Thursday, February 29, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ሰዎች የቢትኮይን ተጠቃሚ መሆናቸው በጥናት ታውቋል›› አቶ ዮናስ ማሞ፣ በፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት የፋይናንስ ወንጀሎች ትንተና ኃላፊ

የሰው ልጅ ቁስን በቁስ ከመለዋወጥ ወይም ከመገበያየት አንስቶ በወረቀት የብር ኖቶች፣ ቼኮች፣ ካርዶችና የኤሌክትሮኒክስ ገንዘቦች የሚገበያይበት ጊዜ ላይ ደርሷል፡፡ አሁን አሁን ደግሞ በዓለም ላይ ከዚህ ቀደም ከነበሩ የመገበያያ የገንዘብ ዓይነቶች በአማራጭነቱ የተለየና እንደ ባለሙያዎች አጠራር ከቁጥጥር አኳያ ሥውር የሆነ፣ ነገር ግን በዓለም ከጫፍ እስከ ጫፍ እየተዳረሰ የሚገኝ የቨርቹዋል ገንዘብ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ነው፡፡ ለመሆኑ የዚህ የቨርቹዋል ገንዘብ (ክሪፕቶ ከረንሲ) ሥርጭት ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ይመስላል? በሕጋዊነቱ ላይ የሚነሱ ብዥታዎች እንዴት ይታያሉ? ከፋይናንስ ጋር በተገናኘ ተልዕኮ የተሰጣቸው ተቋማት በዚህ ጉዳይ ላይ ምን እየሠሩ ይገኛሉ? የሚለውንና ተያያዥ ጉዳዮችን በሚመለከት ኤልያስ ተገኝ በፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት የፋይናንስ ወንጀሎች ትንተና ኃላፊ ከሆኑት አቶ ዮናስ ማሞ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- ለመነሻ እንዲሆነን የቀድሞው የፋይናንስ መረጃ ማዕከል የአሁኑ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት በተለይ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ እንዲሁም ሽብርተኝነትን በገንዘብ ከመደገፍ ጋር ተያይዞ የተመለከተውን ኃላፊነት እንዴት እየተወጣ ነው?

አቶ ዮናስ፡- የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት በዋናነት ሦስት ነገሮች ላይ ትኩረት አድርጎ ይሠራል፡፡ የመጀመሪያው በሕገወጥ መንገድ የሚገኝን ማንኛውንም ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ መጠቀም (Money Laundering) ይቆጣጠራል፡፡ በአዋጅ ቁጥር 780/2005 መሠረት አብዛኞቹ ወንጀሎች ‹‹መኒ ላውንደሪንግ›› በሚባለው ላይ ያመዘኑ ናቸው፡፡ ወንጀሎች ‹‹መኒ ላውንደሪንግ›› ናቸው ለማለት ሁለት መሥፈርቶች ሊሟሉ ግድ ይላል፡፡ ብቻውን ‹‹መኒ ላውንደሪንግ›› የሚባል ወንጀል ስለሌለ ድርጊቱ ገንዘብ ማመንጨት አለበት፣ ወይም ግዴታ ከኋላው አንድ ወንጀል መኖር አለበት፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ጉዳዩ በወንጀለኛ ሕግ መሠረት ከአንድ ዓመት በላይ የሚያስቀጣ ወንጀል መሆን አለበት፡፡ ይህንን ካነሳን ሙስና፣ የሰው ዝውውርና ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር አብዛኞቹ ወንጀሎች መኒ ላውንደሪንግ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ጉዳዮች የተገኘውን ገንዘብ ሕጋዊ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ወንጀሉን የሚገልጽ ይሆናል፡፡ ይህም ሲሆን ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን ገንዘቦች ወደ ባንክ አካውንት ማስገባት፣ ዕቃዎች መግዛት፣ ሪል ስቴት ማበልፀግና መግዛት፣ ወይም ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ሄዶ አክሲዮን መግዛት፣ ይህ ሁሉ ሒደት ‹‹መኒ ላውንደሪንግ›› ተብሎ ይጠራል፡፡ ሁለተኛው ሽብርተኝንትን በገንዘብ መርዳት ነው፡፡ ይህ ተቋም ማናቸውም ሽብርተኝንትን የተመለከቱ ጉዳዮች ይመለከተዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሽብርተኛነትን የሚመለከቱ ናቸው ተብሎ የተቀበላቸውን ዝርዝሮች ወደ እዚህ ተቋም ይልካል፡፡ ይህንን መሠረት በማድረግ ሪፖርቶችን እንልካለን፡፡ በሦስተኛነት ጅምላ ጨራሽ መሣሪያ ብዜትን በገንዘብ መርዳት ነው፡፡ በጠቅላላው ከላይ በተጠቀሱት ሦስቱ ወንጀሎች ላይ እንሠራለን፡፡ ከሰሜኑ ክፍል ሕግ የማስከበር ዘመቻ ጋር ተያይዞ ሽብርተኝንትን በገንዘብ መርዳትን፣ ከአገር ውስጥ እስከ ውጭ ያለው የገንዘብ እንቅስቃሴ፣ ለጦርነቱ የሚሆኑ ገንዘቦች፣ አሁንም በተለያዩ አካባቢዎች የሚደረጉ የሽብር እንቅስቃሴዎችን ለመከላለከል ተቋሙ በተሰጠው ወሰን መሠረት እየሠራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ወቅት ከሽብር ወንጀል ጋር ተያይዞ በአገር ውስጥም ሆነ ድንበር ዘለል የሆነ እንቅስቃሴ የተንሰራፋበት ነው፡፡ በተለይም የፋይናንስ ዘርፉ ጭንቅ ውስጥ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ይህን ፈተና አስመልክቶ ተቋሙ ምን እየሠራ እንደሚገኝ፣ አያይዘውም  የወንጀሉን ስርፀት  ቢያስረዱን?

