Wednesday, March 22, 2023

የደቡብ ሱዳን ተፋላሚዎች ስምምነትና የፈነጠቀው የሰላም ተስፋ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የአፍሪካ ቀንድን ‹‹የሰቆቃ ዜና አጥቶ የማያውቅ ቀጣና›› እያሉ ይጠሩታል የጂኦፖለቲካ ምሁራኑ፡፡ ከሰሞኑ ብቻ በሶማሌላንድ ሃርጌሳ ከተማ በደረሰ ከባድ የእሳት አደጋ ከ2,000 በላይ ሱቆች ነደው፣ ከ28 ሰዎች በላይ ቆስለውና ከ200 ሺሕ ዶላር በላይ የገንዘብ ኪሳራ መድረሱ ሲዘገብ ነው የከረመው፡፡ በትራጀዲ ዜና የተሞላው የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ጦርነት፣ ድርቅ፣ ረሃብ፣ ስደት፣ መፈናቀል፣ ሌላም ሰብዓዊና ተፈጥሯዊ ድቀት በየጊዜው የሚደርስበት ነው፡፡

ይህን መሰል ሰቆቃ አጥቶ በማያውቀው በምሥራቅ አፍሪካ ባለፈው እሑድ ከጁባ የተሰማው ዜና ለቀጣናው በትልቁ የሚጠቀስ በጎ ወሬ ነበር፡፡ ኤ.ኤ.አ. በ2011 ከሱዳን ተገንጥላ አገር ለመሆን የበቃችው ደቡብ ሱዳን ከሁለት ዓመት በኋላ በ2013 ወደ ጦርነት ገባች፡፡ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በዚሁ ግጭት ስትዳክር የቆየችው ደቡብ ሱዳን ወደ ሰላም እንድትመለስ ብዙ ድርድር፣ ሽምግልናና የሰላም ጥረቶች ቢካሄዱም ወደ ሰላም ለመመለስ ከብዷት ነው የቆየችው፡፡ ከእነዚህ ሁሉ አስቸጋሪ ዓመታት በኋላ ባለፈው እሑድ የደቡብ ሱዳን መሪዎች አዲስ የሰላም ስምምነት መፈራረማቸው፣ ከእነሱ አልፎ በችግር ለተተበተበው የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናም ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ዜና ነበር፡፡

ለደቡብ ሱዳን ሰላም መስፈን ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ ወገኖች ብርቱ የማደራደር ጥረት አድርገዋል፡፡ አገሪቱ ነፃነት ተቀዳጅታ እንደ አገር ስትቆም ወደ መሪነት ሥልጣን የመጡት ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና ምክትላቸው ሪክ ማቻር በሥልጣን ሽኩቻ አገሪቱን ወደ ጦርነት ከተቷት፡፡ የቀረቡላቸውን የሰላም አማራጮች ወደ ጎን በመግፋት ጦርነትን የመረጡት ሁለቱ ኃይሎች በጦርነቱ ከ400 ሺሕ በላይ ዜጎችን ካስጨረሱ በኋላ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫና የተለያዩ ስምምነቶችን ለመፈራረም ተገደዱ፡፡ ይሁን እንጂ የተፈራረሙትን ስምምነት ገቢራዊ ለማድረግ ሲያመነቱ የቆዩት ሁለቱ ወገኖች በአውሮፓዊያኑ 2018 ከተፈረመው ትልቅ ስምምነት በኋላ ባለፈው እሑድ አዲስ ስምምነት በመፈራረም ትልቅ የሰላም ዕርምጃ መውሰዳቸው እየተነገረ ይገኛል፡፡

የእሑዱ ስምምነት በተለይ ሁለቱ ኃይሎች ለረዥም ጊዜ ሲያመነቱበት በቆዩት በፀጥታ መዋቅር ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር፡፡ የአገሪቱን የፀጥታ ኃይል በደቡብ ሱዳን ማን ይምራው የሚለው ጥያቄ የሚያጋጭ አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል፡፡ የመከላከያ ሠራዊቱም ሆነ የፖሊስ ኃይሉ አባላት በምን ዓይነት የተዋዕጾ ምጣኔ ይገንባ የሚለው ጉዳይ ሲያጨቃጭቅ መቆየቱ ይነገራል፡፡ አሁን በተደረገው ስምምነት ይህ አጨቃጫቂ ጉዳይ በቁጥር ተለይቶ መቀመጥ የቻለ ሲሆን፣ የፕሬዚዳንቱ ወገን (ማለትም ሳልቫ ኪር) 60 በመቶ እንዲሁም የምክትላቸው ሪክ ማቻር ወገን 40 በመቶ የፀጥታ መዋቅሩን እንዲቆጣጠሩ ከመግባባት ላይ መድረሳቸው የወጣው ዜና ያመለክታል፡፡

