Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

ምክንያታዊ ትውልድን የመፍጠር ንቅናቄና የሥነ ልቦና ክትባት

አቶ ዘላለም ይትባረክ ‹‹ከከፍታ ለመድረስ የማኅበረሰብና የተቋማት ሰብዕና ግንባታ ማዕከል››ን በ2010 ዓ.ም. ከማቋቋማቸው በፊት የሱሰኛ ማገገሚያ ማዕከል በመመሥረት የቅድመ መከላከል ሥራ ይሠሩ ነበር፡፡ በቀደመው ተቋም በርካታ ወጣቶች ከሱስ እንዲላቀቁና እንዲያገግሙ፣ በሕዝብ መገልገያ ቦታዎች ላይ ትምባሆ እንዳይጨስ፣ የቢራ ማስታወቂያ ከቴሌቪዥን እንዲወርድ ከመንግሥትና ከሌሎች በዘርፉ ከሚሠሩ አካላት ጋር በመተባበር ሠርተዋል፡፡ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር የፀረ ሱስ ንቅናቄ መሥራታቸውንም ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን የቀደመውን ተቋም ከመቀለ ዩኒቨርሲቲ ጋር ይሠሩ ስለነበርና የፖለቲካ ልዩነቱ ሲፈጠር የቀደመው ፕሮጀክት በመንጠልጠሉ ወደ አዲስ አበባ መጥተው ጥናት በማድረግ ከከፍታ ለመድረስ የማኅበረሰብና የተቋማት ሰብዕና ግንባታ ማዕከልን መሥርተው በማኅበረሰብ ግንባታ ላይ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ እንደ አገር ያዩት ችግር ሰዎች ለነገሮች ካላቸው ትርጉም፣ ዕይታና የአመለካከት ጋር የተያያዘ እንጂ የተፈጥሮ ሀብት ወይም የሃይማኖት ባለመሆኑ ችግሩን በጋራ ለመቅረፍ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ሥራ ከመጀመራችሁ በፊት በተለያዩ ተቋማት ላይ ጥናት ሠርታችኋል፡፡ ጥናታችሁ ምን አሳየ?

አቶ ዘለዓለም፡- በሠራነው ጥናት እንደ አገር ያየነው ችግር ለነገሮች የምንሰጠው ትርጉም ነው፡፡ ስለነገሮች ያለን ትርጉም፣ ዕይታና የአመለካከት ችግር እንጂ የተፈጥሮ ሀብት ሆነ የሃይማኖት ችግር የለብንም፡፡ አብረን መቆም እንዳንችል ያደረገን ችግራችን ለነገሮች የምንሰጠው ትርጉም ነው፡፡ በመሆኑም የማኅበረሰብ ልማት ማለትም የማኅበረሰብ አቀፍ ንቅናቄ ማድረግ ላይ ወሰንን፡፡ እነዚህ ሥልጠናዎችና ንቅናቄዎች ናቸው፡፡ በዋነኝነት ደግሞ አዲስ ንቃተ ህሊና መፍጠር ነው፡፡ የማኅበረሰብ አቀፍ ንቅናቄ በሥሩ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አለው፡፡ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ‹‹የማኅበረሰብ ልቦና›› የሚል መድበል አለው፡፡ በዚህ ማኅበረሰቡ ላይ አዲስ ሥነ ልቦና ለመፍጠር የሚያስችል ስለሥራ፣ ስለሱስ አደገኛነትና በሽታ ስለመሆኑ ማሳወቅ፣ ሰው ስለተፈጠረበት ምክንያትና ዓላማ የማሳወቅ፣ ስለግንኙነት፣ ችግርን ስለመፍታት፣ ኃላፊነትን ስለመወጣት፣ በቡድን ስለመሥራት፣ ስንፍናን ስለማስወገድ፣ ስለገንዘብና ጊዜ አጠቃቀምና በሌሎች ማኅበራዊ እሴቶች ላይ ትኩረት አድርገን እንሠራለን፡፡ ትኩረታችን አዲስ የማኅበረሰብ እሳቤ መፍጠር ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ችግሩን ለመቅረፍ ምን እየሠራችሁ ነው?

