Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበጅንካና አካባቢው በተፈጠረው ግጭት የተጠረጠሩ ከ100 በላይ ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀርበው የጊዜ...

በጅንካና አካባቢው በተፈጠረው ግጭት የተጠረጠሩ ከ100 በላይ ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀርበው የጊዜ ቀጠሮ ተጠየቀባቸው

ቀን:

  • በግጭቱ 150 ቤቶች መቃጠላቸው ታውቋል

ካለፈው ሳምንት አጋማሽ ጀምሮ በደቡብ ኦሞ ዞን በጅንካና በዙሪያው በሚገኙ አካባቢዎች የተነሳውን ግጭት ሲመሩ፣ ሲያደራጁ፣ እንዲሁም በተለያዩ መንገዶች እጃቸው አለበት የተባሉ 110 ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ቀርበው የምርመራ ጊዜ እንደተጠየቀባቸው የደቡብ ክልል የምዕራብ ኦሞ ዞን አስተዳደር አስታወቀ፡፡ የዞኑ አስተዳደር ባዋቀረው ኮማንድ ፖስት አማካይነት 132 ሰዎች በቁጥጥር መዋላቸውንና ከእነዚህ ውስጥም 22 ያህሉ ጉዳያቸው ተጣርቶ መለቀቃቸው ተገልጿል፡፡

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ፣ የሰላምና ፀጥታ መምርያ ኃላፊ አቶ ደሞ በዛብህ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ተጠርጣሪዎች ውስጥ አራት የፖሊስ አባላት ይገኙበታል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ከተያዙ በኋላ መብታቸው ተጠብቆ በፍርድ ቤት ሒደት ላይ መሆናቸውን ያስታወቁት ምክትል አስተዳዳሪው፣ ምርመራቸው እስከሚጠናቀቅ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እየተጠየቀ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

ይሁንና በዞኑ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት አሁንም ተጠርጣሪዎችን የመያዝና የተዘረፉ ንብረቶችን የማስመለስ ሥራ ላይ በመሆኑ፣ የተጠርጣሪዎች ቁጥር ከዚህም ሊበልጥ እንደሚችል ተገልጿል፡፡

ካለፈው ሳምንት ረዕቡ መጋቢት 28 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ውጥረት ውስጥ በቆየውና ቅዳሜ ዕለት በጂንካ ከተማና አካባቢዋ በተነሳው ግጭት 150 ቤቶችና አንድ መስኪድ መቃጠሉን የተናገሩት አቶ ደሞ፣ በዚሁ ሳቢያ 979 የቤተሰብ አባላት መፈናቀላቸውን አስታውቀዋል፡፡ ግጭቱ ከደቡብ ኦሞ ዞና ዋና ከተማ ጅንካ በተጨማሪ፣ በጋዘርና ቶልታ ከተሞችና ሜፅር ማዘጋጃ ቤት መከሰቱን፣ በዚህም ቁጥራቸው በርከት ያለ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው አስረድተዋል፡፡

የግጭቱ መነሻ ምክንያት የመዋቅር ጥያቄ መሆኑን ለሪፖርተር የገለጹት የዞኑ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምርያ ኃላፊ አቶ መላኩ ለማ፣ በዞንነት ለመደራጀት ጥያቄ ያቀረቡ አራት የአሪ ሕዝብ ወረዳዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ አቶ መላኩ ወረዳዎቹ የክልልነት ጥያቄያቸውን በየራሳቸው ምክር ቤቶች ካፀደቁ በኋላ፣ የዞኑ ምክር ቤትም አፅድቆ ለደቡብ ክልል ምክር ቤት እንዲልክላቸው አቅርበው እንደበር አስታውቀዋል፡፡ ይሁንና የዞኑ ምክር ቤት ጉባዔ ሲያደርግ የወረዳዎቹን የዞንነት ጥያቄ በአጀንዳነት አለመያዙ ማኅበረሰቡን ማስቆጣቱን አክለዋል፡፡

