Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በፖለቲካችን አለመስከን ኢኮኖሚያችን ሕመም ውስጥ ነው

የኢትዮጵያችን ችግር ብዙ ነው፡፡ ፖለቲካው ውስጥ የሚታየው አጭር ዕይታ የአገራችንን መከራ አብሶታል፡፡ በረዥሙ ማሰብ የተሳናቸው ወገኖች ለዚህች አገር እንቅፋት ሆነዋል፡፡ ሠፈርተኝነቱ እየጎላ መሄዱ ትልቁን ሥዕል እያደበዘዘብን ነው፡፡ ይህ አደገኛ አካሄድ አዳማጭና አስተዋይ ኖሮ አንድ ቦታ ላይ መቆም ካልቻለ ከዚህም በኋላ የምንከፍለው መከራ ሊብስ ይችላል፡፡ ብዙዎች አገር ከሚለው ዕሳቤያቸው ወጥተው አካባቢያቸውን የሙጥኝ በማለት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለእነሱም እንደማያዋጣ ማሰብ አለባቸው፡፡ ጦሱ የእነሱም እንደሚሆን አለማሰባቸው በራሱ ያሳዝናል፡፡

በፖለቲካችን ውስጥ የሚታየው ፅንፈኝነትና የተበላሸ አተያይ መልካም ጅምሮችንና ዕሳቤዎችን ሁሉ እያጠፋ መቀጠል የለበትምና ፖለቲካዊ ሕመማችን ለመፈወስ ልባችን ይከፈት፡፡ ሰብሰብ ብሎ ችግርን ለመፍታት የሚያስችሉ ዕድሎችን ገሸሽ ማድረግ አያዋጣም፡፡ የእኔ ይበልጥ ብሎ ፅንፍ የያዙ እንቅስቃሴዎች መልካም ነገር አያመጡልንም፡፡ አሁን ጫንቃችን ላይ የተከመሩ ብዙዎቹ ችግሮቻችንም የዚሁ ውጤት ነፀብራቅ ናቸው፡፡

በፖለቲካችን ውስጥ የሚታየው አደገኛ ፅንፈኝነትና የቡድንተኝነት መንፈስ የፖለቲካ ከባቢውን አልፎ አሁን ላይ ኢኮኖሚው ውስጥም ገብቶ እየረበሸ መምጣቱ ደግሞ የችግሩን ግዝፈት ያመላክታል፡፡

በአገራችን የታየው የኑሮ ውድነት፣ የዋጋ ንረትና ብልሹ የግብይት ሥርዓት የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩትም ፖለቲካ ውስጥ ያሉ የተንሸዋረሩ አመለካከቶች የፈጠሩት  ጭምር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ሕዝብን በንፅህና እንዲያገለገሉ በተለያዩ የመንግሥት የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የተቀመጡ ባለሥልጣናትም የዚሁ ችግር አካል ናቸው፡፡ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች አንፃርም ችግሮችን በሠለጠነ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ችግር ማባባስ ላይ በመጠመዳቸው ከመፍትሔ ይልቅ ብሽሽቅ ውስጥ መግባታቸው ሲደመር ለዚህች አገር መፍትሔ ከየት እንደሚመጣ ግራ ያጋባል፡፡  

አሁን ላይ ደግሞ የፖለቲካችን ሕመም ኢኮኖሚያችንንም እያሳመመ ነው፡፡ የብዙ ወገኖች ያሉበት የግብይት ሥርዓታችን የበለጠ እየተበላሸ ነው፡፡ ይህም በንግዱ ውስጥ የሚሳተፉ ጥቂት የማይባሉ ነጋዴዎች ይህንን ክፍተት በመጠቀም ገበያውን አውከውታል፡፡ እዚህም ሠፈር እየተፈጠረ ያለ ቡድንተኝነት ዜጎች በኑሮ ውድነት እንዲሰቃዩ እያደረገ ነው፡፡ ገበያው እንቢተኞችን እየወለደ ነው፡፡ ለዚህ አባባል ብዙ ምሳሌ ማቅረብ ይቻላል፡፡

ሌላውን ትተን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታዩና ዕርምት ካልተደረገባቸው አደገኛ ሊሆኑ ከሚችሉ ተግባራት መካከል መንግሥት ያወጣቸው ሕጎች ‹‹አላሠራን አለ›› በማለት በአንዳንድ ነጋዴዎች እየተወሰዱ ያሉ ዕርምጃዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ይህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ እንዲተገበር ያደረገውን አንድ መመርያ ይመለከታል፡፡ ይህ መመርያ ላኪዎች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ 80 በመቶውን ያህል በብር ተመንዝሮ፣ ቀሪውን 20 በመቶ ደግሞ በውጭ ምንዛሪ አግኝተው የሚፈልጉትን ዕቃ እንዲያስገቡ የሚደነግግ ነው፡፡  

ድንጋጌው ቀድሞ የነበረውን አሠራር የበለጠ ላኪዎች በውጭ ምንዛሪው መጠቀም የሚችሉበትን መጠን በእጅጉ የቀነሰ ነው፡፡

መመሪያው በዚህ መልኩ እንዲሻሻል የተፈለገበት ምክንያት አሳማኝ ሆነም አልሆነም ሕግ ነውና መተግበሩ አይቀርም፡፡ በእርግጥም መመርያው ሊጎዳቸው የሚችሉ ወይም ያሰቡትን ለማሳካት ያላስቻላቸው መሆኑ ቢታመንም፣ አገርና ሕዝብን ከሚጎዳ ተግባር ተቆጥቦ የመመርያውን ችግር አስረድቶ በዚህ መልኩ መሻሻል አለበት ብሎ መጠየቅ አግባብ ይሆናል፡፡ ጉልበት አለኝና የምፈልገውን ነገር አደርጋለሁ ማለት ፈጽሞ ተገቢ አይሆንም፡፡  

ነገር ግን ይህ መመርያ አላሠራንም ያሉ ነጋዴዎች እንዲህ ከሆነማ እጃችን ያለውን ምርት ለውጭ ገበያ አናቀርብም በማለት ሲሞግቱ ማየት ሊያስደነግጥን ይገባል፡፡ ይህ ልክ ፖለቲካው ውስጥ እንደምናየው የኔ ጥቅም መቅደም አለበት የሚለው ዕሳቤ ኢኮኖሚ ውስጥም እንደገባ ያሳየናል፡፡

መመርያው አገር ካለችበት ወቅታዊ ችግር አንፃር ተሻሽሎ የወጣ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ነገር ግን ለአንዳንዶች ይህ መመርያ አልተመቸም፡፡ ከዚህ ቀደም እንደተለመደው በኪሳራም ቢሆን ምርት ተልኮ በሚገኝ የውጭ ምንዛሪ ዕቃ በማስመጣት የሚገኝ ትርፍ አስቀርቷል፡፡ መመርያው እኔ በፈለኩት መንገድ የተሻሻለ ስላልሆነ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በመጋዘን አግቼ አልክም ማለት ደረጃ ላይ መድረሱ ሊያስፈራን ይገባል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ይህ ምርት መላክ አለበት ሲባል ‹‹አንልክም እስኪ መንግሥት የሚያደርገውን እናያለን›› እስከማለት ከተደረሰ ፖለቲካው ውስጥ የምንመለከተው ትርምስ ኢኮኖሚ ውስጥ ገብቶ ስቃያችንን እየባሰው መሆኑን እንረዳለን፡፡

ይህ አካሄድ ዛሬ በጥቂቶች ላይ እየታየ ሲሆን ነገሩ እየሰፋ ሄዶ ሊፈጥር የሚችለው ቀውስ ሊያሳስበን ይገባል ከዚህ ጉዳይ በተያያዘ እጅግ የሚገርመው ጉዳይ በኢትዮጵያ ላኪ መሆን የሚፈልገው በትክክል ከዘርፉ አተርፋለሁ በሚል እንዳልሆነ በግልጽ እየታየ መሆኑ ነው፡፡

ላኪ መሆን የሚፈለገው ምርቱን በኪሳራም ቢሆን ልኮ ዶላር ለማግኘትና በዚያ ዶላር ዕቃ ከውጭ አምጥቶ ‹‹በጥሩ ትርፍ›› ለመሸጥ እየሆነ ከመጣ ሰነባበተ፡፡ ስለዚህ የወጪ ንግድ እንደ ቢዝነስ ታስቦ እየተሠራበት ያለ መሆኑ እያየን ነው፡፡ ዛሬም የወጪ ንግድ ምርቶችን አከማችተው አንልክም ያሉ ወገኖች እየነገሩን ያሉት ነገር ከወጪ ንግድ የምናገኘውን ጥቅም አስቀራችሁ ሳይሆን እኛ በኪሳራ ሸጠን የምናገኘውን ዶላር ዕቃ አምጥተን እንዳናተርፍ ከለከላችሁን የሚል ይመስለኛል፡፡ አክሳሪ የወጪ ንግድ ተገቢ ነው? ለሁሉም የሚመች ሕግ ላይኖር ይችላል፡፡ ብዙኃኑን የሚጠቅም ሕግ ግን ገዥ ነው፡፡ አሁን እንዲህ ሆኖ ያለው ጥቂቶች እኛን ስላልተመቸን የሚል ነውና እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን ሥር ሳይሰዱ በደንብ መፈተሽ አለባቸው፡፡ ዋናው ነገር ግን በኪሳራ ተሸጠ የሚባለው የወጪ የውጭ ምንዛሪ ይገኝበት በዚያ የሚመጣ ዕቃ የላኪዎችንም ኪሳራ ሸፍኖ ትርፍም ተይዞበት የሚሸጥ በመሆኑ ለዚህ አገር የዋጋ ንረት ሌላው ምክንያት ሆኖ መምጣቱ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ንግድ በሥሌትና በጨዋነት የሚሠራ ነው፡፡ እየከሰሩ ምርትን መላክ እንዴት ተቀባይነት እንዳለው አይገባኝምና በፖለቲካ ውስጥ የምናየው ግራ የተጋባ ሒደት ኢኮኖሚውንም እያጠናውና ከዚህ አዙሪ እንውጣ ለንግዱም ለፖለቲካውም ስኬት ለእኔ ሳይሆን አገሬንም ማለት ከውድቀት ያድናል፡፡ 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት