Saturday, June 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዋሽ ኢንሹራንስ ሊያስገነባ ላቀደው አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት ባለ 30 ወለል የሕንፃ ዲዛይኖችን ለየ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ በአሁኑ ወቅት ከእህት ድርጅቱ አዋሽ ባንክ ጋር በጋራ በዋና መሥሪያ ቤትነት ከሚጠቀምበት ሕንፃ ሌላ ለብቻው ባለ 30 ፎቅ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ለመገንባት የዲዛይን መረጣ አካሄደ።

ኩባንያው ባለፈው ሐሙስ በኢሌሊ ሆቴል ይፋ እንዳደረገው አዲሱን ሕንፃ የሚገነባው በልደታ ክፍለ ከተማ በሊዝ በተረከበው 3,870.7 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ነው፡፡ ለታሰበው አዲስ ሕንፃ ባወጣው የዲዛይን ጨረታ ከተሳተፉ 22 የሥነ ሕንፃ ድርጅቶች መካከል በስድስቱ የቀረቡ ዲዛይኖችን መርጧል።

በዲዛይን መረጣው ጨረታ የመጨረሻ አሸናፊዎች ሆነው የተመረጡት ስድስቱ አማካሪ ድርጅቶችና ባለሙያዎች ኤስ ሰቨን ቢዝነስ፣ ኤምኢኤ ኮንሰልቲንግ፣ ጂዳው ኮንሰልቲንግ፣ ሀይብሬድ ኮንሰልቲንግ፣ ሲሳይ ኦምቦምሳ አርክቴክትና የማ አርክቴክት ኢንጂነሪንግ ናቸው፡፡ 

የጨረታ ሒደቱን በተመለከተ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ጉዲሳ ለገሠ እንደገለጹት፣ በውድደድሩ ለመሳተፍ ፍላጎት ያሳዩትና ሰነድ ያቀረቡት 22 ድርጅቶች ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥ 13 ድርጅቶችና ባለሙያዎች ዲዛይናቸውን አቅርበው ተወዳድረዋል፡፡ 

ለእነዚህ አሸናፊዎች እንደ ደረጃቸው 250 ሺሕ ብር እስከ 50 ሺሕ ብር ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን፣ በዕለቱ ይፋ በተደረገው ውጤት መሠረት በአንደኛ ደረጃ የተመረጠው ኤስ ሰቨን ቢዝነስ በተባለው አማካሪ ድርጅት ያቀረበው ዲዛይን ነው፡፡ 

በዕለቱ የተገለጸው አሸናፊ ዲዛይኖች ብቻ ሲሆኑ፣ ተጫራቾቹ ለማማከር አገልግሎት ያስገቡት የመወዳደሪያ ገንዘብ መጠን እንዳልተከፈተ ታውቋል፡፡ ከዚህ በኋላ ለማማከር አገልግሎት ያቀረቡት የገንዘብ መጠን ተከፍቶ የመጨረሻው አሸናፊ ይለያል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በውድድሩ መሥፈርት መሠረት በዲዛይን ሥራው የመጀመርያ ደረጃ ያገኘው አማካሪ ድርጅት ያቀረበው ዋጋ ታይቶ ተጨማሪ ድርድሮችን በማድረግ የመጨረሻው አሸናፊ ይመረጣል፡፡ ከዚህ አማካሪ ጋር የሚደረግ ድርድር የማይሳካ ከሆነ በዲዛይን መረጣው ሁለተኛ ደረጃ ካገኘው አማካሪ ጋር ወደ መደራደር ሊገባ እንደሚችልም ተጠቁሟል፡፡ 

ሁሉም ተጫራቾች 105 ሜትር ርዝማኔ ያለው የሕንፃ ዲዛይን እንዲሠሩ በቀረበላቸው የሕንፃ ቁመት መሥፈርት መሠረት፣ ሁሉም ተጫራቾች 30 ወለል በላይ የሆነ የሕንፃ ዲዛይን ሠርተው አቅርበዋል፡፡ 