አቶ ዮናስ፡- እንደተባለው ጊዜው በጣም ከባድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የምትገኝበት ጂኦፖለቲክስ፣ የዓለም የፖለቲካ ሁኔታ፣ እንዲሁም ሌሎች የሽብር ወንጀሎች በየቦታው ይገኛሉ፡፡ ከጎረቤት አገር ከሚገኘው አልሸባብ የሽብርተኛ ቡድን አንስቶ፣ የሱዳንም ፖለቲካ ተደምሮ ቀጣናው የሽብርተኛ ቡድኖች መንቀሳቀሻነቱ ሳይረሳ አገሪቱ ካለችበት ሁኔታዎች ጋር ተዳምሮ ያለውን እንቅስቃሴ ማንሳት ይቻላል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ለሽብርተኛ ቡድኖች የጦር መሣሪያዎች በመግዛት የሚደረግላቸው ድጋፍ ሲኖር፣ ይህን ለማድረግ የሚቻለው ደግሞ በገንዘብ ኃይል ነው፡፡ ገንዘብ የሁሉም ወንጀሎች በተለይም የሽብር ወንጀል ደም ነው፡፡ ገንዘብ ከሌለ የሽብር ወንጀልን መፈጸም አዳጋች ነው፡፡ በመሆኑም ገንዘብን መከታተልና መቆጣጠር የዚህ ተቋም ኃላፊነት ነው፡፡ ታዲያ ተቋሙ ይህንን ሲያከናውን በአገር ውስጥ ብቻ የተመለከተውን ሥራ ብቻ አይደለም የሚሠራው ‹‹ኢግመንት›› የሚባል ዓለም አቀፋዊ ተቋም አባል ስለሆነ፣ ከ164 በላይ አገሮች የፋይናንስ ተቋማት ጋር መረጃ የመቀያየር ወይም የማግኘት ሥልጣኑን የሚጠቀም ነው፡፡ እያንዳንዱ የገንዘብ ዝውውር (ትራንዛክሽን) በቀላሉ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በመተጋዝ ሥረ መሠረቱን በመርመርና በመለየት ለሚመለከተው አካል እየተሠራጨ ይገኛል፡፡ ይህም ሽብርተኝትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀሉ ከመፈጸሙ በፊት ገንዘቡን ማገድና ትንተና ሠርቶ ግለሰቦቹ እንዲያዙ ማድረግ የሚያስችለንን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ላይ እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- ለፋይናስ ተቋማት ከዘርፉና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ሥልጠናዎችን እንደምትሰጧቸው ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ የቨርቹዋል ገንዘብን የተመለከቱ ሥልጠናዎችን ከሰሞኑም ሰጥታችኋል፡፡ ይህ የመገበያያ አማራጭ ይፋዊ ባልሆነ መንገድ በኢትዮጵያ ውስጥ አገልግሎት እየዋለ ይገኛል የሚሉ መረጃዎች ይሰማሉ፡፡ ከጉዳዩ ምንነት አንስቶ በዚህ ወቅት በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ቢነግሩን?

አቶ ዮናስ፡- ከጥቂት ሳምንታት በፊት አገር ውስጥ አሉ የሚባሉ ትልልቅ የምርመራ ክፍል ኃላፊዎችን፣ ኮሚሽነሮችን፣ የአዲስ አበባና የፌዴራል ፖሊስ ከፍተኛ ኃላፊዎችን ጨምሮ ሥልጠና ሰጥተናቸው ነበር፡፡ የኢትዮጵያን የገንዘብ ታሪክ ስንመለከት ዕቃን በዕቃ ከመገበያየት አንስቶ እስከ አሞሌ ጨው፣ ከዚያ ቀጥሎም ማርትሬዛ እያለ በ1945 ዓ.ም. ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የወረቀት ብር ለማስተዋወቅ በቅታ ነበር፡፡ አብዛኛው ዓለም ደግሞ ‹‹ፊያት›› የሚባለው ሁሉም አገሮች የሚገበያዩበት ዕውቅና የተሰጠው ገንዘብ አለው፡፡ ስለዚህ እስካለንበት ጊዜ ድረስ ሁሉም አገር ተቀብሎት የሚገበያይበት ገንዘብ አለ፡፡ አሜሪካ ዶላር፣ ቻይና ዩአን፣ ኤርትራ ናቅፋ የሚባል ገንዘብ አላቸው፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ብር የሚባል የመገበያያ ኖት አላት፡፡ ነገር ግን እ.ኤ.አ. ከ2008 ጀምሮ ዓለም ቨርቹዋል ወይም ክሪፕቶ ከረንሲ የሚባል ‹‹የዲጂታል ገንዘብ ነው›› ብለው ሰዎች የሚስማሙበት ገንዘብ መጥቷል፡፡ ቨርቹዋል ከረንሲ ማለት ሰዎች በዲጂታል መገበያያ ገንዘብ በማድረግ እንደ ወረቀት ገንዘብ የሚያገለግል ነው ብለው የሚያምኑበት፣ የማይዳሰስና የማይጨበጥ በኮምፒዩተር ወይም በስልክ ውስጥ የሚገኝ የሚቀበሉት ምልክት ነው፡፡

የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በዚሀ ወቅት ዓለም እየተገበያዩበት የሚገኘውን ገንዘብ ‹‹ፊያት ከረንሲ›› ብለው የሚጠሩት ሲሆን፣ የቨርቹዋል ገንዘብ ሰው ሊይዘውና በቦርሳው ሊያንቀሳቅሰው የማይችል፣ ግብይት ሲፈጸምበት የማይታይ፣ ልውውጡን ለማድረግ ኔትወርክ የሚያስፈልገው፣ ግብይቱ ሲፈጸም ከምልክት ጋር የሚያያዝ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ክሪፕቶ ከረንሲ ቃሉ የግሪክ ሲሆን ክሪፕቶ የተመሰጠረ ማለት ነው፡፡ ሙሉ የቃሉ ትርጉም ሚስጥራዊ የሆነ የመገበያያ ገንዘብ ማለት ነው፡፡ ሳቶሽ ኮሞቶ የሚባል የጃፓን ስያሜ ባለው ግለሰብ አማካይነት ለዓለም የተዋወቀው ይህ መገበያያ (ቢትኮይን)፣ እ.ኤ.አ. በ2008 ተወጥኖ በ2009 ወደ ሥራ የገባ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ በዓለም ላይ ከ1,300 በላይ የቨርቹዋል ከረንሲ የመጣ ሲሆን፣ በመጀመሪያ እንዴት የዚህ ዓይነት መገበያያ ይኖራል በሚል ተቀባይነት እምብዛም ያላገኘ፣ ቀስ በቀስ እ.ኤ.አ. ከ2014 እስከ 2020 ባለው ጊዜ ቁጥሩ ከ1,000 ሺሕ በላይ ያሻቀበ መገበያያ ነው፡፡ በዚህ ወቅት በርካታ የቨርቹዋል ከረንሲ አቅራቢ ድርጅቶች (Virtual Asset Provider) መጥተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ባላችሁ መረጃ መሠረት ኢትዮጵያ ውስጥ የትኛው የቨርቹዋል ገንዘብ ዓይነት ነው የሚንቀሳቀሰው?

