ከሥራ መቀነስና መቋራጥ ጋር ተያይዞ አደጋ ላይ የወደቀው ሠራተኛ ተጨማሪ ችግር ሆኖ የተጋረጠበትን የኑሮ ውድነት ችግር አስመልክቶ፣ መንግሥት አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጥ ተጠየቀ፡፡
ጥያቄው የቀረበው የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ)፣ በ48ኛ መደበኛ ስብሰባው በተለይ እየተባባሰ በመጣው የኑሮ ውድነት፣ በሠራተኛው ላይ እያሳደረ የመጣውን ጫና በተመለከተ ባደረገው ውይይት ማጠቃለያ ላይ፣ የኢሠማኮ ጠቅላይ ምክር ቤቱ ባወጣው የአቋም መግለጫ ነው፡፡
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተው ጦርነትና የእርስ በእርስ ግጭት፣ በቅርቡም የሩሲያና የዩክሬይን ጦርነት የዓለም የሸቀጣ ሸቀጦችንና የግንባታ ዕቃዎችን በማናሩ፣ የዜጎች ኑሮ ሁኔታ ከድጡ ወደ ማጡ መውረዱን ያስታወቀው ኮንፌዴሬሽኑ፣ በዚህ የተረበሸ ገበያ ምክንያት በተፈጠረው የኑሮ ውድነት ከሁሉም በላይ ዝቅተኛ ገቢ ያለው ሠራተኛ ላይ ጫናው በርትቷል ብሏል፡፡
በገበያው አለመረጋጋት ሰበብ እየተንሰራፋ ያለው የኑሮ ውድነት በዝቅተኛ ደመወዝ ኑሮውን ከእጅ ወደ አፍ እየመራ ባለው ሠራተኛ ላይ የፈጠረው ጫና ከአቅም በላይ በመሆኑ፣ መንግሥት ለችግሩ ልዩ ትኩረትና አስቸኳይ መፍትሔ በመስጠት፣ የሠራተኛው ኑሮ እንዲስተካከል የሚያግዙ ዕርምጃዎች እንዲወሰዱ ኢሠማኮ በጥብቅ አሳስቧል፡፡
የኢሠማኮ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በመድረኩ እንደተናገሩት፣ ‹‹ወቅታዊው የኑሮ ውድነት ከወር እስከ ወር ደመወዙን ጠብቆ በሚኖረው ሠራተኛ ላይ እያደረሰ ያለው ችግር የሚነገር አይደለም፤›› ብለዋል፡፡
የጦርነት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተነሱት ግጭቶች፣ እንዲሁም የሩሲያና የዩክሬኑ ግጭት የኑሮ ውድነቱ አባባሽ ምክንያቶች እንደሆኑ ያስታወሱት አቶ ካሳሁን፣ ይህ ባለበት ሁኔታ የሠራተኛው ከሥራ ገበታው መቀነሱ፣ እንዲሁም መቋረጥ ሌላ ችግር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የገንዘብ ዋጋ እያደረ እያሽቆለቆለ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሆነው የኑሮ ውድነት በብዛት ሠራተኛው ላይ ይህ ነው የማይባል ጫና እያሳደረ እንደሚገኝ፣ በውይይቱ ላይ ሐሳባቸውን የሰጡ የኮንፌዴሬሽኑ አባላት አስረድተዋል፡፡
የምግብ ፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ መናር ብቻም ሳይሆን፣ ሠራተኛው የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት የሚሄድባቸው ተቋማትና የመድኃኒት ዋጋ ከአቅም በላይ በመሆኑ ሳቢያ ሕይወቱን እያጣ የሚገኘው ሠራተኛ በምንም ይሙት በምን ‹‹በኮቪድ ሞተ›› የሚል ተቀፅላ ምክንያት እንደሚሰጠው አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል፡፡
ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ጫና ለኑሮ ውድነቱ አንዱ ምክንያት መሆኑ የማይካድ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ የትም ሳይኬድ በየጊዜው መጋዘን ውስጥ ያለ አንድ ሸቀጥ ዋጋው የሚጨምረው በስግብግብ ነጋዴዎችና በተባባሪ ባለሥልጣናት አማካይነት እንደሆነ የሚገልጽ ሐሳብ በውይይቱ ላይ ተሰንዝሯል፡፡
መንግሥት ከሰሞኑ ያደረገው ውይይት ያለውን ችግር ከኅብረተሰቡ አፍ ለመስማት ካልሆነ በስተቀር ችግሩ ጠፍቶት አይመስለንም ያሉት የውይይቱ ተሳታፊዎች፣ በተለይም ከሁሉም በላይ ተጎጂ የሆነው ሠራተኛ በሚገኝበት የተለያየ አደረጃጀት በዝቅተኛ ዋጋ አስፈላጊ የሆነ ግብዓት የሚያገኝበትና የሚሸምትበት ሁኔታ መፈጠር መቻል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ኢሠማኮ ባወጣው የአቋም መግለጫ እንዳመላከተው፣ የሠራተኛው አንኳር ችግር እንደተጠበቀ ሆኖ በተለይም በከተሞች ያለው የኑሮ ውድነት እንዲባባስ ካደረጉት ነገሮች አንዱ የሆነው የመኖሪያ ቤት እጥረት ነው፡፡ እነዚህ ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙት የጋራ መኖሪያ ቤቶች በፍጥነት ተጠናቀው ለዜጎች እንዲተላላፉ ያሳሰበው ኢሠማኮ፣ ዜጎች ገንዘብና ጉልበታቸውን አቀናጅተው በማቅረብ ችግሩን ለመቅረፍ እንዲችሉ መንግሥት የጀመረውን ጥረት እንዲያጠናክር ጠይቋል፡፡
በሌላ በኩል ኮንፌዴሬሽኑ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሠራተኛ በልቶ ማደር እንዲችሉ መነሻ ደመወዝ የሚወስን የደመወዝ ቦርድ እንዲቋቋም በአሠሪና በሠራተኛ አዋጅ ድንጋጌ ላይ መንግሥትም ሆነ የአሠሪና ሠራተኛ ተወካዮች ተወያይተው አጠናቀው፣ አዲስ ለተቋቋመው የሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲላከ አስታውሶ፣ ይህንን ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል የሚመለከት ደንብ መንግሥት እንዲያፀድቅ አበክሮ ጠይቋል፡፡