- ከአማራ ክልል የሚነሱ ታጣቂዎችን በሚመለከት አብን ተቃውሟል
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) መንግሥት ‹‹ሸኔን ማጥፋት›› ከሚለው ውጤት አልባ የዘመቻ አዙሪት ወጥቶ፣ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል እንደጀመረው ሁሉ፣ በኦሮሚያ ክልል ያለውን አለመግባባትም በተመሳሳይ ሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጥሪ አቀረበ፡፡
የኦፌኮ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ቅዳሜ ሚያዝያ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. መደበኛ ስብሰባ በማካሄድ፣ ከአማራ ክልል የሚነሱ የታጠቁ ኃይሎች በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ጥቃት እያደረሱ ነው ማለቱን፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ትናንት ሚያዚያ 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ተቃውሟል፡፡
ኦፌኮ በመግለጫው ካተኮረባቸው ሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል፣ መንግሥት ‹ሸኔን ማጥፋት› ከሚለው ውጤት አልባ የዘመቻ አዙሪት ወጥቶ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል እንደጀመረው ሁሉ በኦሮሚያ ክልል ያለውን አለመግባባትም ተመሳሳይ በሆነ ሰላማዊ አካሄድ እንዲፈታ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ በተጨማሪም የኑሮ ውድነት ዋነኛው መንስዔ አገሪቱ በሁሉም አቅጣጫዎች የገባችበት የእርስ በርስ ጦርነት በመሆኑ፣ የእርስ በርስ ጦርነት ወደሚያስቆም ውይይትና ድርድር ፊቱን ማዞር አለበት ብሏል፡፡
አብንም በኦፌኮ መግለጫ የተነሱት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በኦነግ ሸኔና በክልሉ የፀጥታ ኃይሎች መካከል እየተደረገ ያለውን ግጭት ሰላማዊ መፍትሔ እንዲፈለግለት ጥሪ ማድረጉን ወቅታዊ በሆነውና ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ፈተና ላይ የጣለው የኑሮ ውድነት መፍትሔ እንዲፈለግለት ያደረገውን ጥሪ እንደሚጋራ ጠቅሷል።
ነገር ግን ኦፌኮ ከአማራ ክልላዊ መንግሥት በመነሳት የጦር መሣሪያ የታጠቁ ኃይሎች፣ በተለያዩ ሥፍራዎች በኩል የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትን የታወቀ ወሰን በኃይል በመጣስ፣ ጦርነት አውጀው የመሬት ወረራና የግዛት ማስፋፋት ተግባር ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ ማለቱን አብን ተቃውሟል፡፡
እነዚህ ኃይሎች ሰላማዊ ሰዎችን በመግደል፣ አርሶ አደሮችን ከመሬታቸው በማፈናቀል ክልሉን ወደ የማያባራ የግጭት ቀጣና እየለወጡት እንደሚገኙ ታውቋል ያለው ኦፌኮ፣ በተለይም ይህ የጦር ዘመቻና የመሬት ወረራ በምሥራቅ ወለጋ፣ በሆሮ ጉድሩ ወለጋ፣ በሰሜን ሸዋ፣ ምዕራብ ሸዋና በምሥራቅ ሸዋ ዞኖች በተቀናጀ አኳኋን እየተካሄደ እንደሚገኝ ከአባሎቹና ከአካባቢው ማኅበረሰብ እንደተረዳ ገልጿል፡፡
የኦፌኮን መግለጫ በተመለከተ አብን ባወጣው መግለጫ፣ በኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል እየተደረገ ባለው የፖለቲካ ግብግብ ምክንያት በኦሮሚያ ክልል ለተፈጠረው የፀጥታ መደፍረስና የሰላም ዕጦት የአማራን ሕዝብና የአማራን የፖለቲካ ኃይሎች የጦስ ዶሮ ለማድረግ የሚኬድበትን መንገድ አጥብቆ እንደሚያወግዝ አስታውቋል። ኦፌኮ በመግለጫው የጠቀሳቸው ቦታዎች በንፁኃን የአማራ ተወላጆች ላይ ተደጋጋሚ ጭፍጨፋና መፈናቀል የሚፈጸምባቸው እንደሆኑ የሚታወቅ መሆኑን፣ በግልጽ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች የሚንቀሳቀሱባቸውና ታጣቂዎቹ አብዛኞቹን አካባቢዎችን እንደሚቆጣጠሯቸው ይታወቃል ብሏል፡፡
በእነዚህ አካባቢዎች ለተፈጠረው የፀጥታ መደፍረስና የሰላም ዕጦት አማራ ተጠያቂ የሚሆነው፣ ‹‹ኦነግ ሸኔ አማራ ነው፣ ታጣቂዎቹም የአማራ ገበሬዎች ናቸው፤›› ከተባለ ብቻ ነው ያለው አብን፣ ‹‹ኦፌኮ ኦነግ ሸኔንና ታጣቂዎችን በአማራነት እንደማይከስ ተስፋ እናደርጋለን፤›› ሲል በመግለጫው ጠቅሷል፡፡
ኦፌኮ በመግለጫው ወረራ የሚያካሂዱት ከአማራ ክልል መንግሥት ዕውቅና ውጪ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ‹‹ፅንፈኛ›› ኃይሎች ናቸው ቢባልም፣ ይህ እውነት እንዳልሆነ የሚያመላክቱ ማስረጃዎች አሉ ብሏል፡፡ እንደ ማሳያነትም ከሰሜን ሸዋ ዞን ቅንቢቢት ወረዳ 280 ሔክታር በላይ መሬት ላይ የኦሮሚያ አርሶ አደሮችን በመንቀል መሬቱን የወሰደው የአማራ ክልል ልዩ ፖሊስ እንደሆነ የመንግሥት ሚዲያ ሳይቀር አጋልጧል ያለው ኦፌኮ፣ በተለያዩ አካባቢዎች የመሬት ወረራና የግዛት ማስፋፋት እያካሄዱ ያሉት የአማራ ክልላዊ መንግሥት አካላት እንደሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም ሲል አስታውቋል፡፡
አብን በበኩሉ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እየፈጠሩ ካሉት የፀጥታ መደፍረስና የሰላም ዕጦት በተጨማሪ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በሲዳማ ክልል፣ በደቡብ ክልልና በአማራ ክልል በርካታ አካባቢዎች በንፁኃን ዜጎችና በሕዝብ መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ሲያደርሱ እንደቆዩና እያደረሱ ለመሆኑ ማሳያዎች አሉ ብሏል፡፡ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትና በኦነግ ሸኔ መካከል እየተካሄደ ያለውን ደም አፋሳሽ ግጭትና በተለያዩ የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ያለውን የፖለቲካ ውጥረት ያረግባል በሚል ሥሌት፣ ኦነግ ሸኔ በሚንቀሳቀስባቸውና በሚቆጣጠራቸው የኦሮሚያ አካባቢዎች ከአማራ ክልል የተነሱ ታጣቂዎች ወረራ ፈጸሙ የሚል መግለጫ ማውጣቱ እንዳሳዘነው አብን በመግለጫው አስረድቷል፡፡