Wednesday, March 29, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ከግጭት አዙሪት ውስጥ አለመውጣት የታሪክ ተጠያቂ ያደርጋል!

አገር በሕግ፣ በመርህና በዜጎቿ ስምምነት መመራት ሲያቅታት የውጭ ኃይሎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መጫወቻ እንደሚያደርጓት የታወቀ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን መብቶቻቸውን እያስከበሩ ግዴታቸውን መወጣት የሚችሉት፣ አገራቸው በሕግና በሥርዓት እንድትመራ የማድረግ የጋራ ስምምነት ሲኖራቸው ነው፡፡ ፖለቲከኞች ዋነኛ ግባቸው ሥልጣን መጨበጥ ቢሆንም፣ ሥልጣኑን የሚያገኙበት መንገድ ግን ሕጋዊ እንዲሆን ከማንም በበለጠ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለያዩ የሙያ መስኮች የተሰማሩ ዜጎች አገራቸው ወደፊት እንድትራመድ ማድረግ የሚችሉት፣ በኢትዮጵያ ምድር የሕግ የበላይነት ሲሰፍን ብቻ መሆኑን መረዳት አለባቸው፡፡ የሲቪል ማኅበረሰቦች፣ የሙያና የጥቅም ማኅበራት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ ተቋማትና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችም ለሕግ የበላይነት ልዩ ሥፍራ መስጠት አለባቸው፡፡ አገር የሚመራው መንግሥት ደግሞ ከማንም በተለየ ሁኔታ ሕግ የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ሉዓላዊት አገር ሆና በዓለም አቀፍ መድረክ የምትከበረው፣ ሕግና ሥርዓት ሰፍኖ በሰላም ሲኖርባት ብቻ ነው፡፡ ከውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ነፃ መሆን የሚቻላት፣ ኢትዮጵያውያን በሕግ የበላይነት ሥር መተዳደር ሲችሉ ነው፡፡ ለሕግና ለሥርዓት ትኩረት ባለመሰጠቱ ግን ከግጭት አዙሪት ውስጥ መውጣት አልተቻለም፡፡

አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ሊጣሉ የታቀዱ አደገኛ የማዕቀብ ረቂቅ ሕጎች ያዘጋጀችው፣ ኢትዮጵያውያን ውስጣዊ ጉዳያቸውን በወጉ መከወን አቅቷቸው እርስ በርስ በመባላታቸው ነው፡፡ በኮንግረስና በሴኔት በተለያዩ የመዝገብ ቁጥሮች የቀረቡት ረቂቅ ሕጎች፣ ኢትዮጵያን በአደገኛ ሁኔታ ለመቅጣት የተዘጋጁ በርካታ አደገኛ ማዕቀቦችን መያዛቸው ይታወቃል፡፡ ሰሞኑን ለአሜሪካ ምክር ቤቶች የቀረቡት የማዕቀብ ረቂቆች ከመፅደቅ እንዲዘገዩ መወሰኑ ተሰምቷል፡፡ ረቂቅ ሕጎቹ ከሁለቱ ምክር ቤቶች እስኪወገዱ ድረስ ትግል መደረግ አለበት እያሉ የሚወተውቱ ሲኖሩ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ የተለየ አቋም የሚያራምዱ እንዳሉ በግልጽ እየታየ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ላይ በሚጣሉ ማዕቀቦች ከማንም በላይ የሚጎዱት፣ ወትሮም ቢሆን ከመከራ መላቀቅ ያልቻለውን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን በፖለቲከኞችና በተለያዩ አካላት መካከል የሚስተዋለው ውዝግብ፣ ይህንን አደጋ በውል መገንዘብ የቻለ አይመስልም፡፡ የአገሪቱ ፖለቲካ አሠላለፍ በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሠረተ ባለመሆኑ፣ እያንዳንዱን ድርጊት ከግላዊና ከቡድናዊ ጥቅም አኳያ ብቻ እየተቃኘ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ልዩነትን እያባባሰ አገር እያደማ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ሁኔታ መቀጠል አትችልም፡፡

