Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሊብራላይዜሽን ማድረግ ራስን እንደማጥፋት ነው›› ዓለማየሁ ገዳ (ፕሮፌሰር) የምጣኔ ሀብት ምሁር

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዓለማየሁ ገዳ (ፕሮፌሰር) የኢትዮጵያን የምጣኔ ሀብት ዘርፍ ለብዙ ዓመታት ከተከታተሉና ሒደቱን ጠንቅቀው የሚያውቁ ጉምቱ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ናቸው፡፡ ዓለማየሁ (ፕሮፌሰር) እስካሁንም ድረስ የምርምር ሥራ ከሚሠሩበት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ባሻገር በተለያዩ የዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ጥናቶችን በመሥራትና በተለያዩ ሥራዎች ላይ ተሳትፈዋል፡፡ አሁንም ለዓለም አቀፍ ተቋማት ጥናቶችን በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ ሁለተኛ ቤቴ በሚሏት ጎረቤት አገር ኬንያን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ በተለያዩ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው አገልግለዋል፡፡ ከጉምቱው የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ዓለማየሁ ገዳ (ፕሮፌሰር) አጭር ቆይታ ያደረገው አማኑኤል ይልቃል ስለሰሞነኛው የኑሮ ውድነት ትኩሳትና ተያያዥ ጉዳዮች አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ላይ የኢትዮጵያን ሕዝብ እያማረሩ ካሉ ችግሮች ውስጥ ቀዳሚውን ድርሻ የያዘው የኑሮ ውድነት ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ በቅርቡ ባካሄደው የሕዝባዊ ውይይት ሕዝቡ በኑሮ መወደድ ምን ያህል እንደተማረረ ታይቷል፡፡ የኑሮ ውድነቱን እዚህ ደረጃ ያደረሰው ምንድነው ይላሉ?

ዓለማየሁ (ፕሮፌሰር)፡- የዋጋ ግሽበቱን ያመጡት ችግሮች አራት ናቸው፡፡ አንደኛ የእርሻ ምርታማነት ከሕዝብ ቁጥሩ አብሮ አልሄደም፡፡ ሁለተኛ በኃይለ ሥላሴ ጊዜ የነበረው ሕዝብ ብዛት በአራት እጥፍ ጨምሯል፡፡ በሰብል ያለው ምርታማነት ግን አሁንም ዝቅተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ ጤፍን ብንወስድ በሔክታር 22 ወይም 23 ኩንታል ነው የምናመርተው፡፡ ይኼ ግን በሳይንስ እስከ 60 ኩንታል መድረስ ይችላል፡፡ ስንዴን ብትመለከት እስከ 30 ገደማ መሰለኝ የሚያመርተው እሱም እስከ 60 ሊሄድ ይችላል፡፡ ሁሉም ምርታማነት ከግማሽ በታች ነው፡፡ በኃይለ ሥላሴ ጊዜ 30 ሚሊዮን ሕዝብ የነበረው አሁን ወደ 120 ሚሊዮን ሲደስር ያረስነው መሬት ግን ከዘጠኝ በመቶ ወደ 12 በመቶ  ብቻ ነው ያደገው፡፡ ሦስት በመቶ ብቻ ማለት ነው የጨመርነው፡፡ ስለዚህ ላለፉት 30 እና 40 ዓመታት እርሻ ላይ ስላልሠራን አልተቻለም፡፡  ለዚህ ነው መዋቅራዊ ችግር ነው የምንለው፡፡

