አንድ ሲራራ ነጋዴ መንገድ ሲሔድ ቆይቶ ቀን በምሳ ሰዓት ከአንድ ዛፍ ሥር አረፍ ብሎ ምሳውን ቆሎ ቆርጥሞና ውሃ ጠጥቶ ጉዞውን ሲቀጥል ሁለት መቶ ጠገራ ብር ረስቶ ሄደ።
አንድ ገበሬ አግኝቶለት ያንን ገንዘብ ሊሰጠው ከኋላ እየሮጠ ተከተለውና ‹‹ሰውዬ ቆም ብህ ጠብቀኝ፤ ጥለኸው የሔድከው ገንዘብህን አግኝቼልሃለሁ፤›› አለው። ነጋዴውም ‹‹ያገኘኸው ገንዘብ ስንት ነው?›› ሲለው ‹‹ሁለት መቶ ብር›› አለው።
ነጋዴው ግን ‹‹እኔ የጠፋብኝ ገንዘብ ሦስት መቶ ብር ነው። አንዱን መቶ ብር የት ደብቀህ ነው ሁለት መቶ ብር የምትሰጠኝ። ሞልተህ ካላመጣህ አልቀበልህም እከስሃለሁ። እንዲህ በዋዛ አንላቀቅም›› አለው።
ገበሬውም ገንዘቡን እንደያዘ ወደ ኋላ ተመለሰ። ነጋዴው የመሠረተው የውሸት ክስ በይግባኝ ተይዞ ወደ አፄ ቴዎድሮስ ሲቀርብ የሁለቱን አባባል ካዳመጡ በኋላ ነጋዴውን ምን ያህል ገንዘብ ነው የጠፋህ? ሲሉት ‹‹ሦስት መቶ ጠገራ ብር ነው›› አላቸው።
ገበሬውንም ‹‹ምን ያህል ገንዘብ አገኘህ?›› ሲሉት ‹‹ሁለት መቶ ጠገራ ብር ብቻ ነው›› አለ።
ከዚያ በኋላ ‹‹አንተ ነጋዴው ጠፋብኝ የምትለውን ሦስት መቶ ብር ከጣልህበት ቦታ ፈልገህ አግኝ። ሁለት መቶ ብር ያገኘኸው ገበሬ ደግሞ ሁለት መቶ ብር ጠፋኝ የሚል ሌላ ሰው እስከሚመጣ ድረስ ራስህ ልትጠቀምበት ትችላለህ›› ሲሉ ፈርደው ፋይሉ ተዘጋ።
- መክብብ አጥናው ‹‹የአባቶች ጨዋታ›› (2005)