በአብዩ ብርሌ (ጌራ)
ወጣት እያለሁ ለአገራችን ኋላ መቅረት፣ ለሕዝባችን ድህነት፣ የሁልጊዜ ድርቅ መከሰት፣ ለጭሰኛው መሬት ማጣት፣ ለላብ አደሩ ቀኑን ሙሉ ሲለፋ ውሎ ባዶ እጁን ወደ ቤተሰቦቹ ማምራት፣ ለሁሉም የአገራችን ችግር ተጠያቂው ንጉሡና እሳቸው ከላይ ሆነው የሚመሩት የባላባታዊ ሥርዓት ነው እንል ነበር፡፡ ንጉሡ በሕዝብ አመፅ ሲወርዱ ግን ጭራሽ ከእሳቸው ሥርዓት የባሰ፣ ደርግ የሚባል አውሬ ተተካና አገሪቱን ሊገነባ ይችላል በሚል ተስፋ ተጥሎበት የነበረውና የተማረው ወጣት ትውልድ እንደ ቅጠል እረገፈ፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ ያ መዓት ሲያልፍ ከሁለቱም የሚብስ ሥርዓት ተተካና ሕዝቡ ‹‹እሰይ ጨካኙ ደርግ ተወገደልኝ፣ አሁንስ ዕፎይ ብዬ ችግሬን ችግር አድርጌ፣ ቢያንስ አገሬን በሰላም ይዤ መጪ ዕድሌን አያለሁ፤›› ሲል ፈፅሞ ያላለመው ዓይነት አስከፊ ሥርዓት ደግሞ ወረደበት፡፡
ጭራሽ የኢትዮጵያን ምድር በዘፈቀደ ቆራርሶ፣ በክልልና በቋንቋ በዘር ለያይቶ፣ ለስሙ ለሰፊው ሕዝብ እኩል አከፋፈልኩ በማለት እየተመፃደቀ፣ ደሃውን ዜጋ በጭካኔ፣ በግፍ፣ በሴራና በብልጠት የሚመዘብር፣ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ ሥርዓት ተከሰተ፡፡ ሃይማኖት፣ ዘር፣ ቋንቋና ድንበር አጥር ሆኖ ሳይለያየው በፍቅር ተሳስሮ ለዘመናት የኖረውን ሕዝብ እርስ በርስ የሚያናቁር፣ የሚያፈናቅል፣ የሚያጨራርስ ሥርዓት ቤተ መንግሥት በጉልበት ገብቶ፣ ቀስ በቀስ በአገሪቱ ሥር ሰደደ፡፡ ከዚያም ለዘመናት ተከብራና ታፍራ የኖረችው አገሩ ከእነ አካቴው ጨርሳ እንዳትጠፋበት፣ አገሩን አፍቃሪ ዜጋ ሁሉ ሌትና ቀን መባነንና መጨነቅ ቀጠለ፡፡
እንግዲህ አገራችንና ሕዝባችን ከዘለዓለም መከራ ሊያድን የሚችል ምን ዓይነት መንግሥት ቢመጣ ይሻላል? ከየትስ ነው የሚመጣው? ችግራችን ራሱ መንግሥት የማጣት ነው ወይስ ሌላ የማናውቀው በሽታ በውስጣችን አለብን? እኛ ኢትዮጵያውያን ገናና ታሪክ ያለንና ከሁሉ በፊት ሥርዓተ መንግሥት የነበረን እንዴት አሁን ለእኛ የሚሆን ጥሩ መንግሥት መመሥረት አቃተን? ምንድነው ችግራችን? ስንት ወርቃማ ተመልሶ የማይገኝ ዕድልስ አለፈን?