ሁለተኛው ምክንያት ይኼ መንግሥት ላለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታትና ያለፈው ኢሕዴግም ብሩን አርክሰውታል፡፡ በየቦታው ስጮህ ነበረ፣ አታርክሱት እያልኩኝ፡፡ የዋጋ ንረት ይመጣል እያልን ይኼው መጣ፡፡ እነሱ ኤክስፖርቱን ይጨምርልናል ኢምፖርቱን ይቀንስልናል ለዚህ ነው የምናረገው ነው ያሉት ሳይሳካ የዋጋ ንረቱን እዚህ ደረሰ፡፡ ሁለተኛው የመንግሥት ስህተት ነው፡፡ ሦስተኛው ችግር ብር ማተም ነው፡፡ የበፊቱ ኢሕአዴግ በጣም ነበር ብር የሚያትመው፡፡ 2000 ዓ.ም. አካባቢ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ጠቅላላ ብር 67 ቢሊዮን ዶላር ነበረ፡፡ ጠቅላላ ኪሳችን ውስጥ ባንክ ያለው ተደምሮ፡፡ በአሥር ዓመታት ውስጥ 2012 ዓ.ም. አካባቢ 870 ቢሊዮን ዶላር ሆነ፡፡ 67 ሚሊዮን የነበረው በዓመት በአማካይ 30 በመቶ አደገ፡፡ ዕድገት ተብሎ የተጠቀሰው ነገር በሙሉ በብድርና በብር ማተሙ የመጣ ነበር፡፡ ይኼንን በጊዜው ስጮህ ነበረ የሰማኝ የለም፡፡ አራተኛ ደረጃ ችግሩ ነጋዴው ነው፡፡ ነጋዴው ያልተገባና የሚዘገንን ትርፍ ያተርፋል፡፡ 100 እና 200 በመቶ ነው የሚያተርፉት፡፡ ሌላ አገር 20 በመቶ ካተረፍክ በጣም ቆንጆ ሥራ ነው፡፡ አሜሪካገር አሥር በመቶ ነው የምታተርፈው፡፡ 20 በመቶ ካተረፍክ በጣም ቆንጆ ቢዝነስ ነው፡፡ እስኪ ሽሮ ለመብላት ሂድ ጠቅላላ የሚፈጅባት 15 ብር ነው አይደል? 50 ብር ነው፡፡ አሁን 100 ገብትዋል እንዲያውም፡፡ ስለዚህ እኛ አገር ከትንሽ ነጋዴ እስከ ትልቅ ነጋዴ ድረስ 100 እና 200 በመቶ ካላተረፈ ያተረፈ አይመስለውም፡፡ ስለዚህ የዋጋ ንረቱን ለማቆም እነዚህ ችግሮች ላይ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ችግሮቹ እነዚህ ከሆኑ፣ ለእነዚህ ችግሮች መንግሥት እየወሰደ ያለው ዕርምጃ ምን ይመስላል?

ዓለማየሁ (ፕሮፌሰር)፡- መንግሥት እየወሰደ ያለው ዕርምጃ ለምሳሌ የመጀመርያ ፖሊሲዬን ሰምቶኛል ማለት ነው፡፡ እርሻው ላይ እየሠሩ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኩታ ገጠም የሚሉትና ትንንሽ መስኖዎች የሚሉት ቆንጆ ነው፡፡ ችግር ያለብኝ እኔ ምንድነው? እሳት ማጥፋት ነው የተያዘው፡፡ ዕቅድ አውጥቶ ወጣቶችን በመስኖ ሥራ ላይ ማሰማራት፡፡ በዚያውም የወጣት ሥራ አጥነት ትቀርፋለህ፡፡ የወጣት ሥራ አጥነት እስከ 25 በመቶ ደርሷል፡፡ በጣም ትልቅ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ሦስት፣ አራትና አምስት ከበለጠ ሥጋት ነው፡፡ እኛ ጋር 25 በመቶ ደርሷል፡፡ ወጣቱ ደግሞ ሥራ ካጣ ወደ ፖለቲካዊ ብጥብጥ ነው የሚሄደው፡፡ ስለዚህ ወጣቱን ይኼ ትንንሽ መስኖዎች ላይ ማሰማራት ጥሩ ነው፡፡

በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርታማነትን መጨመር አትችልም፡፡ አሁን ቅድም እንደተራገርኩት በጤፍ፣ በስንዴ፣ በገብስ የምንለውን ምርት በአንድ ጊዜ በሔክታር እጥፍ ማድረግ ይከብዳል፡፡ ማዳበሪያ ይፈልጋል፡፡ ኤክስቴንሽን ሥራ ይፈልጋል፡፡ ፀረ አረም ይፈልጋል፡፡ እነዚህ ደግሞ ዋጋቸው በዚህ ሰሞን ብቻ ሳይሆን ላለፉት አምስት ዓመታት አሥር እጥፍ ነው የጨመረው፣ ከባድ ነው፡፡