ኢትዮጵያ እየገባችበት ያለው ፈተና ሊወገድ ወይም ጫናው ሊቀንስ የሚችለው፣ በሀቅ ላይ የተመሠረተ ንግግር ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ለዚህም እውነተኛ፣ ኃላፊነት የሚሰማቸውና አንድነትን ለማጠናከር የሚያግዙ ዜጎች ወደፊት መውጣት አለባቸው፡፡ በአገር ጉዳይ የሚደረጉ ንግግሮች በሥርዓት ተመርተው ውጤት ሊገኝ የሚችለው፣ ከሴረኝነትና ከመሰሪነት የተላቀቀ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ሲኖር ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አስፈላጊ ጉዳይ በመጥፋቱ ኢትዮጵያውያን በችግሮቻቸው ላይ ከመነጋገር ይልቅ፣ ጠመንጃ አንስተው እርስ በርስ በመጫረሳቸው ነው ኢትዮጵያ በታሪኳ ላይ ጠባሳ እየተፈጠረ ያለው፡፡ ሌላው ቀርቶ በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች አስከትሏል ተብሎ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ውግዘትና ወቀሳ እያሰነዘረ ነው፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎ የዘር ፍጅት ተካሂዷል የሚሉ ጩኸቶችም ይሰማሉ፡፡ በአገር በቀል ባህላዊ ዘዴዎች ግጭትን መከላከል የሚያስችል ትልቅ እሴት ባለባት ኢትዮጵያ፣ ለመስማት የሚዘገንኑ ሰቆቃዎች ተፈጽመዋል፡፡ ከዚህ አደገኛ ማጥ ውስጥ በፍጥነት መውጣት ያስፈልጋል፡፡

ብዙ ጊዜ ስለአገር የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት በሰፊው ሲነገር ይሰማል፡፡ ይህ ጥልቅ የሆነ ጽንሰ ሐሳብ በውስጡ በርካታ ነገሮችን አጭቆ ይዟል፡፡ ከእነዚህ ነገሮች አንዱ ውስጣዊ አንድነትን ከሚሸረሽሩ ድርጊቶች መቆጠብ ነው፡፡ ይህም በሥልጣን ላይ ካለው መንግሥት ጀምሮ እያንዳንዱን ዜጋ ይመለከታል፡፡ መንግሥት የአገርን ብሔራዊ አንድነትና ጥቅም ከማስከበር በተጨማሪ የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ ግዴታው ሲሆን፣ ይህንን ኃላፊነቱን ለመወጣት ደግሞ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል፡፡ በዚህ ኃላፊነቱ እያንዳንዱ ሥራው ለሕዝብ ግልጽ መሆንና ተጠያቂነት ይኖርበታል፡፡ በኢትዮጵያውያን መካከል ልዩነት ሳይፈጠር በእኩልነት የሚኖሩበት ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት ማነፅ አለበት፡፡ እያንዳንዱ እንቅስቃሴው የአገርንና የሕዝብን ጥቅም እንዳይጎዳ ጥንቃቄ ማድረግም እንዲሁ፡፡ በዚህ መሠረት ሥራውን እያከናወነ ለመሆኑ ሕግ አውጪው ፓርላማ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ሲኖርበት፣ ሕግ ተርጓሚው አካል ደግሞ ፍትሕ እንዲሰፍን የሚፈለግበትን ኃላፊነት መወጣት አለበት፡፡ እያንዳንዱ ዜጋም ሕግ እያከበረ ግዴታውን ሲወጣ፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹ መከበራቸውን ያረጋግጣል፡፡ በኢትዮጵያ ምድር እነዚህ ተግባራት ሊከናወኑ ባለመቻላቸው ምክንያት ቅራኔ እየተፈጠረ፣ የውጭ ጣልቃ ገብነቶች እየተበራከቱ ናቸው፡፡

እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ኢትዮጵያ ውስጥ እንኳንስ በጭካኔ ደም የሚያፋስሱ ቅራኔዎች ሊኖሩ ቀርቶ፣ ከዕለት ኩርፊያ የሚዘሉ ጠቦች እንዲፈጠሩ የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታ የለም፡፡ ነገር ግን አገርና ሕዝብ ንቀው ለሥልጣናቸውና ለጥቅማቸው ብቻ የሚራኮቱ ከንቱዎች ናቸው የበዙት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሆነ የተለያዩ ማንነቶች፣ እምነቶች፣ ባህሎች፣ ቋንቋዎችና የመሳሰሉ ልዩነቶቹን እንደ ጌጥ ተጠቅሞ ሲጋባና ሲዋለድ ነው የሚታወቀው፡፡ በኢትዮጵያ አራቱም ማዕዘናት ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚታወቁት ዘመን ተሻጋሪ በሆኑ የጋራ ማኅበራዊ እሴቶቻቸው እንጂ፣ የዘመኑ ነፍሰ በላ ፖለቲከኞች እንደሚያስቡት እርስ በርስ ለመገዳደል የሚፈላለጉ ሆነው አይደለም፡፡ ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ የሚታወቁት በከፍተኛ ፍቅር ለአገራቸው በአንድነት ተሠልፈው መስዋዕት ሲሆኑ እንጂ፣ አገራቸውን ለታሪካዊ ጠላቶች አሳልፈው ሲሰጡ አይደለም፡፡ እነ ዶጋሊ፣ ጉንደት፣ ሰሃጢ፣ መተማ፣ ዓድዋ፣ ማይጨው፣ ካራማራና የመሳሰሉት ህልቆ መሳፍርት የሌላቸው ዓውደ ግንባሮች ይመሰክራሉ፡፡ በዚህ ዘመን ግን አገርና ሕዝብን ከሥልጣን ምኞታቸው በታች ያደረጉ መሰሪዎች፣ በታሪክ የሚያስወቅስና የሚያስወግዝ ደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ ገብተው መከራ ያሳጭዳሉ፡፡ ለውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነትም አገርን ያመቻቻሉ፡፡

አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ትልቅ ትኩረት የሚያስፈልገው ጉዳይ በሕግና በሥርዓት መመራት ነው፡፡ መንግሥትን የሚመራው ብልፅግና ፓርቲ ውስጥ የሚታየው ውስጣዊ ሽኩቻ መላ ካልተፈለገለት፣ ራሱን ብቻ ሳይሆን አገርን ይዞ የመጥፋት ዕምቅ ኃይል አለው፡፡ በተለይ የአማራና የኦሮሚያ ብልፅግና ቅርንጫፎች እያሳዩት ያለው አደገኛ አዝማሚያ፣ ፓርቲውን ከመበተን አልፈው ለአገሪቱም ጦስ እንደሚያስከትል መታወቅ አለበት፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ ከተካሄደው አደገኛ ጦርነት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ሳይወጣ፣ የብልፅግና ፓርቲ ውስጣዊ ዲሲፕሊን መበላሸት የከፋ መዘዝ እንደሚያስከትል መተማመን ያስፈልጋል፡፡ ራሱን በሕግ መግራት ያልቻለ ገዥ ፓርቲ አገር መምራት አይቻለውም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለ ኃጢያቱ ከሚቀጣባቸው በደሎች መካከል ለከት ያጣው የኑሮ ውድነት፣ ግጭትና ውድመት፣ እንዲሁም በሕግና በሥርዓት አለመመራት ይጠቀሳሉ፡፡ ሕዝቡ ባገኛቸው አጋጣሚዎች ሁሉ መንግሥትን በችግሮቹ ላይ ለማሳሰብ ጥረት ቢያደርግም አዳማጭ እያገኘ አይደለም፡፡ በግጭት ውስጥ መኖር ታክቶታል፡፡ ከግጭት አዙሪት ውስጥ አለመውጣት የታሪክ ተጠያቂ ያደርጋል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

በኦሮሚያ ክልል በስድስት ከተሞች የተዋቀረውን ሸገር ከተማን የማደራጀት ሥራ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ስድስት ከተሞች የተዋቀረው ሸገር ከተማን...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

 የክልሎች ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በመከላከያ ሠራዊት ተጠባባቂ ኃይል እንዲካተቱ ጥናት እየተደረገ ነው

የክልሎችን ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በአገር መከላከያ ሠራዊት ተጠባባቂ ኃይል...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...

አይ የእኛ ነገር!

የዛሬው ጉዞ ከጀሞ ወደ ፒያሳ ነው፡፡ መንገዱ ለሥራ በሚጣደፉ፣...

የዓለም ኢኮኖሚ መናጋት ለወቅታዊው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ነው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባለፈው ማክሰኞ መጋቢት 16...

የተዘነጋው የከተሞች ሥራ የመፍጠር ተልዕኮ

በንጉሥ ወዳጅነው አሁን አሁን የአገራችን የሥራ ዕድል ፈጠራ ጉዳይ አንገብጋቢና...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሰላም ዕጦትና የኑሮ ውድነት አሁንም የአገር ፈተና ናቸው!

ማክሰኞ መጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በርካታ ጥያቄዎች አቅርበዋል፡፡ ጥያቄዎቹ በአመዛኙ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠኑ...

ግልጽነትና ተጠያቂነት የጎደለው አሠራር ለአገር አይበጅም!

ሰሞኑን የአሜሪካና የኢትዮጵያ መንግሥታት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የጦር ወንጀሎች መግለጫ ላይ አልተግባቡም፡፡ አለመግባባታቸው የሚጠበቅ በመሆኑ ሊደንቅ አይገባም፡፡ ነገር ግን...

የምግብ ችግር ድህነቱን ይበልጥ እያባባሰው ነው!

በአገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ ተቋማት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከ22 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣...