Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ከደቡብ ክልል ጋር የሚያደርገው የሀብት ክፍፍል እንደዘገየበት ገለጸ

ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ከደቡብ ክልል ጋር የሚያደርገው የሀብት ክፍፍል እንደዘገየበት ገለጸ

ቀን:

  • በደቡብ ክልል ሌሎች አዲስ ክልሎች ሲቋቋሙ ክፍፍል ለማድረግ ማቀዱን አስታውቋል

ቀድሞ በደቡብ ክልል ውስጥ የነበሩ አምስት ዞኖችና አንድ ልዩ ወረዳን ይዞ በኅዳር በወር 2014 ዓ.ም. የተመሠረተው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል፣ ቀድሞ በነበረበት ደቡብ ክልል ውስጥ ያሉ ተቋማትን ሀብት የመከፋፈሉ ሥራ መዘግየቱን አስታወቀ፡፡ ከአምስት ወራት በፊት የተመሠረተው ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ሲመሠረት ከተደረገው የበጀት፣ የተሽከርካሪና የሠራተኞች ክፍፍል ውጪ እስካሁን ምንም ዓይነት የሀብትም ሆነ የዕዳ ክፍፍል እንዳልተደረገ አስታውቋል፡፡ 

ክልሉ፣ በደቡብ ክልል ጥያቄ መሠረት ከሦስት ወራት በፊት ያለውን ሀብትና ዕዳ የሚያጠና ኮሚቴ አዋቅሮ መላኩን ለሪፖርተር የተናገሩት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፣ ነገር ግን ኮሚቴው እስካሁን ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አለማድረጉን አስረድተዋል፡፡ የተዋቀረው ኮሚቴ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ያላቸውን ሀብትና ትርፍ፣ ቋሚ፣ አላቂና ተንቀሳቃሽ ንብረት የመለየት ሥራ መሥራት እንደነበረበት ያስረዱት ነጋሽ (ዶ/ር)፣ ይህንን መነሻ በማድረግ ሦስቱም ክልሎች ‹‹የተቋማቱ ዕጣ ፋንታ ምን ይሁን?››፣ በጋራ ይተዳደሩ ወይስ ይከፋፈሉ የሚለውን የውሳኔ ሐሳብ ማቅረብ እንደነበረበት አብራርተዋል፡፡ ደቡብ ክልል የራሱን ኮሚቴ ማወቀሩን አስታውቆ፣ ሌሎቹም ክልሎች ኮሚቴ እንዲያዋቅሩ ከጠየቀ በኋላ ክፍፍሉን ለማስፈጸም ‹‹ወደኋላ እያለ ነው›› ብለዋል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የተመሠረተው መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም. በተደረገው ሕዝበ ውሳኔ በክልልነት የመደራጀቱ ሐሳብ ከ98 በመቶ በላይ የሆኑ መራጮችን ድምፅ በማግኘት ሲሆን፣ በአንድ ላይ የተሰበሰቡ የካፋ፣ የሸካ፣ የቤንች ሸኮ፣ የዳውሮና የምዕራብ ኦሞ ዞኖች፣ እንዲሁም የኮንታ ልዩ ወረዳ በኅዳር ወር በይፋ ክልል መሥርተዋል፡፡

የደቡብ ክልል ከሕዝበ ውሳኔው ውጤት መታወቅ በኋላ ካወጣው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ የሕዝበ ውሳኔ ውጤት አፈጻጸም ጋር ተያይዞ የሚነሱ አስተዳደራዊና ሕጋዊ ጉዳዮች የሚመራበት ሥርዓት የውሳኔ ሐሳብ (ሞሽን) አንቀጽ ሰባት፣ ስለሀብትና የዕዳ ክፍፍል ሥርዓት ያትታል፡፡ የሞሽኑ አንቀጽ ሰባት ንዑስ አንቀጽ ሦስት በሁለቱ ክልሎች መካከል የሀብት ክፍፍል ሥርዓቱ ድርድርን መሠረት አድርጎ የሚከናወን ሆኖ፣ የሕዝብ ቁጥርን ወይም ቀመርን ወይም አስተዳደራዊ ወሰንን መሠረት በማድረግ ፍትሐዊ፣ ተመጣጣኝና ሚዛናዊ መርሆዎችን በተከተለ አኳኋን እንደሚፈጸም ደንግጓል፡፡ የዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ አራት በደቡብ ክልል መንግሥት ሥር የሚገኙ ተንቀሳቃሽ ያልሆኑ ንብረቶች ክፍፍልን በተመለከተ በሚገኙበት ሁኔታ፣ በመንግሥት የንብረት ሕግ ላይ መሠረት በማድረግ የሚተመንና የክፍፍል ሥርዓቱ እንደሚፈጸም ሲገልጽ፣ ንዑስ አንቀጽ አምስት ደግሞ የቋሚና የተንቀሳቃሽ ንብረቶች ሀብት ክፍፍል ከሕጉ ባሻገር በድርድርም ሊፈጸም እንደሚችል ደንግጓል፡፡