ስለዚህ ምንድነው በአጭር ጊዜ ማድረግ የምትችለው? ሁለቴ ማምረት ነው፡፡ በትንንሽ መስኖ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እዚያ ላይ ኢንቨስት አድርጎ በተለይ ወጣቶችን እንዲሠሩ ዘመናዊ ገበያ መሥራት ማለት ነው፡፡ አንዱ ይኼ ነው፡፡

ሁለተኛ የብር ምንዛሪ ተመንን ቋሚ አድርጉት ብዬ በየቦታው ተናግሬያለሁ፡፡ ዘመዶቻችን ከውጭ የሚልኩልን ሬሚታንስ በስተቀር እሱንም በሕገወጥና ከሕገወጥ ባልሆነው መሀል ያድርጉት፡፡ ትልቁ ብር ነው የሚመጣው፡፡ በዓመት አምስትና ስድስት ቢሊዮን ነው፡፡ ሌላው ትንሽ ነው፡፡ ሦስትና አራት ቢሊዮን ነው፡፡ ፈረንጆች እንኳን የሚሰጡን 1.5 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ ዋናው ሬሚታንስ ነው፡፡ ለእሱ ደግሞ ወደ ሌላ አቅጣጫ በሕገወጥ ለሚሄድ የተለየ ተመን መስጠት ነው፡፡ ለቀረው ግን ፊክስ ማድረግ ነው፡፡ ይኼ የሚታየኝ ለአንድ ዓመት ሁለት ዓመት የዋጋ ንረቱ እስኪረግብ ነው፡፡ ሦስተኛ ችግር ያልኩህ ብር ማተም አይደል? ብር ማተም ዓብይ (ዶ/ር) ከመጣ ወዲያ ቆንጆ ለውጥ አለ፡፡ በበፊቱ ኢሕአዴግ ጊዜ በ30 በመቶ ሲያድግ የነበረውን ወደ 20 በመቶ አወረዱት፡፡ ከዚያ ወደ 19 እያሉ እስከ 17 ድረስ አወረዱት፡፡ ጥሩ እየሄደ ነበር፡፡ አሁን ግን የዚህን ዓመት ስታየው ወደ 30 በመቶ ሄዷል፡፡ ወደ ኢሕአዴግ ጊዜ ተመልሷል፡፡ ስለዚህ እሱ ላይ ማመጣጠን ይፈልጋል፡፡ ዕድገት ቢያመጣም የዋጋ ንረት ያመጣል፡፡ አመጣጥነህ በባለሙያ እዚህ ጋር ብሎ መወሰን ይፈልጋል፡፡ የመጨረሻው የነጋዴዎቹ ነው፡፡ ነጋዴዎቹን ምን ማድረግ ይቻላል? አሁን ነጋዴዎቹን መቆጣጠር አይቻልም፡፡ ለምን ብትለኝ? ጠቅላላ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ቸርቻሪዎች 500 ሺሕ ገደማ በላይ ናቸው፡፡ ጅምላ ነጋዴዎች ወደ ሃያ ናቸው፡፡ ምናልባት ከላይ የሚያከፋፍሉት ሰዎች ጋ ጥብቅ ቁጥጥር ይፈልጋል፡፡ ዘይት የሚያመጣ አለ አይደለ? ከላይ ሞኖፖሊ ፓወር ያላቸውን መቆጣጠር፡፡ ወደ ታች ያሉትን ግን 500 ሺሕ ተቆጣጥረህ አትችልም፡፡

እኔ የሚታየኝ ምንድነው? እንደ መንግሥት በሁለት መንገድ ከእነሱ ጋር መወዳደር ነው፡፡ አንደኛ መንገድ ኢትፍሩትና ኢትዮ ከነማ ከተቋቋሙ አርባና ሃምሳ ዓመት ይሆናቸዋል፡፡ እነዚህ በድሮው ዋጋ እያዋረዱ ለምን ይሠራሉ? የሆነ አሪፍ አስተዳደር አላቸው ማለት ነው፡፡ ያንን ሲስተም ተጠቅመህ በየቀበሌው ወይም በየከፍተኛው መሠረታዊ ዕቃዎች በዝቅተኛ ዋጋ ማቅረብ፡፡ ገብሬውንና ኅብረት ማኅበሩን ብትችል ቀጥታ እንዲገናኝ አድርገህ በዝቅተኛ ዋጋ ማቅረብ፡፡ ለምሳሌ አሁን እሑድ የጀመሩት አሉ፡፡ እነሱን በየቀበሌው አድርገውና ገበያውን ፍጠርላቸው፡፡ ኑ ሽጡ በላቸው፡፡ ገጠር ላሉት አላስከፍላችሁም፣ ብትከፍሉም 100 ብር ነው ብለህ ሜዳውን ማዘጋጀት፡፡ በአጭር ጊዜ የሚታየኝ መፍትሔ ይኼ ነው፡፡

ሁለተኛ ከተማ ውስጥ ደግሞ ያሉት ትልልቅ ሱፐር ማርኬቶች በተለይ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚሸጡትን መንግሥት ይርዳቸው፡፡ ለምሳሌ ኪዊንስ ሱፐር ማርኬትን ውሰድ፣ በእኔ ዕይታ ኪዊንስ ሱፐር ማርኬት በጣም አሪፍ ነው፡፡ ለምን? እርሻው አለው፡፡ ኪዊንስ ሱፐር ማርኬት እርሻውን ከገበያው ጋር ካያያዘው ያዋጣል፡፡ አሁን በቅርብ ገበያው እየጨመረ ነው፡፡ በእርሻው ቢከስርም የሚያመርትበትን እዚህ ጋ ያገኘዋል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እንደ ኪዊንስ ያሉትን ቆንጆ ባለተመጣጣኝ ዋጋ የሆኑትን ሱፐር ማርኬቶችን መርጦ ቦታ ሰጥቷቸው፣ ገንዘብ ሰጥቷቸው ከእነሱ ጋር ስምምነት ማድረግ፡፡ መሠረታዊ ፍጆታዎች ላይ እኔ እሰጣችኋለው፣ ስፖንሰር አደርጋችኋለው፣ ግን መሠረታዊ ምንላቸውን ነገሮችን ጤፍ፣ ሽሮና ሽንኩርት የመሳሰሉትን በምሰጣችሁ ዋጋ ከእኔ ጋር እየተነጋገራችሁ ነው የምትሸጡት ማለት አለበት፡፡  ምክንያቱም እነዚያን በሙሉ መቆጣጠር አትችልም፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ የዘይት ዋጋ ወደ 1,000 ብር ከፍ ሲል፣ መንግሥት ችርቻሮ ገበያውን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት በማድረግ ነጋዴዎችን ወደ ሥርዓት እንደሚያስገባ ማሳሰቢያ ሰጥቶ ነበር፡፡ ይኼ ሐሳብ እንዴት ይታያል?

ዓለማየሁ (ፕሮፌሰር)፡- እኔ ጥሩ አይመስለኝ፡፡ ምክንያቱም እዚህ አገር ላይ ኢምፕሎይመንት ስታይ 69 በመቶው የሚመጣው ከሰርቪስ ዘርፍ ነው፡፡ ከተማ ውስጥ 69 በመቶ በጣም ብዙ  ነው፡፡ ይኼን ሁሉ ሰው ምን ልታደርገው ነው፡፡ ሰዉ በሰርቪስ ነው እኮ የሚተዳደረው፡፡ ሰርቪስ ስትል ብዙ ነገር ትልልቁ ድርሻ ያላቸው ኢትዮጵያ ውስጥ የጅምላና ችርቻሮ ንግድ ነው፡፡ ቀጥሎ መኪና ጥገናና ጋራዦች ናቸው፡፡ እነዚህ ናቸው ሕዝቡን ከተማ ላይ የያዙት፡፡ በዚህ የሚፈጠረውን ሥራ አጥነት ምን ልታደርገው ነው? ይኼ ሁሉ እኮ ሥራ ያጣል፡፡ ሥራ ካጣ መጨረሻ ላይ ራስህንም ይገለብጥሃል፡፡

ለዚህ አንደኛ የአገር ውስጥ ንግዱን መያዝ፡፡ ኬንያ ውስጥ ብትሄድ ለመቆጣጠር ይመቻል፡፡ ሁለት ናቸው፡፡ በጣም ታዋቂ ሱፐር ማርኬቶች፡፡ ከእነዚህን ልትደራደር ትችላለህ፡፡ እኛ አገር አትችልም፡፡ ግን ጥሩ ነገራቸው አምስት መቶ ሺሕ ቸርቻሪ ነው ያለው፣ ሥራ ፈጥረዋል፡፡ እንደነገርኩህ ይኼንን 69 በመቶ የከተማ ሥራ ዕድል ፈጣሪ ዘርፍ ከፍተህ ከውጭ የሚመጡት ቢያጠፏቸው አስበው፡፡ ሲጀመር አንተ ምርት ከሌለህ እነሱ ራሱ የሚመጡ አይመስለኝም፡፡ ምን ሊሸጡ ነው የሚመጡት? ከውጭ ዶላር ይዘውልህ መተው ለአንተ ሸጠውልህ ትርፋቸውን በምን ይዘው ይሄዳሉ? ከውጭ ዘይትና ውኃ ይዘውልህ መጡ እንበል፡፡ እነዚህ ሱፐር ማርኬቶች አተረፉ፡፡ ካተረፉ በኋላስ? በብር ነው አይደል የሚያተርፉት? ብሩን ይዘው የት ይሄዳሉ? ብሔራዊ ባንክ?  ብሐየራዊ ባንክ ሲሄዱ ዶላር ከየት ያመጣል? የሚቀይርላቸው የለውም፡፡ ምክንያቱም በየዓመቱ ስታስበው 18 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ዕቃ እንገዛለን፡፡ የምንሸጠው ግን ሦስት ቢሊዮን ነው፡፡ ከየት አምጥተህ በውጭ ምንዛሪ ትሰጣቸዋለህ?

ሪፖርተር፡- የኑሮ ውድነቱን ካመጡት አሁን የጠቀሷቸው የመንግሥት የተሳሳተ ዕርምጃ ባሻገር ከውጭ የሚመጡ ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት በነዳጅ፣ በስንዴና በሌሎች ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዲኖር አስገድደዋል፡፡

ዓለማየሁ (ፕሮፌሰር)፡- የሚገርምህ አሁን ያልከውን ሪፖርት እየሠራሁ ነበር፡፡ የምሥራቅ አፍሪካን ጠቅላላ 13 አገሮች፣ የአፍሪካ 35 በመቶ ስንዴ ከእነዚህ አገሮች ነው የሚመጣው፡፡ ቀላል ያልሆነ ችግር ነው የሚፈጥረው፡፡ እኛ ጋር ከአውሮፓ የምናስገባው ወደ 30 በመቶ ይሆናል፡፡ ከዚህ ውስጥ 16 በመቶ የሚሆነው ከዩክሬንና ከሩሲያ የሚመጣ ነው፡፡ ይኼ ስንዴን፣ ብረትንና ማዳበሪያን ያጠቃልላል፡፡ እነዚህ በሙሉ የሚወደዱ ናቸው፡፡ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ላይ እንኳን ኢምፓክት አለው፡፡ ምን ታረጋለህ ነው ጥያቄው? ዩክሬን የሱፍ ዘይት የዓለም 30 በመቶ ገደማ አቅራቢ ነች፡፡ ስለዚህ ሱፍ ይወዳዳል፡፡ ግን ሱፍ ሲወደድ ፓልሙም ይወደዳል፡፡ መተኪያ ስለሆነ፡፡ እኛ ጋር ዘይት አንድ ሺህ መግባቱ አይገርምም፡፡ ገና ብረት ይወደዳል፡፡ ፈርትላይዘር አይቀመስም፡፡ እሱ ነው የሚያስፈራኝ እኔ፡፡ አሁን የባሰ ይጨምራል፡፡ ይኼ ነገር አውሮፓ ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ በጦርነቱ የአውሮፓውያን ኑሮ እየተወደደ ነው፣ ደመወዝ ይጨምራል፣ ወጪ ይጨምራል፡፡ የማምረቻ ወጪ ይጨምራል፡፡ እኛ ደግሞ 30 በመቶውን የምናስመጣው ከአውሮፓ ነው፡፡ የሚመጣው  ሁሉ ይጨምራል፡፡