አቶ ዘላለም፡- እንደ አገር እየተቸገርንባቸው ካሉ ጉዳዮች አንዱ ተማሪዎች በትምህርት ዘመናቸው ያላቸው ቆይታና ሥራ ላይ ሲመጡ ያለው መደነቃቀፍ ነው፡፡ ሕይወትን የመምራት ክህሎት የለም፡፡ ከትምህርት ሚኒስቴርና ከአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ጋር በምንሠራው ሥራ ክበባት ላይ ያለውን የኢንቨስትመንት አቅጣጫ መቀየር ላይ እናተኩራለን፡፡ የትምህርት ሥርዓታችን አንካሳ የሆነውም ከውስጥም ከውጭም ችግር ስላለበት ነው፡፡ የመማር ማስተማር ሥርዓቱና ከክበባት ጋር ያለው ሥራ በንድፈ ሐሳብ የተማሩትን በተግባር የማያዩበት ካልሆነ ለውጥ አናመጣም፡፡ ጽንሰ ሐሳብን መሠረት ያደረገ የመማር ማስተማር ሥርዓት ዘርፉን ደካማ አድርጎታል በሚል ክበባት ላይ እንሠራለን፡፡ ትምህርት ቤቶች ክበባትን የሚያዩዋቸው እንደ መዝናኛ ነው፡፡ ነገር ግን የተማሪ አዕምሮ ማሳደጊያ ሥፍራ ነው፡፡ ተማሪ የወላጆቹን የኑሮ ጫና ተሸክሞ ነው ወደ ትምህርት ቤት የሚመጣው፡፡ ስለዚህ ከሚደርስበት የኑሮ ጣጣና የፖለቲካ ውጥንቅጥ እንዲወጣ የምናደርግበት ክበብ ነው፡፡ ጓደኛና ጓደኛ እንዲረዳዱ፣ ችግር ፈቺ እንዲሆኑ፣ የማኅበረሰቡን ችግር ለመፍታትና የበጎ አድራጎት ሥራ ላይ እንዲሳተፉ ሥልጠናውን ማግኘት ያለባቸው ክበባት ላይ ነው፡፡ ክበባት ላይ የተማሪዎች ንቁ ተሳትፎም በመማር ማስተማር ሥርዓቱ ላይ ንቁ ያደርጋቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከሥልጠናዎችና ንቅናቄዎች በተጨማሪ የምትሠሩት ፕሮጀክት ምንድነው?

አቶ ዘለዓለም፡- የተቋማት ሰብዕና ግንባታ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ የመንግሥት ተቋማትን ለማሻሻልና ወጥ የሆነ አሠራር እንዲኖራቸው ለማድረግ እንሠራለን፡፡ እንደ አገር ሹመኛን በመለዋወጥ፣ ሠራተኞችን በመቅጣትና በመሸለም ተቋማትን ለመገንባት ያልተሞከረ ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ችግሩን መፍታት አልተቻለም፡፡ ስለዚህ የዚህ ችግር መነሻ የሚሆነው ሠራተኞች ሥራን የተረዱበት መነሻ ጤነኛ አለመሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ ከብዙ ተቋማት ጋር ስንሠራ ሠራተኞችን ሥራ ምንድነው ብለን ስንጠይቃቸው ‹ሥራ እርግማን ነው› ነው ይሉናል፡፡ አዳም ከፈጣሪ ጋር በነበረው ግጭት የተጣለበት ቅጣት አድርገው ነው የሚያስቡት፡፡ ብዙዎቹን ጸሎታቸው ምን እንደሆነ ስንጠይቅ ‹ጌታ ሆይ ገንዘብ ስጠኝ›› ነበር መልሳቸው፡፡ ብዙዎቹ ሀብት ቁጭ ተብሎ የሚገኝና የሚበላ ይመስላቸዋል፡፡ ሥራ የሚመስላቸው ገንዘብ የሚገኝበት ብቻ ነው፡፡ ሥልጠና ለመስጠት ስንጠራ አበል አለው? ይላሉ፡፡ ትምህርት ቤት ያሉ ተማሪዎች ሁሉ አበል አለ? ማለት ጀምረዋል፡፡ ሥራን፣ ትምህርትን ከገንዘብና ከጥቅም አንፃር ብቻ የማየት ሁኔታ ተቋሞቻችን እንዲበሰብሱ አድርጓል፡፡ ኃላፊነት ኃላፊ መሆን ይመስላቸዋል፡፡ ኃላፊነት ግን እንደ ዘር ነው፡፡ ሰው የዘራውን እንደሚያጭደው ሁሉ፣ ኃላፊነቱን ያልተወጣ ኃላፊ ኃላፊነት የማይወጣውን ያፈራል፡፡ የመንግሥትን ወረቀትና ንብረት እያወደመ ተወው የመንግሥት ነው ይላል፡፡ የተከፈተ ውኃን ዘግቶ የማያልፍ ሰው በሞላበት እንዴት ሰው ልጅ ወልዶ ኃላፊነት እንዲሰማው ሊያደርግ ይችላል? እንዴት ገንዘቡን ያስተዳድራል? ኃላፊነትን የምንወጣው ለራሳችን ብለን ነው፡፡ ለጤናችን፣ ለኑሯችንና ለቤተሰባችን ስንል ነው፡፡ ቁልፍ የሆኑ ጉዳዮችን እያነሳን ነው የተቋማት ግንባታን የምንሠራው፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበረሰባዊ ንቅናቄን በምን መንገድ ትሠራላችሁ?

አቶ ዘለዓለም፡- በመገናኛ ብዙኃን በሚተላለፍ ፕሮግራም የሚሠራ ነው፡፡ ክልልና ዞን አቀፍ የንቅናቄ መድረኮችም አሉን፡፡ ከተለያዩ ሚኒስቴሮች፣ ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በጋራ አገር አቀፍ ንቅናቄዎች ናደርጋለን፡፡ አዲስ ንቃተ ህሊና ኅብረተሰቡ ላይ እስኪፈጠር ንቅናቄ እናደርጋለን፡፡ ከተቋማት ግንባታ አንፃር አሁን የጀመርነው ከሚኒስቴሮች፣ ኤጀንሲዎችና ባለሥልጣኖች ውስጥ ነው፡፡ የሠራተኞች አመለካከት ስለነገሮች የሚሰጡትን ትርጉም መለወጥ ላይ ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ ሥልጠናው ከቤት ጀምሮ ሕይወትን መምራትና በሥራ ቦታ ውጤታማ ሆኖ እንዲሠራ ማስቻል ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህንንም አብረን እንሥራ ከሚሉን አካላት ጋር አብረን እየሠራን ነው፡፡ የሥነ ልቦና ክትባት የሚል ለሁሉም ተቋማት የምንሰጠው ሥልጠና አለ፡፡ አደንዛዥ ዕፅ ብቻ ሳይሆን አደንዣዥ አስተሳሰብ የምንለው አለን፡፡ ሰዎች ስለራሳቸው፣ ስለአገራቸው፣ ስለገንዘብና ስለሌሎችም ያላቸው የተሳሳተ ግንዛቤን እንዲተዉ እንፈልጋለን፡፡ አልችልም፣ አይሆንልኝም፣ ኢትዮጵያ ከመኖር ሞት ይሻላል፣ ወዘተ የሚሉ ብዙ የተዛቡ አመለካከቶች አሉ፡፡ ይህንን መቀየር አለብን፡፡ ብዙዎች እንዲሰደዱ ባርነትን የተሻለ ምርጫ እንዲያደርጉ የሚያደርጋቸው ስለአገራቸውና በዙሪያቸው ስላሉ ነገሮች ያላቸው የተሳሳተ ግንዛቤ ነው፡፡ በማኅበረሰብና በተቋማት ልማት ላይ ሥልጠና ስንሰጥ ሞት እንዳለ ነግረን ማስደንገጥ ላይ እንሠራለን፡፡ እንደ አገር ነጋዴውም ፖለቲከኛውም ላይ እየተስተዋለ ያለው ችግር ሞትን የመርሳት ነው፡፡ ሰው እንደሚሞት ሲረሳ አጠገቡ ላለ ሰው ክፉ ይሆናል፡፡ መዝረፍ ላይ ያተኩራል፡፡ መኖር ያለብን እንደሚሞት ሰው ነው፡፡ መሥራት ያለብን እንደሚኖር ሰው ነው፡፡ አለባብሰን ማለፍ የለብንም፡፡ የተሰጠንን ኃላፊነት መወጣት አለብን፡፡  

