በመደበኛው የፖለቲካ ስያሜ ከሚጠሩት ሦስት የመንግሥት አካላት ማለትም ሕግ አውጭ፣ ሕግ ተርጓሚና ሕግ አስፈጻሚ አካላት በተጨማሪ የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ በሚያበረክተው አስተዋጽኦና ሚና እንደ አራተኛ መንግሥት ይቆጠራል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ የዴሞክራሲ ሥርዓትን የሚያጠናክሩና አላሠራ ካሉ ሕግጋት መካከል እንደገና ከተሻሻሉት ውስጥ፣ በመጋቢት 2013 ዓ.ም. ፀድቆ ወደ ሥራ የገባው የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ይገኝበታል፡፡
በዚህ አዋጅ መሠረት አሁን በሥራ ላይ ያለውን የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በበላይነት የሚቆጣጠሩ ዘጠኝ ገለልተኛ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት እንደሚሾሙ አስቀምጧል፡፡ ለሥራ አመራር ቦርድ ዕጩዎቹን የመመልመልና የማፅደቅ ሒደት ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ እንደሚከናወን፣ ሕዝብ ዕጩዎችን በመጠቆምና በዕጩዎች ላይ አስተያየቶች እንዲሰጥ ዕድል እንደሚሰጠው ይደነግጋል፡፡
በተጨማሪም የሥራ አመራር ቦርድ የዕጩዎቹ ዝርዝር በመገናኛ ብዙኃን ወይም በሌሎች የኤሌክትሮኒክ ማሠራጫዎች ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ በአዋጁ ተብራርቷል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 11 ንዑስ አንቀጽ 6 መሠረት የሥራ አመራር ቦርድ አባላት የፖለቲካ ፓርቲ አባል ወይም ተቀጣሪ መሆን እንደሌለባቸው ይገልጻል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 29 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው ስድስተኛ መደበኛ ስብሰባ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተሰየሙ ዘጠኝ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የቦርድ አባላትን በስብሰባው ከተገኙ 243 የምክር ቤቱ አባላት መካከል በ11 ተቃውሞና በ17 ድምፀ ተዓቅቦ በአብለጫ ድምፅ ሹመቱን ማፅደቁ ይታወሳል፡፡
በፓርላማው ሹመታቸው ከፀደቀላቸው ዘጠኝ የቦርድ አባላት መካከል ለአብነትም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር)፣ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባል የሆኑት አጋረደች ጀማነህ (ዶ/ር) የብልፅግና ፓርቲ አባል ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ የቦርድ አባላት ሀሰን አብዱልቃድር (አምባሳደር)፣ በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር)፣ መሳይ ገብረ ማርያም (ዶ/ር)፣ ወዳጄነህ መሀረነ (ዶ/ር)፣ ቀሲስ ታጋይ ታደለ፣ ኡስታዝ ያሲን ኑሩና ናሲሴ ጫሊ (አምባሳደር) ናቸው፡፡ የተወሰኑት የቦርዱ አባላት የፓርቲ አባል ከመሆን ባላፈ ከጅምሩ የተሾሙት ግለሰቦች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተመርጠው የመጡ እንጂ፣ አዋጁ በሚለው መሠረት ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ ጥቆማና አስተያየት ተሰጥቶባቸው የመጡ አለመሆናቸው ሌላው የቅሬታ ምንጭ ነው፡፡