ስምምነቱ በተፈረመ ዕለት የገዥው ፓርቲ አባልና የአገሪቱ የማዕድን ሚኒስትር ማርቲን ጋማ አቡቻ ጠቃሚ መልዕክት ለሁለቱም ወገኖች አስተላልፈዋል፡፡ ‹‹ዋናው ጠቃሚ ጉዳይ ስምምነት መፈራረም ሳይሆን፣ ስምምነቱን በተግባር መተርጎም ነው፤›› ሲሉ የተናገሩት ማርቲን፣ ‹‹በጁባ ስለሰላም እያወራን በጎን እየተዋጋን ልንቀጥል አንችልም፡፡ የጠብመንጃ ድምፅ የማይሰማበትን ሁኔታ መፍጠር ይጠበቅብናል፤›› በማለት በመልዕክታቸው አክለዋል፡፡

የደቡብ ሱዳን ባለሥልጣናት ለሰላም ስምምነት መፈራረም በጠረጴዛ ዙሪያ መቀመጣቸው የእሑዱ የመጀመሪያቸው አይደለም፡፡ ለስምምነት በተደጋጋሚ እንደተቀመጡት ሁሉ ስለሰላም ሲዘምሩም አዲሳቸው አይደለም ይላሉ የአካባቢው ተንታኞች፡፡ ሪክ ማቻርና ሳልቫ ኪር በአንድ አዳራሽ የሰላም ስምምነት ለመፈራረም ተቀምጠው ከአዳራሽ ውጪ በደጋፊዎቻቸው መካከል ቅልጥ ያለ ውጊያ የተከፈተበትን አንድ አጋጣሚ ያስታወሱ ተንታኞች፣ የአሁኑ የሰላም ስምምነት የጥይት ጩኸትን ያስቆማል የሚለውን በትልቁ ይጠራጠሩታል፡፡

ለእሑዱ የሰላም ስምምነት መፈራረም ዋና አደራዳሪና አሸማጋይ የነበሩት የሱዳን ባለሥልጣናት ግን፣ በአዲሱ ስምምነት ላይ ትልቅ ተስፋ ካሳደሩ ወገኖች አንዱ መሆናቸውን አሳይተዋል፡፡ ስምምነቱ በተፈረመ ዕለት በዚያው በጁባ የነበሩት የሱዳን መከላከያ ሚኒስትር ያሲን ኢብራሂም ያሲን፣ ‹‹ሁለቱ ወገኖች ስምምነቱን ተቀብለው በመፈራረማቸው ለፈጣሪ ምሥጋና ይገባዋል፡፡ ስምምነቱም የደኅንነትና የፀጥታ መዋቅሩን የማደራጃ ቀመር የተገኘበት ነበር፤›› በማለት ነው አድናቆታቸውን የገለጹት፡፡ ያሲን ሐሳባቸውን ሲያክሉ፣ ‹‹የደቡብ ሱዳን ጉዳይ የደቡብ ሱዳናዊያን ብቻ ሳይሆን የሱዳንም የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ ነው፤›› ማለታቸው፣ አገራቸው ለዚህ ጉዳይ የሰጠችውን ትኩረት ትልቅ መሆኑን አመላካች ተብሎ ነው የተገመተው፡፡

