የኢትዮጵያ መንግሥት ከሰሞኑ በተደጋጋሚ እያነሳው ያለውን የፋይናንስ ዘርፍን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት የማድረግ ሒደትን የሚቀርፅና የሚያማክር የመንግሥትና የግል የፋይናንስ ዘርፍ ተዋናዮች ግብረ ኃይል እንዲቋቋም የተጠየቀ፡፡
ግብረ ኃይሉ አባል የሚሆኑት ዘርፎች ፍኖተ ካርታ በመቅረፅ ላለፉት 20 ዓመታት የፋይናንስ ዘርፍን ክፍት ለማድረግ መሠራት የነበረባቸው ሥራዎችን አሁን ላይ ለመተግበር አቅጣጫ እንዲያስቀምጡ መደረግ እንዳለበት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች አሳስበዋል፡፡
‹‹ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ›› የተባለ ተቋም በንግድ ሕጉ የተደረገውን ማሻሻያና የፋይናንስ ዘርፍ ሊበራላይዜሽን በተመለከተ፣ ባለፈው ሐሙስ መጋቢት 29 ቀን 2014 ዓ.ም. የመንግሥት ተወካይ፣ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችና የባንክ ተወካዮችን ያካተተ ውይይት አድርጓል፡፡
በውይይቱ ላይ በ1952 ዓ.ም. ከወጡት አምስት የንግድ ሕግ መጻሕፍት ውስጥ በሦስቱ የንግድ ሕግ መጽሐፎች ላይ ስለተደረገው ማሻሻያና ማብራሪያ የሰጡት፣ በፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ጥናት፣ ማርቀቅና ማጠቃለል ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ በላይሁን ይርጋ ማሻሻያ ያልተደረገባቸው ቀሪዎቹ ሁለት መጻሕፍት የፋይናስ ሕግ ሆነው ራሳቸውን ችለው እንዲወጡ መታሰቡን አስረድተዋል፡፡
እነዚህ ሁለት የፋይናንስ ሕግ መጻሕፍት የማሻሻል ሒደት መጀመሩን ያስረዱት አቶ ይርጋ፣ ለዚሀም ሲባል ከባንኮችና ከመንግሥት የተወጣጡ የባለሙያዎች ቡድን መዋቀሩን አስረድተዋል፡፡ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ባለሙያዎች ለማስመጣት ጥያቄ ቀርቦ ንግግር እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ ይርጋ ማብራሪያ የፋይናንስ ሕጉን ማሻሻል ያስፈለገበት አንደኛው ምክንያት መንግሥት ዘርፉን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት የማድረግ ሐሳብ ስላለው ነው፡፡
ከ15 ዓመታት በፊት የፋይናንስ ዘርፉ ሊበራላይዜሽ ሒደትን በተመለከተ ጥናት ማድረጋቸውን ያስታወሱት ሌላው የመድረኩ አቅራቢና ጉምቱ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ዓለማየሁ ገዳ (ፕ/ር)፣ በጊዜው ሒደቱ ትክክለኛው መንገድ ላይ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰው እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ከ15 ዓመታት በኋላ ሒደቱ በታሰበው ልክ ባለመሄዱ የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ ለውጭ ገበያ ክፍት ለማድረግ የሚያስችል ምንም ዓይነት ሁኔታ አለመኖሩንና ይባሱኑ ለፋይናንስ ቀውስ የሚዳርግ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡
እንደ ዓለማየሁ (ፕ/ር) ገለጻ፣ የኢትዮጵያ ባንኮች አይደለም ከዓለም አቀፍ ባንኮች፣ በቀጣናው ካሉት ባንኮች በተለይ ከኬንያ ባንኮች ጋር የሚወዳደሩበት አቅም የላቸውም፡፡ የፋይናንስ ዘርፉን የመክፈት ሒደት ውስጥ ብዙዎቹ የገቡ ታዳጊ አገሮች የፋይናንስ ቀውስን ማስተናገዳቸውን የሚያስረዱት ዓለማየሁ (ፕ/ር)፣ ሒደቱን ቀስ በቀስና በተለያየ ደረጃ እየከፈቱ የሄዱት የእስያ አገሮች በአንፃሩ የአገር ውስጥ ባንኮቻቸውን ከመዋጥ ማዳናቸውን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ይኼ ሒደት ባለፉት ዓመታት ውስጥ መካሄድ እንደነበረበት ተናግረው፣ ይኼ ሳይደረግ አሁን ላይ ለውሳኔ መቻኮሉ ጥፋቱ እንደሚበዛ አስረድተዋል፡፡ ከዚህም በላይ በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ውስጥ የፋይናንስ ዘርፉን ተቆጣጣሪ የሆነው ብሔራዊ ባንክ አቅሙን ባለማዳበሩ ዘርፉ ክፍት ቢሆን፣ ዘርፉን መቆጣጠር የሚችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡
ዓለማየሁ (ፕ/ር) እንደሚያስረዱት፣ ይኼንን ጉዳይ በተመለከተ አሁን ላይ ትልቁ ሥጋት በኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋት መኖሩ ነው፡፡ የዋጋ ግሽበቱ 35 በመቶ መድረሱን፣ የብር የመግዛት አቅም በፍጥነት እየተዳከመ መሆኑ፣ ከፍተኛ የሆነ የወጪና ገቢ ንግድ ክፍተት መኖሩና የበጀት ክፍተት ያለ መሆኑን አንስተዋል፡፡ እነዚህ ችግሮች ሳይፈቱ የሚደረግ የፋይናንሻል ሊበራላይዜሽን መቶ በመቶ ቀውስ ውስጥ እንደሚከሰት ተናግረዋል፡፡
ዘርፉን ለእነዚህ ችግሮች ክፍት ማድረግ ያለውን አደጋ አስምረው የተናገሩት ዓለማየሁ (ፕ/ር)፣ እነዚህን ችግሮች ፈቶ ዘርፉን ክፍት ለማድረግ ፍኖተ ካርታ መቀረፅ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ፍኖተ ካርተው መቀረፅ ያለበት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ የግል ባንኮችና ብሔራዊ ባንክ አንድ ላይ የፋይናንስ ዘርፍ ግብረ ኃይል በማቋቋም መሆን እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
ግብረ ኃይሉ ፍኖተ ካርታውን ሲያዘጋጅ ተጨማሪ 20 ዓመታት መጠየቅ እንደሌለበት የሚናገሩት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፣ በሦስትና አራት ዓመታት ውስጥ የሚፈጸም ዕቅድ መንደፍ እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡ በዚህም መንግሥት ማክሮ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት የሚሠራውን ሥራ፣ ብሔራዊ ባንኩ የቁጥጥር አቅሙን ለማዳበር የሚፈጽማቸውን ተግባራት፣ እንዲሁም ባንኮች ራሳቸውን ለማጠናከር የሚወስዷቸውን ዕርምጃዎች ዘርዝረው ማስቀመጥ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡ በዚህም መሠረት ዘርፉን ለመክፈት በየዓመቱ የሚወሰዱ ተግባራት ላይ መተማመን መፍጠር እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
በመድረኩ ላይ ሌላው የመነሻ ጽሑፍ አቅራቢ የነበሩት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሥራ ኃላፊና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ አባል ኢዮብ ተስፋዬ (ዶ/ር)፣ ግብረ ኃይል ማቋቋምን ጨምሮ በዓለማየሁ (ፕ/ር) የተነሱ ሐሳቦችን ሙሉ ለሙሉ እንደሚቀበሉ ተናግረው፣ የግብረ ኃይሉ እንቅስቃሴና ሥራ ግልጽ መሆን እንዳለበትም ጭምር ገልጸዋል፡፡