Sunday, February 5, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአበባ አምራቾች ይፈቱልን የሚሏቸው ሁለቱ ማነቆዎች

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአሁኑ ወቅት ዋና ዋና ከሚባሉ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ምርቶች መካከል አንዱ የሆነው አበባ በመንግሥት እየወጡ ያሉ መመርያዎች ዘርፉ ላይ ተፅዕኖ እያሳረፉ እንደሆነ እየተገለጸ ነው፡፡

ከዘርፉ ተዋንያኖች እየተሰማ እንዳለው በቅርቡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የወጣው የአበባ የወጪ ንግድ የመሸጫ ዝቅተኛ ዋጋ ወለልና የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምን የሚመለከቱት መመርያዎች በዋናነት ተጠቅሰዋል፡፡ 

በተለይ የአበባ የወጪ ንግድና የዋጋ ተመንን በተመለከተ የኢትዮጰያ ብሔራዊ ባንክ ያወጣው መመርያ አሁን ባለበት ደረጃ መተግበር የለበትም በሚል የኢትዮጵያ አትክልትና ፍራፍሬ አምራችና ላኪዎች ማኅበር አቤት ብሏል፡፡ 

ተግባራዊ እንዲሆን በወጣው መመርያ መሠረት ኤክስፖርት ማድረግ አስቸጋሪ መሆኑን በመግለጽ መመርያው ይሻሻል ዘንድ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ለግብርና ሚኒስቴር ይህንኑ ቅሬታ ያገናዘበ አቤቱታውን ማኅበሩ እንዳቀረበ ታውቋል፡፡ 

ማኅበሩ በአበባ የወጪ ንግድ አዲሱ የዋጋ ተመን ላይ ያለውን ቅሬታና ሊያስከትል የሚችለውን ችግር በዝርዝር ቢያቀርብም፣ አሁን ባለው ሁኔታ ጉዳዩን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገረበት ከመሆኑ ውጪ ለጊዜው ተጨማሪ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ 

በአዲሱ መመርያ መሠረት አበባ ላኪዎች ከዚህ በኋላ የሚልኩበት የዋጋ መጠን በአማካይ 4.66 ዶላር እንደሆነ የተወሰነ ሲሆን፣ ይህም ቀድሞ ከነበረው ዋጋ 66 የአሜሪካን ሳንቲም ጭማሪ ያሳየ ነው፡፡ ይህ መመርያ እንዲተገበር ጥናቱን አዘጋጅቶ ለብሔራዊ ባንክ ያቀረበው የግብርና ሚኒስቴር ሲሆን፣ ማኅበሩም ሆነ የዘርፉ ተዋናዮች ግብርና ሚኒስቴር ጥናቱን በበቂ ሁኔታ አሰናድቷል የሚል እምነት የላቸውም፡፡ በዚህ መመርያ ቅሬታ ያላቸው አበባ ላኪዎች ለግብርና ሚኒስቴር እና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያላቸውን ቅሬታ አቅርበው በጉዳዩ ላይ ከሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ጋር በግንባር ሲነጋገሩበት መሰንበታቸው የታወቀ ሲሆን፣ ከዚህም በኋላ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ምክክር ያደርጋሉ ተብሎ እየጠበቀ ነው፡፡  

በኢትዮጵያ የአበባ ኢንቨስትመንት ውስጥ ከፍተኛ የገበያ ድርሻ እንዳለው የሚነገርለት የዝዋይ ሮዝ ፕሮዳክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ ሰለሞን ለሪፖርተር እንደገለጹት ደግሞ፣ በአሁኑ ጊዜ በዘርፉ ውስጥ ካሉ ዋና ዋና ችግሮች መካለከል አንዱ በቅርቡ በብሔራዊ ባንክ ያወጣው ዝቅተኛ የዋጋ ተመንን የተመለከተው መመርያ ነው፡፡ ይህ መመርያ ዘርፉ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ እንደሚችል ጠቁመው፣ በተለይ መመርያው ወቅቱን ባላገናዘበ ሁኔታ መውጣቱን ጠቁመዋል፡፡ 

የአበባ ምርት ኤክስፖርትን አሁን በወጣው ዋጋ መሠረት መተግበር አስቸጋሪ እንደሚሆን በመግለጽ፣ ብሔራዊ ባንክም ሆነ ግብርና ሚኒስቴር ይህን መመርያ ዳግም ሊያጤኑት ካልቻሉ አበባ ላኪዎችን ኪሳራ ላይ ሊጥል ይችላል የሚል ሥጋታቸውን ገልጸዋል።

አሁን ባለው ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ በአውሮፓ ያለው ገበያ በቀድሞው ልክ እየሄደ እየሄደ እንዳልሆነ፣ ወደ ሩሲያና ወደ ዩክሬን የሚላከው አበባ ከማዕቀብና ከገበያ ፍላጎት አንፃር ገበያው ችግር እንደገጠመው የሚናገሩት አቶ ኤርሚያስበዚህም ምክንያት የአበባ ዋጋ እንደወደቀና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከሰሞኑ ባወጣው ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ ገበያ ማግኘት ፈጽሞ አስቸጋሪ እንደሚሆን ያስረዳሉ።

በመሆኑ መመርያው የወጣበት ወቅት ነባራዊውን ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ከግምት ያላስገባና ዓለም አቀፍ ገበያው እየሰጠ ያለው ዋጋ ምን ያህል እንደሆነ ያላገናዘበ በመሆኑ መመርያው በድጋሚ ሊታይ እንደሚገባ አቶ ኤርሚያስ ይመክራሉ፡፡

መመርያው የወጣው የአበባ ዋጋ ከፍተኛ በነበረበት ወቅት ቢሆን ኖሮ ችግር ላይኖረው እንደሚችል የሚገልጹት አቶ ኤርሚያስ፣ በሆላንድ ጨረታ ላይ በዜሮ ጭምር እየተወጣ ባለበት በአሁኑ ወቅት አበባው ከሚሸጥበት ዋጋ በላይ እንዲሸጥ የሚያስገድድ መመሪያ ማውጣት ተገቢ እንዳልሆነም ያሰምሩበታል፡፡

ማኅበሩም ሆነ አቶ ኤርሚያስ በዚህ መመርያ አተገባበር ላይ በዋናነት የሚያቀርቡት ቅሬታ መመርያ ከመውጣቱ አስቀድሞ ባለድርሻ አካላት እንዲመክሩበት አለመደረጉ ነው፡፡ መመርያው ከወጣም በኋላ ቢሆን ባለድርሻ አካላትን ጠርቶ ማነጋገር ተገቢ እንደሆነ ይናገራሉ።

የግብርና ሚኒስቴርም ሆነ ብሔራዊ ባንክ አበባ ወደ ውጭ ሲላክ መገኘት የሚገባውን የውጭ ምንዛሪ መጠን ወይም ዋጋ በተመለከተ የተደረገው የጥናት ውጤት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ቢመክር ኖሮ የተሻለ ውጤት ይገኝ እንደነበር የዘርፉ ተዋናዮች ያምናሉ፡፡ 

አሁንም ቢሆን በወጣው መመርያ ላይ ውይይት በማድረግ መፍትሔ የማይበጅ ከሆነ የአበባ የወጪ ንግድ ላይ ተፅዕኖ ከማሳረፉም በላይ የወጪ ንግድ ገቢውን እንደሚጎዳ ያሳስባሉ።

ከዚህ መመርያ ባሻገር አሁን ላይ ለአበባ ላኪዎች ትልቅ ተግዳሮት የሆነው ጉዳይ በብሔራዊ ባንክ ከወራት በፊት የወጣው ሌላ መመርያ ነው፡፡ ይህም ከውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የተተገበረው መመርያ ነው፡፡ በዚህ መመርያ መሠረት ላኪዎች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ መጠቀም የሚችሉት 20 በመቶን ብቻ መባሉ ነው፡፡ አቶ ኤርሚያስ እንደገለጹት፣ በዚህ መመርያ መሠረት አበባ ላኪዎች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ 20 በመቶውን ብቻ እንዲጠቀሙ መወሰኑ ኢንዱስትሪውን እንደሚጎዳ ይገልጻሉ፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው መመርያ የነበረው አሠራር፣ የአበባ ላኪዎች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ 40 በመቶውን መጠቀም ይችሉ እንደነበረና በዚህም ለአበባ ምርት የሚያገለግሉ ግብዓቶችን ከውጭ ለማስመጣት ሲጠቁሙበት መቆየታቸውን ይገልጻሉ። 

አሁን ግን ይህ አሠራር ተለውጦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ላኪዎች ከሚገኙት የውጭ ምንዛሪ 20 በመቶን ብቻ እንዲጠቀሙ መደንገጉ ለአበባ ግብዓት የሚያስፈልጉ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በበቂ ሁኔታ ለማስገባት እንዳላስቻላቸው ገልጸዋል፡፡ ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ 20 በመቶው ብቻ መፈቀዱ ግብዓቶቹን ለማስገባት በቂ ባለመሆኑ የግብዓት እጥረት እየፈጠረባቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ 

በእርግጥ አበባ ላኪዎቹ ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ 80 በመቶ የሚሆነው በብር ተመንዝሮ የሚያገኙት ቢሆንም፣ የአበባ አምራቾች የሚፈልጉትን ግብዓት በአገር ውስጥ ስለማያገኙ ችግር ውስጥ እንዲወድቁ እያደረጋቸው መሆኑንም አቶ ኤርሚያስ አመልክተዋል፡፡ ይህም ችግር ለወራት የዘለቀና በዘርፉ ያሉ አልሚዎችን እየፈተነ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ በበቂ ሁኔታ ከውጭ የሚገቡ ለአበባ የሚሆኑ ግብዓቶች ማግኘት ካልተቻለ ምርቱን በጥራትም ሆነ ብዛት ለማምረት ስለማይቻል የወጪ ንግዱ ሊያስገኝ የሚገባውን ያህል ገቢ ማስገኘት እንደማይችል ታውቆ መንግሥት ለዘርፉ ማነቆ እየሆኑ ያሉትን መመርያዎቹን መፈተሽ እንዳለበት አቶ ኤርሚያስ አስገንዝበዋል፡፡ 

አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ግን አበባ የወጪ ንግድ ዋጋ አሁን ላይ ዝቅ ቢልም፣ ዋጋው ከፍ ባለበት ወቅት ጭማሪ ተገኝቷል ብለው የሚያስገቡ አለመሆኑን ገልጸው፣ እንዲህ ያለው መመርያ ሲወጣ ብቻ ቅሬታ ማሰማታቸው ተገቢ አይደለም ይላሉ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች