Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊስዋሂሊኛ ቋንቋ በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ እንዲካተት ተጠየቀ

ስዋሂሊኛ ቋንቋ በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ እንዲካተት ተጠየቀ

ቀን:

  • የባህል ማዕከል ቦታ በመዲናዋ እንዲኖራቸው አስተባባሪዎች ጠይቀዋል

የስዋህሊ ቋንቋ በኢትዮጵያ የሥራ ቋንቋ እንዲሆንና በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲካተት አፍሪካ ዩናይትድ ኢንሺዬቲቭ (Africa United Initiative Organization) ወይም፣ በኢትዮጵያ የስዋሂሊ ኮሙዩኒቲ በመባል የሚታወቅ ድርጅት ለትምህርት ሚኒስቴር ጥያቄ አቅርቦ መልስ እየጠበቀ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት እንደ ሲቪክ ድርጅት በኢትዮጵያ ተመዝግቦ ፈቃድ ያገኘው ድርጅቱ፣ የስዋህሊ የባህል ማዕከል መገንቢያ ቦታም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጠይቋል፡፡

‹‹ዓላማችን የፓን አፍሪካን የሥራ ቋንቋ የአፍሪካውያን ቋንቋ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ቋንቋዎች ሳይኖሩ ኢትዮጵያም አኅጉራዊና ቀጣናዊ የአፍሪካ ዕቅዶችን መተግበር ያዳግታታል፡፡ አንድ ዓይነት የሥራ ቋንቋ ከሌለን እርስ በርስ መነገድ አንችልም፡፡ ስለዚህ አፍሪካ ንግድ ቀጣናን መተግበር ሊያስቸግር ይችላል፤›› ሲሉ ሚስተር ኢማኒ ዮሐኒ፣ በድርጅቱ በኢትዮጵያ የስዋሊኛ ቋንቋ አስተባባሪና አስተዋዋቂ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

ድርጅቱ 25 ሠራተኞች ያሉት መሆኑን፣ በአሁኑ ጊዜም የኬንያና የሶማሊያ ድንበር አካባቢዎችን ጨምሮ ከ300 በላይ የስዋሂሊ ተናጋሪዎች በኢትዮጵያ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

ስዋሂሊ በ22 የአፍሪካ አገሮች ውስጥ እስከ 200 ሚሊዮን ተናጋሪዎች አሉት ተብሎ የሚታመን ሲሆን፣ አሥራ አንድ አገሮች የመንግሥት የሥራ ቋንቋ  አድርገውታል፡፡

ከወራት በፊት በአዲስ አበባ በተካሄው 35ኛ ጉባዔ፣ የአፍሪካ ኅብረት የስዋሂሊኛ ቋንቋን የኅብረቱ የሥራ ቋንቋ አድርጎ መምረጡ ይታወሳል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ ከታንዛያው ዳሬሰላም ዩኒቨርሲቲ ጋር ስዋሂሊን በሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ ለማስተማር የመግባቢያ ስምምነት ማድረጉም ይታወሳል፡፡

ድርጅቱ ግን ከትምህርት ሚኒስቴር በጎ ምላሽ ካገኘ ስዋሂሊ ከመጀመርያ ደረጃ ጀምሮ እንዲሰጥ አቅዷል፡፡

ይሁን እንጂ አማርኛን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ተናጋሪ ያሏቸው የአፍሪካ ቋንቋዎችን፣ የኅብረቱ የሥራ ቋንቋ ለማስደረግ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ያሉት መሆኑንና ይህም በጎ መነሳሳት መሆኑን ኢማኒ ገልጸዋል፡፡

‹‹ዋናው ግባችን አፍሪካን ከቅኝ ግዛት ቋንቋዎች ነፃ በማድረግ የራሳችንን ቋንቋዎች ለሥራ መጠቀም ነው፡፡ የቅኝ ግዛት ቋንቋ ክፍፍል ነው ያመጣብን፡፡ በራሳችን ቋንቋ  ካልተግባባን በምጣኔ ሀብትና በፖለቲካ መዋሀድ አንችልም፤›› ሲሉ ኢማኒ አስረድተዋል፡፡

‹‹የእኛ ሥራ ስዋሂሊን በኢትዮጵያ ማስተዋወቅ ነው፡፡ ውሳኔው የመንግሥት ነው የሚሆነው፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ ቋንቋዎችም ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ሄደው ተመሳሳይ የማስተዋወቅ ሥራ መሥራት ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኅብረቱን እንደጠየቁት፣ የአፍሪካ ሚዲያ ቢቋቋም፣ የዚህ ሚዲያ ቋንቋ  አፍሪካዊ ቋንቋ  መሆን አለበት፡፡ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሣይኛ፣ ፓርቹጊዝ ወይም ስፓኒሽ ከሆኑ የአፍሪካ ሚዲያ አይሆኑም፤›› ብለዋል፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...