በእኔ ግምት በየጊዜው እየመጣ ሳይሳካለት፣ ጥፋት እያጠፋ የሚሄደውን መንግሥት እንደተለመደው ከማውገዝና ሁልጊዜ ሌላ የማናውቀውን አዳዲስ ከመመኘት ተቆጥበን እስኪ አንዳንዴ ቆም እያልን ራሳችንን በጋራም ሆነ በግል እንጠይቅ፣ ችግራችንን ከሥሩ ለመረዳት እንሞክር፡፡ መንግሥት እኮ ክፉም ሆነ ደግ ከሰማይ አይወርድም፡፡ ከእኛው ውስጥ ተዘርቶ ነው የሚበቅለውና ሥር የሚሰደው፣ የሚያቆጠቁጠውና የሚያድገው፡፡ ዞሮም መልሶ የሚያጠፋንና እርስ በርሳችን የሚያጠፋፋን እኛው ራሳችን እያሳደግነው ነው፡፡ ያ ከሆነ ታዲያ ለምንድነው ካለፈው ጥፋታችንና ተሞክሮአችን ተምረን አገራችንን የሚጎዳ መንግሥት እንደ ገና መልሶ ከውስጣችን እንዳያቆጠቁጥ፣ ወይም ከውጭ እንዳይጫንብን በኅብረት ማስቆም የማንችለው?
ድሮ በትምህርት ገበታ ወይም ኮሌጅ እያለን ስለመንግሥት አፈጣጠር ሲነግሩን፣ ከሕዝብ ተወልዶ፣ በሕዝብ ተወክሎ፣ ሕዝብን ለማስተዳደር የሚተከልና የሚገነባ የኅብረተሰብ አካል ነው ይሉን ነበር፡፡ እንግዲህ እነዚህ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት አገራችንን እያስተዳደሩ ለሚመጣው ትውልድ አሳድገውና ጠብቀው በሰላም ለማውረስ ሳይሳካላቸው ያለፉት የሦስት መንግሥታት ሥርዓቶች (የዛሬውን ገና አዲስ ስለሆነ ለጊዜው ትተን)፣ ከላይ የተማርናቸውን መሥፈርቶች ሙሉ በሙሉ አያሟሉም ነበር ለማለት አያስደፍርም፡፡ ለምን ቢሉ ያለ ምንም ደጋፊና ወካይ ከላይ ዱብ ብለው ነው የመንግሥት ሥልጣን ወንበር ላይ ቁጭ ያሉ ለማለት አፋችንን ሞልተን መናገር የምንችል አይመስለኝም፡፡ በዚህም በዚያ፣ ወጣም ወረደ ለእነዚህ መንግሥታት ሥልጣን ላይ ለመውጣትም ሆነ ሥር ለመስደድ ኃላፊነት ለመውሰድ፣ ወይም መጠየቅ የሚኖርበት ምንጊዜም ከእኛው ከውስጣችን ያለ ይመስለኛል፡፡
በአጭሩ ሰፊውን ሕዝብ ከእዚህ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ብናወጣው፣ ይህ መንግሥት እኔን ይጠቅመኛል በሚል ሥልጣን ላይ እንዲወጣ የሚመኝም ሆነ፡፡ ከወጣም በኋላ እንዲጠናከር፣ እንዲቀጥልና ዕድሜው እንዲረዝም ሽንጡን ገትሮ የሚደግፈውና የሚዋጋለት ምንጊዜም ይኖራል፡፡ ባለፉት ሦስቱም ሥርዓቶች የእዚህ ዓይነት ባህሪ ያለው፣ በጣም ብዙ ሰው ወይም የኅብረተሰብ ክፍል በተለያዩ ወቅቶች የነበረ ይመስለኛል፡፡ ይህ የኅብረተሰብ ክፍል የራሱን ጥቅም ማስጠበቅ እንጂ ለሌላው ወይም ለአገሩ ምንም ደንታ የለውም፡፡ በአንፃሩ በእነዚህ መንግሥታት ዋጋ የሚከፍለው ግን ሰፊው ምስኪን ሕዝብ ነው፡፡
