የአትክልትና ፍራፍሬ ኤክስፖርት ዝቅተኛ መሸጫ ዋጋ ላይ ጭማሪ ከተደረገና ይህም ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ከ15 ቀናት በኋላ ተግባራዊነቱ ለተወሰነ ጊዜ እንዲዘገይ ተወሰነ።
ባመዛኙ ወደ ጎረቤት አገሮች ለዓብነትም ወደ ጅቡቲና ሶማሊያ እንዲሁም ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ኤክክፖርት የሚደረጉ የአትክልትና ፍራፍሬ ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ ወለል ላይ የዋጋ ማስተካከያ ጭማሪ እንዲደረግ የግብርና ሚኒስቴር በመወሰን ይህንኑ ውሳኔውን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታውቆ ነበር።
ብሔራዊ ባንክ በበኩሉ የግብርና ሚኒስቴርን ውሳኔ መነሻ በማድረግ ለሁሉም ባንኮች መጋቢት 16 ቀን ባስተላለፈው የሥራ መመሪያ አትክልትና ፍራፍሬ ላይ የተደረገውን የዋጋ ማስተካከያ አስታውቆ ነበር።
ብሔራዊ ባንክ ለሁሉም ባንኮች በሰጠው የሥራ መመሪያ አትክልትና ፍራፍሬ ኤክስፖርት ላይ የተደረገው ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ ማስተካከያ እ.ኤ.እ. ከኤፕሪል 1 ቀን 2022 ጀምሮ ወደ ትግበራ እንደሚገባ ጠቅሷል።
በመሆኑም ማንኛውም የአትክልትና ፍራፍሬ ኤክስፖርተር ከተሻሻለው ዝቅተኛ ዋጋ በታች መሸጥ እንደማይችል እንዲሁም ሁሉም ባንኮች ከተቀመጠው ዋጋ በታች የባንክ ፐርሚት መፍቀድ እንደማይችሉ አስታውቋል።
በመሆኑም የአትክልት፣ ፍራፍሬና ዕፀ ጣዕም ምርቶች በተስተካከለው ዝቅተኛ መሸጫ ዋጋ እ.ኤ.አ. ከ ኤፕሪል 1 ቀን ጀምሮ ኤክስፖርት መደረግ ከተጀመረ በኋላ የግብርና ሚንስቴር የዋጋ ማስተካከያው ተግባራዊነት ለተወሰነ ጊዜ እንዲዘገይ ወስኗል።
ግብርና ሚንስቴር ይህንኑ ውሳኔውን ለብሔራዊ ባንክ መጋቢት 29 ቀን 2014 ዓ.ም. በላከው ደብዳቤ አስታውቋል።
‹‹የዋጋ ማሻሻያው ትግበራ የሽግግር ጊዜ የሚያስፈልገው ሆኖ ስለተገኘ፣ የተሻሻለው ዋጋ ትግበራ እ.ኤ.አ. እስከ ሜይ 15 ቀን 2022 ድረስ እንዲዘገይ እንጠይቃለን፤›› ሲል በግብርና ሚኒስትሩ ኡመር ሁሴን ተፈርሞ የተላከው ደብዳቤ ላይ ምክንያቱ ተመላክቷል።
በዚሁ ጥያቄ መሠረት የኤክክፖርት ምርቶቹ ቀድሞ በነበረው ዝቅተኛ መሸጫ ዋጋ ኤክስፖርት የሚደረጉ ይሆናል።
እንደ ምንጮች ገለጻ አዲሱ የአትክልትና ፍራፍሬ የወጪ ንግድ ዋጋ በጂቡቲ በኩል ቅሬታ በማስነሳቱ ለስምንት ቀናት አትክልትና ፍራፍሬ ወደ ጂቡቲ ሳይላክ ቀርቷል፡፡
በአዲሱ ዋጋ ላይ የጂቡቲ ንግድና ቱሪዝም ሚኒስቴር ያለውን ቅሬታ ጂቡቲ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አቅርቦ፣ ኤምባሲውም ጉዳዩ እንዲታይ ለኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር በደብዳቤ ማሳወቁና ይህ ደብዳቤ ከተጻፈ በኋላ ብሔራዊ ባንክ ያወጣው መመሪያ ይዘግይ ለመባሉ ዋናው ምክንያት ይኸው የጂቡቲ ቅሬታ ሳይሆን እንዳልቀረ ታምኗል፡፡
የጂቡቲ ንግድና ቱሪዝም ሚኒስቴር የዋጋ ማሻሻያው የጅቡቲን የመግዛት አቅም ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ጋር ያነፃፀረ መሆኑና የዋጋ ማሻሻያው ተግባራዊ መደረግ የተጀመረው የረመዳን ፆም በጀምርበት ወቅት መሆኑ ትክልል እንዳልሆነ በመጥቀስ፣ ቅሬታውን ለኢትዮጵያ መንግሥት እንዳስታወቀ ሪፖርተር ከተመለከታቸው የደብዳቤ ልውውጦች ለመረዳት ችሏል።
የጅቡቲ መንግሥት የዋጋ ጭምሪው ላይ ላነሳው ቅሬታ የጠቀሳቸው ሌሎች ምክንያቶች ደግሞ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለው የኢኮኖሚ ጉዳትና በሩሲያና በዩክሬን ጦርነት ያስከትለው የዋጋ አለመረጋጋት ይጠቀሳሉ።
በተጠሱት ምክንያቶችና ጅቡቲ 80 በመቶ የሚሆነውን የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት የምታገኘው ከኢትዮጵያ መሆኑንና ከላይ በተገለጹት ምክንያቶች የዋጋ ጭማሪው በጅቡቲ ላይ ተፈጻሚ እንዳይሆን የአገሪቱ መንግሥት መጠየቁን ለማወቅ ተችሏል።
በግብርና ሚኒስቴርም የዋጋ ጭማሪው ተግባራዊነት በአጠቃላይ እንዲዘገይ የወሰነውና ይህንንም ለብሔራዊ ባንክ ያስታወቀው ከዚህ የጂቡቲ ቅሬታ በኋላ መሆኑንም እየተገለጸ ነው፡፡
የግብርና ሚኒስቴር የአትክልት፣ ፍራፍሬና ዕፀ ጣዕም የወጪ ንግድ ዋጋን ማሻሻል ያስፈለገው ባደረገው ጥናት መሠረት በጎረቤት አገሮችና መካከለኛው ምሥራቅ የፍጆታ ፍላጎትና የመግዛት አቅም ማደጉ ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋውን ለማሻሻል መሠረታዊ ምክንያት እንደሆነ ይገልጻል።