ሞሽኑ የሀብት ክፍፍሉ፣ ከክልሉ ምሥረታ በኋላ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ መፈጸም እንዳለበት ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ ባይኖርም፣ ዕዳን በተመለከተ ግን አንቀጽ ሰባት ንዑስ አንቀፅ ሰባት በደቡብ ክልል መንግሥት የሚገኙ ማናቸውም ዕዳዎች ክፍፍል ቀመርን መሠረት አድርጎ አዲሱ ክልል ሥራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እንደሚከፋፈሉ ደንግጓል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ሲደራጅ ያለው የሕዝብ ብዛት፣ ከደቡብ ክልል አጠቃላይ ሕዝብ ብዛት 19.4 በመቶውን የሚይዝ በመሆኑ፣ ከክልሉ ሀብትና ዕዳ ይህንኑ መጠን እንዲካፈል ተወስኗል፡፡ በዚህም ደቡብ ምዕራብ እስከ ኅዳር 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ከደቡብ ክልል ጋር አብሮ ሲያወጣው ከነበረው ወጪ ቀሪ የሆነ ሀብት 19.4 በመቶ፣ የፌዴራል ድጎማ በጀትና 122 ተሽከርካሪዎችን ተካፍሏል፡፡

ክልሉ በደቡብ ክልል ውስጥ በነበረበት ወቅት አብሮ ያፈራቸው ሌሎች ሀብቶችን በተመለከተ እስካሁን ክፍፍል አለመደረጉን የሚያስረዱት ነጋሽ (ዶ/ር)፣ ክልሉ የቀሩ ሀብቶችን ክፍፍል ማድረግ ሰባት አባላት ያሉት ኮሚቴ ማዋቀሩን አስታውሰዋል፡፡ ይሁንና በክልሉ ተዋቅሮ የተላከው ኮሚቴ ምንም ዓይነት ሥራ ሳይሠራ ሦስት ወራት ማለፋቸውን ገልጸው፣ ለደቡብ ክልል ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብም ምላሽ አለመገኘቱን አስታውቀዋል፡፡

ነጋሽ (ዶ/ር) የሀብት ክፍፍል ባለመደረጉ የተነሳ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል እየተቸገረ መሆኑን ተናግረው፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን የማዘዝ ሥልጣን ያለው ደቡበ ክልል በመሆኑ፣ ተቋማቱ የልማት ሥራዎችን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል እንዲሠሩ ማድረግ አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡ በደቡብ ክልል ውስጥ ይገኛሉ ከተባሉት የልማት ድርጅቶች ውስጥ የደቡብ ዲዛይንና ግንባታ ቁጥጥር፣ ድርጅት የደቡብ ገጠር መንገድ ሥራዎች ድርጅት፣ እንዲሁም የደቡብ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ይገኙበታል፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅት ባልሆኑ የመንግሥት ተቋማት ውስጥም እንደ የመንግሥት ቢሮና ሕንፃ፣ የመገልገያ ቁሳቁሶች፣ ማሽነሪ፣ የላቦራቶሪ ዕቃዎች፣ የአይሲቲ መሣሪያዎች፣ የቅየሳ መሣሪያዎች ጭምር ክፍፍል እንዳልተደረገባቸው የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ‹‹በእያንዳንዱ ካቢኔ ቢሮና ተጠሪ ተቋማት ውስጥ ያለው ሀብት ቀላል አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ሀብቱን ብቻውን እያስተዳደረ ያለው ደቡብ ክልል ነው፣ ሁለቱ ክልሎች ግን ከዚህ ውጪ ነን፤›› ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ሁለቱ ክልሎች ደርሻቸውን ሊያገኙ እንደሚገባ ካልሆነም በጋራ እንዲያስተዳድሩ መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት ኅዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም. በተደረገው ሕዝበ ውሳኔ 98.5 በመቶ ድምፅ በማግኘት አሥረኛ የኢትዮጵያ ክልል ሆኖ የተደራጀው ሲዳማ ክልል ራሱን ችሎ ሲወጣ፣ ባለው የሕዝብ ብዛት መጠን የደቡብ ክልልን 20 በመቶ ድርሻ እንዲወስድ ተወስኗል፡፡ በዚህም መሠረት ከፌዴራል የድጎማ በጀት 20 በመቶውንና በክልሉ ካሉ ተሽከርካሪዎችም 20 በመቶውን ማለትም 168 ተሽከርካሪዎች የተቀበለ ሲሆን፣ እንደ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሁሉ ከዚህ ውጪ ያሉ ሀብቶች ላይ ክፍፍል እንዳላደረገ የሲዳማ ክልል የፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታመነ ተሰማ ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡ ኃላፊው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የተመሠረተው፣ የሲዳማ ክልል ሌሎች ቀሪ ሀብቶችን ለመከፋፈል በሒደት ላይ እያለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ተንቀሳቃሽ የሆኑና ያልሆኑ ንብረቶችን በተመለከተ እስካሁን ምንም ዓይነት አቅጣጫ አለመቀመጡን የሚናገሩት አቶ ታመነ፣ በልማት ድርጅቶች ላይ ግን የሀብትና ዕዳ ልየታ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ክፍፍል ይደረግበት የተባለውን ሀብት የያዘው የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በበኩሉ በክልሉ ያሉ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ሀብትና ዕዳ ክፍፍል የተመለከቱ ቅድመ ሥራዎችን ለመሥራት፣ ከሦስቱ ክልሎች የተዋቀሩት ኮሚቴዎች ሥራ ላይ ናቸው ብሏል፡፡  እነዚህ ኮሚቴዎች የተዋቀሩት ይህንን ሥራ ለመምራት በሞሽን በተቋቋመው ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት መሠረት በመሆኑ ኮሚቴዎቹ ሀብቶቹን የመመዝገብ፣ የማደራጀት፣ የመሰነድና የመለየት ኃላፊነት እንዳላቸው የክልሉ የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

አቶ ተፈሪ እንደሚያስረዱት እነዚህ ኮሚቴዎች ይኼንን ሥራ እየሠሩ የሚቆዩ ቢሆንም፣ የሀብት ክፍፍሉ ሊደረግ የታሰበው ክልል ለመሆን ጥያቄ እያቀረቡ ካሉ ሌሎችም ዞኖች ጋር አብረው ነው፡፡ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ዞኖችን የክልልነት ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ የልማት ድርጅቶቹን ሀብት አሁን ከሲዳማና ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ጋር የመከፋፈል ሒደት አስቸጋሪ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጿል፡፡

አቶ ተፈሪ፣ ‹‹በደቡብ ክልል የቀሩ ዞኖችም ይህንን ጥያቄ እያነሱ ስለሆነ፣ ሕዝቡ በዚህ መልክ እንደራጅ ሲሉ አጠናቀን አብረን እንወስናለን ብለን ነው ያሰብነው፤›› ብለው፣ ይህም በ2015 በጀት ዓመት ይከናወናል የሚል እምነት እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡ የደቡብ ክልል የመንግሥት የልማት ድርጅቶችም ቢሆኑ በአዲሶቹ ክልሎች ውስጥ ያለ ገደብ እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና ሲዳማ ክልሎች ግን ሌሎች የክልሉ ዞኖች ወደ ክልልነት ሲያድጉ፣ በጋራ የሀብትና የዕዳ ክፍፍል ይደረጋል የሚለውን ሐሳብ እንደማይቀበሉ ተናግረዋል፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሁለቱም ክልሎች ባለሥልጣናት ከሁለቱ ክልሎች ጋር የሚደረገው ክፍፍል አሁንም ማድረግ እንደሚቻል ገልጸው፣ ደቡብ ክልል ለሁለቱ ክልሎች ክፍፍል ካደረገ በኋላ የሚቀረውን ሀብት በቀጣይ ክልል ከሚሆኑ መዋቅሮች ጋር መካፈል እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ (ዶ/ር)፣ ሌሎች ዞኖች ክልል ሆነው የመውጣታቸው ጉዳይ ላይ እርግጠኛ ሆኖ መናገር እንደማይቻል ከተናገሩ በኋላ፣ ‹‹ደቡብ ክልል ከልማት ድርጅቶቹ ብቻውን እየተጠቀመ ነው፤›› የሚል ወቀሳ ሰንዝረዋል፡፡

የደቡብ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ፣ ደቡብ ክልል ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ብቻውን እየተጠቀመ ነው የሚለውን ሐሳብ አጣጥለውታል፡፡ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ኪሳራ ላይ ያሉና የሠራተኞቻቸውን ደመወዝ መክፈል የማይችሉ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ‹‹ክልሉ እንኳን ለብቻው ሊጠቀም ለደመወዝ ክፍያ ድጎማ እያደረገ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ይልቁንም ክልሉ የሲዳማ ክልል ሲደራጅ ከራሱ በጀት የሠራተኞቹን ደመወዝ ሲከፍል እንደቆየ፣ አሁንም ቢሆን ከአመራር ውጪ ላሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ሠራተኞች ደመወዝና የደረጃ ዕድገት እየሰጠ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል አዲስ እንደ መሆኑ እንደ ቢሮ ያሉ መሠረተ ልማቶች ማግኘት አስቸጋሪ ሊሆንበት እንደሚችል ጠቅሰው፣ ‹‹ደቡብ ክልል እንዲያውም ካለው ላይ አሳልፎ እየሰጠ ነው፤›› ብለዋል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...