በትዊተር ገጻቸው ስለስምምነቱ አጭር መግለጫ ያወጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ‹‹ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ጎን ትቆማለች፡፡ ዘላቂ ሰላም በደቡብ ሱዳን ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍም ኢትዮጵያ ዝግጁ ናት፤›› በማለት ነበር ለስምምነቱ ያላቸውን ድጋፍ የገለጹት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ይህን ቢሉም ኢትዮጵያ እሑድ መፈረሙ ለተነገረው የሰላም ስምምነት የነበራት ሚና እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ነው ታዛቢዎች የሚናገሩት፡፡ በአሁኑ ስምምነት ከዚህ ቀደም በደቡብ ሱዳን ጉዳይ ጉልህ የዲፕሎማሲ ሚና የነበራቸው እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮችና እንደ ኢጋድ ያሉ ተቋማት ሳይሆኑ፣  ሱዳንና ኡጋንዳን የመሳሰሉ አገሮች ሚናቸው መጉላቱ እየተነገረ ነው፡፡ ይህ ለምን እንደሆነ የሚያብራራ የዲፕሎማሲ ምንጭ ባይገኝም፣ ነገር ግን የደቡብ ሱዳን ጉዳይና የቀጣናው አገሮች ሚና ገጽታቸው እየተቀየረ መምጣቱን ነው ብዙ ታዛቢዎች የሚናገሩት፡፡

የደቡብ ሱዳንን ቀውስ ማን አደራደረ ከሚለው በማንኛውም መንገድ ቢሆን የቀውሱ ዕልባት ማግኘት ጉዳይ እንደሚቀድም ብዙ ታዛቢዎች ያሳስባሉ፡፡ የቅርብ ሰሞን ሪፖርቶች ለአሥር ዓመታት የዘለቀው የደቡብ ሱዳን ቀውስ ከአገሪቱ አልፎ ለቀጣናው የተረፈ ችግር መፍጠሩን ይጠቁማሉ፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘንድሮ አስቸኳይ ዕርዳታ የሚፈልጉ የደቡብ ሱዳን ዜጎች ቁጥር 6.8 ሚሊዮን መሆኑን በመጥቀስ፣ ከሰሞኑ 1.7 ቢሊዮን ዶላር በጀት እንደሚያስፈልግ ይፋ አድርጓል፡፡ ተመድ  የቀውሱን ተደራራቢነት ከፍ በማድረግ ከአገሪቱ ሕዝብ 2/3ኛ የሚሆነው ወይም ዘጠኝ ማሊዮን ሰው ዕርዳታ ጠባቂ ነው ይላል፡፡ ይህ ሁሉ ሕመምና ድቀት ላለባት አገር ተፋላሚ ወገኖች ጦርነት ለማቆም የሚያስችል ወሳኝ ስምምነት ለመፈራረም መብቃት ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም ይላሉ በርካታ ተንታኞች፡፡

በወቅታዊው የደቡብ ሱዳን ሰላም ስምምነት ላይ ሐሳባቸውን ለሪፖርተር ያጋሩ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የደቡብ ሱዳን ምሁር ስምምነቱን ‹‹ትልቅ ዕርምጃ›› ቢሉትም፣ ነገር ግን በዘላቂነቱና በአተገባበሩ ላይ ብዙ ጥያቄ እንዳላቸው ነው የተናገሩት፡፡ በአዲስ አበባ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን እየሠሩ ያሉት ምሁሩ የደቡብ ሱዳን ግጭትና የአገረ መንግሥት ምሥረታ ጥረትን የሚፈትሽ ጥናት እያካሄዱ መሆኑን በመጥቀስ፣ ‹‹ስሜ ሳይጠቀስ ለጉዳዩ ካለኝ ቅርበት ተነስቼ ምሁራዊ ዕይታዬን ላጋራችሁ›› ባሉት መሠረት፣ የደቡብ ሱዳን ሰላም ስምምነትና የሚገጥመውን ፈተና በሰፊው አብራርተዋል፡፡

‹‹የአሁኑ ስምምነት ምንም አዲስ ነገር የለውም፤›› ሲሉ ሐሳባቸውን የጀመሩት ምሁሩ፣ ‹‹ኤ.ኤ.አ. በ2018 በተፈረመው የስምምነት ሰነድ ላይ እሑድ የተፈረመው የመግባቢያ ነጥብ በግልጽ ተቀምጦ ነበር፤›› ሲሉ የስምምነቱን ሒደት ያስረዳሉ፡፡ ‹‹በ2018 እዚሁ በአዲስ አበባ የተፈረመው የሰላም ስምምነት የያዛቸው አንቀጾች ወደ መሬት መውረድ ባለመቻላቸው፣ ተከታታይ ድርድሮች በሱዳን ካርቱም ሲካሄዱ ነበረ፤›› በማለትም ያስረዳሉ፡፡

የስምምነት ሰነዱ መተግበር ያቃተው ደግሞ በተለይ ሳልቫ ኪር በሚመሩት መንግሥት የፖለቲካ ቁርጠኝነት ማጣት እንደሆነ የጠቀሱት ደቡብ ሱዳናዊው፣ ሳያግባቡ ከቆዩ ወሳኝ ጉዳዮች አንዱ ደግሞ የፀጥታ መዋቅር የማደራጀት ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹የመከላከያ ሠራዊቱ፣ የፖሊስ ኃይሉና የደኅንነት ተቋሙ ከምልመላ ሒደት ጀምሮ እንዴት እንደሚሠለጥንና ምን ዓይነት ሚና እንዳለው ሁለቱ ወገኖች አልተግባቡም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም በፀጥታ መዋቅሩ ውስጥ የሚገባው የሰው ኃይል ቁጥር ተዋጽኦም ሌላው አጨቃጫቂ ነጥብ ነበር፤›› በማለት የሚጠቅሱት ምሁሩ፣ ይህ ሒደት በመንግሥት ሰዎች ትኩረት ማጣት ለሦስት ዓመታት ሲንከባለል መቆየቱን አስረድተዋል፡፡

‹‹የሳልቫ ኪር መንግሥት ስምምነቱን ለመቀበል ሲሸሽ ቢቆይም በመጨረሻ ተቀብሎታል፤›› ብለው፣ በመንግሥት ወገን በኩል፣ ‹‹ተቃዋሚዎች በፀጥታ መዋቅሩ ውስጥ ከሚገባው በላይ ቁጥርና ሥልጣን ካልተሰጠን የሚል ሙግት እያነሱ ነው›› ተብሎ ክስ እንደሚሰነዘር ነው ያብራሩት፡፡

ተቃዋሚዎች በየፀጥታ መዋቅሩ የምክትልነት ሥልጣኖችን እንዲይዙ የተስማሙ ቢሆንም፣ መንግሥት ግን ይህንንም በስምምነቱ መሠረት ለመልቀቅ በማመንታቱ ጉዳዩ ሲገላበጥ መክረሙንና ግጭቱ ከስምምነቱም በኋላ መቀጠሉን ምሁሩ አስረድተዋል፡፡ የሥልጣንና የቁጥር ክፍፍሉ ይህን ያህል ሳያግባባቸው ከቆዩ በሀብት ክፍፍልና ምደባ ላይ ለመስማማትም ይቸግራቸዋል ብለው እንደሚገምቱ ምሁሩ ይገልጻሉ፡፡ ከዚህ በመነሳትም የሰላም ስምምነቱ ወደ መሬት የመውረዱን ጉዳይና ዘላቂነቱን ጥያቄ ምልክት ውስጥ እንደሚከቱት ያስረዳሉ፡፡

‹‹ሱዳኖች፣ ኡጋንዳዎችና ሌሎች የቀጣናው አገሮች ለደቡብ ሱዳን  ሰላም መስፈን መትጋታቸው ተገቢነት ያለውና ጠቃሚ ነው፤›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያ ሚና እየቀነሰ መጥቷል የሚለውን ድምዳሜ እንደማይቀበሉት ነው የሚያስረዱት፡፡ ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ሰላም መስፈን ብዙ አስተዋጽኦ እንደነበራት የሚያስታውሱት ምሁሩ፣ ‹‹አሁን የምትገኝበት ውስጣዊ የፖለቲካ ሁኔታ ለዚህ ኃላፊነት ጉልህ ሚና እንድትጫወት የሚያስችል አይደለም፤›› በማለት አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡

ስለደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ምስቅልቅል ጥቅል ምሥል ሲሰጡ፣ ‹‹ግጭቱ የፖለቲካ ልሂቁ የፈጠረው ነው፤›› በማለት ነው ምላሽ የሰጡት፡፡ በጋራ ለደቡብ ሱዳን ነፃ መውጣት የታገሉ የፖለቲካ ኃይሎች በስተመጨረሻ ሥልጣኑን ሲይዙ በፖለቲካና ኢኮኖሚ ጥቅም መጋጨት እንደመረጡ በመጥቀስ፣ አገሪቱ የተጓዘችበትን አሳዛኝ የድቀት መንገድ ተርከዋል፡፡ ደቡብ ሱዳን የተረፋትን የነዳጅ ሀብት ብቻ ሳይሆን የአገሪቱን ሀብት ወደ መቀራመት ፖለቲከኞቹ እንደገቡ የገለጹት ምሁሩ፣ ‹‹እዚህ ውስጥ ብዙ ከባድ የምዝበራና ሙስና ወንጀሎችም አሉ፤›› በማለት ነው የጦርነቱ ገጽታ ያሉትን በሰፊው ያስረዱት፡፡

ምሁሩ እንዳሉትም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የደቡብ ሱዳን ጦርነት ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን የምዝበራ ገጽታ እንዳለው ሲናገር ነው የከረመው፡፡ በቅርቡ ብቻ የሚላስ የሚቀመስ ላጡ ደቡብ ሱዳናዊያን ሊውል ይገባ የነበረ 80 ሚሊዮን ዶላር መጥፋቱን ነው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይፋ ያደረገው፡፡ የአገሪቱ የነዳጅ ምርት ገቢ በቀጥታ ወደ ባለሥልጣናት ኪስና ለጦር መሣሪያ መግዣ እንጂ፣ ለተራበው ደቡብ ሱዳናዊ እንደማይውል ለረዥም ጊዜ ሲዘገብ ቆይቷል፡፡

የደቡብ ሱዳን ተፋላሚዎችን ለማግባባትና በአገሪቱ ሰላም ለመፍጠር ጎረቤት ኢትዮጵያ ከቢሾፍቱ፣ ከአዳማ እስከ አዲስ አበባ ተደራደሩ እያለች ስትጋብዝ መቆየቷ ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ በተጨማሪም ከ600 ሺሕ ላላነሱ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች የመማር ዕድልን ጨምሮ መጠለያ ሰጥታለች፡፡ በደቡብ ሱዳን ጦርነት ብዙ ችግር ኢትዮጵያ ስትቀበል መቆየቷን ከሁሉ የበለጠ የሚያሳየው ደግሞ ከደቡብ ሱዳን ድንበር ተሻግረው ጥቃት የሚሰነዝሩ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ጥቃትና ዕገታ ተደጋግሞ የተከሰተባት መሆኑ ነው ይላሉ የፖለቲካ ተንታኞች፡፡

ለዚህ ይመስላል የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ኃይሎችን በፀጥታ መዋቅር አደረጃጀት ላይ የመስማማት ዜና ኢትዮጵያን ጨምሮ በቀጣናው ያሉ አገሮችና ቀጣናዊ ተቋማት ዕርምጃውን በበጎ የተቀበሉት፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ)፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ ኡጋንዳን ጨምሮ ደቡብ ሱዳንን የተጎራበቱ አገሮች በተናጥል ስምምነቱን አወድሰውታል፡፡

በስምምነቱ ማግሥት ለረዥም ጊዜ መስማማት ተስኗቸው የቆዩትና የደቡብ ሱዳን ግጭት ምንጭ የሆኑት ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና ምክትላቸው ሪክ ማቻር በአካል ተገናኝተዋል፡፡ የመስማማት ሳይሆን የተስማሙባቸውን ነጥቦች ወደ ተግባር በመተርጎም ብዙ ሲታሙ የቆዩት ሁለቱ መሪዎች፣ የአሁኑን ስምምነት እንዳያበላሹት ታዛቢዎች ይሠጋሉ፡፡

የኢትዮጵያው ቲንክ ታንክ ቡድን አማኒያ አፍሪካ፣ ‹‹የዓለም ሁሉ ትኩረት ወደ ዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት በዞረበትና ሌሎች የዓለም ጉዳዮች በተረሱበት ወቅት የደቡብ ሱዳን ተፋላሚዎች መስማማት ታላቅ ዕድል ነው፤›› ሲል ስለስምምነቱ አስረድቷል፡፡ በቅርቡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የደቡብ ሱዳን ተፋላሚዎች የመጨረሻ ዕድላቸው መሆኑን በመጥቀስ፣ እ.ኤ.አ. በ2018 የፈረሙትን ስምምነት በሥራ ላይ እንዲያውሉ ሲያስጠነቅቅ ከርሟል፡፡ ይህ ሁሉ ታልፎ እሑድ በፀጥታ መዋቅር አደረጃጀት ላይ ስምምነት ለመፈረም የበቁት ሁለቱ ወገኖች፣ ይህን ዕድል ካበላሹት ደግሞ ሌላ ዕድል ማግኘታቸውን የሚጠራጠሩ ታዛቢዎች ብዙ ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -