Wednesday, June 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ፍራንኮ ቫሉታ ምን ዓይነት ውጤት አስገኘ?

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ሚያዚያ 7 ቀን 2013 ዓ.ም. ያቋቋመው የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ ባደረገው ስብሰባ ከ250 ሺሕ ዶላር ወይም ተመጣጣኝ የውጭ አገር ምንዛሪ በላይ ሆኖ ምንጩ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እየተረጋገጠ መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦቶችን ማለትም ዘይት፣ ስኳር፣ ሩዝና የሕፃናት ወተት ያለ ውጭ ምንዛሪ ፈቃድ (በፍራንኮ ቫሉታ) ለስድስት ወራት ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ወሰኖ ነበር፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴው በወቅቱ ውሳኔውን ለማሳለፍ ገፊ ነበሩ ካላቸው ምክንያቶች ውስጥ መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች የአቅርቦትና የፍላጎት አለመመጣጠን የተነሳ በአገሪቱ የዋጋ ንረት በመባባሱ አንዱ ነበር። በመሆኑም አቅርቦትን በመጨመር በአቅርቦትና በፍላጎት መካከል ያለውን ክፍተት በማጥበብ የዋጋ ንረትን ማረጋጋት እንዲቻል ፍራንኮ ቫሉታን በመጠቀም ሸቀጦችን ወደ አገር እንዲገባ ውሳኔ ከሳልፎ ነበር፡፡

ይህ ውሳኔ ለመጀመርያ ስድስት ወራት ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ በተጨማሪነት የመሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች የጉምሩክ ቀረጥና ታክስ ማሻሻያ ተዘጋጅቶ ከነሐሴ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ እንዲተገበር ተደርጓል።

በዚህ ውሳኔ መሠረትም ስንዴ፣ ዘይት፣ ስኳርና ሩዝ ከቀረጥና ታክስ ላልተወሰነ ጊዜ ነፃ እንዲሆኑ፣ ፓስታ፣ ማካሮኒና እንቁላል ደግሞ ተጨማሪ ዕሴት ታክስ እንደተነሳላቸው የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቆ ነበር።

በሳለፍነው ሳምንት መባቻ ደግሞ የገንዘብ ሚኒስቴር በዚህ ወቅት እየተስተዋለ ያለውን የዋጋ ንረት ማረጋጋት እንዲቻልና በርካታ የውጭ አገር የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን አዎንታዊ ሚና መጫወት እንዲችሉ የፍራንኮ ቫሉታ ፈቃድ በተፋጠነ ሁኔታ እንዲፈቀድላቸው ጥያቄ አቅርበዋል በማለት ዘይት፣ ስንዴ፣ ስኳር፣ የሕፃናት ወተትና ሩዝ በፍራንኮ በጉምሩክ ኮሚሽን በኩል በቀጥታ እየተፈቀደ እንዲገባ መንግሥት ማወጁን አስታውቋል፡፡

ወደ መሬት ሲወርድ በአፈጻጸም ደረጃ ሌላ መልክ ሊኖረው ቢችልም ፍራንኮ ቫሉታ የሚለው ሸቀጦችን ያለ ውጭ ምንዛሪ ፈቃድ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ መፍቀድ በቀጥታ ሲተረጎም፣ ሕጋዊ ከሆነ ምንጭ የሚገኝ የውጭ ምንዛሪ ማለት ሲሆን፣ ይህም የባንክ ቤት ፈቃድ ሳያስፈልግ ከውጭ አገር ዕቃ ለማስገባት የሚያስችል የፈቃድ ዓይነት ማለት ነው።

አሁን ያለውን የዋጋ ንረት ለማርገብ ከባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር አንስቶ የተፈቀደው ፍራንኮ ቫሎታ አንድ አማራጭ እንጂ፣ ዘላቂ መፍትሔ ስለማይሆን  የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት ተጨማሪ መፍትሔዎች እንደሚያስፈልጉ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ሲያሳስቡ ቆይተዋል፡፡ 

የፍራንኮ ቫሉታው መፈቀድ ከአማራጭነቱ ባሻገር ሌላ ችግር እንዳያመጣ መጠንቀቅ ይገባል ሲባል የቆየ ሲሆን፣ ይህም በፍራንኮ ቫሉታ ለሚገባው ዕቃ አስመጪው የሚያቀርበውን የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ብሔራዊ ባንክ ያረጋግጣል ቢባልም፣ ብሔራዊ ባንክ የገንዘቡን ምንጭ እንዴት ያረጋግጣል? ለሚለው ጥያቄ እስካሁን የተሰጠ ማብራሪያ የለም።

ግለሰቦች ይህንን ዕድል በመጠቀም ከጥቁር ገበያ ዶላር እየገዙ የተፈቀዱትን ዕቃዎች በፍራንኮ ቫሉታ ስም በማስገባት እንደገና የጥቁር ገበያው ጡንቻ እንዲፈረጥም ያደርጋል የሚል ሐሳብን ከሥጋትም አልፎ በገሃድም ተፅዕኖ መፍጠሩን በወቅቱ በርካታ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ሲያሳስቡ ነበር። 

ብሔራዊ ባንክ አንድ ሰው በሌላ አገር አለኝ የሚለውን የውጭ ምንዛሪ በምን መልኩ ሊያረጋገጥ እንደሚችል ግልጽ ባልሆነበት፣ ለበጎ የታሰበው በፍራንኮ ቫሉታ ሸቀጦችን የማስገባት ውሳኔ ሌላ ችግር እንዳያመጣ የማስጠንቀቂያ ሐሳቦችም ሲንሸራሸሩ እንደቆዩ የሚዘነጋ አይደለም፡፡

የፍራንኮ ቫሉታ መብት መፈቀድ ጥቁር ገበያን ለመቆጣጠር ሲባል በውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ላይ የወጡ የተሻሻሉ መመርያዎችን የሚፃረር እንደሆነም የሚከራከሩ ባለሙያዎች አሉ። የተሻሻሉት መመርያዎች ዋነኛ ግብ በጥቁር ገበያ የሚፈጸመውን ሕገወጥ ድርጊት ለመከላከል ቢሆንም፣ በሌላ በኩል ፍራንኮ ቫሉታ ተፈቀደ ማለት ጥቁር ገበያን መደገፍ ሊሆን እንደሚችል ሌላው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የሚያቀርቡት አስተያየት ነው፡፡ 

ከዚህ ቀድም ሪፖርተር በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ ኃላፊ እንደተናገሩት፣ ፍራንኮ ቫሉታን አስመልክቶ የዳሰሳ ጥናት ስላልተደረገ ምን ውጤት አስገኘ የሚለውን በወቅቱ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም ብለው ነበር። 

በወቅቱ እንደተገለጸው፣ ፍራንኮ ቫሉታን የሚመለከተው አካል ብሔራዊ ባንክ ቢሆንም፣ ለገንዘብ ሚኒስቴር በርካታ ሰዎች የፍራንኮ ቫሉታ ፈቃድ ለማግኘት ማመልከታቸውን ሲያቀርቡ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ግለሰቦች ምን ያህል አመጡ? ምን ያህል ገበያ አረጋግተዋል? የሚለው ፍተሻ እንደሚያስፈልገው አስምረውበት፣ ሆኖም የፍራንኮ ቫሉታው ዕርምጃ ባይወሰድ ኖሮ ከዋጋ ንረቱ ጋር በተያያዘ የባሱ ነገሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ አስታውቀው ነበር፡፡ 

መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች ያለ ውጭ ምንዛሪ ፈቃድ በቀጥታ እየተፈቀደ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ መወሰኑ ውጤቱ ታይቷል ወይ የሚለው መሠረታዊ ጉዳይ ሲሆን፣ ይህም ሲደረግ ገበያውን በማጥናት ገበያው ውስጥ የዋጋ ንረት አለ ወይ? የፍጆታ ዕቃዎች እጥረት አለ ወይ? የአገር ውስጥ አምራቾች ምን እያደረጉ ነው? ምን ያህል ፍላጎትን እያረኩ ነው? የሚለው መሠረታዊ ጥያቄዎች እንደሆኑ ይነገራል፡፡

የዋጋ ንረት በታክስ ብቻ የሚፈለገውን የዋጋ መቀነስ ስለማያመጣ አቅርቦትን ለመጨመር መንግሥት በከፍተኛ ወጪ በመግዛት በዝቅተኛ ዋጋ ለኅብረተሰቡ ከሚያቀርባቸው ከነዚህ መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች በተጨማሪ በሌሎች አካላት የሚገባውን በማከል አቅርቦቱ በከፍተኛ ደረጃ ይጨምር ዘንድ ያለውጭ ምንዛሪ ሸቀጦችን የማስገባት አሠራር መፈቀዱ፣ እየታየ ላለው ከፍተኛ የዋጋ ንረት ጊዜያዊ ማስተንፈሻ ጥሩ የመፍትሔ አማራጭ እንደሆነ የማይክዱ በእርግጥ ብዙ ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ በዚያው ልክ የኑሮ ውድነት ችግርን ለመፍታት ያለውጭ ምንዛሪ ፈቃድ የተመረጡ ሸቀጦችን ከውጭ አገሮች እንዲገቡ መንግስት መወሰኑ በጥቁር ገበያ የተገኘን የውጭ ምንዛሪ ሕጋዊ የማድረጊያ አንዱ መንገድ እንዳይሆንና ለጥቁር ገበያው (Black Market) መስፋፋት ጥሩ መንገድ እንዳይከፍት መንግሥትን እያስጠነቀቁ የሚገኙ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በርካታ ናቸው፡፡

የውጭ ምንዛሪ ምንጭን ማሳወቅ እንደ ግዴታ መቀመጡ ተገቢ ቢሆንም ፤ ብሔራዊ ባንክ ምንጩን የማረጋገጥ ግዴታ ተከታትሎ የማስፈጸም አቅሙ ደካማ ከሆነ መመርያው አደገኛ መሣሪያ የመሆን ዕድል እንደሚኖረው ይገለጻል። በተመሳሳይ በውጭ አገር የንግድ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ምንጩ እርግጠኛ ያልሆነና የተከማቸ የውጭ ምንዛሪን በብሔራዊ ባንክ በር በኩል እንዳያጥቡት (Money Laundering) መጠንቀቅ እንደሚገባ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች አሁንም ቢሆን እያሳሰቡት የሚገኝ ጉዳይ ነው፡፡

የዳያስፖራ አካውንት ተጠቃሚዎች ሬሚታንስን ጠልፈው ያስቀሩ ነበር ተብሎ በብሔራዊ ባንክ የመመርያ ማሻሻያ መደረጉ ሌላው የሚታወስ ጉዳይ ሲሆን፣ መመርያው እንዲሻሻል ከተደረገ በኋላ፣ ፍራንኮ ቫሉታ መፈቀዱ በተመሳሳይ ሁኔታ ዳያስፖራዎቹ ሕጋዊ ለማስመሰል ሬሚታንሱን ጠልፈው በአንድ አካውንት በማስገባት ዕቃውን ቢያስመጡ ብሔራዊ ባንክ እንዴት ሊቆጣጠርና ሕጋዊ ነው ብሎ ሊፈቅድ ይችላል የሚለው አሳሳቢ ጉዳይ እንደሆነ ይነገራል፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያ የሆኑት አቶ ዋሲሁን በላይ ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት የእንደዚህ ዓይነት ውሳኔዎችን ፋይዳ መገምገም የሚገባው አካል ቢኖር መንግሥት ይላሉ፡፡ 

‹‹ገንዘብ ተለውጦ ምን ተገኘ?፣ ነዳጅ ተደጉሞ ምን ተገኘ?፣ የተዛባው ማይክሮ ኢኮኖሚው ተስተካከለ ወይ?፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች ተደጎሙ ወይ?፣ ምርትና ምርታማነትስ አደገ የሚለውን በመገምገም ለሕዝቡ ይፋ ማድረግ የሚገባው አካል መንግሥት ነው›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡

በፍራንኮ ቫሉታ ፈቃድ የተገኘው ጥቅም ወይም ጉዳት በንግግር ሳይሆን በቁጥር ተደግፎ መቅረብ እንዳለበት የተናገሩት የኢኮኖሚ ባለሙያው፣ የሚታይ ነገር ባልቀረበበት ሁኔታ በራሱ ሐሳቦችን ማንሸራሸር አስቸጋሪ እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡

ፍራንኮ ቫሉታ ብቸኛ መፍትሔ ሰጪ አማራጭ ሳይሆን መቆጣጠር ከታቻለ የተወሰነ አስተዋጽኦ ሊኖረው የሚችል መፍትሔ ነው ያሉት አቶ ዋሲሁን፣ ስለሆነም ምንም አስተዋጽኦ የሌለው ነገር ነው ተብሎ የሚተው እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡ 

ለምሳሌ አንድ ሰው አንድ ሺሕ ቶን ስንዴ ወደ አገር ውስጥ አስገብቶ ለጥቂት ሰው ቢደርስ አስተዋጽኦ የለውም ሊባል አይችልም፣ ነገር ግን አገርን እንደመምራትና እንደ ማክሮ ኢኮኖሚ አስተዳደር ግን ብዙኃኑ ነው ወይ እየጠቀመበት ያለው? የሚለው ጉዳይ መሰላት እንዳለበት ይመክራሉ፡፡ 

ምክንያታቸውንም ሲያስቀምጡ፣ ‹‹ምንም ጊዜ ቢሆን ይህ ዓይነቱ ጉዳይ ሲሠራ ከብዙኃኑ አንፃር መታየት ስለሚገባው ነው፡፡ ይህ ባልተሰላበት ሁኔታ ፍራንኮ ቫሉታ መጥቀም አልመጥቀሙ የሚያረጋግጥ ግልጽ ሪፖርት በሚመለከተው አካል ሲቀርብ አይታይም፤›› ብለዋል፡፡

ይህም ቢሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የዋጋ ንረት በጣም ከፍተኛ እንዳይሆን ካዳረጉ ነገሮች መካከል ፍራንኮ የተወሰነም ቢሆን ሚና አልነበረውም ብሎ መናገር ከባድ እንደሆነ አቶ ዋሲሁን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከ16 ወራት በላይ ግጭት ውስጥ የቆየ፣ ደብረ ብርሃን ድረስ በዘለቀና በተንሰራፋ ጦርነት ሳቢያ የሚታረሱ መሬቶችን እንቅስቃሴ የከለከለ እንደነበር ያስረዱት አቶ ዋሲሁን፣ በሌላ በኩልም በምዕራብና ደቡብ ምዕራባዊ የአገሪቱ ክፍሎች መደበኛ የምርት ማምረት ሒደት ውስጥ ከመገኘታቸው ጋር ተያይዞ፣ እንደ ቦረናና ሱማሌ ክልሎችን ቀላል በማይባል ሁኔታ በድርቅ መጎዳታቸውን ያስታውሳሉ፡፡ 

በዚህ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተጣለው ማዕቀብ ሲታከልበት የዋጋ ንረቱ አርባ በመቶ ውስጥ ሊቆይ የቻለው የተወሰኑ የመንግሥት የፖሊሲ ድጋፎች በመኖራቸው እንደሆነ የኢኮኖሚ ባለሙያው ያስረዳሉ፡፡

የተወሰኑ ቁሶች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ መደረጉ፣ ሌሎች ሸቀጦችም በፍራንኮ ቫሎታ እንዲገቡ መደረጋቸው እንዲሁም የመንግሥት ድጎማዎች እንዲቀጥሉ መደረጋቸው በጠቅላላው ሲደመሩ የዋጋ ንረቱ በጣም በከፍተኛ ሁኔታ እንዳይመነጨቅ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ይጠቀሳሉ፡፡

ከተዓማኒነት አንፃር የፍራንኮ ቫሉታ ዕድል እንዲጠቀሙ ፈቃድ የተሰጣቸው አካላት መረጃ ሊቀርብ እንደሚገባ የገለጹ ሲሆን፣ የዚህን ያህል ሰዎች መጥተው አስፈቅደው፣ ይህንን ያህል የሚሆኑት ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል፣ ይህን ያህል መጠን ያለው ነገር ተገኘ ካልተባለ አስቸጋሪ እንደሆነ የኢኮኖሚ ባለሙያው አስረድተዋል፡፡ መንግስት በሚፈቅደው የውጭ ምንዛሪ ግለሰቦች ምን እንዳስመጡ ወይም በፍራንኮ ቫሉታ አስታከው ሌሎች ግብዓቶች ማምጣት አለማምጣታቸው ተፈትሾ ሪፖርት ማቅረብ የፈቃጁ አካል ኃላፊነት እንደሆነ ይገለጻሉ፡፡

‹‹ፍራንኮ ቫሉታ ከሥጋት ነፃ እየሆነ የሄደ አሠራር ነው ብሎ መገመት ትንሽ ያስቸግራል፣ ምክንያቱም በወንጀል የተገኘ ገንዘብንም በእግረ መንገድ ሕጋዊ ለማድረግ ዕድል ይሰጣል፤›› ብለዋል።

መንግሥት ፍራንኮ ቫሉታን ሲፈቅድ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መግባቱን ያሳያል የሚሉት ባለሙያው አቶ ዋሲሁን፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ቢኖርበትም ይህንን ችግር በቀጣዮቹ ጊዜያት ውስጥም በቂ የውጭ ምንዛሪ አግኝቶ እንደሚፈታው እርግጠኛ በመሆኑ የፈቀደው ዕድል መሆኑን ያስረዳሉ።

‹‹መንግሥት የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን እስኪፈታ ድረስ ትንሽዬ በመሸነፍ፣ የውጭ ምንዛሪ ያላችሁ እየመጣችሁ እያስፈቀዳችሁኝ ሸቀጦችን አስገቡበት፡፡ ሌላ ምርመራ ውስጥ አልገባም እያለ ነው፤›› ሲሉ የፍራንኮ ቫሉታ የተፈቀደበትን አንድምታ አስረድተዋል፡፡ 

አሠራሩ ጥንቃቄ ካልተደረገበት ግን ግለሰቦች በትይዩ ገበያ (Parallel/Black Market) ገዝተው ያስቀመጡትን ወይም ያጠራቀሙትን የውጭ ምንዛሪ የሚያጥቡበት ወይም ሕጋዊ የሚያደርጉበት ሁኔታን እንደሚችል አሳስበዋል።

በሌላ በኩል ሕጋዊ ያልሆነን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብን (Money Laundering) የሚለው ተግባር ላይ የሚያሳርፍ ይሆናል ብለዋል፡፡ ይህንን ደግሞ መንግሥትም የሚረዳው ጉዳይ እንደሆነ አቶ ዋሲሁን አስረድተዋል፡፡

ፍራንኮ ቫሉታን ለረዥም ጊዜ ላይ ማቆየት አጠቃላይ አሠራሩን ጤነኛ እንዳይሆን ያደርጋል ያሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው፣ ዓመትና ከዓመት በላይ ለሆነ ጊዜ ፍራንኮ ቫሉታን ፈቅዶ ማቆየት መንግሥት ከፍተኛ የሆኑ ነገሮችን የሚያሳጣው እንደሆነ  ተናግረዋል፡፡ ተቋማዊ አሠራር ደካማ እየሆነ በመጣ ቁጥር ገበያውም የራሱን የሆነ አሻጥር እየፈጠረ ወይም ለዚያ ምቹ እየሆነ እንደሚመጣ፣ ይህም በመደበኛው ገበያና በጥቁር ገበያው መካከል ያለው የምንዛሪ ልዩነትም እየሰፋ እንዲሄድ የራሱን ሚና የሚጫወት ይሆናል ብለዋል፡፡

መንግሥት በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ወይም ጭንቅ ውስጥ በሚገባበት ጊዜ  ከባባድ ውሳኔ እንዲወስን ይገደዳል ያሉት አቶ ዋሲሁን፣ ፍራንኮ ቫሉታንም የፖለቲካዊ፣ የማኅበራዊና ኢኖሚያዊ ጫናው ከፍተኛ መሆኑን ከመረዳት አንፃር መንግሥት እንዲቀጥል ያደረገው ጉዳይ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

እንደ ባለሙያው አስተያየት ከሁሉም በላይ ወሳኝ የሆነው ጉዳይ የፋይዳ ሪፖርት ማቅረብ ሲሆን፣ የማክሮ ኢኮኖሚን የሚመሩት አካላትም ይህንን ፋይዳ የሚያሳይ ሪፖርት ማቅረብ ይገባቸዋል ብለዋል።

ፍራንኮ ቫሉታን ለረዥም ጊዜ እንዲቆይ ከተፈቀደ ግን፣ ዶላርን በመሸጥና በመግዛት መካከል ያለውን ልዩነት በማግኘት የሚያገኘውን ገቢ በመሸርሸር የመንግሥትን የበጀት ጉድለት ሊያሰፋው እንደሚችል ባለሙያው ገልጸዋል።

መንግሥት የሆነ ቦታ ላይ መጨከን እንዳለበት የሚገልጹት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ተንታኙ፣ ለምሳሌ የነዳጅ ብክነት የሚበዛ ከሆነ መንግሥት መኪኖች ወደ አገር እንዳይገቡ መከልክል እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ 

ነዳጅ በጣም የሚፈጁትን አሮጌ መኪኖች ላይ፣ ማደያዎች ላይ ኮስተር ማለት አስፈላጊ እንደሆነ በምሳሌ የተናገሩት ባለሙያው፣ ስለሆነም የፋራንኮ ቫሉታ ጉዳይ ታይቶና ተመዝኖ ፋይዳው ካመዘነ እንዲቀጥል፣ ካልሆነ ደግሞ መወሰድ የሚገባው ጠቃሚ ዕርምጃ መውሰድ እንዳለበት ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

የጥቁር ገበያ ዋጋ በጣም እየናረ ከመጣ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ሸቀጦች ዋጋቸው ውድ እንደሚሆን ይጠበቃል ያሉት አቶ ዋሲሁን፣ ግለሰቦች እንዲያስገቡ የተፈቀደላቸው ሸቀጦች አንገብጋቢ በመሆናቸው ከማምጣት ወደ ኋላ የሚሉበት ሁኔታ እንደማይኖር ገልጸዋል።

የጥቁር ገበያ መለጠጥ ብቻ ሳይሆን ታች ያለው ሙስናና ቢሮክራሲ በራሳቸው ዋጋ የሚያንሩ እንደሆኑ የገለጹ ሲሆን፣ ሸቀጡን ወደ አገር ውስጥ ያስገባው ነጋዴ በየጉምሩክ ጣቢያውና ሌሎች ቦታዎች የሚጠየቃቸውን የጎንዮሽ ገንዘቦች በሚያመጣቸው ዕቃዎች ዋጋ ላይ እየደመረ ሄዶ መጨረሻ ላይ ሸማቹ የዚህ ሁሉ ጭማሪ ገፈት ቀማሽ እንዳይሆን ሥጋታቸውን አነስተዋል።

በእንደዚህ ዓይነት አስቸጋሪ ወቅት ውስጥ ሁለት ነገሮች በመንግሥት እጅ ላይ የሚወድቁ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ዋሲሁን፣ የግብይት ሁኔታ ላይ የሚታየውን ክፍተት ቶሎ ብሎ ለማስታገስ መንቀሳቀስ የመጀመርያው ነው፡፡ ይህ የአጭር ጊዜ መፍትሔም ጭምር ሲሆን፣ ከዓለም ወቅታዊ ሁኔታ በተለይም ከሩሲያና ዩክሬን ጦርነት፣ ከአሁናዊው ከድርቅ ጋር ተያይዞ በዓለም አቀፉ የምግብ ድርጅት (ፋኦ) የቀረበውን ቀጣናዊ ከድርቅ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን በማጤን ለረዥም ጊዜ የሚሆኑትን መፍትሔዎች ከወዲሁ ማሰብ የግድ እንደሚል ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በሁለት ነገሮች እየተጨነቀ ይገኛል ያሉት አቶ ዋሲሁን፣ አንደኛው ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ሁኔታው የፈጠሩበት ጫና ሲሆን፣ በሌላ በኩል በአገር ውስጥ የፀጥታ ችግር ያለባቸው አከባቢዎች ከመብዛታቸው ጋር ተያይዞ የምርታማነት ሥርዓቱ በአግባቡ ካለመሄዱ ጋር የሚገናኝ ነው፡፡

ከዚህ በመነሳት የፀጥታ ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች የሰላም ሁኔታ ማስተካከል መሠረታዊ ጉዳይ ሲሆን፣ ይህም ደግሞ ለገበያ አሻጥሮች ምቹ በመሆኑና ዜጎችም ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ለመሥራት ያላቸውን መተማመን ዝቅ ስለሚያደርገው ነው፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች