- አዲስ አበባ ተወካዮቿን አሳድጋለች
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ ጉልህ አበርክቶ ካላቸው ክለቦች መካከል ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚጠቀሱት ኢትዮ ኤሌክትሪክና ኢትዮጵያ መድን እንዲሁም ለኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እንግዳ የሆነው ለገጣፎ ለገዳዲን ጨምሮ ሦስቱ ክለቦች ወደ ፕሪሚየር ሊጉ አድገዋል፡፡ ዘንድሮ 30 ክለቦች በሦስት ምድብ ተከፍለው ሲያከናውኑት ቆይተዋል፡፡
ከእንግዳው ለገጣፎ ለገዳዲ በስተቀር በኢትዮጵያ እግር ኳስ ጉልህ ድርሻ ካላቸው አንጋፋ ክለቦች ተርታ የሚጠቀሱት ኢትዮ ኤሌክትሪክም ሆነ ኢትዮጵያ መድን፣ በሁለት ታላላቅ የእግር ኳስ ባለሙያዎች መሠልጠናቸው ይነገርላቸዋል፡፡ ሁለቱ ክለቦቹ በተለይም ኤሌክትሪክ ከ50ዎቹ ጀምሮ ለብሔራዊ ቡድን ተተኪ ተጨዋቾችን በማፍራትም ይጠቀሳሉ፡፡
ሁለቱ ክለቦች በተጨዋችነት ዘመኑ አፍሪካውያን የእግር ኳስ ክዋክብት እንዲህ እንደ አሁኑ ባልገነኑበት ወቅት በምዕራባውያን ዕይታ ውስጥ ገብቶ እንደነበረ በሚነገርለት መንግሥቱ ወርቁ መሠልጠናቸው ሌላው የሚያመሳስላቸው ታሪክ እንዳላቸው ይነገርላቸዋል፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ መድን በ1985 ዓ.ም. በአፍሪካ ክለቦች የውድድር መድረክ (ካፍ ካፕ) ላይ በአንጋፋው አሠልጣኝ መንግሥቱ ወርቁ እየሠለጠነ፣ እስከ ግማሽ ፍፃሜ በመድረስ ይጠቀሳል፡፡
ይሁንና ኢትዮጵያ መድን ቀድሞ በሚታወቅበት ጥንካሬው ከመዝለቅ ይልቅ እየደከመ በመምጣቱ፣ ፕሪሚየር ሊጉ አሁን በሚጠራበት ስያሜ በተደጋጋሚ በመውረድና በመውጣት ከሚጠቀሱት ተርታ ለመቆየት ተገልዷል፡፡ ለዚህ ማሳያው ክለቡ በ1996 የውድድር ዓመት ወደ ታችኛው ሊግ ወርዶ በ1999 ዓ.ም. እንደገና መምጣቱ፣ በ2002 ወርዶ እንደገና በ2005 ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ካደገ በኋላ፣ ከሁለት ዓመት በኋላ በ2006 ተመልሶ የወረደበት አጋጣሚ ይጠቀሳል፡፡ ዘንድሮ ከ14 ዓመታት በኋላ በአሠልጣኝ በፀሎት ልኡልሰገድ እየተመራ እንደገና ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደገ ክለብ ሆኗል፡፡
እንደ ኢትዮጵያ መድን ሁሉ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመርያዎቹ ዓመታት በቀድሞ አየር ኃይል ማስተር ቴክኒሻን ሐጎስ ደስታ አሠልጣኝነት በ1993 ዓ.ም. የሦስት ዋንጫ ባለቤት በመሆን የሚታወቀው፣ የቀድሞ መብራት ኃይል የአሁኑ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ በ1990 እና በ1993 የውድድር ዓመት የሊጉ አሸናፊ ነበር፡፡ ክለቡ በዚያኑ ዓመት በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ ከአልጄሪያው ካቢላ ክለብ ጋር የመጫወት ዕድልም አግኝቷል፡፡
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በመንግሥቱ ወርቁና በማስተር ቴክኒሻን ሐጎስ ደስታና በሌሎችም ታላላቅ አሠልጣኞች እየሠለጠነ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እስከ 2010 የውድድር ዓመት ድረስ ከዘለቀ በኋላ፣ በዚያኑ ዓመት ወደ ታችኛው ሊግ ወርዶ ከአራት ዓመት በኋላ በአሠልጣኝ ክፍሌ ቦልተና እየተመራ ፕሪሚየር ሊጉን በ2015 የውድድር ዓመት ከተቀላቀሉ አንደኛው ሆኗል፡፡
በ2015 የውድድር ዓመት በፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ መሆኑን ያረጋገጠው እንግዳው ለገጣፎ ለገዳዲ ነው፡፡ በአሠልጣኝ ጥላሁን ተሾመ የሚሠለጥነው ለገጣፎ ለገዳዲን ጨምሮ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደጉት ሦስቱ ክለቦች ተመልሰው ወደ ታችኛ ሊግ ላለመውረድ ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸው የሚናገሩ አልጠፉም፡፡
በሌላ በኩል ለወትሮ በክልል ከተማ ክለቦች የበላይነት ተወስዶባት የቆየችው አዲስ አበባ ተወካዮቿን አሁን ላይ ከአራት ወደ ስድስት ከፍ ማድረግ ችላለች፡፡
ይሁንና ጅማሮውን በሐዋሳ አድርጎ ድሬዳዋ ላይ አሁን ደግሞ በአዳማ ያደረገው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ፣ የ17ኛ ሳምንት የጨዋታ መርሐ ግብሩን እያከናወነ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት አሸናፊውን ጨምሮ ወራጆቹ እነማን ይሆናሉ የሚለውን ለማወቅ ክለቦቹ ካላቸው ተቀራራቢ ነጥብና ችሎታ አኳያ ለመገመት አዳጋች ሆኗል፡፡
በዚህ የሒሳብ ሥሌት መሠረት አንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና ካልሆኑ በስተቀር፣ መከላከያና አዲስ አበባ እግር ኳስ ክለቦች ከሥጋቱ የራቁ አለመሆናቸው ነጥባቸውን ተመልክቶ ለመረዳት አያዳግትም፡፡