አቶ ዮናስ፡- ከኢትዮጵያ አኳያ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራበትና ክትትሎች የሚደረግበት የመጀመሪያውን ክሪፕቶ ከረንሲ ዓይነት ቢትኮይን ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ክሪፕቶ ከረንሲ የራሱ የሆነ መገለጫዎች ያሉት ሲሆን፣ የመጀመሪያው ‹‹ዲሴንትራላይዝድ›› (ማዕከላዊ ያልሆነ) ስለሆነ ማንም ሰው አይቆጣጠረውም፡፡ በዓለም የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ ባንኮች የራሳቸው የሆነ ‹‹ሴንትራላይዝድ›› (ማዕከላዊ) የሆነ ዳታ ቤዝ አላቸው፡፡ ቨርቹዋል ከረንሲ ዲሴንትራላይዝድ ስለሆነ በተለያዩ ኮምፒዩተሮች ላይ ተበታትኖ ይገኛል፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ የግብይት እንቅስቃሴ በተለያዩ ኮምፒዩተሮች ላይ በተመሳሳይ መረጃ ተበትኖ ይገኛል፡፡ ሁለተኛ የመገበያያው አጠቃላይ አቅርቦት 21 ሚሊዮን ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያም ሆነች አሜሪካ ገንዘብ ሲያጥራቸው ገንዘብ ያትማሉ፣ ገደብ የለውም፡፡ ነገር ግን ሳቶሺ ኮሞቶ የቢትኮይን ፕሮቶኮል ላይ እንደተገለጸው፣ አጠቃላይ የመገበያያው መጠን 21 ሚሊዮን ብቻ ነው፡፡ ለግለሰቦች ተሸጦ ደግሞ  የሚያልቀው 2140 መጠን ድረስ ነው፡፡ ይህ የቢትኮይን መጠን በተለያየ መንገድ ለግለሰቦች እንዲደርስ ይደረግና እሱ ብቻ እየተንቀሳቀሰ በዲጂታል መንገድ እንዲቀጥል ይሆናል፡፡ ዓላማቸውም መንግሥት የማይቆጣጠረው፣ ግለሰቦች ወይም ማንም የማይታወቅ ሰው የመሠረተውና የሚመራው ማድረግ ነው፡፡ አከፋፈቱ ላይ ግለሰቦች ራሳቸውን ኮምፒዩተር ወይም ላፕቶፕ ተጠቅመው የሚከፍቱት ነው፡፡ በተለምዶ በባንኮች ሥርዓት ውስጥ የሚገኘውንና ኬዋይሲ (ኖዊንግ ዩር ከስተመር) በሚባል ዓለም አቀፍ አሠራር የሚገኘውን እያንዳንዱ ባንክ ገንዘብ የሚያንቀሳቅስለትን ደንበኛ መረጃ የሚሞላው ፎርም ይገኛል፡፡ ወደ ክሪፕቶ ሲመጣ ግን በኢንተርኔት አማካይነት የሚከፈት ስለሆነ ማንም ተቆጣጣሪ አካል የለውም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያህል ይህን የመገበያያ ዓይነት ይዞ የሚገኝ ሰው አለ? ቢባል፣ በብሔራዊ ባንክም ሆነ በሌሎች አካላት መረጃው የለም፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ መገበያያ መንግሥት የማይቆጣጠረው፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ  ውስጥ ከትልልቅ ሆቴሎች አንስቶ በተለያዩ ቦታዎች በተናጠልና በህቡዕ የሚንቀሳቀሱ አካላት ጥቅም ላይ እያዋሉት እንደሚገኙ ይገለጻል፡፡ ክሪፕቶ ከረንሲን (ቢትኮይን) በኢትዮጵያ ውስጥ አገልግሎት ላይ መዋሉ ወንጀል ነው ወይ? ወንጀልስ የሚያስብለው ነገር ምንድነው?

አቶ ዮናስ፡- ይህንን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት አንድ ኢትዮጵያዊ እንዴት ክሪፕቶ ከረንሲ ወይም ቢት ኮይን ማግኘት ይችላል የሚለውን እንመልከት፡፡ የመጀመሪያው ኦንላይን ላይ ቢትኮይን ከሚሸጡ ሰዎች ወይም ኩባንያዎች ላይ አንድ ግለሰብ ወይም ኢትዮጵያዊ ሊያገኝና ሊገዛ ይችላል፡፡ ሁለተኛው አገልግሎት መስጠት ሲሆን፣ ይህም አገልግሎት በሚሰጥባቸው ትልልቅ ሱፐርማርኬቶች፣ አስጎብኚ ድርጅቶች፣ መኪና መሸጫዎች ይህንን አገልግሎት መሰጠት ቢጀመር ከዚያ ተቋም ሊያገኝ የሚችልበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ‹‹ማይኒንግ›› የሚባለው መንገድ ወይም ደረጃ ሲሆን፣ የባንክን ሥራ ተክቶ መንግሥት የማይቆጣጠረውና ግለሰቦች የሚቆጣጠሩት የፋይናንስ ሥርዓት ማድረግ ነው፡፡ በሌላ መንገድ ማይኒንግ ማለት አክሲዮን የሚሸጥ ደርጅት ነው፡፡ እያንዳንዱ በቢትኮይን የሚፈጸም ግብይት (ትራንዛክሽን) የሒሳብ መዝገብ ላይ ለመመዝገብ ትልልቅ ኮምፒዩተሮች (ሱፐር ኮምፒዩተሮች) ያስፈልጋሉ፡፡ ይኼ ደግሞ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎትን ይጠይቃል፣ የተለያዩ ሰርቨሮች ያስፈልጋሉ፡፡ ይህንን ማድረግ በጣም ውድ ስለሆነ እንደ ሩሲያ፣ አሜሪካ፣ አንድ አሁን ያላስታወስኩት ሌላ ተጨማሪ አገር የአክሲዮን ድርሻ ይሸጣሉ፡፡ ያንን ኢትዮጵያዊም ሆነ ሌላ ዜጋ በመግዛት ማይኒንጉን (ማባዣውን) ይገዛል፡፡ ማይኒንጉ ትራንዛክሽን ለመመዝገብና ለማረጋገጥ፣ እንዲሁም ቢትኮይን እየተወደደና እየቀነሰ ሲመጣ ለመመዝገብ የሚቻልበት ነው፡፡ የቢትኮይን ማምረቻ መሣሪያ የኤሌክትሪክ ፍጆታው ከፍተኛ ስለሆነ ወጪውም ከፍተኛ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ በየትኛው መንገድ ነው ታዲያ እየተሠራበት ያለው?

አቶ ዮናስ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ማይን ለማድረግ፣ ከሌሎች ኦንላይን ገበያዎችም ሆነ ሼር የሚገዛበትም አጋጣሚ እንዳለ፣ መቀመጫቸውን ሌላ አገር ያደረጉ ድርጅቶች  ኢትዮጵያ ውስጥ ቅርንጫፍ እንዳላቸው መረጃው አለ፡፡ እነዚህ ቡድኖችም ሆኑ ግለሰቦች ግብይቱን የሚያድርጉት በውጭ አገሮች ገንዘብ ስለሆነ፣ በሌላ መንገድ ከሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ጋር ይገናኛል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከላይ በተጠቀሱት ሦስት አማራጮች አንድ ሰው ቢትኮይን ሊያገኝ ይችላል፡፡  ይህ የግብይት ዓይነት ኢትዮጵያ ውስጥ ለአደጋ የተጋለጠ ነው፡፡ ከተቋሙ ሥራና ኃላፊነት አንፃር ሼሩን ለመግዛት፣ ለመሸጥና ማይን ለማድረግ አንድ ኢትዮጵያዊ ቀጥታ ገንዘብ ልኮ የሚገዛበት መንገድ ወይም አማራጭ ስለሌለ፣ ቀጥታ የመግዣውን መንገድ ማድረግ የሚችለው ገንዘቡን በሕገወጥ መንገድ በውጭ አገር ማሰባሰብ፣ እንዲሁም ወደ አገር ወስጥ የሚመጣውን የውጭ ምንዛሪ እዚያው እንዲቀር ማድረግ ይሆናል፡፡ ስለዚህ በወንጀል የተገኘ ገንዘብ የሚንቀሳቀስበት አጋጣሚ ስላለ ጉዳዩ አሳሳቢ ነው፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በዓመት 72 ቢሊዮን ዶላር የሚሆኑ የቢትኮይን ግብይቶች ለሕገወጥ ግብይት ይውላሉ፡፡ በአጠቃላይ በቢትኮይን ከሚደረገው ግብይት ወይም ትራንዛክሽን 44 በመቶ የሚሆነው ለአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር፣ ሽብርተኝነትን በገንዘብ ለመርዳት፣ ለሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርና ለሌሎች ወንጀሎች ጥቅም ላይ ነው የሚውለው፡፡ ይህን የሚያደርጉ ግለሰቦችን ማንነት ማወቅ አይቻልም፡፡ ራሳቸው ከፍተው ኦፕሬት ስለሚያድርጉት ለወንጀል ተጋላጭ ነው፣ በሳይበርም የሚደረግ ነው፡፡ እነዚህን ግለሰቦች የመዘገባቸው፣ ሪፖርት የሚቀበላቸውና የሚቆጣጠራቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሌለ ማን ምን እያደረገ እንደሆነ አይታወቅም፡፡ በዚህም ገንዘብ ለማሸሽ፣ ከአገር ለማስወጣት ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ በሌላ በኩል በሙስና፣ እንዲሁም በተለያየ መንገድ የተገኘ ገንዘብ ሽብርተኝትን ለመደገፍ እንደሚውል ይታወቃል፡፡ በአንዳንድ ዘገባዎች ላይ ሲገለጽ ሰምታችሁ ከሆነ፣ የአልሸባብ ሽብር ቡድን ክንፍ የሆነ አካል ክፍያን በቢትኮይን  ከማድረጉ ጋር የተያያዙ ዘገባዎች ወጥተዋል፡፡ ሰሜን ኮሪያም ለኒዩክሌር ማበልፀጊያ የሚሆን ገንዘብን በቢት ኮይን ክፍያ አድርጋ ከሌሎች አገሮች ጋር እንደምትገበያይ ታውቋል፡፡ እጅግ በጣም ትልልቅ ወንጀሎች የሚፈጸሙበት የግብይት ሥርዓት ስለሆነ ብሔራዊ ባንክም፣ ገንዘብ ሚኒስቴርም፣ እንዲሁም የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት የማይቆጣጠሩት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከላይ ካነሱት አንፃር የኢትዮጵያ ተጋላጭነት ምን ይመስላል? ከሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርና ለሽብርተኝነት ተጋላጭ ከመሆኗ አኳያ መንግሥትም ሆነ የእናንተም መሥሪያ ቤት ምን እየሠራ ነው?

