Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅአብረን እንስከን - 3           

አብረን እንስከን – 3           

ቀን:

 በአሰፋ ጉያ
! ታላቁ ባለቅኔ ሎሬቱ. . .
ያገር አድባርየሕዝብ ዋርካው  እሳት ወይ አበባ መሆን አቃተን  እያለ፤
ስለጥበብ፥ ስለ ሕዝበዓለም እድሜ ልኩን እንደተብሰለሰለ
ቢቸግረውአብረን ዝም እንበልእንዳለ፤
ከነቁጭቱከነህልሙ እንደዋዛ ዘንበልከንበል አለ፡፡
ግርምቴ . . .
ተፈጥሮ በነጠላና በህብር በፈጣሪ ጥበባት መዋቀሩን ላስተዋለ
የተነጣጠለ፥ የተቃረነ ቢመስልም
በፈጣሪና በተፈጥሮ ሕግጋት ነው ተገማምዶ፥ ተሳስቦ  በአብሮነት የተሳለ፡፡
የኛ ሰዎች ግና…!
ገና ከማለዳው ዳዴ እያሉ
ሲዋረሩ   ሲሳደዱ እየዋሉ
በሕግ አምላክ!  . . .   በሕገ መንግሥት! እየተባባሉ፣
ቁርጥራጭ ብረታ ብረት እየተሳሳሉ
በሆነ ባልሆነው እርስ በርስ አንገት ለአንገት ሲቀላሉ ስለምን በከንቱ ዋሉ?
የኛ ጉዶች፡
በምላስናጠመንጃ እየተቋሰሉ
በዛቻበፉከራ ተጋግለው ሲገዳደሉ እየዋሉ
በየቤተሃይማኖታቱ ደጃፎች ብፁዕ ለመምሰል እየተማማሉ፣
በየሸንጎውበየፓርላማው እጃቸውን ሰቅለው   ፍትሐዊነት፣ እኩልነት ነግሧል እየተባባሉ፤
በዕውንም ሆነ በህልማቸው ግን ለበቀል ለየጣዖታቱ ለየአድባራቱሳይቀር ስለምን ስለት ተሳሳሉ፤
ስንቱ ሲቀላ ይበቃ ይሆን? ዕርቅ ለማውረድአብሮነት ለመባባሉ፡፡
ትከሻ ለትከሻ ተለካክተን
በቃላት ድምቀት፥ በጩኸት ብልጫ ተወናብደን
በባህል፥በታሪከ ትርክት ተቀራርነን
በሴራ ቦለቲካ ተወናብደን
ከእስራቱግርፋቱ፥ ከደም አዙሪቱ መውጣት ካቃተን  
ምነው ለሕዝባችን እፎይታ ብለን፥ ለአንድ አፍታ እንኳ ብንሰክን አብረን፡፡
ወገኖቼ . . .
በማናውቀው፥ በማያስማማን ሚዛን ተመዛዝነን
በቃላት ጋጋታ፥ በሕግ መሰል አንቀጻት ተደናቁረን
መደማመጥ መግባባት ካቃተን
እባካችሁ . . .
ሰላም አናደፍርስ፥ ሕዝብ አናጫርስ፥ አገር አናፍርስ በደመነብስ ተደናብረን፡፡
ከአልቦ በታች ቁልቁል እንዳይሆን ነጋችን፤
ምናለ  ብንሰክን አብረን
ሕዝባችንን ከእልቂት፥ አገራችንን ከብተና ለማዳን ብለን፡፡
ቃልእምነትመሀላ በሥጋ ተበልጦ ቁልቁል ከምንወድቅ
በምድር ለዓመታት በሰደድ፥በሰማይ በሲዖል እሳት ዝንተ ዓለም ከምንነድ
አይሻልም ይሆን ወገኔ?
አብረን ሰክነን በአገራችን መቻቻልን፥ ሰላምን ብናጸድቅ፡፡
ሁሉም በየጎራው፥ ቀዳማይአቅኚው እኔ ብቻ ነኝ፥ ካለ
እርስ በርስ ተጧጡዞ ያለልኬት ዋጥከኝ ከተባባለ
በጥላቻና . . . በንቀት አገር ምድሩ ከተበካከለ
የሥነህሊና ሚዛኑ ቁልቁል ከተከነበለ
ከዚህ በላይ ውድቀትድቀትሞትማ ከቶ የታለ?
ወገኖቼ . . .
ይሻል ይሆናልካልን እስቲ አብረን እንሂድ
ወደ ክልሎቹ ተሰባስበን  እንንጎድ
ሕገ መንግሥትይቀደድ!…አይቀደድ! ብለን፥ ቸኩለን ሳንፈርድ፣
ብርሃን ርቆን፥ ጨለማ ውጦን በሰቀቀን ከምንደርቅ
እባካችሁ! በቅድሚያ የሕዝባችንን ዕንባ አብረን በጋራ እናድርቅ፡፡
ከድምጽ ማጉያና ከእጅ መዳፍ ጭብጨባ እንገለል
ለአንድ አፍታ እንኳንከየአደባባዮቹና  ከየአዳራሾቹ እንነጠል
እንደጥንቱ በዛፎች ጥላ ሥር በእውነትለእውነት ብለን እንጠለል
አንድምብዙም  ሆነን በየወጋችንበየባህላችን  አብረንሰላምእርቅ  እንበል፡፡
ከዓባይ ማዶ ወደ ቤኒሻንጉልጉሙዝ ወደ ህዳሴው ግድብ እንውረድ አብረን፤
በፋሲል ግንብ . . .በጣና ዙሪያ እስክስታ እናውርድ ወገብ ለወገብ ተያይዘን፤
የፍቅር ጮራ ለኩሰን፥  የጥላቻውን ግንብ እናፍርስ ተጋግዘን፡፡
ላሊበላ ሂደን፥ እግዚኦ ማረን! እንበል
የፈጣሪን ቡራኬ መለኮቱን እንዳለ እንቀበል፡፡
እንሂድ ጋምቤላ ከለማለሙ አገር አብረን
በባሮ ወንዝ ላይ በፍቅር መርከብ ላይ ተቃቅፈን፡፡
ወደጥንታዊቷ አክሱም እንዝለቅ
በየገዳማቱአድባራቱ እንውደቅ
ከአዴታቱ እጅ ተቋድሰን አምባሻውን
በበረከቱ እንፈወስ እርስ በእርስ ከልብ ተመራርቀን፡፡
! ማሬዎ! –ማሬዎ!   አብረን እያልን
ሀባቦመርጋ ጉራቻእርቁን በእጃችን ጨብጠን
ቢሾፍቱሆራ አርሰዲ ለኢሬቻ እንውረድ ተጃጅበን፡፡
ወደ አርባ ምንጭ እንዝለቅተሰባስበን
ለሕዝብ ክብር፥ ለወገን ፍቅር ብለን፥ ከኒያ ደጋግ ሕዝቦች ጋር ተቃቅፈን
እርጥብ ሳር በእጃቸን ጨብጠን፥ በመሬት ላይ  እንውደቅ አብረን፡፡
ወደ ቦረና ከአንጋፋዎቹ ቀዬ አብረን እንዝለቅ
በአንደበተ ርቱዓኑ፥ በአንጋፋዎቹ አባገዳዎቹ  እንመረቅ
የገዳዲሞክራሲ ችግኙ በሁሉም ሥፍራ በህብር እንዲጸድቅ፡፡
ወደ ጅማወደ ከፋ ሽምጥ እንጋልብ
ከቡናው ረከቦቱ ዙሪያ እንሰብሰብ
አቦል ጀባ! በረካ ጀባ!  እየተባባልን እርስ በርስ እንካካብ፡፡
ሐረር ጀጎል፥ ደገሃቡር ሶማሌ፥ ድሬ ሼህ ሁሴን አብረን እንዝለቅ
አስቶፍሩላህ!…አላሁ አክበር!  ብለን ከፈጣሪያችን ጋር እንታረቅ፡፡