የመጀመርያ ደረጃ ውጤት የተሰጠው ዲዛይንም ከምድር በታች አራት ወለሎች ያሉት ባለ 30 ፎቅ ሕንፃ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከዚህ በኋላ በሚካሄደው የፋይናንሻል ምዘና (የገንዘብ መጠን ግምግማ) እና ድርድር በማከናወን የመጨረሻው ዲዛይን ከተመረጠ በኋላ፣ የግንባታ ሥራውን ለመጀመር የሚያስችለውን የኮንትራክተር መረጣ ተካሄዶ ወደ ግንባታ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡ አሁን ላይ የግንባታ ዋጋውን በትክክል ማወቅ ባይቻልም፣ የሕንፃው ግንባታ ከሦስት ቢሊዮን ብር ያላነሰ ወጪ ሊጠይቅ እንደሚችልም ተገምቷል፡፡ 

የአዋሽ ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንዳስታወቁት፣ ኩባንያቸው ራሱን የቻለ አዲስ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ ለማካሄድ መነሳቱ የኩባያውን ኢንቨስትመንት ባለብዙ ፈርጅ ለማድረግና ለማጠናከር ታስቦ ነው፡፡

‹‹ኩባንያችን ከግል የኢንሹራንስ ኩባንዎች ግንባር ቀደም የመሪነት ሚናውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ራዕይ 2030 ትራንስፎርሜሽና የአሥር ዓመታት ስትራቴጂ ወደ ሥራ ትግበራ ገብቷል፤›› ያሉት አቶ ጉዲሳ፣ ‹‹የአዲሱ ሕንፃም ስትራቴጂው በሚተገበርበት የመጀመርያ ዓመት የአዲስ ሕንፃ ግንባታ ይጀመራል፤›› ብለዋል፡፡

ግንባታውን በቶሎ በመጀመርም በስትራቴጂው የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት እንደሚጥር አመልክተዋል፡፡

አዲሱ ሕንፃ ግንባታ ኩባንያው የደረሰበትን የዕድገት ደረጃ የሚያሳይ ጭምር ይሆናል ያሉት አቶ ጉዲሳ፣ እየጠነከረ የመጣውን ውድድር አሸንፎ ለመውጣትም አጋዥ እንደሚሆን ጠቁመዋል። የኢንሹራንስ ኩባንያው የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ከበደ ቦረና በበኩላቸው፣ ‹‹አዲሱ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ ሲታቀድ ኩባንያው ባለፉት 27 ዓመታት የዕድገትና የስኬት ጉዞ ይበልጥ የሚጠናክርበት ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ እጅግ የጠነከረ ውድድር በመጪው ጊዜ እንደሚኖር ከመቼውም ጊዜ በላይ እየታየ መሆኑን ያስታወሱት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ ‹‹ኩባንያቸው ተወዳዳሪ ሆኖ ለመዝለቅ ስትራቴጂክ የሆኑ ውሳኔዎችን መወሰን ግድ እንዳለውና የታቀደው የሕንፃ ግንባታም የዚህ አካል ነው፤›› ብለዋል፡፡

አዋሽ ኢንሺራንስ ኩባንያ በአሁኑ ሰዓት በዋና መሥሪያቤትነት የሚጠቀምበት ሕንፃ ከእህት ኩባያው ጋር በጋራ በገነባው ባለ 16 እና 18 ወለል ባለው ሕንፃ ነው፡፡

አዋሽ ኢንሹራንስ አሁን እየተጠቀመበት ካለው የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ በተጨማሪ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ አራት የሚሆኑ ሕንፃዎች አሉት፡፡ ኩባንያው በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ 27 ዓመታት የቆየ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የተፈቀደ ካፒታል 1.2 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ አጠቃላይ የሀብት መጠኑ ደግሞ 3.5 ቢሊዮን ብር እንደደረሰም ለማወቅ ተችሏል፡፡     

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች