Sunday, June 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የከተማ አስተዳደሩ ለኮንዶሚኒየም ግንባታ ከንግድ ባንክ ከጠየቀው ብድር ከግማሽ በታች ተፈቀደለት

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የጋራ ቤቶች ግንባታን ለማከናወን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተበደረው 54 ቢሊዮን ብር ዕዳ ያለበት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ለቀሪ ሥራዎች ማስኬጃ ከጠየቀው 5.4 ቢሊዮን ብር ብድር ውስጥ 2.5 ቢሊዮን ብር እንዲያገኝ ተፈቀደለት፡

አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በግንባታ ላይ ያሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለማጠናቀቅና ተቋራጭ ባልገባባቸው ሳይቶች ሥራ ለማስጀመር ብድር የጠየቀው ከወራት በፊት ሲሆን፣ ብድሩ ከመፈቀዱ በፊት የመረጃ ማጥራት ሥራዎች መከናወናቸውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮርፖሬት ደንበኞች ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉነህ ለማ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ ሙሉነህ ገለፃ ከብድሩ መፈቀድ በፊት ብድር የተወሰደባቸው ፕሮጀክቶች ያሉበት ሁኔታ፣ እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ ብድር የመመለስ አቅም ጥናት ተደርጎበታል፣ ይኼም ሁለቱ አካላት ሲሠሩበት ከነበረው አካሄድ የተለየ ነው፡፡

ፕሮጀክቶቹ ያሉበትን ሁኔታ የሚያጠና ቡድን የተዋቀረው ከሁለቱም አካላት መሆኑን የሚያስረዱት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ ባንኩ ከዚህ በፊት የተወሰደውን ብድር የማስመለስ ኃላፊነት እንዳለበትና ለዚህም ጥናቱ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይሁንና በገንዘብ ሚኒስቴር ዋስትና የከተማ አስተዳደሩ አሁን ከጠየቀው 5.4 ቢሊዮን ብር ውስጥ ከግማሽ በታች የሚሆነውን እንዲያገኝ ተፈቅዶለታል፡፡ በከተማ አስተዳደሩ በኩል መሟላት ያለባቸው ቀሪ ሥራዎች እንደተጠናቀቁ ብድሩ እንደሚሰጥ ምክትል ፕሬዚዳንቱ አክለዋል፡፡

አቶ ሙሉነህ እንደተናገሩት በሁለቱ አካላት በኩል የሚደረገው ጥናት ያልተጠናቀቀ በመሆኑ፣ የተጠየቀውን ብድር ተቀንሶ የተሰጠ ሲሆን የከተማ አስተዳደሩ ጥያቄ በዚህ በጀት ዓመት ያልተያዘ መሆኑ ብድሩ ሙሉ ለሙሉ ላለመሰጠቱ ሌላ ምክንያት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሁን ካፀደቀው ብድር ውጪ ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ አምስት ቢሊዮን ብር ብድር ያቀረበ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት ብድር ሲያቀርብ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ የቀረበው 2.5 ቢሊዮን ብር ብድር ለከተማ አስተዳደሩ የደረሰው ዘግይቶ በመሆኑ የቤቶቹ ግንባታ ሥራ የተጀመረው የበጀት ዓመቱ ከተጀመረ ሦስት ወራት በኋላ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በመጀመሪያው አጋማሽ 139 ሺሕ ግንባታ ለማከናወን የተያዘው ዕቅድ አለመሳካቱን የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሪት ያስሚን ሙሀረቢን፣ በየካቲት ወር መጀመሪያ ላይ በተካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ጉባዔ ላይ ተናግረው ነበር፡፡

የከተማ አስተዳደሩ የጋራ ቤቶችን ለመገንባት የጠየቀው ገንዘብ ከፍተኛ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ሙሉነህ፣ በሁለቱ አካላት በኩል እየተደረገ ካለው ጥናት ባሻገር የብድር አቅርቦቱ በምን ዓይነት መልኩ ይቀጥል የሚለውን የሚመለከት ዕቅድ እንደሚዘጋጅ ገልጸዋል፡፡

ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ ከዚህ በፊት የፕሮጀክት አፈጻጸም ጋር ተያይዞ በታዩ ችግሮች የተነሳ፣ ፕሮጀክቶቹ ያሉበትን ሁኔታ መገምገም ቢያስፈልግም አሁን ላይ ግን ፕሮጀክቶቹን በተመለከተ በባንኩ ዘንድ ያለው መተማመን መጨመሩን ተናግረዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ከ17 ዓመታት በፊት ባስጀመረው የጋራ ቤቶች የግንባታ እስካሁን 316 ሺሕ ቤቶችን ለነዋሪዎች ቢያቀርብም፣ አሁንም የቤት ባለቤት ለመሆን የተመዘገቡ ከ650 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች አሉ፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ከሦስት ዓመት ገደማ በፊት የ20/80 ቤቶች 13ተኛ ዙርና የ40/60 ቤቶች ሁለተኛ ዙር ዕጣ አውጥቶ የነበረ ሲሆን እስካሁን ዕጣ የወጣባቸውን ቤቶች አስረክቦ አላጠናቀቀም፡፡ ለዚህ አንደኛው ምክንያት የፋይናንስ እጥረት መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡

በዘጠኝ በመቶ ወለድ የወሰደው ብድር እየጨመረበት ያለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎቹን የቤት ባለቤት ለማድረግ የተለያዩ አማራጮችን በማየት ላይ ነው፡፡ በ2005 ዓ.ም. በተደረገው ምዝገባ የተሳተፉና አቅም ያላቸው ሰዎችን ማኅበር አቋቁመው 70 በመቶውን ወጪ በመቆጠብ መሬት ከከተማ አስተዳደሩ የሚወስዱበትን መንገድ አዘጋጅቷል፡፡ በዚህም አሥር ሺሕ ሰዎች መመዝገባቸው ተገልጿል፡፡ ሌኛው አማራጭ የመንግሥትና የግል አልሚዎች ሽርክና ሲሆን መንግሥት መሬትና መሠረተ ልማት ሲያቀርብ የግል አልሚዎች ደግሞ ገንዘብና ሞያ ይዘው በመምጣት የሚገነቡትን ቤት በሕዝብ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ የታሰበ ነው፡፡

በግል አልሚዎችና መሬት ባላቸው ግለሰቦች መካከል የሚደረግ ሽርክናም በከተማ አስተዳደሩ አማራጭነት ተወስዷል፡፡ በዚህ አማራጭ መሬት ያላቸው ግለሰቦች አልሚዎች ቦታው ላይ ቤት እንዲገነቡበት ስምምነት ላይ በመድረስ የመሬቱ ባለቤት ከተገነባው የቤት ህንፃ ላይ ድርሻ እንዲኖረው የሚያደርግ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች