እሑድ ሚያዝያ 2 ቀን 2014 ዓ.ም. በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ ቀጣና ሦስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ጀርባ፣ ተደራጅተው የመሬት ወረራ ሲፈጽሙ 150 ሕገወጦች መያዛቸውን ክፍለ ከተማው አስታወቀ፡፡ በሕገወጥ መንገድ የተገነቡ ያላቸውን 67 ቤቶችና 43 አጥሮችን በጀሞ ወረዳ አንድ መንደር ሦስት አካባቢ ማስፈረሱን፣ ሕገወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ መበራከቱንና ከዚህ ሕገወጥነት ጀርባ ሥውር እጆች መኖራቸውን ለሪፖርተር ገልጿል፡፡
ክፍለ ከተማው ሰፊ በመሆኑና ያልለሙ መሬቶች ያሉበት በመሆኑ ምክንያት፣ በሕገወጥ የመሬት ወረራና የቤት ግንባታ ወንጀሎች በተደጋጋሚ እንደሚፈተን የክፍለ ከተማው ኮሙዩኒኬሽን ገልጿል፡፡ ሕገወጥነትን ለመከላከልም ከፖሊስና ከደንብ ማስከበር ጋር በመተባበር፣ የክፍለ ከተማው የመሬት ወረራና ሕገወጥ ግንባታ መከላከል ግብረ ኃይል የተጠናከረ ዕርምጃ በመውሰድ ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ሕገወጥነትን ለመከላከል በተወሰዱ የሕግ ማስከበር ዕርምጃዎች ከወንጀሉ ጀርባ ሥውር እጆች መኖራቸው እንደተረጋገጠ የገለጹት የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ዮናስ ጌታቸው፣ ወንጀሉ የሚከናወነው በተቀናጀ መንገድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
‹‹ምስኪኖችን፣ ቤትም ሆነ መሬት ወይም ሌላ ንብረት የሌላቸውን ሰዎች ከሌላ አካባቢ እያመጡ የሚያሰፍሩ ሥውር እጆች አሉ፡፡ በሕገወጥ መንገድ የተያዘው መሬት ሕጋዊ ይሆንልናል በሚል ምኞት ሰዎችን መጠቀሚያ በማድረግ፣ የመሬት ወረራና ሕገወጥ ግንባታን ከጀርባ የሚያስፈጽሙ አካላት እንዳሉ ተደርሶበታል፤›› ሲሉ የተናገሩት አቶ ዮናስ፣ በሁሉም መስክ የሚስተዋሉ ሕገወጦችን የመከላከሉ ዕርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
እሑድ ዕለት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ጀርባ በአካባቢ ጥበቃ ለአረንጓዴ ልማት እንዲውል ፈቃድ የሰጠውን ቦታ ደን በመጨፍጨፍ ለወረራ የተንቀሳቀሱትና በፖሊስ የተያዙት 150 ግለሰቦች፣ ቦታውን ለሃይማኖት ተቋም መገንቢያነት ሊያውሉት ነበር ተብሎ የተናፈሰው ወሬ ከእውነት የራቀ መሆኑን አቶ ዮናስ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በጀሞ ወረዳ አንድ መንደር ሦስት ቤቶችና አጥሮች የፈረሱባቸው ግለሰቦችም፣ ይዞታውን በሕገወጥ መንገድ መያዛቸው የተረጋገጠና ራሳቸው ሕገወጥነቱን ያመኑ ናቸው፤›› ሲሉ የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
ክፍለ ከተማው በመሬትና ግንባታ አስተዳደር በኩል የሚታዩ ሕገወጥነቶችን ለመከላከል የሚያስችል የተጠናከረ ዕርምጃ መጀመሩን አቶ ዮናስ ይናገራሉ፡፡ ኅብረተሰቡ በሕገወጥ መንገድ በሚደረግ ግንባታና መሬት ወረራ የአገር ሀብት ከመውደም እንዲታደግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በዋናነት ደግሞ አቅመ ደካማ የሆኑ ዜጎችን በጊዜያዊ መደለያ በማታለል፣ ለመሬት ወረራና ለሕገወጥ ግንባታ ማስፈጸሚያነት የሚዳርጉ ሥውር እጆች ከሕገወጥ እንቅስቃሴ እንዲታቀቡ አቶ ዮናስ አሳስበዋል፡፡