በዚህ መካከል ፓርላማው አዋጁን በመጣስ ሹመት በማፅደቁ ውሳኔውን እንደገና ይመለስና ይመልከት፣ ካልሆነ ግን የቦርድ አባላቱ ሕጋዊነት ጥያቄ ከመግባቱ ባለፈ ከጅምሩ ከአንድ ዓመት በፊት የፀደቀው የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ነፃና ገለልተኛ ሆኖ እንዲቋቋም በሚል የቀረበው ምክንያት በከንቱ ነበር የሚሉ የዘርፉ ተቆርቋሪቋዎች በዝተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ሚያዝያ 3 ቀን 2014 ዓ.ም. የቦርድ አባለቱን ሹመት በተመለከተ ባወጣው መግለጫ፣ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ላይ ቦርዱንም ሆነ ባለሥልጣኑን የሚመሩት ግለሰቦች ከፓርቲ አባልነትና ወሳኝ ከሆነ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ነፃ እንዲሆኑ ከፍተኛ ትግል የተደረገበት ቢሆንም፣ ባለፈው ሳምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቦርድ አባላት ሹመት በአዋጁ ከተቀመጠው ድንጋጌ ያፈነገጡ መሆኑን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
አዋጁ የዕጩዎች ምልመላ የኢትዮጵያን ብዝኃነት ያማከለ ፌደራላዊ ውክልና እንዲኖረው ይደረጋል ቢልም፣ ይህ አለመደረጉና በመገናኛ ብዙኃንም ሕዝቡ እንዲጠቁም ዕድል እንዳልተሰጠው፣ አስተያየትም አለመሰጠቱንና አንዳንድ የፓርላማ አባላት ይህንኑ በተመለከተ ላነሷቸው ጥያቄዎች በምክር ቤቱ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር የሰጧቸው ምላሾች ተገቢ ሆነው እንዳላገኟቸው አክሎ አብራርቷል፡፡
በምክር ቤቱ የተሾሙ የቦርድ አባላት ሰብሳቢውን ጨምሮ ሌሎች አባላት የብልፅግና ፖርቲ አባላት ብቻ ሳይሆኑ፣ ቁልፍ የመንግሥት ሥልጣን ላይ የተቀመጡ ግለሰቦች መሆናቸው በመግለጫው አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም ከተሾሙት ግለሰቦች መካከል አንድም የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያ አለመካተቱን፣ በመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ አግባብነት ካላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በሚለው መሥፈርትም እነማን እንደተመረጡ ግልጽ አለመሆኑን፣ እንዲሁም ከሲቪክ ድርጅቶች እንዲካተቱ የተመረጡት ሁለት ግለሰቦችም ከ3,000 በላይ የሲቪክ ድርጅቶች ባሉበት አገር ሁለቱም ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ መሆናቸው የአዋጁን መንፈስ የሚቃረን ሆኖ እንዳገኘው ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡
ከፍተኛ ትግልና ተሳትፎ ተደርጎበት የወጣው የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ግልጽ የሆነ የሕግ ጥሰት ሲገጥመው መከላከል የዘርፉ ተዋንያን ብቻ ሳይሆን፣ የሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ድርሻ በመሆኑ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የቦርድ አባላት ሕገወጥ አመላመልና የአሿሿም ሥርዓት እንዲታረም ምክር ቤቱ ጠይቋል፡፡
ጉዳዩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸው አካላትም ይህ ሕግን የተፃረረ አካሄድ እንዳይደገምና ልምድ ሆኖ በመንግሥት ሥርዓት ውስጥ እንዳይቀጥል ድምፅ ያሰሙ በማለት ጥሪ ያቀረበው ምክር ቤቱ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ሹመቱ በአዋጁ መሠረት እንዲከናወን በደብዳቤ ማሳወቁን አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር ቅዳሜ ሚያዚያ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. የቦርድ አባላት ሹመትን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፣ የቦርድ አባላቱ ሹመት መጋቢት 2013 ዓ.