ሪፖርተር፡- በየተቋማቱ እየሄዳችሁ ከምትሰጡት የሕይወት ክህሎትና አመለካከትን የመለወጥ ሥልጠና በተጨማሪ በትምህርት እንዲካተት ሠርታችኋል?

አቶ ዘለዓለም፡- ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ጋር እየሠራን ነው፡፡ በዋነኝነት የትምህርት ቤት ማኅበረሰብ የሚባሉትን ዳይሬክተር፣ ተቆጣጣሪ፣ መምህራን፣ ጥበቃ፣ ተማሪዎችና ወላጆች አሉ፡፡ ሥልጠናውን በአዲስ አበባ  በሁሉም የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ሰጥተናል፡፡ ተከታታይ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ሠርተናል፡፡ ምክንያታዊ የሆነ ትውልድ መፍጠር ላይ ነው ያተኮርነው፡፡ እኔ ባለፈው ሕይወቴ ላይ ሱሰኛ ነበርኩ፡፡ አስቸጋሪ ነበርኩ፡፡ ትናንትና ለሱስ ይዘረጋ የነበረ እጄ ዛሬም ያው የእኔ እጅ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ላይ ሱስ የሚያስይዝ ነገር ሳይሆን ብዕር ይዟል፡፡ እጄ፣ አንደበቴ የእኔ ሆኖ አመለካከቴ ተለውጧል፡፡ አንድ መተግበሪያ በተሳሳተ መረጃ ሲሞላ እንደማይሠራ ሁሉ፣ አዕምሮም በውሸት ዕውቀት  ሲሞላ ትእዛዝ የሚሰጠው ውሸት መር  ዕውቀት ስለሆነ  አይሠራም፡፡ ለመተግበሪያው ማስተካከያ ዕርማት እንደሚያስፈልገው ሁሉ፣ አመለካከቱ በውሸት የተሞላ ሰውም ከውስጡ የሚያወጣለት ሥልጠና ያስፈልዋል፡፡ የተሳሳተ ዕውቀት ሱሰኛ አድርጎኝ ነበር፡፡ ትክክለኛ ዕውቀት ደግሞ ሕዝብን እንዳገለግል አድርጎኛል፡፡ ሕዝብንም የተሳሳተ ዕውቀት ለጥፋት ይዳርገዋል፡፡ የእውነት ዕውቀት፣ ትርጉምና መረዳት ሲኖር ደግሞ ለልማት ያበቃዋል፡፡ ሰው እንዲያለማም እንዲያጠፋም የሚያደርገው ነገሮችን የሚገነዘብበትና የሚረዳበት ሁኔታ ነው፡፡ ሥራ እንዳንሠራና እንድንጠላ አድርጎ ተቋሞቻችን እንዲበሰብሱ፣ በሙሰኞች እንዲሞሉ፣ ኃላፊነት በማይሰማቸው አመራሮች እንዲመሩ ያደረገው አዕምሮ ውስጥ ያለው ስለሥራ ያለን ግንዛቤ ነው፡፡ በመሆኑም ከሳይንስ፣ ከተለያዩ ልምዶች ዓይተን አመለካከታችንንና ለነገሮች ያለንን ሐሳብ ለመቀየር ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ ከዚህ ቀደም ከነበረው አረዳድ በተለየ ሌላ ትርጉም እንዲሰጥና እንዲለወጥ እየሠራን ነው፡፡ ለዚህም የሥነ ልቦና ክትባት የሚል ሥልጠና እንሰጣለን፡፡

ሪፖርተር፡- የሥነ ልቦና ክትባት ምንድነው?

አቶ ዘለዓለም፡- ይህ ለሁሉም ሰው ከታዳጊ እስከ አዋቂ፣ በሁሉም የትምህርትና የሥራ ደረጃ ላለ ሰው የምንሰጠው ሥልጠና ነው፡፡ በዋነኝነት ችግርና መፍትሔ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ለምሳሌ ሥራን መጥላት ችግር ነው፡፡ የሚያመጣው ዘርፈ ብዙ በሽታ አለ፡፡ ስንፍና በክርስትናም በእስልምናም ኃጢዓት ነው፡፡ ስንፍና በሽታን፣ ድህነትን፣ የዕድሜ ማጠርን ስቦ የማምጣት ኃይል አለው፡፡ ከሁሉም በላይ ባርነትን ያመጣል፡፡ ብዙዎቹ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል አቅጣጫዎች  ሲታዩ ነጮችን ማሸነፍ ላይ ያጠንጥኑ እንጂ ራሳችንን ማሸነፍና ከድህነት መውጣት ላይ ያጠነጠኑ አይደሉም፡፡ ‹‹ኖ ሞር›› የምንለውም ነጮቹን ማሸነፊያ ነው፡፡፡ ለምን ካልን ባሪያ ስለሆንን የእነሱን ዕርዳታ ተገን አድርገን ስለምንኖር፡፡ የዚህ መሠረታዊ ምክንያቱ ደግሞ ሥራ መጥላታችን ነው፡፡ ሥራ የሚወድ ሕዝብ ነፃ ሕዝብ ነው፡፡ ምክንያቱም በራሴ፣ በላቤ ሠርቼ እኖራለሁ፣ የማንም ጥገኛ ባሪያ ሆኜ መኖር አልችልም ብሎ ስለሚያምን ማለት ነው፡፡ ያ ችግራችን ነው፡፡ ዛሬ ደብዳቤ መጻፍ፣ የተለያዩ ጉዳዮች መከሰት ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ ራሳችን ሠርተን ራሳችንን ለመቻል ያለብን ስንፍና ያመጣብን ችግር ነው፡፡ እንደ አገር ራሳችንን ችለን ቢሆን፣ ራሳችንን እንከላከል ነበር፡፡ ለዚህ ችግር መፍትሔ አዘጋጅተናል፡፡ ለምሳሌ የኮሮና ክትባት የተሠራው ከኮረና ቫይረስ ነው፡፡ መድኃኒቱ የተቀመመው ከችግሩ ነው፡፡ እኛም አገር አንዱ ችግር ኃላፊነትን አለመወጣት ነው፡፡ ንብረት ይሰበራል፣ ይባክናል፣ ለምን ሲባል የመንግሥት ነው ይላል፡፡ ኃላፊነት ወስዶ ማስተካከል አይፈልግም፡፡ ዛሬ እንደ አገር እያስተናገድነው ያለው ችግር መነሻ ትናንት ያልተወጣነው ኃላፊነት ነው፡፡ ዛሬም ግን እጃችንን እየቀሠርን እንጂ፣ እኔ ጥፋተኛ ነኝ ብለን ማየት አልቻልንም፡፡ ስለዚህ እንዴት ኃላፊነትን እንወጣ? ኃላፊነት ባለመወጣታችን ከገባንበት ባርነት እንዴት እንገላገል? የሚለውን ማየት አለብን፡፡ ሰው ኃላፊነት መውሰድ ካልቻለ እንደ አገርም ሆነ እንደ ግለሰብ ካለንበት ችግር መውጣት አንችልም፡፡ ሰው ነፃ የሚወጣው ኃላፊነት መሸከም ሲችልና እኔ ተጠያቂ ነኝ ሲል ነው፡፡ ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ ነች፡፡ ከዚህ ችግር በአጭር ጊዜ መውጣት የምንችው እያንዳንዳችን ኃላፊነታችንን ስንወጣ ነው፡፡ መወሰን አለመቻልም ሌላው ችግራችን ነው፡፡ እንደ አገር ሀብት እየባከነ ያለው መወሰን በማይችሉ አመራሮች አማካይነት ነው፡፡ ለተቋማት መበስበስ ምክንያቱ ቆይ በኋላ፣ ቆይ ነገ፣ የሚል በመብዛቱ ነው፡፡ ጊዜ ግን ሕይወት ነው፡፡ በጊዜ መቀለድ ማለት በሕይወት መቀለድ ነው፡፡ ውሳኔ መወሰን የማይችል አመራር በሰው ሕይወት ነው የሚቀልደው፡፡ ለምሳሌ በርካታ አመራሮች ስብሰባ ላይ ናቸው እንበል፡፡ እነሱ ሥር ያለው መወሰን ስለማይችል ብቻ እነሱ ስብሰባ ላይ በሆኑባቸው ቀናት ሁሉ የአገር ንብረት፣ ጊዜ፣ ሥራ ይባክናሉ፡፡ መወሰን አለመቻል ሸክምን ያበዛል፡፡ አገር ወደሚፈለገው ዕድገት መሻገር የምትችለው ሰዎች ሲወስኑ ነው፡፡ ሰዎች መወሰን ሲችሉ የራሳቸውንም ሕይወት ያሻሽላሉ፡፡ ማኅበረሰባችን ከድህነት እንዲወጣ ከፈለግን ውሳኔ መስጠት፣ ውሳኔ የሚሰጡ ሰዎችን በተዋረድ ማብዛት አለብን፡፡ ሌላው ጠባቂነት ነው፡፡ ካልታዘዘ፣ ካልተነገረውና አድርግ ካልተባለ የማይሠራ ሰው መሆን የለብንም፡፡ የሚያዋጣ ነገር ላይ ሁሉም መወሰን አለበት፡፡ ዕቅድን መጥኖ አቅዶ መተግበርንም እናስተምራለን፡፡  

ሪፖርተር፡- ከየትኞቹ ተቋማት ጋር  አብራችሁ ትሠራላችሁ?

አቶ ዘለዓለም፡- ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር የ10,000 ወጣቶች ሥራ ፈጠራ ላይ አብረን እንሠራለን፡፡ በ11ዱም ክፍላተ ከተሞች ላይ ወጣቶችን ከስደትና ከአደገኛ ዕፅ ለመከላከልና ሥራ ፈጠራ ላይ አነቃቂ ሥራ እንሠራለን፡፡ ከምግብና መድኃኒት  አስተዳደር ባለሥልጣን፣ ከኢትዮጵያ ጤና መድን አገልግሎት፣ ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ፣ ከኢትዮጵያ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩትና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር አብረን እንሠራለን፡፡ ለዚህም ጥናት አድርገን ነው ሥራ የጀመርነው፡፡ ከእኛ ጋር አብሮ የሚሠራ መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገ ማሻ ቴክኖሎጂ የሚባል ድርጅትም አለ፡፡ ከእነዚህ ጋር ሆነን የተቋማት የሥርዓት ችግርን እንፈታለን፡፡ ይህ በተለያዩ አፕልኬሽኖች ተጠቅመን የተቋማትን የአሠራር ሥርዓት የምናዘምንበትና የምናቀላጥፍበት ነው፡፡  

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

በኦሮሚያ ክልል በስድስት ከተሞች የተዋቀረውን ሸገር ከተማን የማደራጀት ሥራ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ስድስት ከተሞች የተዋቀረው ሸገር ከተማን...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...