ስለዚህ ምን ታደርጋህ? ከባድ ጥያቄ ነው፡፡ በአጭር ጊዜ መመለስ አይቻልም፡፡ ግን አንድ የሚታየኝ ይኼንን ነገር ወደ ዕድል መለወጥ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ አንዳንድ አገሮች ቀውስ ሲመጣ ወደ ፀጋ ይለውጡታል፡፡ ለምሳሌ እኛ ለአፍሪካ የስንዴ ገበያ መሸጥ እንችላለን፡፡ ይቺን አሁን መንግሥት እንደ ስትራቴጂካዊ ለውጥ ቢያስብባት፣ በዚህ ምክንያት በሠፈራችን ብቻ ትልቅ ገበያ ይፈጠራል፡፡ በዓመት አፍሪካ ሦስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ስንዴ ከእነዚህ አገሮች ትገዛለች፡፡ ከሠራንበት ይኼ ዕድል ነው፡፡ አራትና አምስት ዓመት ከሠራንበት፡፡ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጀመረው ስንዴ እንደ ኤክስፖርት ታርጌት ብናደርግ ይኼ ሰፊ ገበያ ነው፡፡  አንዱ የሚታየኝ እሱ ነው፡፡ ሌላው የእነ ሩሲያ ጦርነት ለሚያመጣው ችግር የአጭር ጊዜ መፍትሔ ብዙ መሠረታዊ ዕቃዎች ዋጋቸው አንድ ዓይነት መደረግ ያለበት ይመስለኛል፡፡ መብራትና ውኃ መንካት የለብህም፡፡ ይኼ ጊዜ ይለፍ፡፡ የጦርነቱ ተፅዕኖ አለ፣ አንበጣው፣ የድርቁ ተፅዕኖ አለ፣ ኮቪድ-19 አለ፣ ይኼ ሁሉ ተጨምሮ መብራት፣ ውኃና የቤት ኪራይ ቢቻል ሌሎችንም ሽሮና ዳቦ ላይ መሠረታዊ ፍጆታዎች ላይ አንድ ዓይነት መደረግ አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ይኼ ዞሮ መንግሥት ላይ ተፅዕኖ አይፈጥርም?

ዓለማየሁ (ፕሮፌሰር)፡-   ከዚያኛው ጫና ይሻለዋል፡፡ ዋጋውን ለቆት ከሚገለበጥ ይሻለዋል፡፡ እኛ ጥሩ ስለሆንን እንጂ ሌላ አገር እኮ ግልበጣ ተጀምሯል፡፡ የእኛ ሕዝብ ቻይ ነው፡፡ ይችል፣ ይችልና አንድ ነጥብ ላይ ሲደርስ ግን ይገለብጥሃል፡፡

ሪፖርተር፡- ከሰሞኑ ስለፋይናንስ ዘርፉ ሊበራላይዜሽን በተደጋጋሚ እየተነገረ ነው፡፡ ይኼ ዓይነት የዋጋ ንረት እንዴት ይታያል?

