Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየትምህርት ሚኒስትሩ የፓርላማ አባላትን ይቅርታ ጠየቁ

የትምህርት ሚኒስትሩ የፓርላማ አባላትን ይቅርታ ጠየቁ

ቀን:

የትምህርት ጥራት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን ተናግረዋል

የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የተቋማቸውን የስምንት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ሲያቀርቡ፣  ‹‹እንዲሁም ተደክማችኋል ባጠቃልል ሳይሻል አይቀርም፣ ከመተኛታችሁ በፊት…›› በማለት ባሰሙት ንግግር፣ ከአባላቱ በቀረበባቸው ቅሬታ ምክንያት ይቅርታ ጠየቁ፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ የ2014 ዓ.ም. የተቋማቸውን የስምንት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም፣ መጋቢት 29 ቀን 2014 ዓ.ም. 243 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በተገኙበት አቅርበዋል፡፡

ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) ለፓርላማው ለማቅረብ 40 ደቂቃ ያህል የወሰደው ሪፖርታቸው ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩ ያደረጉት ይህ ንግግራቸው፣ የምክር ቤቱን አባላት ቅሬታ ፈጥሮባቸው ነበር፡፡

‹‹ቀደም ሲል መድረክ ላይ ሲነሳ የነበረው ነገር መታረም አለበት፡፡ ይህ የተከበረ ምክር ቤት ነው፡፡ ስለዚህ የተከበረው ምክር ቤት እንቅልፍ ከመተኛቱ በፊት በሚል ከተከበረ ሚኒስትር የማይጠበቅ በምክር ቤቱ ላይ ተናግረዋልና ምክር ቤቱን ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው፤›› በማለት አንድ የምክር ቤት አባል ሐሳባቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ አባላቱም ሐሳባቸውን በጭብጨባ ደግፈውታል፡፡

የምክር ቤቱን ጥያቄ ተከትሎ ሚኒስትሩ ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) ‹‹በጣም ይቅርታ እጠይቃለሁ፣ እኔ ቅድም ትንሽ ዘና እንበል ለማለት ብዬ ነው እንጂ፣ ምክር ቤቱ ይተኛል ብዬ አልነበረም፡፡ ቅሬታ ያቀረቡትን የምክር ቤት አባል ስላበሳጨዎት ይቅርታ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ፕሮቶኮል በደንብ አይገባኝም፣ አይለመደኝም፤›› በማለት ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡

ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን በመጥቀስ፣ የሚስተዋለውን ውስብስብ ችግር ለመፍታት እንደ መንግሥትም ሆነ ማኅበረሰብ ከፍተኛ የሆነ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

ለአብነትም የትምህርት ጥራት መለኪያዎች መሠረት ተደርገው ባለፉት ዓመታት በተካሄዱ ጥናቶች፣ በአገሪቱ ካሉ 47 ሺሕ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በትንሹ የሚፈለገውን ስታንዳርድ የሚያሟሉት 10.8 በመቶ የሚሆኑት ብቻ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉንም ነገር የፖለቲካ ማስፈጸሚያና ትርፍ ማግኛ ተደርጎ የሚወሰደው ነገር መስተካከል አለበት ብለዋል፡፡

‹‹በርካታ የግል ኮሌጆች የዲግሪ ወፍጮ ቤቶች ሆነዋል፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ የትምህርት ሥርዓቱ መሠረታዊ የተዓማኒነት ችግር ውስጥ በመግባቱ ምክር ቤቱ ጉዳዩን እንደ ቀላል ሊያየው አይገባም ሲሉ አሳስበዋል፡፡

‹‹የትምህርት ሥርዓቱ ክፉኛ ወድቋል፡፡ እንስማማ፣ እንደ አገር እንስማማ፤›› በማለት የጠየቁት ብርሃኑ (ፕሮፌሰር)፣ ‹‹ለዚህም ይረዳ ዘንድ ፖለቲካንና ትምህርትን እንለይ፡፡ ትምህርትን ከዚህ ከአካባቢ ፉክክር እንለይ፡፡ በ30.7 ሚሊዮን ተማሪዎች ሕይወት ላይ አንፍረድ፤›› በማለት ጠይቀዋል፡፡

በእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት እየተሰጠ ነገር ግን እንግሊዝኛ ቋንቋ የሚችል መምህር አለመኖሩን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በሚያስተምሩት ትምህርት ምዘና ተሰጥቷቸው ከ50 በመቶ በላይ በማምጣት ያለፉት መምህራን 30 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ በሕግ የትምህርት መስክ የመንግሥትና የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለመውጫ ፈተና ከተቀመጡት 2,852 ተማሪዎች ውስጥ የማለፊያ ነጥቡን አምጥተው ማለፍ የቻሉት 50 በመቶ ብቻ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

ከትምህርት ጥራት ጋር አያይዘው ሲናገሩ እንደ ኅብረተሰብ አደጋ ውስጥ እየከተተ ያለ የሞራል ክስረት፣ ሥርዓቱን እያበላሸ ያለ ችግርና መጠገን ያለበት ያሉት በፈተና ወቅት የሚታይ የፈተና ስርቆት ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በ2013 ዓ.ም. በነበረው አገር አቀፍ ፈተና ወቅት ፈተና ለመስረቅ መሣሪያ ከታጠቁ ኃይሎች ጋር በነበረ ግብግብ፣ ሦስት የፌዴራል ፖሊስ አባላት ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ለአብነት አውስተዋል፡፡

የትምህርት ሥርዓቱ ከፖለቲካ ሥርዓት ጋር በመገናኘቱ ምክንያት የተወሰነ ቡድንን ለመጥቀም በሚል በየክልሉና ወረዳ የሚገኙ የመንግሥት ባለሟሎች ጭምር የተሳተፉበት የፈተና ስርቆት መኖሩን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

በ2014 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን በጦርነትና በድርቅ ምክንያት 5.2 ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውን፣ እንዲሁም በአፋርና በአማራ ክልሎች ከ3.2 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከሁለት እስከ ስድስት ወራት ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነው እንደቆዩ ተናግረዋል፡፡

በግጭት ክስተቶች ሳቢያ በአማራ 1,086፣ አፋር 65፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ 55፣ በኦሮሚያ 165፣ በደቡብ ክልል 22 በድምሩ 1,393 ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ሲወድሙ፣ በተመሳሳይ በአማራ 3,082፣ በአፋር 415፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ 335፣ በኦሮሚያ 919፣ በደቡብ 131 በድምሩ 4,882 ትምህርት ቤቶች በከፊል ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በትግራይ ክልል ባሉ ትምህርት ቤቶች ሲያስተምሩ የነበሩ መምህራን አዲስ አባባ መጥተው ምደባ ከጠየቁት ውስጥ በጊዜያዊነት በሌሎች አካባቢዎች ለመመደብ ከክልሎች ጋር ውይይት ቢደረግም፣ ማስተናገድ እንዳልተቻለ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታው ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ በትግራይ ክልል ባሉ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ሲያስተምሩ የነበሩ ከ1,600 በላይ መምህራን በጊዜያዊነት በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተመደቡ መሆናቸውን፣ በተመሳሳይ በዚሁ ክልል በተመሳሳይ ከ22 ሺሕ በላይ ተማሪዎች በሌሎች ዩኒቨርሰቲዎች ምደባ እንደተደረገላቸው አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...