የሰው ገንዘብ ስፈልግ ዘዴ ብዬ የያዝሁት ባያዩኝ መስረቅን፣ ቢያዩኝ መሳቅን፣ ብችልም ታግዬ ሲሆን ገድዬ፣ ባይሆንም ማምለጥን ነበርና፤ ሁልጊዜ የታለልሁበት ይህ ዘዴ ዛሬ ከመዓት ላይ ጣለኝ፡፡ ነገር ግን ሞቱ ለእኔም ለእናንተም ደግ አይደለምና እንዳትገድሉኝ፡፡ ብትገድሉኝ ደሜን የሚበቀሉ መሰሎቼ አሉኝ፡፡ ይልቅስ ከፍልጡና ከዱላው ይህንም ከመሳሰለው ከእርግጫውና ከክርኑ፣ ከጥፊውም ጨማምሩልኝና ወደ ሥራዬ ልሂድ አላቸው፡፡
ማን አለህና ዱላህን ቀምሰህ፣ በፍልጥ ቀልጠህ፣ በጥፊ ተወልውለህ፣ ገና ወደ ወህኒ ቤት ትገባለህ ብለው ቢያስፈራሩት፣ ዛሬስ ከወህኒ ቤት አገባችሁኝ፡፡ የደንቡን ተቀጥቼና ታስሬ ከተፈታሁ በኋላ የእናንተ መግቢያ ወዴት ይሆን? የማለት ዛቻ ቢዝትባቸውና በእጃቸው ወድቆ ሳለ ኋላ የተነሳሁ እንደሆነ የማለት ጉራ ቢነዛባቸው ገና ለገና ሳይሆን አይቀርም በማለት ሐሳብ ገባቸውና ሁለተኛ አይልመድህ ብለው ያንኑ ምሱን አቅምሰው ለቀቁት፡፡ መልቀቃቸው ደግ አልሆነም ሌባና ውሻ በትር አያስመርረውም፡፡
- ሰንደቅ ዓላማችን መጋቢት 22 ቀን 1935 ዓ.ም.