በእኔ አስተያየት እንግዲህ እዚህ ላይ ነው ዋናው ችግር ያለው፡፡ ሁሉም መንግሥት የራሱ ወካይ፣ ተከላካይ፣ ደጋፊ ወይም ከእዚያ አልፎ ሕይወቱን ሳይቀር በግድም ሆነ በውድ አሳልፎ የሚሰጥለት የኅብረተሰብ ክፍል አለው ማለት ነው፡፡ አንዳንዶች ይህን ለሥልጣን ወይም የራሱን መንግሥት ለማምጣት የሚሻኮተውንና የሚታገለውን “የፖለቲካ ልሂቅ” ብለው ይጠሩታል፡፡ ልብ በሉ! ይህ ሁሉ ሲሆን ሰፊውን ሕዝብ ዞር ብሎ የሚያየው ወይም ከጤፍ የሚቆጥረው የለም፡፡ ይሁን እንጂ ይህ “ልሂቅ” የሚባለው አካል ሰፊውን ሕዝብ ለራሱ መሣሪያ ወይም ሥልጣን መወጣጫ አያደርገውም ማለት አይደለም፡፡ እንዲያውም ብዙ ጊዜ ፈላጭ ቆራጭ መንግሥታት ሥልጣን የሚይዙትም ሆነ የሚወድቁት በሕዝብ አመፅ ተደግፈው ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሕዝቡ ጭቆናና ግፍ አንገፍግፎት በመንግሥት ላይ አመፅ ቢያነሳም ብዙ ጊዜ አይሳካለትም፡፡ ከባድ መስዋዕት ከፍሎም ለእሱ የሚሆን መንግሥት አያገኝም፡፡ ድሉን በልሂቃኑ ይቀማልና፡፡
የሚገርመው ግን እንደ አዲስ የሚመጡት መንግሥታትም ካለፉት ስህተት አይማሩም፡፡ ሕዝቡን ይበዘብዙታል፣ ግፍ ይሠሩበታል፣ እንደ ገና ለአመፅ ያስነሱታል፡፡ በመጨረሻ እነሱም ይወድቁና ሌላ ጉልበተኛ መንግሥት ሕዝቡንም ቀስቅሶ አነሳስቶ፣ የራሱን ልሂቃንም ይዞ ሥልጣን ይጨብጥና ይቀጥላል፡፡ ባለፉት 50 ዓመታት የአገራችን ዕጣ ከሞላ ጎደል ይህን ይመስል ነበር ቢባል ከእውነት የሚርቅ አይመስለኝም፡፡ በቅርቡ እንኳን እንዳየነው የኢሕዴግ መንግሥት በሕዝብ አመፅ ከወደቀ በኋላ ምንም እንኳን አገራችን እስከ ዛሬ ድረስ ከቀውስ ባትወጣም፣ ለመጀመርያ ጊዜ ማንም ሳያስገድደው ሕዝቡ ግልብጥ ብሎ ወጥቶ፣ ድምፁን በመስጠት የሚወክለውን መንግሥት ለመምረጥ ችሎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህ መንግሥትም ዛሬ በልሂቃኑ እንዳይጠለፍ ያሠጋል፡፡
ምንም እንኳን በሕዝብ ይመረጥ እንጂ ከፊቱ ብዙ ከባድ ፈተናዎች ግን ተጋርጠውበታል፡፡ እነዚህን ውስብስብ የአገራችን ችግሮች ደግሞ ያለ ሕዝብ ድጋፍ ሊወጣቸው አይችልም፡፡ የሚያሳዝነው ግን ጥሩ ሲሠራ ሆይ ሆይ ብለው ለጊዜው ከሚያሞግሱት ይልቅ፣ ስህተት ሲሠራ ቶሎ ብለው የሚያወግዙት የሚበዙ ይመስላል፡፡ ስህተት እንዲሠራና ሕዝብ እንዲያምፅበት የሚመኙለትም እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡ የአገራችን ፖለቲካ ከልሂቃን ሴራ ምንጊዜም ወጥቶ አያውቅም፡፡ አንዱ ትልቁ መድኃኒት ያላገኘንለት ሕመምም እሱ ነው፡፡ እስኪ ተደጋግፈን ይህን በስንት ትግልና ዕድል፣ ከስንት ዓመታት በኋላ የተገኘውንና በሕዝብ ፍላጎት የተመሠረተውን መንግሥት፣ እንደ ምንም ብለን የተወሳሰቡትን የአገራችን ችግሮች በጋራ እየፈታን እንዲዘልቅ እናድርገው እያለ፣ ከልቡ የሚጨነቅና የሚያስብ ልሂቅ ስንት እንዳለ ለመገመት ያዳግታል፡፡ እርግጥ በዋነኝነት ይህ እንዲሆን ማመቻቸት የሚገባው መንግሥት ራሱ እንደሆነ ደግሞ ማመን ያስፈልጋል፡፡ ችግሩ ግን በሕዝብ ቢመረጥም እንኳን፣ አሁንም መንግሥትን የሚዘውሩትና የሚያሽከረክሩት ከአገሪቱ ልሂቃን የወጡ ስለሆኑ ስንቶቹ በሴራው የፖለቲካ ባህላችን ያልተበከሉ ናቸው የሚለው ራሱ አጠያያቂ ነው፡፡ እንግዲህ ታዲያ ይህን ልሂቃኑን የተጠናወተውን ሕመም እንዴት ነው ማዳን የሚቻለው?
ያም ሆነ ይህ አንድ መንግሥት በትክክል አልሠራም እያሉ እሱን ብቻ ማውገዝና በላዩ በላዩ መረባረቡ ምንም መፍትሔ እንደማያመጣ፣ ቢያንስ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት በሦስቱ ሥርዓቶች በሚገባ ያየን ይመስለኛል፡፡ ችግሩ ይህን ሀቅ አምኖ የሚቀበል ግን ብዙም የለም፡፡ እስኪ መንግሥትን ማውገዝ ለጊዜውም ቢሆን አቁሜ ራሴን ልመርምር የሚል ብዙም ያለ አይመስለኝም፡፡ ዋናው ችግር ለዘመናት ወደ ኋላ እየዞርን በማየት አልፈነው በመጣነው ጎዳና እየተነታረክን፣ ሁልጊዜ ወደ ሰማይም አንጋጠን ወደፈጣሪያችን እየፀለይን አንገታችንን ደፍተንም ራሳችንን ይዘን እያለቀስን ሁሉ ሞከርነው ግን፣ ከአገራችን የፖለቲካ አዙሪት እስከ ዛሬ ምንም መውጫ ጎዳና ማግኘት አልቻልንም፡፡ ወደፊታችንም ለማየት አቅም አላገኘንም፡፡
እስኪ የሚረዳን ከሆነ አንዳንዴ ቆም እያልን ራሳችንን እንጠይቅ፡፡ “ያልተማረ” ከምንለው ከሕዝባችንም ለመማር እንሞክር፡፡ ለምንድነው እስከ ዛሬ ለሕዝብና ለአገር የሚሆን መንግሥት መመሥረት ያልቻልነው? ለምንድነው አንድ መሆንና መስማማት የሚያቅተን? ዓለም በሙሉ የሚያከብራትን አገራችንን ለምንድነው የምናዋርዳት? ወደኋላ ያስቀረናት? ለምንድነው ሕዝባችንን ለዘለዓለም ረሃብ፣ ድርቅ፣ ድህነት፣ ጉስቁልና፣ በሽታ፣ ጦርነት፣ መፈናቀል የዳረግነው? ሰላም፣ ዕርቅና መቻቻል ለምን ራቁን? ለራሳችን ሳይሆን ለሚመጣው ትውልድና ለአገራችን ማሰብ እንዴት አቃተን? እስኪ ሁላችንም በእዚህ ፆም ወራት ሱባዬ እንደገባን ሆነን በማሰብና በመፀለይ ለእነዚህ ጥያቄዎች ሌትና ቀን መልስ እናፈላልግ፡፡ በአንድ ልብ በቅንነት ካሰብን እኮ ምናልባት እንደ ጥንት ወላጆቻችን፣ አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን በህልም ሊገለጽልን ይችል ይሆናል፡፡ ፀሎት ከልብ ከተፀለየ እኮ የቋንቋ፣ የዘር፣ የብሔር፣ የክልልና የሃይማኖት ልዩነት አያግደውም፡፡ ሁላችንም ለእዚህች የምታኮራ ግሩም ባለ ታሪክ አገር የኢትዮጵያ ዜጎች ነንና፡፡ ፈጣሪ ይህችን ክብርና ዝና የሞላትን ታሪካዊ አገራችንን ኢትዮጵያን ይጠብቅልን! ለሕዝባችን ሰላም፣ ዕርቅና አንድነት ፍቅር ያውርድልን! አሜን!!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