የክልሎችን የድጎማ በጀት የሚቆጣጠር ኮሚሽን እንዲቋቋም እንቅስቃሴ መጀመሩን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ።
ክልሎች ከፌዴራል መንግሥት የሚያገኙትን የድጎማ በጀት የሚቆጣጠረው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የበጀት ክፍፍሉ ራሱን በቻለ ተቋም እንዲመራ በጥናት የተደገፈ እንቅስቃሴ መጀመሩን፣ በፌደሬሽን ምክር ቤት የፊስካል ጉዳዮችና የክልሎች የተመጣጠነ ዕድገት ጥናት ዳይሬክተር ዋቅቶሌ ዳዲ (ረዳት ፕሮፌሰር) ለሪፖርተር ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ ለክልሎች የሚሆን የበጀት ድጎማ ሲያደርግ የቆየ መሆኑን፣ በእነዚህ ጊዜያት የተለያዩ ችግሮች ሲያጋጥሙ መቆየታቸውን አስረድተዋል፡፡ በተለይ የድጎማ በጀቱ አመዳደብና የሽግግር ሥርዓቱ የአድልኦ ችግሮች እንዳሉበት ሲወሳ እንደነበር አክለዋል፡፡
ይህንን መሠረት በማድረግም በ2013 ዓ.ም. ምክር ቤቱ በበጀት ክፍፍሉ ላይ ያሉ ችግሮችን ለመለየት የሚያስችል ጥናት ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
በፎረም ኦፍ ፌዴሬሽን የገንዘብ ድጋፍ የተደረገው ጥናት በርካታ ችግሮች የተለዩበት መሆኑን የገለጹት ዋቅቶሌ (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ በተለይም የሕዝብ ቁጥር አለመታወቁ የበጀት አመዳደቡን አስቸጋሪ ማድረጉን ያሳየ መሆኑንና ክልሎችም የፍትሐዊነት ቅሬታ እንዲያቀርቡ አድርጓል ብለዋል።
ከዚህ በፊት የነበሩ አማካሪዎች ትክክለኛ መረጃ እያቀረቡ አልነበረም ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ለዚህም ትክክለኛ የሕዝብ ቁጥርንና የክልሎችን የመሠረተ ልማት ጥያቄ መሠረት አድርጎ የድጎማ በጀቱን ለማከፋፈል አገር አቀፍ የሕዝብና ቤት ቆጠራ እስኪደረግ እንዲጠበቅ ተደርጓል ብለዋል፡፡
የክፍፍል ሥርዓቱ በፌዴሬሽን ምክር ቤት መመራቱ የፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የጥቅም ግጭት አለበት የሚል ጥያቄ አስነስቷል ብለዋል፡፡ በሀብት ክፍፍሉ የሚፈጠሩ ክፍተቶችም በክልሎች መካከል ግጭት እንዲፈጠር ምክንያት መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የሚሰጠው የድጎማ በጀት ለታለመለት ዓላማ መዋሉን የሚቆጣጠር አካል ባለመኖሩ፣ ክልሎች በተመሳሳይ ምክንያት በየዓመቱ የበጀት ጥያቄ እንደሚያቀርቡና በርካታ ሀብት እንደሚባክን ጥናቱ አመላክቷል ብለዋል፡፡
የጥናቱን ግኝቶች መሠረት በማድረግ ከየትኛውም ፖለቲካዊ ፍላጎት የፀዳና በሕዝብ የተመረጡ አባላት ያሉት ኮሚሽን መቋቋም እንዳለበት ምክር ቤቱ እንዳመነበት፣ በዚህም መሠረት ለማቋቋም እንቅስቃሴ መጀመሩን ዋቅቶሌ (ረዳት ፕሮፌሰር) ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽኑን ለማቋቋም በቀረበው ምክረ ሐሳብ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የበጀት ድጎማ ቋሚ ኮሚቴ አባላት የሆኑት የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች መስማማታቸውን አስረድተዋል፡፡ በቀጣይም የኮሚሽኑን መቋቋም ዕውን ለማድረግ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይቀርባል ብለዋል፡፡