አቶ ዮናስ፡- በተቋም ደረጃ የሌሎች አገሮችን ብንወስድ ለምሳሌ ጣሊያን፣ ኖርዌይ፣ ስዊድን፣ ሜክሲኮ፣ ጃፓን፣ አሜሪካና ዩናይትድ ኪንግደምን የመሳሰሉ አገሮች የተለያዩ የአሠራር ማዕቀፎችን አውጥተው መቆጣጠርና ማጥፋት ባይችሉም፣ ፈጽሞ ማጥፋቱ አስቸጋሪ ስለሆነ ባወጡት ማዕቀፍ መሠረት የቨርቹዋል አሴት አገልግሎት አቅራቢዎችን የመቆጣጠርና በእነርሱ ላይ ሕግ የማውጣት አሠራር አላቸው፡፡ ሕጋዊ ያደረጉ አገሮችም ይገኛሉ፡፡ አውስትራሊያና ካናዳ በዚህ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ወንጀል ነው ብለው የከለከሉ አገሮችም አሉ፡፡ ስለዚህ ከዚህ ግብይት ጋር ተያይዞ በዓለም ላይ ሦስት ዓይነት አተያዮች ሲኖሩ፣ እነዚህም ሕጋዊ ያደረጉ አገሮች አሉ፣ አንዳንዶቹ ይቆጣጠሩታል፣ አንዳንዶቹ ድግሞ ወንጀል አድርገው ከልክለዋል፡፡ ነገር ግን ይህን መገበያያ ሕግ አውጥቶ በክሪፕቶ ከረንሲ ነው የምገበያየው ብሎ የሚንቀሳቀስ አገር ግን የለም፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ሁኔታ አምጥተን ስናየው በዓለም ላይ የሚደርሰው ተጋላጭነት ሁሉ ይደርስባታል፡፡ 72 በሊዮን ዶላር ሕጋዊ ያልሆነ እንቅስቃሴ ወይም ዝውውር የሚንቀሳቀስበት ከሆነ፣ አንድ አገር ብቻ ተለይቶ የሚቀር አይሆንም፡፡ ቢትኮይን ከአጠቃላይ ግብይቱ 44 በመቶ የሚሆነው ለሕገወጥ እንቅስቃሴ ነው የሚውለው፡፡ በኢትዮጵያ ክሪፕቶ ከረንሲን በተለይም ቢትኮይንን የምንከታተልበት፣ ሪፖርት የምናደርግበት፣ ለአደጋ ተጋላጭነታችንን የምንለይበት፣ ራሱን የቻለ አቅራቢዎቹንም ሆነ መገበያያውን በተናጠል አንስቶ የሚፈቅድም ሆነ የሚከለክል ሕግ የለንም፡፡ ነገር ግን እንደ ፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት በቨርቹዋል መገበያያ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ምን ይመስላል የሚለውን በተመለከተ ጥናት ተደርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- በጥናቱ ምን ተገኘ?

አቶ ዮናስ፡- አንዳንድ ግለሰቦች በልበ ሙሉነት ሚዲያ ላይ ጭምር ቀርበው ቢትኮይን የሀብታቸው ምንጭ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በመንግሥት ሚዲያዎች ቀርበው በክልል ዋና ዋና ከተሞች ‹‹ሀብታም የሚያደርግ መንገድ›› እየተባለ ግለሰቦች ሀብታቸውን መንግሥት ወደ የማይቆጣጠረው ቨርቹዋል ገንዘብ እንዲቀይሩ ፕሮሞት የሚደረግበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ በትልልቅ ሆቴሎች በየሳምንቱና በየቀኑ የተለያዩ ዓውደ ጥናቶች የሚደረጉበት፣ ወደ እዚህ ቢዝነስ የሚገቡ አዳዲስ ሰዎች የሚመለምሉበት አሠራር ተዘርግቶ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ ቢትኮይንን ለማስፋፋት መጠነ ሰፊ እንቅስቀሴ እየተደረገ ይገኛል፡፡ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ምርመራ የጀመረባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ለአብነትም አንድ ግለሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢትኮይን እየሸጠ ከ15 ሺሕ በላይ ግለሰቦች የቢትኮይን ዋጋ ይጨምራል ብሎ ገንዘቦችን እንደሚቀበል መረጃ ያለ ሲሆን፣ ይህንን በጋራ ለመሥራት ዕቅድ ተይዟል፡፡ የቢትኮይን ማምረቻ ወደ አገር ውስጥ ሊገባ ሲል እንደተያዘም መረጃ ተገኝቷል፡፡

ሪፖርተር፡- መገበያያው በኢትዮጵያ በሕግ ስለመከልከሉ ማረጋገጫው ምንድነው?

አቶ ዮናስ፡- በብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት የኢትዮጵያ ሕጋዊ የመገበያያ ገንዘብ ብሎ ያስቀመጠው ብር ነው፡፡ የብር ሥራን ተክተው የሚሠሩ አገልግሎቶች ሊንቀሳቀሱ የሚችሉት ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ሲሰጣቸው ብቻ ነው፡፡ በሌላ በኩል የብሔራዊ የክፍያ ሥርዓት አዋጅ 718/2011 ቢትኮይንን የማይዳስስ በማለት ያላካተተ ሲሆን፣ ይህ ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ መሥራት እንደሚችል ፈቃድ የሰጠ አይደለም፡፡ ሕጉ ስለዲጂታል ክፍያ የሚያትት ቢሆንም፣ ነገር ግን ዲጂታል ክፍያ ውስጥም ቨርቹዋል ገንዘብ ወይም ቢትኮይንን ያካተተ ወይም ለእሱ ፈቃድ የሰጠ አይደለም፡፡ ሌላው የብሔራዊ ባንክ አዋጅ የሆነው 591/2008 በተመሳሳይ የአገሪቱ የመገበያያ ገንዘብ ብር እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ ከብር ውጭ ሌሎች ዕውቅና ያላቸው ነገሮች ወደ ብር ተቀይረው ሕጋዊነት አግኝተው እንደሚሠሩ ነው የሚደነግገው፡፡ የባንክ ቢዝነስ አዋጅ 1159/2019 በተመሳሳይ የዲጂታል ፋይናንስ አግልግሎት አቅራቢዎች ለሆኑ የፋይናንስ ተቋማት ዕውቅና ሰጥቷል፣ ቢትኮይንን ግን ዕውቅና አልሰጠውም፡፡ ስለዚህ በእኛ አገር ባሉ ሕጎች በሙሉ ቢትኮይን ሕጋዊነቱን የሚያሳይ ማስረጃ የለም፡፡ ሕጋዊነቱን የሚያሳይ ማስረጃ ብቻም ሳይሆን፣ ሕገወጥ ድርጊት ነው ብሎ ወይም ቢትኮይንን አስመልክቶ የተዘጋጀ ሕግ የለም፡፡