ም. የፀደቀውን የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 ድንጋጌዎች የጣሰ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ለአብነትም የቦርድ አባላት ዕጩዎችን የመመልመልና የማፅደቁ ሒደት፣ እንዲሁም የቦርድ አባላት የተመረጡበት መሥፈርት ግልጽ አለመሆንና አዋጁን በመፃረር የፖለቲካ ፓርቲ አባላት የቦርዱ አባል መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
በመሆኑም የፓርላማው ውሳኔ የቦርድ አባላት ሥራቸውን ሲያከናውኑ ከፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጣልቃ ገብነት ወይም ተፅዕኖ ገለልተኛና ነፃ መሆን አለባቸው በሚለው ድንጋጌ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ የሚያሳድር ከመሆኑም በላይ፣ ድንጋጌውን የሚፃረር ተጨማሪ ስህተት መሆኑን በመግለጫው አትቷል፡፡
ይህ ግልጽ የሆነና የማያሻማ የሕግ ጥሰት ያለበት፣ የሚዲያ ዕድገትን በእጅጉ የሚጎዳ እንደሆነና ሕዝብም በሕግ አውጭው ተቋም ላይ እምነት እንዳይኖረው የሚያደርግ መሆኑን አመላክቷል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያፀደቃቸውን አዋጆችንና ድንጋጌዎችን ተፈጻሚነታቸውን በትኩረት መከታተል ስለመቻሉ ጥያቄ የሚያጭር›› መሆኑን በመግለጽ፣ ፓርላማው ውሳኔውን የሚያጤንበትን አማራጭ በድጋሚ እንዲመለከት ጠይቋል፡፡
የቁምነገር መጽሔት ዋና አዘጋጅና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ ታምራት ኃይሉ፣ የቦርድ አባላቱ ሹመት ከምልመላው ጅምሮ ስህተት የተፈጸመበት አካሄድ መሆኑንና በአዋጁ ከተቀመጡት መሥፈርቶች ያፈነገጠ ውሳኔ ነው ብለዋል፡፡
በመሠረቱ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ እንዲሻሻል ካደረጉት ምክንያቶች መካካል አንዱ ገለልተኛ የተቋም ኃላፊዎችና የቦርድ አመራሮች እየተሾሙለት ባለመሆኑ ምክንያት እንደሆነ በመጠቆም፣ ለዚህም ተቋሙ ነፃና ገለልተኛ እንዲሆን ከአዋጁ ዝግጅት ጀምሮ ብዙ ጥረቶች መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ ከሰሞኑ በፓርላማው የታየው የሕግ ጥሰት የፖለቲካ አባል መሆን ብቻ ሳይሆን፣ ቁልፍ የመንግሥት ተቋማትን የሚመሩ የመንግሥት አካላትና የብልፅግና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑ ግለሰቦች መሾማቸው ከዓመታት በፊት ይህንኑ ተቋም በእነ አቶ በረከት ስሞኦን ሲመራ እንደነበረው ሁሉ ያንን ስህተት የመድገም አባዜ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
‹‹በብልፅግና ፓርቲ ተመርጠው የገቡ የቦርድ አባላት ባሉበት ተቋሙ እንዴት ብሎ ገለልተኛ ሊሆን እንደሚችል ግራ የሚያጋባ ስለሆነ፣ ትልቅ የሆነ የሕግ ጥሰት የተፈጸመበት በመሆኑ እንዲስተካከል እንፈልጋለን፤›› ብለዋል፡፡
ጉዳዩ የሚዲያ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ለሕግ የበላይነት ቆሜያለሁ የሚሉ ሁሉ ሊከራከሩለት እንደሚገባ የጠየቁት አቶ ታምራት፣ ይህ ውሳኔ በዚሁ እንዲቀጥል ከተፈቀደ ግን በአዋጁ እንደተቀመጠው ነፃና ገለልተኛ የሚዲያ ተቆጣጣሪ ተቋም እንዳይኖር የሚያደርግና የመንግሥት አጀንዳን የሚደግፉ ሚዲያዎች በነፃ እንዲንቀሳቀሱና የመንግሥትን የተሳሳተ አካሄድ የሚገመግሙትን ደግሞ መቅጣት ላይ የሚያተኩር እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ከፍተኛ አማካሪው አቶ እሸቱ ገለቱ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የመገናኛ ብዙኃን አዋጁ ገና ከጅምሩ ከመፅደቁ በፊት ሙያተኞች እየተሰበሰቡ ከአሥር ጊዜ በላይ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
ይህ ውይይት በመሠረታዊነት ሊደረግ የታሰበው ከዚህ በፊት ከነበረው አሠራር በፍፁም ለመላቀቅ በማሰብ እንደነበር፣ በተለይም በመገናኛ ብዙኃንን አሠራር ውስጥ እንዲህ ዓይነት ሹመት የሚሰጣቸው ግለሰቦች የመንግሥት ጡንቻ ማሳያ እንደነበሩ አቶ እሸቱ አውስተዋል፡፡ አዋጁ ከመነሻው እንዲሻሻል ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት ከዚህ ቀደም የነበረው አዋጅ የነበረበት አሳሪ ችግር እንዲቀረፍ ተብሎ በመሆኑ፣ አሁንም የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣንም ሆነ የሥራ አመራር ቦርድ አባላቱ ነፃ ሆነው ካልተቋቋሙ የአዋጁ ሚና ምንም ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ሕግ አውጭው አካል ሕግ ሲጥስ መገናኛ ብዙኃንም ሆኑ ሌሎች ይመለከቱኛል የሚሉ አካላት ይህንን ጉዳይ የሕዝብ አጀንዳ ማድረግ እንደሚገባቸው አቶ እሸቱ ተናግረዋል፡፡ ውሳኔው ከመነሻው የአዋጁን ዓላማ የሚጣረስ በመሆኑ፣ ‹‹ሁሉም ድምፁ እስኪሰማ ድረስ መጮህ አለበት፣ በዚህ ዓይነት ሕግ የጣሰ አካሄድ የት ሊጥለን ይችላል?›› ብለዋል፡፡
የፓርላማውን ውሳኔና የቦርድ አባላቱን ስብጥር በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕግና አስተዳደር መምህሩ አቶ አሮን ደጎል፣ አዋጁ ሲታይ በእርግጥ ቦርዱ ይቅርና ባለሥልጣኑ ራሱ ተግባርና ኃላፊነቱን ሲወጣ ከማንኛውም ዓይነት አግባብነት ከሌላቸው ከተቋሙ ኃላፊነቶች ጋር ከማይሄዱ ፍላጎቶችና ተፅዕኖዎች ጋር ገለልተኛ መሆን እንዳለበት በግልጽ ያስቀምጣል ብለዋል፡፡ በተለይም ከመንግሥት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከሚቆጣጠረው የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ፣ ከንግድና ከሌሎች ማኅበራዊ ቡድኖችና ተቋማት ጋር ተቋሙ አራምዳቸዋለሁ ብሎ ከሚያስባቸው ተግባራት ውጪ ካሉ ፍላጎቶች በነፃ መንቀሳቀስ እንዳለበት እንደሚገልጽ፣ ተቋሙ ገለልተኛ መሆን አለበት ከተባለ በተቋሙ ውስጥ ያለ ማንኛውም አካል ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ነፃ መሆን ይኖርበታል ብለዋል፡፡
በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ላይ የቦርድ አባላት ዕጩዎችን የመመልመልና የማፅደቁ ሒደት ሲታይ ሕዝቡ ዕጩ ግለሰቦችን የመጠቆምና በዕጩዎች ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ዕድል እንዲሰጠው ይደረጋል ተብሎ መደንገጉ፣ የአማራጭ ጉዳይ ሳይሆን በግድ በሕዝቡ መጠቆም እንዳለባቸው የሚያሳይ መርህ መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡
ይህ ማለት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሚና መምረጥ ሳይሆን፣ የቀረቡላቸውን ሰዎች በፓርላማው የማሾም ብቻ እንደሚሆን አቶ አሮን አክለዋል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዋጁ የተጠቀሱትን አሠራሮች ሳይከተሉ አቅርበው ከሆነ፣ የአዋጅ ጥሰት ተፈጽሟል ማለት ስለሚሆን እንደገና ጥቆማና ምልመላ ተካሂዶ ቦርዱ መሾም እንደሚኖርበት አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል ፓርላማው ራሱ የሚያወጣቸውን ሐጎች ማክበር የማይችል ከሆነ የፓርላማው ሕጋዊነት ላይ ጥያቄ ስለሚያስነሳ ራሱን ሊፈትሽ ይገባል ያሉት አቶ አሮን፣ ሁኔታው በዚሁ ዝም ብሎ ከቀጠለ ቦርዱ ሥራው ተዓማኒት ስለማይኖረው ተፈጻሚም አይሆንም፣ የተሾሙት ሰዎችም ሕጋዊ እንዳልሆኑ ስለሚታወቅ ተቀባይነት አይኖራቸውም፣ ለሥራቸውም ቢሆን አመቺ ሁኔታ አይፈጠርም ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በአዋጁ አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 1 እንደተደነገገው የቦርዱ አባላት ፆታዊ ተዋፅኦን ከግምት ውስጥ በማስገባት ተመርጠው በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚሰየሙ ዘጠኝ አባላት ይኖሩታል ሲል፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሚና የሥነ ሥርዓት (Ceremonial) እንደሚሆን የሚገልጽ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በኔዘርላንስ የሚኖሩትና በሕገ መንግሥትና ዴሞክራሲ ግንባታ ጉዳይ አማካሪ የሆኑት አደም ካሴ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የሕግ የባላይነት ሲባል ፓርላማው ራሱ ያወጣውን ሕግ ማክበር አለበት የሚለው ላይ መሰመር አለበት፡፡ በተለይ ደግሞ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና ለሚዲያው ማደግ ወሳኝ ከሆኑ ጉዳዮች አኳያ ምክር ቤቱ ሕግ መከተል አለበት እንጂ፣ እንዲያው ከአስፈጻሚው አካል የሚመጣውን ማስፈጸም ማለት የሚያሳየው ፓርላማው ራሱ ተቋማዊ ችግር እንዳለበት ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ፓርላማው ራሱን እንደቻለ ተቋም ከሕግ አስፈጻሚው ተለይቶ የሕግ ክፍል ኖሮት፣ ከአስፈጻሚው አካል የሚመጡ ነገሮችን በራሱ መንገድ እያብላላ የሚሄድበት አሠራር አለመኖሩንና ተቋማዊ ድክመት መኖሩን፣ እንደ ፓርላማ ራሱን ችሎ የማሰብ አቅም እንደሌለው የሚያመላክት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
‹‹በሌላ በኩል ፓርላማው ሥራ አስፈጻሚው ሲያጠፋ ይቆጣጠረዋል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ነገር ግን ፓርላማው እንዲህ ዓይነት ስህተት ሲሠራ አንደኛ በሕዝብ ተቃውሞ ይደርስበታል፡፡ ከዚያ አለፍ ሲልና ነገሮች የማይስተካከሉ ከሆነ ደግሞ ወደ ፍርድ ቤት ሄዶ ሁኔታውን መቃወም ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡
ፍርድ ቤቶችን በሥልት የመጠቀም ተቋማዊ አሠራር በመዘርጋት ውጤቱን የማይቀይረው እንኳ ቢሆን ከሚዲያ ሽፋን ወደ ሕጋዊ ጉዳይ ለማሳደግ የሚሠሩ ከሲቪክ ማኅበራት፣ ከተፎካካሪ ፓርቲዎችና ከሚዲያ ባለሙያዎች ማኅበራት ይህንን ጉዳይ ወደ ፍርድ ቤት መውሰድ አለባቸው ሲሉ አክለዋል፡፡
ስለዚህ ይህ ጉዳይ ዝም ብሎ መታለፍ የለበትም ያሉት ምሁሩ፣ ፓርላማውም ኃላፊነት እንዳለበትና እየተነሳ ያለውን ጉዳይ ስህተት ከሆነ ማረም እንደሚኖርበት፣ የማያርም ከሆነ ደግሞ በፍርድ ቤት መጠየቅ እንዳለበት አክለው ገልጸዋል፡፡
ፓርላማው ጭቅጭቅ ባስነሳው ጉዳይ ላይ መልስ አለመስጠቱ ትልቅ ስህተት መሆኑን የገለጹት አደም (ዶ/ር)፣ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ እንኳን የሕግ የበላይነት የሕግ ገዥነት የለም፤›› ብለዋል፡፡
አልፎ አልፎ እንዲህ ዓይነት የሕግ ስህተት ሊከሰት እንደሚችል የጠቆሙት አደም (ዶ/ር)፣ በዚህ ልክ ከፓርላማው ሲመጣ ሕዝቡ በሕግ ላይ የሚኖረው እምነት አሁንም የሞተ ስለሆነና ጭራሹንም ሊገድለው የሚችል በመሆኑ ጉዳዩ እንደ ቀላል መታየት የለበትም ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ስለዚህ የሚመለከታቸው አካላት የፖለቲካ ፓርቲዎችም ጭምር ይህ ጉዳይ ግልጽ የሕግ ጥሰትን የሚያሳይ በመሆኑ፣ ሕጋዊ ዕርምጃዎችን ተከትለው በፍርድ ቤት ሳይወሰንና ዕልባት ሳያገኝ ተፈጻሚ እንዳይሆን ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ መጠየቅ አለባቸው፣ መሆንም አለበት ብለዋል፡፡ ምናልባት ፍርድ ቤቶች እንኳ ባይስማሙ ጉዳዩን በትኩረት እንዲታይ ያደርገዋል በማለት ገልጸዋል፡፡
