የተገጣጣሚ አካላት ቃሊቲ በሚገኘው ፋብሪካው የሚያመርት ሲሆን፣ አምስት ሺሕ ቤቶችን በአንድ ዓመት ውስጥ ገንብቶ ለማጠናቀቅ ዕቅድ ይዟል፡፡ የኮርፖሬሽኑ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምርያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥንፉ፣ ዕግዱ ባይመጣ ኖሮ ኮርፖሬሽኑ፣ ውል ከተወሰደበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን በርካታ ቤቶችን የመሥራት ዕቅድ ነበረ ብለዋል፡፡ ክረምት ከመግባቱ በፊት ከ90 በላይ የሚሆኑትን ብሎኮች ኮንክሪታቸውን ከአፈር በላይ አውጥቶ የማጠናቀቅ ዕቅድ እንደነበረም ተናግረዋል፡፡

ፍርድ ቤት የግንባታ መሬቱ ላይ ዕግድ ቢጥልም፣ ኮርፖሬሽኑም ሆነ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ፣ እግዱ ለፕሮጀክቱ እክል ይሆናል የሚል ሐሳብ የላቸውም፡፡ ኮርፖሬሽኑ መሬቱ ላይ ያለው ሥራ ቢታገድም አሁንም ድረስ የተገጣጣሚ አካላትን፣ እንዲሁም በርና መስኮቶችን እያመረተ መሆኑን አቶ ጥንፉ ተናግረዋል፡፡ ሁለቱም አካላት ተገጣጣሚ አካላቱ ከተመረቱ መገጣጠሙ ብዙም ጊዜ እንደማይወስድ ገልጸዋል፡፡

ይሁንና ኮርፖሬሽኑ የግንባታ ሥራውን መቀጠል የሚችለው የፕሮጀክቱ ባለቤት የሆነው የከተማ አስተዳደሩ መሬቱን ነፃ ሲያደርግለት መሆኑን አስታውቋል፡፡ ጉዳዩ በፍርድ ቤት የተያዘ ቢሆንም የከተማ አስተደዳሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተነጋግሮ ቦታውን ያስለቅቃል የሚል እምነት እንዳለው አቶ ጥንፉ አስረድተዋል፡፡

የቤት ልማት ትግበራና የሥራ ዕድል ፈጠራ ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተሩ ኪያ (ኢንጂነር) በበኩላቸው፣ ከፕሮጀክቱ ባህሪ አንፃር መገጣጠሙ ትንንሽ ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ የመሬት ሥራው መቆሙ ሥጋት እንደማይሆን ገልጸው፣ ግንባታው ቢቆምም ለተወሰነ ጊዜ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በ1997 ዓ.ም. የተጀመረው የመንግሥት የጋራ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት 17 ዓመታት ቢያስቆጥርም፣ እስካሁን የመጀመሪያ ተመዝጋቢዎችን በሙሉ ማዳረስ አልቻለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የከተማ አስተዳደሩን የ54 ቢሊዮን ብር ዕዳ ባለቤት አድርጎታል፡፡ የተገጣጣሚ ቤቶቹ ግንባታ ይፋ በተደረገበት ዕለት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ ለቤቶቹ ግንባታ በተወሰደው ብድርና በተገነቡት ቤቶች ቁጥር መካከል ልዩነት እንዳለ ተናግረው ነበር፡፡

የከተማ አስተዳደሩ እንደሚገልጸው፣ የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ ከፍተኛ ክፍተት ይታይባቸዋል፡፡ በተለይ ከ2006 ዓ.ም. እስከ 2010 ዓ.ም. በአገሪቱ ውስጥ ከነበረው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ጋር ተይይዞ ኮንትራክተሮች ክትትል ሳይደረግባቸው ሥራቸው ‹‹ልቅ›› የነበረ በመሆኑ፣ ፕሮጀክቶቹ ለሌብነትና ለዝርክር አሠራር እንደተጋለጡ ወ/ሮ አዳነች በየካቲት ወር መጀመሪያ ላይ በተካሄደው የከተማዋ ምክር ቤት አንደ ዓመት የሥራ ዘመን አንደ መደበኛ ጉባዔ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...