ዓለማየሁ (ፕሮፌሰር)፡- ይኼ አሁን ያወራነው ሁኔታ በኢኮኖሚክስ ምንድነው የሚባለው? ዓብይ ኢኮኖሚው ተናግቷል (Macroeconomics Instability) ነው የሚባለው፡፡ ዓብይ ኢኮኖሚ የምንለው አሁን ያወራነው የዋጋ ንረት ነው፡፡ የምንዛሪ ተመን ያልተረጋጋ መሆኑ ዶላር ከ29 በአንድ ዓመት ውስጥ 50 ገባ፡፡ በኢምፖርትና ኤክስፖርት መካከል ያለው ክፍተት በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሊብራላይዜሽን ማድረግ ራስን እንደማጥፋት ነው፡፡

ይኼ ነገር እንዲሳካ ዓብይ ኢኮኖሚው የተረጋጋ መሆን አለበት፡፡ አለበለዚያ ቀውስ ይፈጥራል፡፡ ስለዚህ እኔ የምመክረው ግብረ ኃይል ይቋቋም፡፡ መንግሥትና ብሔራዊ ባንክ፣ ምርምር የሚሠሩ ምሁራን፣ የግል ባንክ በጋራ ሆነው ግብረ ኃይል ያቋቁሙና የአራት ዓመት ዕቅድ ያውጡ፡፡ በአራቱ ዓመት ውስጥ ይኼ ሊብራይዜሽን የተባለው ደረጃ፣ በደረጃ ማስኬድ፡፡ ‹‹ሞድ ኦፍ ፋይናንስ›› ይሉታል፡፡ አንድ የፋይናንስ ተቋም ዝም ብሎ አይመጣም፡፡ በተለያየ ሞድ ነው የሚመጣው፡፡ ሞዶቹን መለየት ከለየህ በኋላ በእያንዳንዱ ሞድ ምን ዓይነት የተቆጣጣሪ አካል አቅም ያስፈልጋል? የሚለውን ትለየዋለህ፡፡ ተቆጣጣሪና ሱፐር ቫይዘር የሆነው ብሔራዊ ባንክ ይኼንን አሁን ልክፈተው፡፡ ቀጥዬ ደግሞ ይኼንን ልክፈተው እያለ ይሄዳል፡፡ ቻይናዎች ይኼንን ነው ያደረጉት፡፡ ፋይናንሻል ሊበራላይዜሽን ላይ የተሳካላቸውም በሒደት ስላደረጉት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በተደጋጋሚ የሚነሳው ሐሳብ መንግሥት የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ክፍት በማድረግ ከገንዘብ ተቋማት የውጭ ምንዛሪን ለማግኘት ይፈልጋል የሚል ነው፡፡ አሁን ላይ ካለው የውጭ ምንዛሪ ክምችት እጥረት አንፃር መንግሥት ከዚህ የተሻለ ምን የውጭ ምንዛሪ ማግኛ መንገድ አለው?

ዓለማየሁ (ፕሮፌሰር)፡-   እሱ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ይሆናል፡፡ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ምንድነው? ከማን ጋር ስምምነት ልፍጠር? ከምዕራባውያኑ ጋር ተስማምቼ፣ እነሱ የሚሉኝን አድርጌ፣ ብር ላግኝ፣ ሌላ አማራጭ አለኝ ወይ? ከቻይናና ከቱርክ ኢኮኖሚክስ ጋር ተነጋግሬ በእነሱ መንገድ ልሂድ? ለምሳሌ ኢራን እንደዚያ ነው ያደረገችው፡፡ ከቻይና ጋር ተስማምታ በአምስት ዓመታት ውስጥ 400 ቢሊዮን ዶላር እንዲልኩ ተስማማች፡፡ እኛ ላይ እንደሚያስፈራሩን እንደ ኤችአር 6600 ዓይነት ሲያደርጉባት አንደኛ ከቻይና ጋር ስምምነት አደረገች፡፡ በአምስት ዓመታት የነዳጅ ዘርፏ ላይ ከታይላንድ ጋር ከዙሪያዋ ካሉ ጋር መነገድ ጀመረች፡፡ ከነጮቹ ተፅዕኖ ነፃ የሆነ ሥርዓት ገነባች ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እሱም አማራጭ ነው፡፡ ዝም ብለህ ቀውስ ውስጥ ከምትገባ ፋይናንሻል ዘርፉን ከከፈትክ ቀውስ ውስጥ እንደምትገባ ሳይታለም የተፈታ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ከአሜሪካ በኩል እየመጣ ያለው ማዕቀብ በእንዲህ ዓይነት መንገድ ማለፍ የሚቻል ነው?

ዓለማየሁ (ፕሮፌሰር)፡- እኔ አላውቀውም ፖለቲካዊ ጥያቄ ነው፡፡ ይኼ ፖለቲካና ስትራቴጂ ይፈልጋል፡፡ ግን ሁልጊዜ በመሪ ደረጃ መርህ መሆን ያለበት፡፡ ምሥራቅም፣ ምዕራብም ሳትል ብሔራዊ ጥቅምህን እየተመለከትህ ሁለቱን እንዴት ነው የማጣጥመው ነው የምትለው፡፡ ስለዚህ ይኼ የፋይናንሻል ዘርፍ ክርክር አይደለም፡፡ የዴቨሎፕመንት ስትራቴጂ ክርክር ነው፡፡ ለምሳሌ ነጮቹ ለምን ይኼን ያደርጋሉ? ብለህ ብታስብ በቀይ ባህር በኩል ያለውን መስመር ይፈልጋሉ፡፡ የቻይና ‹‹ቤልት ኤንድ ሮድ›› በዚህ ጋር ነው የሚያልፈው፣ እነሱን መቋቋም ይፈልጋሉ፡፡ መካከለኛው ምሥራቅ አገሮችን ለመደገፍ ይፈልጋሉ፡፡ ስለዚህ የፋይናንሻል ነገር ነጥብ ናት፡፡ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ፖለቲካል ስትራቴጂውን ዓይተህ መንገድ ማውጣት አለብህ ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በምጣኔ ሀብቱ ብዙ ችግር ውስጥ ነን፡፡ የኑሮ ውድነቱ፣ ጦርነት፣ የኮቪድ-19 ተፅዕኖና ድርቅ አለ፡፡ አሁን ደግሞ ማዕቀብ እየመጣ ነው፡፡ እዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ ለመፍትሔው የእናንተ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ድርሻ ምንድነው? በኢኮኖሚክ ካውንስሉ በኩልም?

ዓለማየሁ (ፕሮፌሰር)፡- እኔ የምችለው አሁን ከአንተ ጋር እያደረግሁ ያለሁትን ማድረግ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ካውንስል ውስጥ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት እስካሁን መሥራት አልቻልንም፡፡ እኔ እስካሁን ከካውንስሉ ያልወጣሁበት ምክንያት ለመታገል ነው፡፡ ካውንስሉ በሕግ ወጥቶ፣ በሕግ ሥርዓት ውስጥ እንዲገባ ነው፡፡ ብንችል፣ ብንችል ሕገ መንግሥቱ ውስጥ እንዲገባ ለመታገል ነው፡፡ እስካሁን ያለሁት ለዚህ ለመታገል ነው፡፡ መንግሥት ጋር ዳተኝነት አለ፡፡ እኛም ጋር ችግር ነበረብን፡፡ እስካሁን አልተቻለም፡፡ ግን ለመንግሥት ሕጉን አውጥተን ሰጥተናል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስተር ዓብይ በጎ ፈቃደኝነት ነው ካውንስሉ የተቋቋመው፡፡ ግን ከበጎ ፈቃደኝነት እንዳይሆን ማንም ቢመጣ የግድ እንዲኖር አድርገን ሕጉን አውጥተን ሰጥተናቸዋል፡፡ እሱ ከፀደቀ ስኬታማ ነኝ፣ ማማከሩን ተወውና፡፡

እኔ አሁን ያደረኩግሁ ያለሁት ይኼ መስመር እየሠራ ስላልሆነ ወደ ሚዲያው እመጣለሁ፡፡ በጋዜጠኞች በኩል እነዚህ ሰዎች እንዲሰሙ፡፡ ሕጉ እስኪወጣ እጄን አጣጥፌ አገሩ ከላዬ ላይ ከሚፈርስ በእናንተ በኩል እየሞከርኩ ነው፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች