Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኢትዮ ቴሌኮም የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በተከሰሱበት ከባድ የሙስና ወንጀል ጥፋተኛ ተባሉ

የኢትዮ ቴሌኮም የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በተከሰሱበት ከባድ የሙስና ወንጀል ጥፋተኛ ተባሉ

ቀን:

የሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ወንድም በነፃ ተሰናበቱ

በሶማሌ ክልል የሞባይል ማስፋፊያ ማማ (ታወር) ግንባታ ጋር በተያያዘ 221,804,693 ብር ጉዳት በማድረስ ወንጀል፣ ነሐሴ 21 ቀን 2011 ዓ.ም. ክስ ተመሥርቶባቸው የነበሩት የቀድሞ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት አቶ አማረ አምሳሉ ጥፋተኛ ተባሉ፡፡

አቶ አማረ ጥፋተኛ የተባሉት ክሳቸው በሌሉበት ታይቶ ሲሆን፣ በወቅቱ ማለትም ክሱ እንደተመሠረተ ሊቀርቡ ባለመቻላቸውና የጋዜጣ ጥሪም ተደርጎላቸው ባለመቅረባቸው ነው፡፡

ከአቶ አማረ ጋር ተከሰው የነበሩ ዘጠኝ የኢትዮ ቴሌኮም የተለያዩ ክፍሎች ኃላፊዎች የነበሩ ቢሆኑም፣ ክሳቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው ሲከታተሉ የነበሩት የሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ወንድምና በኢትዮ ቴሌኮም የኤንጂፒኦ (NGPO) የአፕሊኬሽን ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ዳኘው፣ የኔትወርክ ኢንፍራስትራክቸር ፕሮግራም ዳይሬክተር የነበሩት አቶ አብዱልሃፊዝ አህመድና የቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ፕሮጀክት ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ማስረሻ ጥላሁን የቀረበባቸውን ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መከላከል መቻላቸውን አብራርቶ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ የፀረ ሙስና ወንጀል ችሎት በነፃ አሰናብቷቸዋል፡፡ በተቋሙ የኤንጂፒኦ ምክትል ፕሮግራም ዳይሬክተር የነበሩት አቶ አይተንፍሱ ወርቁ በብይን መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ መሰናበታቸውን ፍርድ ቤቱ የሰጠው ፍርድ ያሳያል፡፡ ሌሎቹ አቶ አማረን ጨምሮ ስድስት ተከሳሾች፣ ክሳቸው በሌሉበት ታይቶና ጥፋተኛ ተብለው ዓቃቤ ሕግ የቅጣት አስተያየት እንዲያቀርብ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ (ፍትሕ ሚኒስቴር) በኢትዮ ቴሌኮም በተለያዩ ኃላፊነት ላይ በነበሩት አሥር ግለሰቦች ላይ ክስ የመሠረተው፣ ግለሰቦቹ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1ሀ) 407(1ሀእናለ)፣ እና (3) ድንጋጌዎችን በመተላለፍና ሥልጣናቸውን አላግባብ በመጠቀም፣ በሕዝብና መንግሥት ላይ ጉዳት አድርሰዋል በማለት መሆኑን ፍርዱ ያብራራል፡፡

ተከሳሾቹ ለራሳቸው ወይም ለመከላከያ ኢንዱስትሪ ሴክተር ጥቅም ለማስገኘት በማሰብ፣ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን ሥራ አመራር ቦርድ ጥቅምት 18 ቀን 1997 ያፀደቀውን የግዥ መመርያና የፌዴራል መንግሥት የግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 649/2001ን በመተላለፍ፣ የሶማሌ ክልል የሞባይል ማስፋፊያ ማማ (ታወር) ግንባታ አገልግሎት ግዢ በቀጥታ ከኢትዮጵያ መከላከያ ኢንዱስትሪ ሴክተር እንዲገዛ ስምምነት መፈጸማቸውን፣ ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቶ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ ተቀራራቢ የአየር ንብረትና የመሬት አቀማመጥ ላለው አፋር ክልል በ99,905,731 ብር የተገዛውን የሞባይል ኔትወርክ ማስፋፊያ ማማ ግንባታ የከተማ ልማት ሚኒስቴር በዝቅተኛ ዋጋ አቅርቦ ሳለ፣ ከመከላከያ 321,710,424 ብር እንዲገዛ በማድረግ 221,804,693 ብር በመንግሥት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቶ አቅርቦ ነበር፡፡

በኢትዮ ቴሌኮም የግዥ መመርያ መሠረት ውል የገባው መከላከያ ኢንዱስትሪ ሴንተር፣ ያለ ተቋሙ ፈቃድ ወይም ማሳወቅ እየተገባ ሳያሳውቅ ሥራውን ለንዑስ ተቋራጭ በ44,333,306 ብር አሳልፎ በመስጠት፣ የተጋነነ 277,377,118 ብር ጥቅም ማግኘቱን በክሱ አካቶ ነበር፡፡ በአጠቃላይ ተከሳሾቹ ከሕግና መመርያ ውጪ ሥልጣናቸውን አላግባብ በመጠቀም፣ ለሶማሌ ክልል የሞባይል ማስፋፊያ ግንባታ አገልግሎት የግዢ ውል በመፈጸም፣ በሕዝብና መንግሥት ላይ 295,586,120 ብር ጉዳት ማድረሳቸውን በዝርዝር አቅርቦ፣ ምስክሮችን በማሰማት የሰነድ ማስረጃዎችን በማቅረብ በእስር ላይ ሆነው ክርክር ሲያደርጉ በነበሩት አቶ ኢሳያስን ጨምሮ ዘጠኝ ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይ ሲሰጥ፣ አቶ አይተንፍሱ መከላከል  ሳያስፈልጋቸው በነፃ ተሰናብተዋል፡፡

ተከላከሉ የተባሉት ተከሳሾች የመከላከያ ምስክሮቻቸውን አቅርበው አሰምተዋል፡፡ ተከሳሾቹ አቶ ኢሳያስና አቶ አብዱልሃፊዝ መከላከያ ምስክሮቻቸው ከመመስከራቸው በፊት፣ ራሳቸው (ተከሳሾቹ) በወንጀለኛ መከላከያ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 142(3) ድንጋጌ መሠረት የመከላከያ ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡

አቶ ኢሳያስ በሰጡት የመከላከያ ቃል እንዳብራሩት፣ የሞባይል ማስፋፊያ ማማ (ታወር) ግንባታ ያለ ጨረታ ለመከላከያ የተሰጠው በክልሉ በወቅቱ የነበረው የፀጥታ ሁኔታ አስቸጋሪና ከመከላከያ ውጪ ያለ አጃቢ በአካባቢው መንቀሳቀስ ስለማይቻል ነው፡፡ በወቅቱ የግል ኮንትራክተር ተገኝቶ ትርፍ እንደሚያገኝ ተነግሮት እንዲሄድ ሲጠየቅ ‹‹አልሄድም›› ማለቱንና ሥራው ለመከላከያ የተሰጠው በኮሚቴ ድርድር ተደርጎ እንደሆነ በማብራራት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የድርድር ሥራውን የኢትዮ ቴሌኮም ማኔጅመንት እንደሚያውቀውና የወቅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ድርድሩ ቀርቦላቸው ሁኔታው አሳማኝ መሆኑን ተረድተው ሥራው እንዲሠራ ማድረጋቸውንም መስክረዋል፡፡ አቶ ኢሳያስ ኤንጂፒኦ (NGPO) ሕጋዊ አይደለም ስለመባሉም፣ ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ኦፊስና ኤንጂኤንፒሲኤስኦ (NGNPCSO) ተብሎ የነበረው ተጠቃሎ፣ ከግንቦት 21 ቀን 2001 ዓ.ም. ጀምሮ ኤንጂፒኦ (NGPO) መባሉንና ሌሎች ጉዳዮችን አቶ ኢሳያስ መስክረዋል፡፡ አቶ አብዱልሃፊዝና አቶ ማስረሻም በተመሳሳይ ሁኔታ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡

የቀድሞ የጦር ኃይሎች ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሳሞራ የኑስን ጨምሮ ሌሎችም የመከላከያ ምስክሮች ቀርበው መስክረዋል፡፡

ጄኔራል ሳሞራ በሰጡት ምስክርነት፣ እሳቸው ከ1983 ዓ.ም. እስከ 1987 ዓ.ም. ድረስ የምሥራቅ ዕዝ አዛዥ ነበሩ፡፡ ከ1993 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ሆነው ሲሠሩ፣ በሶማሌ ክልል የነበረው የፀጥታ ሁኔታም አስቸጋሪና አካባቢው ላይ ኦኤልኤፍ (OLF) እና የታጠቁ አካላት ተቆጣጥረውት የነበሩና የልማት ሥራዎችን ለመሥራት መከላከያ ተመራጭ እንደነበር ይህም የሆነ በመንግሥት ዕውቅና መሆኑን መስክረዋል፡፡ በአካባቢው በ1998 ነዳጅ ፍለጋ ሥራ ላይ የተሰማሩ የቻይና ዜጎችና ኢትዮጵያውያን መገደላቸውንና ከጅግጅጋ ጎዴ ያለውን 50 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመሥራት ስምንት ዓመታት የፈጀውን ሥራ መከላከያ መሥራቱንም አክለዋል፡፡ የጎዴ ትልቁን ግድብ ሳትኮን የሚባል ኩባንያ ጀምሮት መሥራት ባለመቻሉ የመከላከያ ኮንስትራክሽን መሥሪያ ቤት እንደጨረሰው በመግለጽ፣ በክልሉ የነበረውን ችግር መስክረዋል፡፡

በክልሉ ከ1999 ዓ.ም. እስከ 2003 ዓ.ም. ድረስ የክልሉ የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊና ከዚያም በኋላ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ይሠሩ የነበሩትና አሁን በእስር ላይ የሚኙት አቶ አብዲ መሐመድ (አብዲሌ)ም የመከላከያ ምስክር ሆነው በሰጡት ምስክርነት፣ ክልሉ በኦሮሚያ በኩል ኦነግ፣ በሶማሌ በኩል የሶማሌያ አማፂያን አልሸባብ፣ አሊትሀድና ኦብነግ ይወጡ ይገቡ ስለነበር ችግር እንደነበር አስረድተዋል፡፡ ሌሎችም የመከላከያ ምስክሮች ቀርበው የመከላከያ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ተከሳሾቹ የሰነድ ማስረጃዎችንም አቅርበዋል፡፡ እነ አቶ ኢሳያስን በመወከል ክርክር ያደረጉት ጠበቃ ሃፍቶም ከሰተና ጠበቃ አቶ ዘረሰናይ ምሥግና ነበሩ፡፡

ዓቃቤ ሕግ ተከሳሶቹም የክርክር ማቆሚያ ሐሳባቸውን አቅርበው ከጨረሱ በኋላ ፍርድ ቤቱ አቶ ኢሳያስ፣ አቶ አብዱልሃፊዝና አቶ ማስረሻ የቀረበባቸውን የክስና ማስረጃ ‹‹ተከላክለዋል? ወይስ አልተከላከሉም?›› የሚለውን ጭብጥ ይዞ  መዝገቡን መርምሯል፡፡

ፍርድ ቤቱ መዝገቡን መርምሮና ከተገቢው ሕግ ጋር አገናዝቦ በሰጠው ፍርድ በእስር ላይ የከረሙት አቶ ኢሳያስ፣ አቶ አብዱልሃፊዝና አቶ ማስረሻ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበባቸውን ክስ፣ የሰው ምስክርነትና የሰነድ ማስረጃ በተገቢ ሁኔታ ማስተባበል በመቻላቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ሲል መጋቢት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ፍርድ ሰጥቷል፡፡ በሌሉበት ጥፋተኛ በተባሉት አቶ አማረን ጨምሮ ስድስት ተከሳሾች ላይ ዓቃቤ ሕግ የቅጣት አስተያየት እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...