አክለውም ይህ የሚያሳየው ፓርላማው እንደ ተቋም ራሱን ያልቻለ መሆኑን፣ ካለው የፓርላሜንታዊ ልምድ ፓርላማው ብዙ ጊዜ ተቃዋሚዎችን መቆጣጠር እንጂ አስፈጻሚ አካሉን ሲቆጣጠር ስለማይታወቅ ክስተቱ የሚገርም አይደለም ብለዋል፡፡
አደም (ዶ/ር) እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የፓርቲ ጉዳይ ሳይሆን ከሕግ የበላይነት ጋር የሚያያዝ በመሆኑ፣ በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ ፓርላማው ራሱንም ያስገምተዋል ብለው፣ ምክንያቱም ቢያንስ ቢያንስ በራሱ ቁጥጥር ሥር ያሉ መሠረታዊ የሆኑ ጉዳዮችን በትክክል መፈጸም አለበት ሲሉ አሳስበዋል፡፡
‹‹ሕግ ማክበር ሥልጡንነት ነው፣ ምክንያቱም ሕግ ካለማክበር አመፅ ይፈጠራል፣ ሥልጣን በተወሰነ አካል ብቻ ይያዛል፣ ጉልበተኝነት ይስፋፋል፣ ሕዝብ ሥልጣን ላይ ባለው አካል ጥርጣሬን እንዲያሳድሩ ያደርጋል፣ አገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖራት ደርጋል፤›› ያሉት ደግሞ የሕግ ምሁሩ አቶ አምደ ገብርኤል አድማሱ ናቸው፡፡
ይህ ሕግ በአገሪቱ ያለው የሚዲያ ዘርፍ እንዲድግና እንዲሻሻል፣ ብዙ ገንዘብ ወጥቶበት በሕዝብ እንደራሴዎች የፀደቀ በመሆኑ ይህን የአገር ሕግ ሦስቱንም የመንግሥት አካላት የሚመለከት በመሆኑ በዝምታ ሊታለፍ እንደማይገባ አስረድተዋል፡፡
አንዳንዴ በስህተት፣ አልፎ አልፎ ደግም ሆነ ተብሎ ሕግ ሲጣስ ውሳኔዎች ውድቅ እንደሚደረጉ የጠቀሱት አቶ አምደ ገብርዔል፣ ይህ ውሳኔ ተፈጻሚ እንዳይሆን የሚመለከታቸው አካላት አቤት ማለት አለባቸው ብለዋል፡፡ ምናልባት ግን የፓርላማ አባላት እየቆዩ አንዴ ለስብሰባ እንደሚገናኙ በመጥቀስ፣ ለምክር ቤት የሚመጡ ውሳኔዎች ላይ መሥፈርቱ ምንድነው? ሥነ ሥርዓቱ ምን ይላል? አሠራሩ እንዴት ይተረጎማል? የሚሉትን ጉዳዮች ሁሉም የምክር ቤት አባል ላያውቁ ስለሚችሉ መንግሥት እንዲህ ዓይነት አሠራሮችን ለአባላቱ በግልጽ ማስረዳት እንዳለበት አብራርተዋል፡፡
ሕዝብ ከአዋጁ ውጪ የተሾሙ የቦርድ አባላት መሆናቸውን ካወቀና ካሰበ፣ በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸውን ሰዎች ማስቀመጡ ውጤቱ በሕዝብ ተቀባይነት ሊኖረው እንደማይችል አክለው ተናግረዋል፡፡
‹‹ዴሞክራሲ በድብቅ አያድግም፣ ዕድገት በዚህ ሁኔታ አይመጣም፣ ነገር ግን የሚፈለገው ለውጥ የሚመጣው ሕግን በመከተል በመሆኑ፣ ሕግን ማክበር ዘመናዊነትና አዋቂነት በመሆኑ፣ መንግሥት እንደ መንግሥትነቱ ለሕጎች መከበር ቅድሚያ መስጠት አለበት፣ ዜጎች ሕግ እንዲያከብሩ ቅድሚያ ራሱ መንግሥት አክብሮ ማሳየት አለበት፤›› ያሉት ምሁሩ፣ በሚጠበቀው ልክ ሆኖ አለመገኘት ደግሞ ከሕዝብ ጋር አለመተማመንን እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡ ፓርላማው እንደዚህ ዓይነት ውሳኔ የተላለፈባቸውን ጉዳዮች ለማየት ቢፈልግ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሠራርና የአባላት የሥነ ምግባር ደንብ ላይ በግልጽ መሥፈሩን አስረድተዋል፡፡
በደንቡ ውሳኔ የተሰጠበትን ጉዳይ እንደገና ስለማየት በሚያትተው አንቀጽ 49 መሠረት፣ ውሳኔን እንደገና ለማየት የሚያስችሉ ሦስት ጉዳዮች ተብራርተዋል፡፡ በዚህ መሠረት ምክር ቤቱ ውሳኔ ሲሰጥ የነበረው ጉድለት ታርሞ ወይም እንደገና ተሟልቶ ከቀረበ፣ ቀደም ሲል በተወሰነው ጉዳይ ላይ ምክር ቤቱ መሠረታዊ የሕግ ወይም የፍሬ ነገር ስህተት መፈጠሩ ከታወቀና መንግሥት በጉዳዩ ላይ በቂ ማብራሪያ በመስጠት እንደገና እንዲታይ ከጠየቀ መሆኑ ተገልጿል፡፡