በምሥረታ ላይ ከሚገኙ ባንኮች ከፍተኛ የተከፈለ ካፒታል ይዞ የፋይናንስ ገበያውን ለመቀላቀል ያኮበኮበው አማራ ባንክ፣ ዘመናዊ የሞጁላር የመረጃ ማዕከል አገልግሎት የሚያገኝበትን የሊዝ ኪራይ ስምምነት፣ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ፈጽሟል፡፡
የባንኩ ምሥረታ በተለያዩ ምክንያቶች እንደዘገየ የሚነገረው አማራ ባንክ፣ ከኢትዮ ቴሌኮም የቀረበለት የሞጁላር መረጃ ማዕከል አገልግሎት፣ ባንኩ ወደ ሥራ የሚገባበትን ጊዜ ያቀረበለት እንደሆነ ሁለቱ ኩባንያዎች የመግባቢያ ሰነድ በተፈራረሙበት መድረክ ተገልጿል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ በመድረኩ እንዳስታወቁት፣ 80 ሚሊዮን ደንበኞችን መሸከም የሚችል አቅም ያለው የኩባያው ሞጁላራይዝድ የመረጃ ማዕከል፣ የአማራ ባንክ ምንም ዓይነት የዳታ ማዕከል መገንባት ሳይኖርበት የፋይናንስ አገልግሎቶቹን ለደንበኞቹ ለማቅረብ የሚያስችለው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በቴሌኮም ኦፕሬተሩ የቀረበው አማራጭ፣ ባንኩ የራሱን የመረጃ ማዕክል ለመገንባት የሚፈጅበትን ጊዜ በእጅጉ የሚቀንስ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፣ ሀብትን በጋራ ከመጠቀም አንፃርም በተቋማቱ መካከል የተደረገው ስምምነት በበጎ መልኩ የሚነሳ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም የገነባው ግዙፍ የመረጃ ማዕከል ጊዜው ከሚጠይቀው ቴክኖሎጂ ጋር የተመጋገበ ነው ወይ? የሚለውን፣ በአንክሮ የመከታተል ኃላፊነቱን እየተወጣ ለአማራ ባንክ አገልግሎቱን የሚያቀርብ እንደሆነ የተናገሩት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ በዚህም አገልግሎት ላይ የባንኩ ሚና የሚሆነው ከቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶቹ ቦታ ሆኖ አገልግሎቶችን ማስተዳደር ነው ብለዋል፡፡
ወ/ሪት ፍሬሕይወት እንዳስታወቁት፣ በሞጁላር የዳታ ማዕከሉ የሚቀርበው አገልግሎት ቅርንጫፎችን ማገናኘት ብቻም ሳይሆን፣ ቅርንጫፎች ከመረጃ ማዕከሉ ጋር ያላቸውን ግንኙነት 24 ሰዓት በተቀላጠፈ መንገድ እንዲሳለጥ የሚያስችል ነው፡፡ ይህም የባንኩን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሥርዓት በዚህ እጅግ ዘመናዊና ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃውን በጠበቀ የመረጃ ማዕከል አማካይነት አስተማማኝ አገልግሎት ለደንበኞቹ ለመስጠት የሚያስችለው ይሆናል ተብሏል፡፡
የመረጃ ማዕከሉ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ምርትና አገልግሎቶችን መስጠት ለሚፈልጉ ድርጅቶች በአጭር ጊዜ የመረጃ ቋቱን በመጋራት ወደ ሥራ እንዲገቡ የሚያስችላቸው እንደሆነ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ አስረድተዋል፡፡
የአማራ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ሔኖክ ከበደ ስምምነት በተደረገበት ወቅት እንደተናገሩት፣ አማራ ባንክ በቴክኖሎጂው ዘርፍ የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን ወደ ትልቅ ደረጃ የሚያሸጋግር ይሆናል ብለዋል፡፡
ባንኩ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ ለመምጣት እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ያስታወቁት አቶ ሔኖክ፣ በትልቅ ግዝፈት ወደ ገበያው ለመግባት ለሚያደርገው ሥራ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የተደረገው ስምምነት አጋዥ ይሆናል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ሁለት የሞጁላር ዳታ ማዕከላትን እስካሁን እንደገነባ ያስታወቀ ሲሆን፣ ተጨማሪ በግንባታ ላይ ካሉት ሦስት ማዕከላት ጋር ተዳምሮ አምስት የዳታ ማዕከላት በቅርቡ እንደሚኖሩት ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል ኢትዮ ቴሌኮም በሳምንቱ መጀመሪያ የመደበኛ ባለገመድ ኢንተርኔት አገልግሎትን ከሚያዳርሱ አምስት አገር በቀል የቴክኖሎጂ ድርጅቶች ጋር የአጋርነት ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
ዌብ ስፕሪክስ አይቲ ሶሉሽን፣ ቪቫ ቴክ ትሬዲንግ፣ ዘርጋው አይኤስፒ፣ ስካይ ኔት አይቲ ሶሉሽንና ዱሌ ቢዝነስ ግሩፕ የተባሉት አጋር ድርጅቶች፣ ኢትዮ ቴሌኮም መደበኛ ብሮድባንድ አገልግሎትን ለደንበኞቹ ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ አብረውት የሚሠሩ ተቋማት እንደሆኑ ታውቋል፡፡