ሪፖርተር፡- ታዲያ ሕግ ሊበጅለት አይገባም?

አቶ ዮናስ፡-  ከላይ እንደገለጽኩት ‹‹ፋይናንሺያል አክሽን ታስክ ፎርስ›› የሚባል ዓለም አቀፍ ሁሉንም የፋይናንስ ደኅንነት ተቋሞች በበላይነት የሚመራ ተቋም የሚያዘጋጀው ምክረ ሐሳብ አለ፡፡ በዚያ ምክረ ሐሳብ መሠረት ይህ ቨርቹዋል መገበያያ በተለይም ቢትኮይን በሕገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ መጠቀም፣ ሽብርተኝትን በገንዘብ መርዳት፣ የጅምላ ጨራሽ መሣሪያ ብዜትን በገንዘብ መርዳትና ለመሳሰሉ ጉዳዮች ሁሉ አደጋው ይህ ቨርቹዋል መገበያያ በተለይም ቢትኮይን ነው ብሎ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ አገሮች ቢትኮይንን ወይም ሌሎች የቨርቹዋል መገበያያዎችን በመጠቀም የሚፈጸሙ ወንጀሎችን አደጋቸውን ማጥናት አለባቸው፡፡ ለዚያም እኩል የሆነ የመከላከያ መንገድ ማዘጋጀት እንዳለባቸው ተቋሙ ያዛል፡፡ ይኼንን መሠረት በማድረግ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ባለፈው ዓመት ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ ከኢንሳ፣ እንዲሁም ጣና ኮፐን ሃገን ከተባለ የውጭ ድርጅት ጭምር የተሳተፉበት ጥናት ተካሂዷል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ  የቢትኮይን እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስል ጥናት ተደርጓል፡፡ በተገኘው ውጤትም ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ሰዎች የቢትኮይን ተጠቃሚ እንደሆኑ፣ እነዚህ ሰዎች በከተሞችና በክልሎች እንደሚንቀሳቀሱ፣ የተለያዩ የዩቲዩብ ቻናሎችን ከፍተው ሰዎች ገንዘባቸውን እዚያ እንዲያስቀምጡ የሚያስተዋውቁና ሚዲያዎችን በመጠቀም ማስታወቂያ እንደሚሠሩ የተገኘው ውጤት ያሳያል፡፡ በኢትዮጵያ ሁኔታ ሲታይ ሽብርተኝትን በገንዘብ መደገፍ፣ በሕገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ለመጠቀም ተጋላጭ መሆናችን የተለየበት የጥናት ጽሑፍ አለ፡፡ ይህ የጥናት ጽሑፍ በጣም በተሻለ መንገድ ተጠንቶ ሕጎች መውጣት አለባቸው ብለን እናምናለን፡፡ ዓምና የተገኘውን ጥናት መሠረት በማድረግ በዚህ ዓመት ከዚያ የተሻለ ዓለም አቀፍ ልምዶችን የጨመረ፣ ከዚያም ሕጎችን ያካተተ ጥናት እንዲሠራ ከላይ ከተጠቀሱት ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሥራት ላይ እንገኛለን፡፡ ጎን ለጎን የግንዛቤ መስጫ ሥራውም የዚህ አንዱ አካል ነው፡፡ የተለያዩ አገሮች ተሞክሮን በማየት ለእኛ አገር የሚመጥነውን ሕግ በብሔራዊ ባንክ በኩል እንዲወጣና አደጋውን በማሳየት የበኩላችንን ጥረት እያደረግን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ጉዳይ እየተስፋፋበት ካለው ፍጥነት አኳያ በኢትዮጵያ እየተሠራ ያለው ሥራ ምን ያህል የፈጠነ ነው? ጥናቱስ ምን ይላል?

አቶ ዮናስ፡- እውነት ለመናገር መገበያያው በጣም በቅርብ ጊዜ ለዓለም ገበያ የቀረበ ነው፡፡ የዛሬ 12 ዓመት ገደማ ወደ ገበያ ከገባበት ጊዜ አንስቶ በዓለም ላይ እየተስፋፋ ቢመጣም፣ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ የሚመለከታቸውን አካላት በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ጉዳዩን የተመለከተ ሕግ ያስፈልጋል ሲባል ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ችግር ለመለየትም በግለሰብ አካውንት፣ በትራንዛክሽን ዳራ፣ ስልክን በመፈተሽ፣ ዌብ ሳይትን በመቆጣጠር የሚደረግ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ራሱን የቻለ ችግር ነው፡፡ የግብይት መንገዱ እንዳለ እንጂ፣ በምን ያህል መጠን እንዳለ፣ ምን ያህል ሰው የቢትኮይን እንዳለው፣ ለመለየት አይደለም፡፡ እንኳን ኢትዮጵያን በቴክኖሎጂ የበለፀጉ አገሮችን የፈተነ ነው፡፡ ዘግይተናል ለማለት ባይቻልም፣ በዚህ ወቅት ግን ካለፈው ዓመት አንስቶ የተደረጉትን ጥናቶች መሠረት በማድረግ ተጨማሪ ጥናቶችን በማድረግ በስፋት በጉዳዩ ላይ መሠራት እንዳለበት፣ እሱን ብቻ የተመለከተ የሕግ ማዕቀፍ ሊዘጋጅ እንደሚገባ፣ ይህም ሲሆን የግብይት ዓይነቱን መከልከል ነው? ቁጥጥር ማድረግ ነው? ወይስ ሕጋዊ አድርገን እንቀበል? የሚለውና ሌሎች የብሔራዊ ባንክ አስተዋፅኦን መሠረት አድርጎ የሚመለሱ ይሆናሉ፡፡

ሕገወጥ የገንዘብ ዝወውር እንዲህ በቀላሉ የሚፈታ ችግር አይደለም፡፡ ምንጩን ማድረቅ እስካልተቻለ ድረስ በየመንገዱ በማሳደድ የሚፈታ አይደለም፡፡ ብሔራዊ መታወቂያ አለመኖሩ በራሱ ግለሰቦች በሕገወጥ መንገድ መታወቂያ አውጥተው እንዲንቀሳቀሱ ያደርጋቸዋል፡፡ በተጨማሪም በፋይናንስ ተቋማት አንዳንድ ሙያቸውን የማይጠብቁ ግለሰቦችና የባንክ ባለሙያዎች ለዚህ ወንጀል የሙያ ድጋፍ ሲደርጉ ይስተዋላል፡፡ አንዳንድ የሕግ ክፍተቶችም እንዳሉ ሳይዘነጋ፣ እነዚህ ጉዳዮች ከተቀነሱ ድርጊቱን መቀነስ ይቻላል፡፡ በተጨማሪም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት ያለ መሥራታቸው ችግር የሚፈጥረውን ክፍተት መድፈን ከተቻለ፣ ብሔራዊ መታወቂያ አገልግሎት ላይ ከዋለ፣ የሚጣረሱትን ሕጎች በተለይም በብሔራዊ ባንክና በገቢዎች ሚኒስቴር አካባቢ ያሉ ሕጎች ከተስተካከሉ ወይም ከተሻሻሉ፣ የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ ገብተው ከሕግ ያፈነገጠ ሥራን በተለይም ባንክ ውስጥ ተሰግስገው የውጭ አገሮችን ገንዘብ ሌላ ጥቅም ላይ የሚያውሉ፣ ከሕገወጥ የዶላር አዘዋዋሪዎች ጋር የሚሠሩ ሰዎችን ነቅሶ ማውጣት ከተቻለ የሚቀንስበት ዕድል ይኖራል፡፡ በተለይም ባንኮች አካባቢ ከሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሰዎች ትንተና በመሥራት ለሕግ እንዲቀርቡ በማድረግ ረገድ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የዋጋ ንረቱን ለማርገብ የተተገበረው የገንዘብ ፖሊሲ ውጤታማ ነው ለማለት ያስቸግራል›› አቶ አሰግድ ገብረመድህን፣ የፋይናንስ ባለሙያና አማካሪ

የዓለም ኢኮኖሚ በተለያዩ ተግዳሮቶች እየተፈተነ ነው፡፡ በተለይ የዋጋ ንረት መጠኑ ይለያይ እንጂ፣ የእያንዳንዱን አገር በር አንኳኩቷል፡፡ መንግሥታት ይህንን ችግር ለማርገብ የተለያዩ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ...

‹‹በአመራሮቻችን የተነሳ የፓርቲያችን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል›› አቶ አበባው ደሳለው፣ የአብን አባልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ከተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአመዛኙ የተሻለ ሕዝባዊ ድጋፍ ያገኘ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተወዳዳሪ...

‹‹የግሉን ዘርፍ በመዋቅር መለያየት የነበሩ ችግሮችን ከማባባስ ውጪ መፍትሔ አያመጣም›› አቶ ሺበሺ ቤተማርያም፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ

አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በኢኮኖሚክስ፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲና ዕቅድ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማግኘት ለ36 ዓመታት የዘለቀ የሥራ ልምድ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በዕቅድና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ በዓለም አቀፍ...