ቀደምት ከሚባሉ የኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች መካከል አንዱ የሆነውን ሐዋሳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካን ከመንግሥት የገዛው ሐዋሳ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ፓርክ አክሲዮን ማኅበር የፋብሪካውን ነባር ማሽነሪዎች በማስወገድ አዳዲስ መሣሪያዎችን በመትከል የጨርቃ ጨርቅ ምርቶችን ለማምረት እየሠራ መሆኑን አስታወቀ።
ሐዋሳ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ፓርክ አክሲዮን ማኅበር የቆዩ ማሽነሪዎችን አስወግዶ አዳዲስ ማሽነሪዎችን ለመትከል ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የመደበ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱም በመካሄድ ላይ መሆኑንና በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ወደ ምርት እንደሚገባ አስታውቋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ፋብሪካውን በአዲስ የማምረቻ መሣሪያዎች የመተካቱ ሥራ በመጠናቀቅ ላይ እንደሆነም ተገልጿል። ፋብሪካውን በአዲስ መልኩ ለማደራጀት፣ የመሣሪያ ተከላውና ሕንፃውን ለማደስ ሥራ እስካሁን ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አህመድ አብዳሩፍ ገልጸዋል፡፡
ፋብሪካውን ለማዘመንና ቀደም ሲል በመንግሥት ይተዳደር በነበረበት ወቅት ይመረቱ የነበሩ የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶችን በሙሉ ለመቀየር መታቀዱን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ አዳዲስ ማሽነሪዎችን በመትከል ሁለት ዓይነት አዲስ ምርቶች እንደሚመረቱ አስታውቀዋል።
አዲስ ማሽኖች ከተተከሉ በኋላ ፋብሪካው ሁለት የምርት መስመሮች የሚኖሩት ሲሆን፣ በአንደኛው የምርት መስመር ‹‹ክሊኒከር›› የተባለውን ክር እንደሚመረት ተናግረዋል። ለዚህም የሚሆኑ አዳዲስ ማሽነሪዎች ተከላ መጠናቀቁን ሰሞኑን ፋብሪካው በተጎበኘበት ወቅት ተገልጿል፡፡
በኢንዱስትሪ መንደሩ ሁለተኛ የምርት መስመር ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው ደግሞ በተለየ ሁኔታ የፖሊስተር ምርት እንደሚመረትበት ተገልጿል። ለዚህ የምርት መስመር የሚያገለግሉ የአዳዲስ ማሽነሪዎች ተከላ እየተከናወነ ሲሆን፣ ተከላውን ለማጠናቀቅ የሚያግዙ የተወሰኑ ቀሪ ዕቃዎችን በመግጠም ለሥራ ዝግጁ ይሆናል ተብሏል፡፡
እነዚህ ቀሪ ዕቃዎች በአሁኑ ወቅት ጂቡቲ የሚገኙ በመሆኑ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ገብተው ከተገጠሙ በኋላ ሁለቱም የምርት መስመሮች በአጭር ጊዜ ወደ ምርት እንደሚገቡ ይጠበቃል።
በእነዚህ የፋብሪካው አዳዲስ ማምረቻዎች የሚመረቱት ምርቶች ለኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ግብዓቶችን የሚያመርቱ ይሆናል ተብሏል፡፡
እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፣ በተለይ የፖሊስተር ጨርቅ ያመርታል ተብሎ የሚጠበቀው የፋብሪካው የማምረቻ መስመር ለምርት ግብዓትነት የሚጠቀምበትን ዋነኛ የጥሬ ዕቃ ግብዓት ከአገር ውስጥ የሚጠቀም ይሆናል፡፡ የፖሊስተር ምርቱን ለማምረት ግብዓት የሚሆኑት ጥሬ ዕቃዎች አገልግሎት የሰጡና የወዳደቁ የፕላስቲክ ምርቶች መሆናቸውን ኃላፊው ገልጸዋል።
አነስተኛ የጥሬ ዕቃ ከውጭ የሚገባ ቢሆንም፣ አብዛኛው ጥሬ ዕቃ አገልግሎት ላይ የዋሉ የፕላስቲክ ምርቶች ታጥበውና ተፈጭተው በግብዓትነት እንደሚውሉ ኃላፊው አስረድተዋል። በዚህ የምርት መስመር በቀን አሥር ቶን ፖሊስተር የማምረት አቅም ያለው መሆኑ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የክር ማምረቻው ደግሞ በቀን ሰባት ቶን የማምረት አቅም እንደሚኖረው አስረድተዋል። እነዚህ በፋብሪካው የሚመረቱ አዳዲስ ምርቶች ለአገር ውስጥ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ብቻ ሳይሆን፣ ለውጭ ገበያም የሚቀርቡ ናቸው ተብሏል፡፡
ኩባንያው የሐዋሳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብካሪን በአዲስ ከማደራጅት ባለፈ፣ በዚያው የሐዋሳ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ቅጥር ግቢ ውስጥ ባለው ሰፊ ቦታ በኢትዮጵያ የመጀመርያ የተባለውን የግል የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ እያካሄደ ነው፡፡ ፓርኩ እየተገነባበት ያለው አጠቃላይ የቦታ ስፋት 25 ሔክታር ሲሆን፣ በ11 ሺሕ ካሬ ሜርት ቦታ ላይ የሚያርፉ 14 ሼዶች እንደሚነቡም ታውቋል።
ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ይጠይቃል የተባለው ይህ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ግንባታ ሥራ መጀመርያ ላይ ታስቦ የነበረው በሁለት ቢሊዮን ብር ግንባታውን ለማከናወን ነበር፡፡ የግንባታው የመሠረተ ድንጋይ ከተቀመጠ በኋላ ግን የዲዛይን ለውጥ ተደርጎ የበለጠ ለማስፋፋት መወሰኑን ለማወቅ ተችሏል።
የዲዛይን ለውጥ መደረጉ የግንባታ ሥራው እንዲዘገይና የግንባታ ወጪውንም ወደ አራት ቢሊዮን ብር ያሳደገው መሆኑን የኩባንያው ሥራ አስፈጻሚ ገልጸዋል፡፡ ከ14ቱ ሼዶች ሌላ የኢንዱስትሪ ፓርኩ የአንድ መስኮት አገልግሎት መስጫ ማዕከል፣ የእሳት አደጋ መከላከያ፣ የመኖሪያ አፓርትመንቶችና የውኃ ማጣሪያ ማዕከሎች እንሚገነቡ ተገልጿል።
የግንባታ ሥራውን የሚያከናው ነው ‹‹ሲኖማ›› የተባለው የቻይና ኩባንያ ሲሆን፣ ይህ ኩባንያ ከዚህ ቀደም ወደ አራት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት ይታወቃል፡፡ የሐዋሳ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ፓርክ የግንባታ ሥራ በአሁኑ ወቅት 37 በመቶ የተከናወነ ሲሆን ከዲዛይን ለውጡ ባሻገር፣ በዋና ዋና የግንባታ ግብዓቶች ላይ የታየው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪና አጋጥሞ የነበረው የውጭ ምንዛሪ እጥረት አጠቃላይ ግንባታው በታሰበው ፍጥነትና በዕቅዱ መሠረት እንዳይጓዝ ተፅዕኖ ማድረጋቸው ተጠቅሷል፡፡
በተለይም የብረታ ብረትና የሲሚንቶ ምርት አቅርቦት ላይ የተከሰተው እጥረትና ዋጋ መናር ፕሮጀክቱ በተፈለገው ፍጥነት እንዳይከናወን ምክንያት መሆናቸውን የገለጹት ሥራ አስፈጻሚው፣ ይህም ቢሆን ሥራው ሳይቋረጥ እየተሠራ በመሆኑ ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ እንደሚያልቅ ገልጸዋል። የኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሕይወት ታደሰም ይህንኑ አረጋግጠዋል።
ግንባታውን ለማፋጠንም የስቲል ስትራክቸርና የኤሌክትሪክ ሥራዎች ምርት እንዲመረት ከአንድ የቻይና ኩባንያ ጋር ውል ተገብቶ በአሁኑ ወቅት የምርት ሥራ በመካሄድ ላይ መሆኑን የፋብሪካው ኃላፊዎች ገልጸዋል።
በመሆኑም የሚመረቱትን ብረታ ብረትና ስቲል ስትራክቸር ገጣጥሞ ለሥራ ዝግጁ ማድረጉ ጥቂት ወራትን ብቻ የሚፈርጅ ይሆናል ተብሏል፡፡ ይህንን ሥራ በቶሎ ለማጠናቀቅ ግን የአገር ውስጥ የግንባታ ግብዓቶች አቅርቦት ችግርና ቀሪውን የግንባታ ወጪ ለማጠናቀቅ ከባንክ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው ብድር በቶሎ መለቀቅ ወሳኝ መሆናቸውን ከኃላፊዎቹ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡
እስካሁን የፓርኩን ግንባታ ወጪ የኩባንያው በራሱ የገንዘብ ምንጭ እሸፈነ መቆየቱን የሚገልጹት የኩባንያው የሥራ ኃላፊዎች፣ ለቀሪው ግንባታ የሚሆነውን ተጨማሪ ፋይናንስ ከባንክ ለማግኘት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ ብሔራዊ ባንክ ባንኮች ብድር እንዳይሰጡ በመመርያ ጥሎት የነበረው ዕግድ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
አሁን በባንክ ብድር ላይ የተጣለው ዕግድ በመነሳቱና ይኼንን የሚያህል ግዙፍ ፕሮጀክት በራስ አቅም ብቻ መገንባት አዳጋች በመሆኑ፣ ለአንድ የመንግሥት ባንክ የብድር ጥያቄ አቅርበው ውጤቱን እየጠበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኩ ግንባታ ሲጠናቀቅ የሚፈጠሩትን 14 የማምረቻ ሼዶች ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ የጨርቃ ጨርቅ ኩባንያዎች እንደሚከራዩ ለማወቅ ተችሏል።
የቀድሞውን ፋብሪካ በአዲስ ማሸነሪዎች ተክቶ ወደ ሥራ ሲገባ ለ1,200 ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ይሆናል ተብሏል፡፡ በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ሥር የሚገነቡት 14 ሼዶች ሙሉ በሙሉ በአምራቾች ሲያዙ ደግሞ ከ25 እስከ 30 ሺሕ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ተገምቷል፡፡
ኩባንያው የሐዋሳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካን በግማሽ ሚሊዮን ብር ከመንግሥት የተገዛ መሆኑ ይታወሳል፡፡