ለትንግርትም . . .
እንሂድ አፋር፥ ከቅድመ ዘራችን ከእናታችን ሉሲ አገር
እንድትተርክልን ከእሳተ ገሞራ በጉርብትና የመኖርን ታላቅ ሚስጥር
ለሚሊዮን ዓመታት አጽም ሳይፈራርስ የመዝለቁን ልዩ ቀመር፡፡
እኛው ግንበየአምስት ዓመቱ፥ ውረድ!…አልወርድም! ከምንባባልበት
4 ኪሎው ወንበር ከምንዶልት፥ ከምንፋጅበት
ለሕዝባችን ለአገራችን ብለን በቅድሚያ አብረን ብንሰክንለት፡፡
ምናለ ጎበዝ! ጐበዛዚት! ለዚህ ታላቅ ሕዝብ በቅድሚያ ብናስብለት፤
በሰቀቀን ባይባዝንበት፥ በችጋርበጠኔ ባይረግፍበት፣፣
ሎሬቱ እንዳለው፡
« . . . . . . .
ዳግመኛ ሞት ሳንሞት፥ አዲስ ቀን ሳይጨልምብን
ድፍን ደመና ሳይቋጥር፥ ክረምት ውርጅት ሳይወርድብን
. . . . . . . ፡፡»
ወገኖቼ . . .
በኮሮና እና በብረት መሃል ተወጥረን
ጦርነቱ ከሚፈጀን፣ በሽታና ረሃቡ ከሚያረግፈን
ምናለ መሰዳደቡ መቆሳሰሉና መጨራረሱ ለጊዜው ቢቀርብን፡፡
እናም፡
እንደ ሰው መኖር፥ እንደ አገር መቀጠል ካለብን
ለአንድ አፍታ እንኳን፥ አሐዳዊ!…ፊዴራላዊ፥  ቃለ ግነቱን ገተን፤
ባንስማማም ለጊዜው እንኳ  . . . ሃቡልቱ ዱቢን  ብለን
አደይ አበባ ሆነን
ሕዝባችንንአገራችንን ብናድን አብረን ሰክነን፡፡

 

“”””

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