ረዕቡ ዕለት በጅንካ ከተማ በተደረገው ሠልፍ፣ ‹‹ምክር ቤቱ ጥያቄያችንን አፍኗል›› በሚል ተቃውሞ ሲቀርብ እንደበር ያስረዱት ኃላፊው፣ ‹‹ሰላማዊ ሠልፍ ሲደረግ ከሌሎች ነዋሪዎች ጋር ግጭት ተከስቶ ተቃውሞው መልኩን እየቀየረ መጣ፤›› ብለዋል፡፡ ይሁንና የከተማው ፖሊስና የደቡብ ልዩ ኃይል የዕረቡ ዕለትን ክስተት ተቆጣጥረው የዞኑ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ፣ የዞንነት ጥያቄውን በአጀንዳነት ላለመያዙ ይቅርታ መጠየቁንና በቀጣይ እንደሚወያይበት ማስታወቁን ገልጸዋል፡፡

የዞኑ አስተዳደር መግለጫ እስከ ዓርብ ያሉትን ቀናት ሰላማዊ ማድረጉን የተናገሩት አቶ መላኩ፣ በጂንካ የገበያ ቀን በሆነው ቅዳሜ ሚያዝያ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ግን ከቀኑ 8፡00 አካባቢ ጀምሮ በከተማዋ ውስጥ ባሉ ሁለት ገበያዎች ረብሻ ተነስቶ ገበያተኞችና ነጋዴዎች ላይ ጉዳት መድረሱን አብራርተዋል፡፡ እንዲሁም ረብሻ ፈጥረዋል በተባሉት ሰዎችና ቤቶች እንዳይቃጠሉና እንዳይዘረፉ ለመከላከል በሞከሩ ሰዎች መካከል ግጭት በመነሳቱ፣ የክልሉ ልዩ ኃይልና የፌዴራል ፖሊሶች ግጭቱን ለመቆጠጠር በወሰዱት ዕርምጃ አስለቃሽ ጭስ እንደተኮሱና የማቁሰል አደጋም እንዳደረሱ ኃላፊው አክለዋል፡፡

የቅዳሜው ሁነት በዚህ ሳያበቃ ከጂንካ ከተማም ውጪም ተዛምቶ እንደ ጋዘር፣ ቶልታና ሜፅር ባሉ አካባቢዎች ቤቶች ሲቃጠሉና ሱቆች ሲዘረፉ፣ እንዲሁም ሰዎች ወደ ጫካ ሲሸሹ እንደበር የገለጹት አቶ መላኩ፣ የአካባቢው ገበሬዎችና የፀጥታ ኃይሉ ቅዳሜ ዕለት ለሊቱን የተኩስ ልውውጥ ሲያደርጉ ማደራቸውን አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ቅዳሜ የነበረው ሁኔታ አደገኛ ነበር፤›› ካሉ በኋላ፣ የመከላከያ ሠራዊት ቅዳሜ ሌሊት ወደ ጅንካ መግባቱን አስረድተዋል፡፡

እሑድ ሚያዝያ 2 ቀን 2014 ዓ.ም. ጂንካ፣ ጋዘር ወረዳ ከተማ፣ ሜፅር ማዘጋጃ፣ ቶልታ ማዘጋጃ፣ በርካ ቀበሌ፣ ውባመር ቀበሌ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተጥሎ ምንም ዓይነት የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ መታገዱንና ነዋሪዎች መንቀሳቀስ የሚችሉት ከንጋት 12፡00 እስከ ምሽት 2፡30 ብቻ እንዲሆን መደረጉን አቶ መላኩ ተናግረዋል፡፡ በዚሁ ዕለት የመከላከያ ሠራዊት ሁኔታውን በመቆጣጠሩ የተዘጉ መንገድና ሱቆች በመጠኑ እንደተከፈቱና ለዜጎች ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማድረስ መሞከሩን ገልጸዋል፡፡ ሰኞ ዕለትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተሻሽሎ ባለሦስት እግር ተሸከርካሪዎች፣ ማክሰኞ ዕለት ድግሞ ባለሁለት እግር ተሸርካሪዎች እንዲንቀሳቀሱ መፈቀዱን አስረድተዋል፡፡

እስካሁን 979 ቤተሰቦች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸው ቢታወቅም፣ ግጭቱን በመሸሽ በጫካ ውስጥና በሌሎች ቦታዎች የተጠለሉ ሰዎች ብዛት ከዚህም እንደሚበልጥ ገልጸዋል፡፡ ዞኑም የተፈናቀሉ ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ ከውኃ፣ ጤና፣ ግብርናና ሌሎች ተቋማት የተወጣጣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን መላኩን አስታውቀዋል፡፡

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...